Tuesday, April 23, 2024

አንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ወቅታዊ ቁመና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከሰሞኑ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት ዓውደ ርዕይ መርሐ ግብር በሳይንስ ሙዚየም፣ ‹‹ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ›› በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

የዲፕሎማሲ ሳምንት ፕሮግራሙ ከተቋቋመ 116 ዓመታት ያስቆጠረውን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ሥራና ከዚያም ቀደም ባለው ጊዜ በነበሩት የኢትዮጵያ ነገሥታት የተካሄዱ የውጭ ግንኙነት ክንውኖችን በፎቶ፣ በጽሑፍና በቪዲዮ የሚዳስስ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ዲፕሎማቶች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል፡፡ የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ ታሪክ በማሳየት ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረኮች የተጫወተቻቸውን ሚና ማስተዋወቅ የሚል ትልም የያዘ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ116 ዓመታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ ክብር በዓለም ዙሪያ ሲያስጠብቅ የነበረና የዘለቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ የውጭ ፖሊሲ የአንድ አገር የውስጥ ሁኔታ ነፀብራቅ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ሥነ መንግሥት አሠራር ልምድ ያላትና ሉዓላዊነቷን ሳታስደፍር ነፃነቷን አስከብራ የኖረች አገር መሆኗን፣ ከአገሮች ጋር ያለው ግንኙነት ዘመን ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን በባለብዙ ወገን መድረኮች ለአብነትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረት መሥራች፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ሰነዶች ስምምነቶችና ኮንቬንሽኖች ከመጀመሪያ ፈራሚዎች መካከል ያለች አገር መሆኗን አውስተዋል፡፡

በታሪክ ሒደት ኢትዮጵያን በበጎ የሚያስጠሯት የዲፕሎማሲ ስኬቶችን ያስመዘገበች፣ በመሪዎቿ አማካይነት ተደማጭነት ያላት አገር ሆና ዘመንን እንደተሻገረችና በተዘጋጀው የዲፕሎማሲ ዓውደ ርዕይ ላይ የተመለከቷቸው ለዕይታ የቀረቡ ምሥሎችና ቅንብሮች ትዝታ እንደቀሰቀሱባቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ…›› አሉ ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹…ከሁሉም በላይ ግን ከታሪኩ ጋር ያልታረቀ ሕዝብ ብዙ ሩቅ እንደማይሄድ ያሳየ መሆኑን፣ ታሪክ በጎም መጥፎም ነገሮችን ይመዘግባል፣ ታሪክ በየጊዜው አገሪቱን ያስተዳደሩ ሰዎችን ጭምር ይመዘግባል፣ ታሪክ ይፈርዳል፣ የታሪካችን አካል መሆኑን ግን ምንም ሊለውጠው አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ታሪኩን የካደ፣ ታሪኩን ለመበረዝ የሞከረ፣ ታሪክን ለማጥፋት የሞከረ የሚጠፋም ከሆነ የሞከረ ሕዝብ፣ ታሪኩን መጋፈጥ ያቃተው ነውና መሠረቱ የተናጋ ይሆናል፤›› ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

‹‹ያንኑ ጥፋት እንዳንደግም፣ ወደድንም ጠላንም ከታሪካችን ጋር መታረቅ ብቻ ሳይሆን መማር አለብን፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹በዚህች ምድር ላይ እስካለን ድረስ ከዚህ ለማምለጥ የሚቻል አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገቢውን ተቀባይነትን ለማግኘትና ብሎም ለመደመጥ የጋራ ቤታችንን ማስተካከልም ይጠበቅብናል፡፡ እርስ በርስ እየተዋጋን የውጊያ ዓውድማ ሆነን ዜጎችን እያጣን ወደፊት መሄድና ማደግ አይቻልም፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ‹‹ወይም ደግሞ ሌሎች በሠሩት ጀብድና በቀደዱት ፈር ብቻ በመመካት የዛሬና የነገ የዲፕሎማሲ ሥራ መጠናከር አይችልም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ትውልዶች የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ፕሬዚዳንቷ ዲፕሎማሲ የማይዳሰስ፣ የማይለካ፣ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተከለለ ክበብ ዓይነት አድርገው ለሚወስዱ ሰዎች ፕሮግራሙ ግልጽ ተደርጎ መከፈቱን አድንቀዋል፡፡

