Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአዲስ አበባ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረው የስደተኞች ምዝገባ በአፋጣኝ እንዲጀመር ኢሰመኮ አሳሰበ

በአዲስ አበባ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረው የስደተኞች ምዝገባ በአፋጣኝ እንዲጀመር ኢሰመኮ አሳሰበ

ቀን:

  • በርካታ ኤርትራውያን ለእስራትና ለእንግልት መዳረጋቸው ተገልጿል

በአዲስ አበባ ከተማ ሲከናወን የነበረው የስደተኞች ምዝገባ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በመቋረጡ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠለሉ በርካታ ኤርትራውያን የመዘዋወር መብታቸው መገደቡን፣ የተወሰኑት ደግሞ ለእስራት መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡ ከሁለት መቶ በላይ ኤርትራውያን በሕይወታቸው ላይ አደጋ ሊደርስ ይችላል ብለው ወደ የሚሠጉባት ኤርትራ በግዳጅ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ከ2014 ዓ.ም. እስከ 2015 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የመጀመሪያውን የስደተኞችና የጥገኝነት ጠያቂዎች ሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ የሚዳስስ ባለ 47 ገጽ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት፣ ከትናንት በስቲያ ታኅሳስ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ይፋ አድርጓል፡፡

ሪፖርቱ የስደተኞችና የጥገኝነት ጠያቂዎችን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ የተለዩ ያላቸውን መልካም ጅማሮዎችና አሳሳቢ ሁኔታዎችን ያካተተ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት መካከል ግንኙነት ከተጀመረ በኋላ፣ በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች ኢትዮጵያ መግባታቸውን አስታውሷል፡፡ ነገር ግን ለስደተኞቹ የሚደረገው ምዝገባ በመቋረጡ በአሁኑ ጊዜ ኤርትራውያን ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

በአሁኑ ጊዜ ኤርትራውያኑ ‹‹ማስረጃ የላችሁም›› በሚል ምክንያት ለእስር መዳረጋቸውን፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸው መገደቡን፣ ለስደተኞች የሚደረገው ጥበቃና ከለላን ጨምሮ ላሉባቸው ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት አደጋ ውስጥ መውደቁን ተረድቻለሁ ብሏል፡፡ ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወይም ፍልሰተኞች መሆናቸው በአግባቡ ሳይጣራና ጉዳያቸው በሕግ አግባብ ሳይታይ፣ እንዲሁም ወደ መጡበት አገር ቢመለሱ ሊደርስባቸው የሚችለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሳይጠና መሆኑን በመግለጽ፣ ድርጊቱ ተገዶ ካለመመለስ መርህ ጋር የሚጣረስና ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን የዓለም አቀፍ ሕጎችን ያላከበረ መሆኑን ኮሚሽኑ አክሏል፡፡

ለስደተኞች የሚደረገው የምዝገባና የሰነድ አገልግሎት ተቋርጦ በነበረበት ወቅት፣ ኤርትራውያኑ ተገደው ወደ መጡበት አገር እንዲመለሱ መደረጉ ኮሚሽኑ ከለያቸው አሳሳቢ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች አንዱ መሆኑን ገልጾ፣ በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. በስደተኞችና በጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የዘፈቀደ እስር እንዲቆም ጥሪ አቅርቦ እንደነበር አስረድቷል፡፡

ኢሰመኮ በክትትልና በምርመራ ሥራው በ17 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችና ሳይቶች፣ ከ650,000 በላይ በሚሆኑ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ክትትልና ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል በሚገኙት ቡርአሚኖና ሄላወዪን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች፣ ከዚህ በፊት ለሶማሊያ ስደተኞች ይሰጥ የነበረው የመታወቂያ ካርድ አገልግሎት በመቋረጡ፣ አብዛኛዎቹ ስደተኞች መታወቂያ ስለሌላቸው በነፃነት መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ገልጿል፡፡ መታወቂያ የተሰጣቸው ስደተኞችም መታወቂያቸው የአገልግሎት ጊዜው ስላለፈበት እንዲታደስላቸው ቢጠይቁም፣ ምላሽ አለማግኘታቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በጎረቤት አገሮች በተከሰቱ መጠነ ሰፊ ግጭቶች ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም፣ አዳዲስ ስደተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ተገቢው ጥበቃ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የስደተኞችና የተመላሾች አገልግሎት ለስደተኞች የመታወቂያ ዕድሳት፣ እንዲሁም አዲስ መታወቂያ መስጠት መጀመሩን ያሳወቀ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባ የአሁኑ ሪፖርቱ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ አለመጀመሩን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የመታወቂያ ካርድ አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት የተወሰኑ ስደተኞች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ለእስር እየተዳረጉ መሆኑን፣ ሕጋዊ ሰነዶችን ለማግኘት በሚፈጠረው ችግር ሳቢያ የተወሰኑ ስደተኞች ሐሰተኛ የቀበሌ መታወቂያና የሪፈራል ሕክምና ወረቀት በመጠቀም ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ለመንቀሳቀስ ጥረት እንደሚያደርጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ስደተኞች ውስጥ መታወቂያቸው ያልታደሰ ከቦታ ቦታ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ከመገደቡ በተጨማሪ፣ ለእስራት መዳረጋቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

ኢሰመኮ በአዲስ አበባ ከሦስት ዓመታት በላይ ተቋርጦ የቆየው የስደተኞች ምዝገባ በአፋጣኝ እንዲቀጥልም አሳስቧል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ900 ሺሕ በላይ የውጭ ስደተኞች መካከል የደቡብ ሱዳን 417,419 (45 በመቶ)፣ የሶማሊያ 302,195 (31 በመቶ)፣ የኤርትራ 167,391 (18 በመቶ)፣ የሱዳን 50,564 (5 በመቶ)፣ የኬንያ 4,034 (1 በመቶ) መሆናቸው ይነገራል፡፡

በኮሚሽኑ መረጃ መሠረት የስደተኞች ብዛትና አሠፋፈር በክልሎች ሲታይ ጋምቤላ 383 ሺሕ፣ ሶማሌ 301 ሺሕ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 79 ሺሕ፣ አዲስ አበባ 76 ሺሕ፣ አፋር 58 ሺሕ፣ አማራ 22 ሺሕ፣ በተለያዩ ሥፍራዎች 14 ሺሕ፣ በቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አምስት ሺሕ፣ በኦሮሚያ አራት ሺሕ፣ በትግራይ ሁለት ሺሕ ናቸው፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚያስረዳው ለሴቶች፣ ለሕፃናት፣ ለአረጋዊያንና ለአካል ጉዳተኞች የሚደረገው ድጋፍ የጤና ሁኔታን፣ ዕድሜን፣ ፆታን፣ እንዲሁም የአካል ጉዳትን ከግምት ያላስገባ ከመሆኑም በላይ፣ በመንግሥትም ሆነ በተራድኦ ድርጅቶች የሚቀርበው ድጋፍ በመጠንም ሆነ በዓይነት እጅግ አነስተኛ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...