Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየባህር ማዶ ሙዚየሞች የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች የሚመልሱት መቼ ነው?

የባህር ማዶ ሙዚየሞች የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች የሚመልሱት መቼ ነው?

ቀን:

በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ ምክንያቶች የአገራችን ቅርሶች ከአገር ወጥተዋል፡፡ ከእነዚህ ከወጡት ቅርሶች አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት በ1860 ዓ.ም. በመቅደላ ጦርነት ወቅት በእንግሊዞች የተዘረፉት ናቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰበሰቧቸውን ቅርሶች በመቅደላ አስቀምጠው ስለነበር በጦርነቱ ወቅት በብዛት ሊዘረፉና ሊወሰዱ ችለዋል፡፡

በመቅደላ ጦርነት ከ250 በላይ በሚሆኑ ዝሆኖች ተጭነው ከተወሰዱት ታሪካዊ ቅርሶች፣ መካከል ብራናዎች፣ ታቦታት፣ የወርቅና የብር መስቀሎች፣ ዘውዶች፣ አልባሳትና ሌሎችም ቅርሶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ከ156 ዓመታት በፊት ከመቅደላ የተዘረፉና በተለያዩ ግለሰቦች እጅ ይገኙ የነበሩ ቅርሶች ቅዳሜ ታኅሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በብሔራዊ ሙዚየም ርክክብ ተደርጎላቸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የባህር ማዶ ሙዚየሞች የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች የሚመልሱት መቼ ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ታሪካዊ ቅርሶቹን የቅርስ ባለሥልጣን በተረከበበት ጊዜ
ፎቶ ቅርስ ባለሥልጣን

በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) እንዳሉት፣ የአገሪቱ ታሪካዊ ቅርሶች በተለያዩ ጊዜያት ከአገር ተዘርፈው በውጭ አገር ሙዚየሞች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ቅርሶች መካከል ደግሞ በ1860 ዓ.ም. በመቅደላ ጦርነት ተዘርፈው በእንግሊዝ አገር የሚገኙት አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡

እነዚህን በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ቅርሶች ለማስመለስ ከአፄ ዮሐንስ 4ኛ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ልዩ ልዩ ጥረቶች የነበሩ ቢሆንም የተፈለገውን ያህል ግን ርቀት መጓዝ አልተቻለም፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የእንግሊዝ መንግሥት፣ ‹‹በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አገር ውስጥ የገቡ ቅርሶች የእንግሊዝ ቅርስና ሀብት ናቸው፤›› የሚል አሳሪ ሕግ ስላለው ቅርሶችን ለማስመለስ በየዘመኑ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቅርሶች ወደ አገር እንዲመለሱ ማድረጉ በተለያዩ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና በእንግሊዝ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅንጅታዊ ሥራ በመሠራቱ ጥቂት የማይባሉ ቅርሶች በመመለስ ላይ ናቸው፡፡

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ሼሄራዝድ ፋውንዴሽን ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር ከሦስት ዓመት በፊት አሥራ ዘጠኝ የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶችን ወደ አገር እንዲገቡ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ ተዘርፈው በእንግሊዝ ከሚገኙና ወደ አገር ከተመለሱ ቅርሶች መካከል አብዛኞቹ ከሙዚየሞች ሳይሆን ከግለሰቦች እጅ የተገኙ መሆናቸውን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አገር የተመለሱት የቀንድ ዋንጫዎች፣ ታሪካዊ ጋሻና ሕይወታቸው በዚያው ያለፈው የልዑል ዓለማየሁ ለለላ ፀጉር ፈቃደኛ ግለሰቦች ያስረከቧቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመቅደላ ጦርነት ወቅት ከአገር የተዘረፉና በሙዚየሞችና በአብያተ መጻሕፍት፣ በግለሰቦችም እጅ የሚገኙትን ታሪካዊ ቅርሶች ለማስመለስ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ቅርሶቹን ወደ አገር የማስመለሱ ጥረት ውጤት እያመጣ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

አሁን ወደ አገር ከተመለሱት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች መካከል አንድ ታሪካዊ ጋሻ፣ ሦስት በብር የተለበጡ የቀንድ ዋንጫዎች፣ የልዑል ዓለማየሁና የሞግዚቱ የካፒቴን ስፒዲ ዘለላ ፀጉሮች (በስጦታ የተገኙ) ስለ ልዑል ዓለማየሁ የተጻፉ ደብዳቤዎች መሆናቸውንና እነዚህም ቅርሶች በሁለተኛ ዙር ወደ አገር የገቡ ናቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች ወደ እናት አገራቸው ለመመለስ በቀጣይም ኤምባሲው ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራና ከንጉሣውያን ቤተሰቦች ጋር በመነጋገር፣ እንደ ሼሄራዝድ ካሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ከግለሰቦችና ከኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ጋር ኤምባሲው በትብብር እየሠራ እንደሚገኝም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

የልዑል ዓለማየሁና የካፒቴን ስፒዲ የፀጉር ዘለላን ለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያስረከቡት የካፒቴን ስፒዲ ቤተሰቦች መሆናቸውን የተናገሩት የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ፀጉሮቹ የተገኙት በፖስታ ታሽገውና ስም ተጽፎባቸው እንደሆነ፣ በቀደመው ጊዜ በንጉሣውያን ቤተሰቦች ዘንድ ፀጉር በሚቆረጡበት ወቅት ማስታወሻ የማስቀመጥ ልማድ የነበረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ካፒቴን ስፒዲ ልዑል ዓለማየሁን በሞግዚትነት ተቀብሎ ያሳደገና ከአገር አገር ሲዘዋወርም ይዞት የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የስፒዲ ፀጉርም ከዓለማየሁ ፀጉር ተነጥሎ መቀመጥ የለበትም በማለት ቤተሰቦቹ ወስነው ቅርሱን አብረው ያስረከቡ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

ወደ አገር ከገቡትና በብሔራዊ ሙዚየም ርክክብ ከተደረገላቸው ታሪካዊ ቅርሶች መካከል በሦስቱ የቀንድ ዋንጫዎች ላይ ቅርሶቹ የመቅደላ ስለመሆናቸው ማስታወሻ ተጽፎባቸው የተገኘ መሆኑንም አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በብሪትሽ ሙዚየም ከአገራችን የተዘረፉ አሥራ አንድ ታቦታት በምድር ቤት ውስጥ ተቆልፎባቸው እንደሚገኙና እነዚህን ቅርሶች ለማስመለስና ወደ አገር ቤት ለማምጣት የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከእንግሊዝ ኤምባሲና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በጥምረት እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

በመቅደላ ጦርነት ወቅት የአፄ ቴዎድሮስን መስዋዕትነት ተከትሎ በ1860 ዓ.ም. በእንግሊዝ ወታደሮች ከመቅደላ አምባ የተዘረፉት ቅርሶች ከሁለት ሺሕ በላይ ሲሆኑ፣ በተለይ ከአምስት መቶ በላይ የጽሑፍ ቅርሶች (ብራናዎች)፣ የተለያዩ የወርቅና የብር መስቀሎች፣ የንጉሣውያን የወርቅ ዘውዶችና ጌጣጌጦች፣ አልባሳት፣ ጽላቶችና ሌሎችም የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶች በእንግሊዝ የተለያዩ ሙዚየሞችና በግለሰቦች እጅ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

የልዑል ዓለማየሁ ፀጉርና በመቅደላ ጦርነት የተዘረፉ ቅርሶች አቀባበልና ርክክብ ላይ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...