ዲፕሎማሲ በአገሮች መካከል ላይ ግንኙነት እንዲኖርና ግንኙነቱ እየዳበረ እንዲሄድ የሚያደርግ ጥበብና ተጨባጭ ተግባር ስለመሆኑ ገልጸው፣ በአገሮች መካከልም መልካም ግንኙነት የሚጀመረው ከጎረቤት በመሆኑ ቅድሚያ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡

ዘመኑ የደረሰበት የሰው ሠራሽ አስተውሎት እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ‹‹ዲፕሎማሲው ከወቅቱ ጋር የሚራመድና የበለጠ ትጋትን የሚጠይቅ በመሆኑ ከፊታችን ያለው ሥራ ቀላል አይደለም፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ዲፕሎማሲ ምን እንደሆነ መረዳት፣ ወደ ሕዝቡ መቅረብ፣ እንዲታወቅ ማድረግና ጥያቄ ካለ እንዲቀርብ ማድረግ በብዙ መንገድ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ብዙ ውጣ ውረድን ያለፈ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ገልጸው፣ ‹‹ለአብነትም ባለፉት ሦስት ዓመታት ተፈትኖ ያለፈ መሆኑን ክፉኛ ተረድተነዋል፤›› ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ታሪክ ሲታወስ በዓለም አቀፍ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ የተከናወኑትን ወሳኝ የዲፕሎማሲ ክስተቶች፣ ከራሷ አልፋ የአፍሪካ ጥቅም አስከባሪ ሆነው ከሚነሱ አገሮች ቀዳሚውን ቦታ የሚሰጣት አገር መሆኗ ይነገራል፡፡

ለአብነት እንኳ ከ1960ዎቹ ዓ.ም. መነሻ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለበርካታ የአፍሪካ ፀረ ቅኝ ግዛትና ፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴዎች ትልቅ ፖለቲካዊ ድጋፍ በመስጠት የምትታወቅ ሲሆን፣ በቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመን በደቡብ አፍሪካ፣ በዚምባቡዌና፣ በናሚቢያ ለነበሩ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ወታደራዊ ሥልጠና፣ ቁሳዊና ዲፕሎማሲያዊ ዕርዳታዎች ያደረገችው አስተዋጽኦ ተሰንዶ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል በቡድን 20 እና ቡድን 8 ስብሰባዎች፣ እንዲሁም ደግሞ በአየር ለውጥ ድርድሮች፣ በአፍሪካና በቻይና የትብብር ፎረም፣ እንዲሁም በአፍሪካ፣ ህንድና ደቡብ ኮሪያ የትብብር መድረኮችና በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያንና አፍሪካን ያልወከለችበት ጊዜ አልነበረም፡፡

የውጭ ግንኙነት ዋነኛ ማጠንጠኛ የሆነውና በሥራ ላይ ያለው ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአገር ውስጥ በሚታዩ የበረቱ የፖለቲካ ውይይቶችና የክርክር ዓውዶች ውስጥ እምብዛም የማይታማና ለክርክር ሲቀርብ የማይስተዋል፣ የበርካታ ተዋንያንን ቀልብ የሚስብ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ስለመሆኑም ይነሳል፡፡ ይሁን አንጂ ለሁለት አሠርት ዓመታት ያገለገለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና፣ በዓለም አቀፍ የኃይል አሠላለፍ ግንኙነቶች መለዋወጥ፣ እንዲሁም በአገር አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች መቀያየር ሳቢያ እንዲሻሻል ማድረግ ማስፈለጉን መንግሥት ከዓመታት በፊት ያስታወቀ ቢሆንም እስካሁን ተሻሽሎ ወደ ሥራ አልገባም፡፡

 የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው አለመሻሻሉ አሁን ዓለም ከደረሰበትና  ከወቅቱ ውጭ ግንኙነት ዳራ ጋር ሊራመድ የሚችልና በዓለም መድረኮች እኩል ተዋናይ የሚያደርግ ፖሊሲ አስፈላጊነቱን በመጥቀስ፣ በሥራ ላይ ያለው ሰነድ እንዲሻሻል ከዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሲነሱ ይደመጣል፡፡

