Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገንዘብ ሚኒስቴር ከ79 ሺሕ በላይ ቤቶችን ለማስገንባት አቅም ላላቸው አልሚዎች ጥሪ አቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የመጀመሪያዎቹ ቤቶች ለኢቢሲና ለቤቶች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች ይተላለፋሉ

በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር ያለው የመንግሥትና የግል አጋርነት ዲፓርትመንት 79,800 ቤቶችን ለማስገንባት አቅም ላላቸው አልሚ ድርጅቶች ጥሪ አቀረበ፡፡ ቤቶቹ በአብዛኛው ለመንግሥትና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞች እንደሚገነቡ ታውቋል፡፡

የገንቢዎችን አቅም ለመለካት የወጣው የተወዳዳሪነት መጠየቂያ (Request for Qualification) እንደሚያመለክተው፣ ገንቢዎች በራሳቸው የፋይናንስ አቅም ቤቶቹን ዲዛይን ማድረግ፣ መገንባት፣ መሠረተ ልማትና አገልግሎት ማቅረብ፣ ማስተዳደርና ጥገና ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመንግሥትና በግል አጋርነት አሠራር መሠረት፣ መንግሥት የአልሚዎቹን ወጪ ከቤቶቹ ተጠቃሚዎች በሚሰበስበው ገንዘብ ይሸፍናል ተብሏል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር በመንግሥት አሠራር መሠረት ቤቶቹን ገንብተው ለማቅረብ ፍላጎት ያሳዩ አልሚዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን፣ እስከሚቀጥለው ወር ድረስ የመወዳደሪያ ሰነዱን የማይመለስ አሥር ሺሕ ብር እየከፈሉ ከራሱ በመግዛት መወዳደር ይችላሉ ብሏል፡፡ ለዚሁ ሥራ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አልሚዎች የተጋበዙ ሲሆን፣ ሁለቱ በመጣመር መወዳደር እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ የሚኒስቴሩ ሰነድ እንደሚያሳየው ከሆነ ከፍተኛ የቤት ፍላጎትና የአቅርቦት ክፍተት መኖሩን፣ ይህንን ችግር ለማቃለል ብሔራዊ የመንግሥትና የግል አጋርነት ምክር ቤት በአፋጣኝ የ79,800 ቤቶቹን ግንባታ አፅድቋል፡፡

ከሚገነቡት ቤቶች ውስጥ በቅድሚያ የሚያልቁት 1,600 ቤቶች ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች፣ እንዲሁም 2,000 ያህሉ ደግሞ ለኢቢሲ ሠራተኞች ይሰጣሉ ተብሏል፡፡ በተለይ የኢቢሲ ሠራተኞች፣ ‹‹ለረዥም ዓመታት ቤት ይሰጣችኋል ብንባልም ዘግይቷል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥትና የግል አጋርነት አሠራርና አዋጅ በ2010 ዓ.ም. ያፀደቀ ቢሆንም፣ በዚህ አሠራር እስካሁን የተሳካ ፕሮጀክት የለም፡፡ የአዳማ-አዋሽና የሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገዶችን፣ እንዲሁም የፀሐይና የኃይድሮ የኃይል ማመንጫዎችን ጨምሮ፣ አሥራ ሰባት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በአጋርነት ለመገንባት ተይዞ የነበረው ዕቅድም ሳይሳካ  መቅረቱ ይታወሳል፡፡

በተለይ የውጭ ባለሀብቶች በመንግሥትና በግል አጋርነት አሠራር ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የውጭ ምንዛሪ ዋስትና ሲጠይቁ የቆዩ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሚቀርበው ዝቅተኛ የታሪፍ ድርድር ዋነኛው የችግሩ መንስዔ ነበር፡፡

እነዚህን ችግሮችና ሌሎች ለመንግሥትና ለግል አጋርነት አተገባበር የሚያስፈልጉ ሕጎችን በማካተት አዋጁ ባለፈው ዓመት ተሻሽሎ በፓርላማው የፀደቀ ሲሆን፣ የ79,800 ቤቶችም ግንባታ በአዲሱ አዋጅ የሚተገበር የመጀመሪያው ፕሮጀክት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቤቶቹ በተለያዩ ኮንትራክተሮች ተከፋፍለው ይገነባሉ ተብሏል፡፡ በቀጣይ ሆስፒታልን ጨምሮ ሌሎች መንግሥት ብቻውን ፋይናንስ ማድረግ ያልቻላቸው ፕሮጀክቶች፣ በመንግሥትና በግል አጋርነት ለመገንባት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ በዚህም መንግሥት እያጋጠመው ያለውን ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ያቃልላል ተብሎ ተስፋ ተጥሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች