Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየካንሰር ሕመምና በሽታውን ለመከላከል የሚደረግ አገራዊ ጥረት

የካንሰር ሕመምና በሽታውን ለመከላከል የሚደረግ አገራዊ ጥረት

ቀን:

ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች እስከ ቅርብ ጊዜያት ትኩረት ሳይሰጣቸው በመቆየታቸው፣ በፈጣን ሁኔታና በአሳሳቢ ደረጃ በመስፋፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ ካንስር፣ የልብ ሕመም፣ ስኳር፣ የደም ግፊት፣ በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚያጋጥሙና ሌሎች ተመሳሳይ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች በመጨመራቸው፣ ወገኖችና በማኅበረሰብ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አልቀረም፡፡

በኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁጥር እያደጉና የዜጎችን ሕይወት እየነጠቁ ካሉ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል የካንሰር ሕመም በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ የካንሰር ሕመምን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጤና ሚኒስቴር ሥር ብሔራዊ የካንሰር መቆጣጠሪያ ዕቅድ ተነድፎ ወደ ሥራ ከተገባ ጥቂት የማይባል ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ዛሬም ሕመሙ የብዙዎችን ሕይወት በመንጠቅ የአገሪቱ የጤና ሥጋት ከመሆን አልዘለለም፡፡

የካንሰር ሕመም በማናቸውም የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሰዎች ላይ ሊከሰት የሚችል የጤና እክል ሲሆን፣ የሕፃናት የደም ካንሰር፣ የጡት ካንሰር፣ የማኅፀን በር ካንሰር፣ የአጥንት ካንሰር፣ የዓይን ካንሰር፣ የሳንባ ካንሰርና የመሳሰሉት የበሽታው ዓይነቶች ደግሞ በስፋት የሚከሰቱና እስከ ሞት የሚያደርሱ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህንን ለበርካታ ወገኖች ሞት ምክንያት የሆነውን የካንሰር ሕመም ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ፣ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የድርሻቸውን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ 

ከእነዚህ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መካከል ደግሞ የካንሰር ሕሙማንን ሥቃይ ለመቀነስና ታክመው የሚድኑበትን አመቺ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ፣ ላለፉት ሃያ ዓመታት በርካታ ተግባራትን በመከወን ላይ የሚገኘው ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ አንዱ ነው፡፡

ሶሳይቲው የጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ባልሆኑ ሕመሞች፣ በተለይም የካንሰር ሕመምን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍና በዚህ አገራዊ ችግር ላይ የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በማኅፀን በር ካንሰር፣ በጡት ካንሰር፣ በሕፃናት የደም ካንሰርና በሳንባ ካንሰር ለሚታመሙ ሕሙማን ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በፈጠረው የቅብብሎሽ መረብ አማካይነት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚመጡና የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ሕፃናትና ሴቶች የካንሰር ሕሙማን በማኅበራዊና በሥነ ልቦና ማዕከሉ ውስጥ ተቀብሎ የምግብ፣ የመጠለያ፣ የትራንስፖርት፣ የመድኃኒትና የምርመራ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም 160 የሚሆኑ የካንሰር ሕሙማንና አስተማሚ ቤተሰቦች በማዕከሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ በማኅበራዊና ሥነ ልቦና ማዕከል ውስጥ ድጋፍ ከሚደረግላቸው የካንሰር ታማሚዎች መካከል ወጣት አለኸኝ ቢተው አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ ውልደቱና ዕድገቱ ጎጃም ደብረ ማርቆስ ሲሆን፣ ባጋጠመው የጤና ችግር ምክንያት በአካባቢው ባሉ የተለያዩ የጤና ተቋማት ሲመላለስ ቢቆይም፣ በሽታው ሊታወቅ ባለመቻሉና ሕመሙም እየባሰበትና እየፀናበት በመሄዱ ወደ ባህር ዳር መምጣቱን ይናገራል፡፡

ባህር ዳር የሚገኙ የሕክምና ተቋማትም የበሽታው ዓይነት ካንሰር እንደሆነና ሕክምናውም የሚሰጠው አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሆኑን ነግረውት፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ እየተመላለሰ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡

በአሁኑ ወቅት በየስድስት ወራት በቀጠሮ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እየተመላለሰ የደም ካንሰር የሕክምና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ የሚናገረው ወጣቱ፣ ተማሪ እንደመሆኑና ቤተሰቦቹም አቅመ ደካሞች በመሆናቸው፣ የሕክምና፣ የመድኃኒት፣ የምግብ፣ የመጠለያና የትራንስፖርት ወጪዎችን በመሸፈን ሶሳይቲው ከፍ ያለ ድጋፍ ያደረገለት መሆኑን ይናገራል፡፡ ቀደም ሲል በየአሥራ አምስት ቀናት መድኃኒት ይወስድ እንደነበር፣ አሁን ግን ሕክምናውን ሙሉ በሙሉ በማግኘቱና ሐኪሞች የሚሰጡትን ምክር ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ መድኃኒት መውሰድ እንዳቆመና ከሕመሙ በማገገም ላይ እንደሚገኝም አስረድቷል፡፡

የደም ካንሰር ታማሚ የሆነ የስድስት ዓመት ወንድ ልጇን እያስታመመች በዚህ ማዕከል  ያገኘናት ወ/ሮ ዓለሚቱ ሳሙኤል እንደምትናገረው፣ ልጇ ሕፃን ተካበ እንዳሻው የደም ካንሰር በሽታ እንዳለበት የታወቀው ከስድስት ወራት በፊት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል፡፡

ከሆሳዕና ከተማ መምጣቷን የምትገልጸው ወ/ሮ ዓለሚቱ፣ የልጇ ሕመም የደም ካንሰር መሆኑ ታውቆ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምናውን እስኪጀምር ድረስ በአካባቢዋ በሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት መመላለሷንና የበሽታው ዓይነት ሊታወቅ አለመቻሉን ትገልጻለች፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለአንድ ወር ያህል ልጇ ተኝቶ የደም ካንሰር ሕክምና ጊዜም ሆነ በሳምንት አራት ጊዜ የታዘዘለትን መድኃኒት ግዥ ወጪ እየሸፈነ፣ ለልጇ በሕይወት መቆየት የኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ ከፍ ያለ ድጋፍ እያደረገላት እንደሚገኝ ትናገራለች፡፡ 

አቶ ወንዱ በቀለ የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንስር ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ በደም ካንሰር ሕመም ምክንያት የአራት ዓመት ልጃቸው በሞት መነጠቃቸውን ተከትሎ በደረሰባቸው ሐዘንና ቁጭት ሌሎች ሕፃናትና ዜጎችን ከዚህ በሽታ ለመታደግ ሶሳይቲውን ለመመሥረት መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ትኩረት ሳይሰጣቸው በመቆየታቸው እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ መሆናቸውንና ከእነዚህም መካከል ካንሰር አንዱና ቀዳሚው ነው የሚሉት አቶ ወንዱ፣ ሶሳይቲው ካንሰርን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ከምሥረታው ጀምሮ ትርጉም ያለው ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በካንሰር ሕመም ዙሪያ ላለፉት ሁለት አሠርታት በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኙና የማኅፀንና የጡት ካንሰርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደ አገር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠትና ዕድሜያቸው ከ30 እስክ 49 ዓመት የሆኑ ሴቶች ወደ ጤና ተቋም ሄደው የማኅፀን በር ቅድሚያ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራታቸውንም ይናገራሉ፡፡  

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ የካንሰር ሕመም ተጠቂዎች ለካንሰር ሕክምና ወደ አዲስ አበባ መጥተው በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የመቆያ ቦታ ባለማግኘት ለመጠለያ፣ ለምግብ፣ ለትራንስፖርትና ለሥነ ልቦና ድጋፍ ዕጦት ችግር በሚዳረጉበት ጊዜ፣ ሶሳይቲው ለሕሙማኑና አስተማሚዎቻቸው ሙሉ የትራንስፖርት ወጪዎችን በመሸፈን፣ ነፃ የመኝታና የማረፊያ አገልግሎት፣ እንዲሁም ሕክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች ሲሆን፣ በተጨማሪም ሕሙማኑ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የማይሰጣቸውን/የማያገኙትን የምርመራና የመድኃኒት ወጪዎችንም እንደሚሸፍን ይገልጻሉ፡፡

አቶ ወንዱ እንደሚናገሩት፣ ሶሳይቲው ዕርዳታ ለሚሹ የካንሰር ሕሙማን ተገቢውን ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር፣ ካንሰርን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በሚደረገው አገር አቀፍ እንቅስቃሴ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ጋር በተለይም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ተባብሮ በመሥራት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ነው፡፡

በበለፀጉት አገሮች ቀዳሚ የሞት መንስዔ ካንሰር መሆኑን፣ ይህም ሕመም ለረዥም ጊዜ ያደጉት አገሮች በሽታ ሆኖ ይቆጠር እንደነበር፣ አሁን ግን በታዳጊ አገሮች እየታየ ያለው አዝማሚያ ይህንኑ አካሄድ እየተከተለ መሆኑን የኢፒዲሚዮሎጂ መረጃዎች ይጠቁማሉ ያሉት አቶ ወንዱ፣ ከዚህም በመነሳት ሶሳይቲው ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመተባበር ጤናማ አፍሪካ (Healthy Africa) የተሰኘ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች የልህቀት ማዕከል ፕሮጀክት ለመገንባት ዕቅድ ይዞ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ እየጨመሩና እየተስፋፉ በመምጣት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ የሚገኙትን ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን፣ በተለይም ካንሰርን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ መንግሥት ብቻውን ለመወጣት የማይቻለውን ክፍተቶች በመሙላት ረገድ የልህቀት ማዕከሉ ከፍ ያለ ሚና የሚጫወት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ከ45 በላይ ዲፓርትመንቶች፣ እጅግ ዘመናዊ የምርመራና የሕክምና ማዕከላት፣ የምርመራና የሥርፀት ማዕከል፣ የሕሙማንና ቤተሰቦች፣ እንዲሁም የሐኪሞች ጊዜያዊ ማረፊያ፣ ዘመናዊ የምግብና ካፍቴሪያ አገልግሎት፣ የስፖርትና መዝናኛ ሥፍራዎች የሚኖሩት መሆኑንም አቶ ወንዱ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...