በሌላ በኩል በሥራ ላይ ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚኖርን ግንኙነት በተለየ ሁኔታ ትኩረት የሚሰጥና ግንኙነቱን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንደሚመራው ይገልጻል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በተለይም የኤርትራ ሠራዊት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መሳተፍ፣ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ መግባት፣ የሱዳን ጦርነት ተሳታፊ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው የተለያየ ግንኑነት፣ በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለው የደበዘዘ ግንኙነት፣ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የፈረመቸው የባህር በር የማግኘት ስምምነትና በሶማሊያ በተፈጠረው የፖለቲካ ግለት የተነሳ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር አብሮ ከመኖር ይልቅ ወደ መነቋቆር መግባቷን በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማጠንጠኛ አንዱ የሆነውን ለጎረቤት አገሮች የሚሰጥ የተጋመደ ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ ስለመግባቱ ሲነሳ ይደመጣል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ በደርግ ዘመነ መንግሥት በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ የደኅንነት ምክትል ሚኒስትርና የኢንተለጀንስ ከፍተኛ ባለሙያ የነበሩት አስማማው ቀለሙ (ዶ/ር)  ለሪፖርተር ሲናገሩ፣ ከዚህ ቀደም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደበርና የብሔራዊ ደኅንነት፣ አንድነትና ጥቅም፣ እንዲሁም ብሔራዊ ልማትን ለመጠበቅ ዲፕሎማሲ ዋነኛ ሚና ተጫውቷል ይላሉ፡፡

 በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አቅምና ቁመና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን ነፃ ለማውጣትና ለማደራጀት፣ የአፍሪካ አንድነትን ለማቋቋም ትልቅ ሚና ነበረው ብለዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት የነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ግምት ውስጥ በማስገባት የአገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ ከአንድ ሚኒስቴር ይልቅ እንደ አገር ታስቦበት ትልቅ ሥራ ስለመሠራቱም ያስረዳሉ፡፡

 በዚህም የተነሳ አገሪቱ ከፍተኛ ተደማጭነትና ተሰሚነት እንደነበራት አውስተው፣ እንደ እነ አቶ አክሊሉ ሀብተወልድና አቶ ከተማ ይፍሩን የመሳሰሉ ታላላቅ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በውጭ ጉዳይ ሥራ ላይ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ያስታውሳሉ፡፡  አክለውም በደርግ ጊዜም ይሁን በኢሕአዴግ ዘመን በውጭ ጉዳይ የተሠራው ሥራ ቀላል አልነበረም የሚሉት ምሁሩ አሁንም ቢሆን የማይካዱ እሴቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በማቋቋም ብቻ ዲፕሎማሲ አይሠራም የሚሉት አስማማው (ዶ/ር) ይልቁንም በውጭ ግንኙነት ስራ ሦስት ቁልፍ ጉዳዮች የግድ መኖር እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ የመጀመርያ ቁልፍ ያሉት ጉዳይ በአገር ውስጥ ያለው የአመራርና የሕዝብ ግንኙነት መጣጣምና አንድነት ወይም ጥንካሬ መኖር፣ ለአገሩና ለአካባቢው የሚቆረቆር አመራር ሲፈጠርና መሪውን የሚደግፍ ሕዝብ ሲኖር በውጭም ተደማጭነት ይኖራል ይላሉ፡፡ በዚህ ውስጥ በሕዝብና አመራር መካከል የሚኖረው መሰላሰል የውጭ ጉዳይ ሥራ ጥንካሬና ተፈሪነት እደሚኖረው ያብራራሉ፡፡

በሁለተኛው ደረጃ ትልቁ ጉዳይ ያሉት የአገር ስትራቴጂክ ሀብትና ጂኦግራፊካዊ አቀማመጥ ሲሆን፣ ለምሳሌ በውጭ አገር የማይገኙ ማዕድናት፣ የባህር ወደብና መሰል ሀብቶች ሲኖሩ በአገሮች ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት አለመፍጠር ማለት ትልቅ ነገር ማጣት መሆኑን ይረዳሉ ይላሉ፡፡

ሦስተኛው ጉዳይ የውጭ ደጋፊ ኃይል መኖር መሆኑንና ለምሳሌ በአሜሪካ፣ በቻይና፣ በሌሎች አገሮች፣ በቀጣናዎችና በዓለም አቀፋዊ ኃይሎች ዘንድ የፖለቲካ ተፅዕኖ (Sphere of Influnce) ሲኖሩ የመደገፍ ዕድል ይጨምራል በማለት ያክላሉ፡፡

ይሁን አንጂ እነዚህ ሦስት ቁልፍ ጉዳዮች በማይኖሩበት ወቅት አንድ ችግር ውስጥ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት ኢትዮጵያ በደርግ ወቅት የሶሻሊስት ወንድማማችነት በሚለው ውስጥ የዓለም አቀፍ ሶሻሊዝም አካል ስትሆን፣ የሶሻሊስት አባል አገሮች ድጋፍ እንደሰጧትና ማንም ሊያጠቃ ሲመጣ አለን ከጎንሽ ነን ይሉ እንደነበር አውስተው፣ የጠቀሷቸው ጉዳዮች በሌሉበት ግን ዲፕሎማሲ ዋጋ የሌለው ነገር ነው ብለዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የደሃ አገሮች 80 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት በዲፕማሲ ጥረት በሚመጣ የውጭ የብድር አቅርቦትና የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስማማው (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያም እነዚህ ነገሮች ሊሳኩ የሚችሉት በአገር ውስጥ ሰላምና የፖለቲካ ድጋፍ ሲኖር ቢሆንም፣ አሁን የሚታየው ግን ይህ የሌለ መሆኑንና ዲፕሎማሲውም መጎዳቱን ማሳያ ነው ይላሉ፡፡

ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጥንካሬና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከላይ የጠቀሷቸው ሦስቱ ጉዳዮች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለአብነት የውስጥ ሰላም ዕጦት የሚያመጣውን የውጭ ጫና ሲያብራሩ ሶማሌ በኢትዮጵያ ሦስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ወረራ ስትፈጽም በሦስቱም ጊዜ የውስጥ ድካም መኖሩን ዓይተው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የመጀመርያው በደርግ ጊዜ የመንግሥት ግልበጣ ሲሞከር መንግሥት ተዳክሟል፣ ወታደሩ ተዳክሟል፣ አንድነቱ ተዳክሟል ብለው ወረራ አደረጉ፡፡ ከዚያ በፊትም የእነ መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በተደረገበት ወቅት ሶማሌ የመጀመርያውን ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ማድረጓን ያስታውሳሉ፡፡ በተመሳሳይ በሱዳን በኩል የታየውም ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን የጦርነት አጋጣሚ በመጠቀም 58 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ገብተው የጦር ኃይል ማስፈራቸውን፣ አሁንም ቢሆን ሱዳን በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መሆኗ እንጂ ኢትዮጵያ ገብታ ወረራ የማትፈጽምበት ሁኔታ አይኖርም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በዚህ ሁሉ የምንረዳው ነገር ትልቁ ኃይል የውስጥ ሰላምና አንድነት መፍጠር ለዲፕሎማሲ ትልቁ ጉዳይ ስለመሆኑ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ አሁን ከአጎራባች አገሮች ጋር የሚታወየው የግንኙነት መልክ ታይቶ አይታወቅም ያሉት አስማማው (ዶ/ር)፣ ‹‹ምናልባት ከጅምሩ ለኢትዮጵያ አጎራባች የነበሩት ቅኝ ገዥዎች በተለይም ጣሊያኖች፣ ፈረንሣዮችና እንግሊዞች ነበሩ፡፡ እነሱ ጋር ተዋግተን ድንበራችን አስከብረን ኖረናል፡፡ አገሮቹ ነፃ ከወጡ ወዲህ ግን አሁን ያለንበት አገራዊ ውስጣው ሁኔታ አንድነት፣ መረጋጋትና ሰላም በማጣታችን ለዚህ ሁሉ ተግዳሮት ፈጥሮብናል፣ ድክመታችንም ይኼው ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከኤርትራም፣ ከሶማሊያም፣ ከሱዳንም ሆነ ከኬንያ ጋር ያለው የውጭ ግንኙነት አሥጊ መሆኑን ገልጸው ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የተዋጋችው ጦርነት ለኬንያም ጭምር እንደነበር አብራርተዋል፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ አልሸባብ መጀመሪያ ያጠቃው ኬንያን እንጂ ኢትዮጵያን እንዳልነበረና ብዙ ውድመት ያደረሰው በኬንያ ላይ ነበር ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የጎረቤቶቿን ሰላም የምትፈልገው ኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል ልካ ሰላም ለማስጠበቅ መሥራቷን ተናግረዋል፡፡ በተቃራኒው አሁን ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር እንዳልሆነች በምታወጣቸው መግለጫዎች እየታዩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ያላትን ግንኙነት መመርመርና ማየት፣ የዲፕሎማቲክ ዘዴዎችን መዳሰስና መፈተሽ ያስፈልጋታል፡፡ ይህን ካላደረግን ግን ለአገሪቱ ከባድ ኪሳራ የሚያመጡ ነገሮች ይፈጠራሉ ብዬ እሠጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በውጭ ግንኙነት ረገድ ወዳጅ አመራረጥና ከየትኛው ወገን ጋር መወዳጀት እንዳለባት ታውቅበት ነበር የሚሉት አስማማው (ዶ/ር)፣ ‹‹አሁን ከየትኛውም ወገን ጋር የሆንን አይመስለኝም፤›› ይላሉ፡፡ ከአንዱ ወይም ከሁለቱም ለመሆን የዲፕሎማሲ ጥበብ ያስፈልጋል የሚሉት አስማማው (ዶ/ር)፣ ‹‹አሁን የሆነ አገር ከኢትዮጵያ ጋር ነው ለማለት የምችልበት ሁኔታ ላይ አይደለሁም፤›› ብለዋል፡፡ የውስጥ አንድነትን አስጠብቆ በመሄድ ይህንን የወዳጅነት ሚዛን መጠበቅ እንደሚቻል፣ ነገር ግን በውስጥ ያለው ሰላም እየራቀን ከሄደ ወዳጆቻችን እየራቁ መሄዳቸው አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ የሺጥላ ወንድሜነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የውጭ ግንኙነት የሚመራበት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በ2002 ዓ.ም. ወጥቶ የነበረ ቢሆንም የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት በ2010 ዓ.ም. ይሻሻላል የሚል ቃል ተገብቶ ነገር ግን እስካሁን አለመሻሻሉን ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለይተው እንዳያውቁ፣ ተልዕኳቸውን በግልጽ እንዳይረዱና ወደ ተልዕኮ ሲሄዱ የሚላኩበትን ሚና ሳይረዱ ምን እንደሚሠሩና የተላኩበትን ሥራ እንዴት እንደሚያስፈጽሙ ሰነድ አልባ እንደሚሆኑ ይናገራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ፖሊሲው ተሻሽሎ ለሕዝብ ይፋ ባይደረግም ለዲፕሎማቶች ተቆንጥሮ የሚሰጥና ለሥራቸው የሚሆን አጭር ሰነድ መሰጠቱ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ተሻሽሎ አለመውጣቱ ለኢትዮጵያና ለዲፕሎማቶች ውጤታማነት ከተቀመጠው ግብ አንፃር አሳክተዋል ወይም አላሳኩም የሚለውን መለካትና መገምገም እንደማይቻልና የተጠያቂነት ጉዳይን የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ፖሊሲው የጎረቤት አገሮችንም ሆነ ቀጣናዊ ኃይሎችንና ኃያላን አገሮች ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ ምን ዓይነት ትልም እንዳላት፣ ምን ማድረግ እንደምትፈልግ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ በምን መልኩ መሳተፍ እንደምትፈልግ ግልጽ ሥዕል የማያስቀምጥ በመሆኑ፣ የተሻሻለና ወቅቱን የጠበቁ ፖሊሲ በሌለበት ግን ይህ የኢትዮጵያ አቋም በግልጽ ያልታወቀ (Gray area) እንደሚሆን ያስረዳሉ፡፡

ያልተሻሻለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መጀመሪያ ሲወጣ የነበሩት ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣሙ መሆናቸውን፣ በሥራ ላይ ያለው የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ለአሁኑ ሥራ አመቺና አራማጅ ያልሆኑ ጉዳዮች እንዳላቸው የሚገልጹት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ ለአብነትም በቀደመው ፖሊሲ ኤርትራን እንደ ትልቅ ባላንጣ በመግለጽ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነትን መበየኑን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት አሁን ጥያቄ ውስጥ ቢገባም፣ ከዓመታት በፊት በነበረው ለውጥ የተሻለና ወዳጅነት የተፈጠረበት፣ ነገር ግን ፖሊሲው ያልተቀረፈና ባላንጣ አድርጎ ያስቀመጠበት ወቅት እንደነበር አውስተዋል፡፡ ስለዚህ ከአንድ አገር ጋር ከባላንጣነት ወደ ወዳጅ ስትመጣ ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት ተብራርቶ በግልጽ መቀመጥ አለበት ብለዋል፡፡

አንድ ፖሊሲ ከአሥር ዓመት በላይ አገልግሎት መስጠት የሌለበት ቢሆንም አሁን ላይ በርካታ ዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ለውጦች በመምጣታቸው ለምሳሌ የወደብ ፖለቲካውና በሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመታሰቡ በፊት የነበረ መሆኑ፣ የአገሪቱ ፍላጎትና ሥምሪት እንደ አዲስ ተፈትሾ የውጭ ግንኙነት የመጫወቻ መንገዱ መገለጽ አለበት ብለዋል፡፡

የሺጥላ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከዓባይ ወንዝ ጋር የተጠላለፈ ፖለቲካ እንዳልነበርና ከኤርትራ ውጪ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንዳልነበራት አውስተው፣ የአፍሪካ ቀንድ ዋነኛ የሰላም መሪ (Anchor) እና የአፍሪካ መቀመጫም እንደመሆኗ ከሕዝብ ብዛቷም አንፃር ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆና መቆየቷን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከህዳሴው ግድብ ግንባታ በኋላ በተለይ ከዓባይ ውኃ ጋር በተገናኘ በቀጣናው መጠላለፍ መታየቱን፣ በተለይ ኢትዮጵያ ከአልበሽር መውረድ በኋላ ከሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት እየቆየ መበላሸቱንና ግብፅ ከጀርባ እየነካካች ፀብ ውስጥ እንደከተተቻት፣ ከሶማሊያ ጋር ያለው ግንኙነት ከዕለት ወደ ዕለት እየተበላሸ አሁን ወደ ለየለት ደረጃ መውረዱ፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው ሰላም ቀርቶ ወደ ባላንጣነት የመግባት አንድምታ መታየቱ በዋነኝነት ቀጣናው ላይ ካለው የጂኦ ፖለቲካው ፉክክርና ጣጣ ጋር የተገናኘ ነው ይላሉ፡፡

በቀደመው ጊዜ ኢትዮጵያ ኃላፊነት የሚሰማት ቀጣናውን የምታረጋጋ ለምሳሌ በሱዳን በሶማሌ ችግር ሲፈጠር አረጋጊ ተብላ የነበረችው አሁን ግን በጂኦ ፖለቲካው አለመረጋጋት ፉክክርና መጠላለፍ ምክንያት፣ ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ከማምጣት ባለፈ ኃላፊነት የማይሰማትና ረባሽ አገር ተብላ መፈረጇን ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም በአገር ውስጥ የሚታየውን ችግር መፍታትና በጂኦ ፖለቲካው እንዴት መጫወት እንዳለበት የሚናገሩት የሺጥላ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከግብፅ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከምዕራቡ ዓለምና ከምሥራቁ ዓለም ጋር የምታደርጋቸው ግንኙነቶች ጥበብ በተሞላበት መንገድ የማይከናወኑ ከሆነ ከጎናችን ይሆናሉ ተብለው የሚታሙ አገሮችም የበለጠ ጠላትና ባላንጣ እንደሚሆኑ ይገልጻሉ፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው ኢትዮጵያን በማግለል መጠቀሚያ ያደርጓታል ብለዋል፡፡ ከማን ጋርና በምን መልኩ እንደምትጫወት፣ ከትኞቹ ኃይሎች ጋር መሠለፍ እንደምትፈልግ የምትመራበት ሰነድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአገሮች ጋር ያላት ግንኙነት የዲፕሎማሲ ጥበብ ያስፈልገዋል የሚለውን በተደጋጋሚ የሚናገሩት የሺጥላ (ዶ/ር)፣ በቀደማዊ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን የጎላ አሠላለፍን በማየት ወዳጅን የመለየትና የማበጀት አዝማሚያ እንደነበር ነገር ግን ኢሕአዴግ እንደመጣ የነበረው ምሥራቅና ምዕራብ አሠላለፍ በመፍረሱ ምክንያትና አሜሪካ ብቻ ጎልታ የወጣች በመሆኗ፣ ኢሕአዴግ ከአሜሪካም ከሌሎቹም አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማስቀጠል መቻሉን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ላይ የተፈጠረው አዲስ የጎራ አሠላለፍ እንደ አዲስ በማንሰራራቱና አሜሪካ በአንድ በኩል፣ ቻይና በሌላ በኩል፣ ሩሲያ በሌላ በኩል፣ ሌሎችም እንዲሁ በመሠለፋቸው የአሁኑ መንግሥት የኢሕአዴግን ዓይነት አሠላለፍ አይፈቅድም  ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለውጥ መጣ በተባለበት ወቅት ከምዕራባውያኑ ጋር አሁን ደግሞ ከምዕራቡም ከምሥራቁም  የማይመስል ግንኙነት ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡

ከብሪክስ ጋር ያለው ግንኙነት ወደፊት እንዴት እንደሚሄድ አሁን አይታወቅም የሚሉት የሽጥላ (ዶ/ር)፣ በአጠቃላይ የአገሪቱን የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ተንትኖ የሚያቀርብ ፖሊሲና የአገሪቱን ጥቅም በሚገባ የሚያውቅ ለዚህም መከበር የሚሠራ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -