Wednesday, June 19, 2024

የአገር ገጽታ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ይደረግ!

መልካም ተግባራት ሲከናወኑ ለአገር ጠቃሚ በመሆናቸው ይበል ማለት ቀድሞም የነበረ፣ አሁንም ያለና ወደፊትም ሊቀጥል የሚገባ ጠቃሚ እሴት ነው፡፡ ለአገር ልማትና ዕድገት ፋይዳ ያላቸው ተግባራት ሲወደሱ፣ ሕግና ሥርዓት እንዳይኖር የሚያበረታቱ ድርጊቶች መወገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ መልካም ነገሮችን ለማወደስም ሆነ አይረቤ ድርጊቶችን ለማውገዝ የጎራ አሠላለፍ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በልማት ገስግሳ ከድህነት አረንቋ ውስጥ እንድትወጣ የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች፣ በሕገወጥነትና በሥርዓተ አልበኝነት እንዳይደነቃቀፉ የጋራ ዕሳቤ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ በአንድ በኩል ለልማት የሚደረጉ ጥረቶች ሲበረታቱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ጥረቶች የሚያሰናክሉ አጓጉል ድርጊቶች እንዲወገዱ በሕግና በሥርዓት መመራት ይገባል፡፡ ድህነትን ለመቅረፍ እንቅልፍ አጥተን እናድራለን የሚሉ ወገኖች፣ ዓይናቸው ሥር ድህነትን የሚያባብሱ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንዳላዩ መሆን የለባቸውም፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ አስመራሪ ከሆነው የድህነት አረንቋ ውስጥ ተመንጥቃ የምትወጣው፣ ሕግና ሥርዓት ተከብሮ ዜጎች በመንግሥት ጥበቃ ሲተማመኑ ነው፡፡ መንግሥት በያዘው ዕቅድ መሠረት ልማት ላይ ሲረባረብ፣ እግረ መንገዱን የሕገወጥነት መፈልፈያ የሆኑ ብልሹ አሠራሮችን ያስወግድ፡፡

መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ሲገነባ፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ሲያበረታታ፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን የሚያነቃቁ ሪዞርቶችን ሲገነባ፣ የበጋ ስንዴ እርሻ ሲያስፋፋ፣ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን የሚረዱ የፖሊሲ ዕርምጃዎች ሲወስድና ልማትን የሚያግዙ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን የሕግና ሥርዓት መከበር ጉዳይ በፍፁም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ሕግና ሥርዓት በማይከበሩበት ሁኔታ ልማትን ማካሄድ አይቻልም፡፡ ከልማቱ ጎን ለጎን የሕግ የበላይነት ጉዳይ መታሰብ አለበት፡፡ ዜጎች ለልማቱ ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ አኳያ ብቻ ሳይሆን፣ በሕግ የተረጋገጡላቸው መብቶቻቸው መከበር አለባቸው፡፡ ሕገወጦች የዜጎችን ተሽከርካሪዎች፣ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም ጥረው ግረው ያፈሯቸውን ሌሎች ንብረቶች በጠራራ ፀሐይ ሲዘርፉ ዝም መባል የለበትም፡፡ ሕግ አውጭው ፓርላማ፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥትና የሕግ ተርጓሚው አካል የሆኑ የፍትሕ አካላት የተጣለባቸውን ሕዝባዊ አደራ መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ንብረቶቻቸውን በጉልበተኞች የተነጠቁ ዜጎች በይፋ ወጥተው ‹የሕግ ያለህ› ሲሉ፣ ሁሉም የመንግሥት አካላት በፍጥነት ተንቀሳቅሰው ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ መወሰን አለባቸው፡፡

እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ጉዳት ደርሶብናል የሚሉ ወገኖች ለፖሊስ፣ ለዓቃቤ ሕግ ወይም ለፍርድ ቤት በፍጥነት አቤት ማለት እንዳለባቸው ነው፡፡ ሕገወጥነትን መከላከል የሚቻለው ማንም ተበዳይ ነኝ የሚል ወገን አቤቱታውን ለሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት በፍጥነት በማስታወቅ ነው፡፡ ይህንን ሒደት ሳይጀምሩ በቀጥታ ወደ ሌላ አካላት በመሄድ ጉዳይን ለማስጨረስ የሚኬድበት ርቀት ፍትሕ እንዲሰፍን አያግዝም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለመገንዘብ እንደተቻለው አንዳንድ ግለሰቦች ተገቢውን ሕጋዊ መንገድ ሳይከተሉ፣ ጉዳያቸውን በጉቦ ወይም በሌላ መማለጃ ለማስፈጸም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሕገወጥነት ተባባሪ ሆነዋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ የሄዱበት ጉዳይ ተጨማሪ ኪሳራ አድርሶባቸው ነገሮች ከተበላሹ በኋላ፣ ወደ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወይም ወደ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ማማተር ሲጀምሩ መፍትሔ ፍለጋው ይወሳሰባል፡፡ ስለዚህ ሕጋዊ መንገዶችን በመከተል መብትን ማስከበር ተመራጩ መንገድ ስለሆነ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ተቋማትና የፍትሕ አካላት በራፍ ማንኳኳት የግድ መሆን አለበት፡፡ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ እያከናወነ ለመሆኑ ማረጋገጫ ለማግኘትም ያግዛል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአስፈጻሚውም ሆነ የሕግ ተርጓሚው አካላት አመራሮች ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ዜጎች በየዕለት ሕይወታቸው ከሚገጥሟቸው ፈተናዎች በመነሳት መሞገት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሕዝብ ተመራጮች ለሕግ፣ ለመረጣቸው ሕዝብና ለህሊናቸው ተገዥ መሆን ስላለባቸው ሕገወጥነትን በፅናት መታገል አለባቸው፡፡ የአስፈጻሚው መንግሥት አካላትን የሚመሩ ግለሰቦችም ቢሆኑ በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ተጠያቂነት በመገንዘብ፣ ለአገርና ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ሕገወጥ ድርጊቶችን መከላከል ተቀዳሚ ኃላፊነታቸው ነው፡፡ የዳኝነት አካሉም ቢሆን ሥራውን በነፃነትና በገለልተኝነት ከማከናወን ጀምሮ፣ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋሬጣ የሚሆኑ ድርጊቶችንና ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ አለበት፡፡ ሕግ ተርጓሚው አካል በዚህ መንፈስ ኃላፊነቱን ሲወጣ ለአገር ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ዕፎይታ ነው፡፡ ሦስቱ የመንግሥት አካላት እርስ በርስ ሚዛናዊ ቁጥጥር ፈጥረው እየተናበቡ ሲሠሩ፣ ዜጎች የሕገወጦችና የሥርዓተ አልበኞች መፈንጫ አይሆኑም፡፡ በጉልበታቸው እንዳሻን እንሁን የሚሉ አደብ ስለሚገዙ ሕግና ሥርዓት ይከበራል፡፡ በየቦታው በጉልበት መሬት የሚወሩ፣ የግለሰቦችን ንብረት የሚዘርፉና ዜጎችን የሚያሰቃዩ ሥርዓት ይይዛሉ፡፡

ሕግና ሥርዓት ሲከበር ለዘለቄታዊ ሰላም መስፈን ጥርጊያው ይመቻቻል፡፡ በአገር ውስጥ የእርሻ፣ የንግድ፣ የትምህርትና የሌሎች ዘርፎች እንቅስቃሴዎች በስፋት ሲቀላጠፉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በብዛት ይገኛል፡፡ ነባሮቹንም ሆነ አዳዲሶቹን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ የቱሪስት መስህቦችን ለመጎብኘት ቱሪስቶች ይጎርፋሉ፡፡ በሁሉም ክፍላተ ኢኮኖሚዎች ለመሰማራት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዕውቀታውን፣ ገንዘባቸውንና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የሚረዱ ልምዶችን ይዘው ይመጣሉ፡፡ በየቦታው ሰዎችን እያገቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚጠይቁ ሽፍቶችንና ከተማ ውስጥ መሽገው የዜጎችን ንብረት የሚቀሙ ጉልበተኞችን በሕግ ማለት ካልተቻለ፣ የሚታሰበው ልማትም ሆነ ዕድገት ጉም እንደ መጨበጥ ይቆጠራል፡፡ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ ሥራውን ሲያከናውን፣ ራሱ ሕግ እያከበረ የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ብልሹ አሠራሮችን የሚያሰፍኑና የሕገወጦች ወኪል የሆኑ በሙሉ በሕግ ሥርዓት መያዝ አለባቸው፡፡ እነሱ አደብ ሳይገዙ ስለሕግና ሕጋዊነት ለመነጋገር አይቻልም፡፡ ዜጎችም በመንግሥት ላይ እምነት አይኖራቸውም፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ለዲፕሎማሲው ዓለም አዲስ አይደለችም፡፡ ቀድሞ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል፣ በመቀጠልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መሥራች፣ የአፍሪካ ኅብረት እንዲመሠረት ተጋድሎ ያደረገችና የኅብረቱ መቀመጫ፣ ከኒዮርክና ከጄኔቫ በመቀጠል የዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ፣ እንዲሁም በፀረ ኮሎኒያሊስት ታጋይነት በግንባር ቀደምትነት ስሟ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ታሪካዊት አገር ናት፡፡ ሰሞኑን የአፍሪካ የልማት ባንክ የውጭ አገር ሠራተኞቹ በተፈጸመባቸው ድብደባ ምክንያት ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ውሳኔ ላይ ሲደርስና የውሳኔውን ምክንያት ሲያብራራ፣ መንግሥት ምላሽ አለመስጠቱና ክስተቱን በዝምታ ማለፉ ተገቢ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ዝርዝሩን ትተን ሕግ ከማስከበር አኳያ ጥያቄ በተቋሙ ቀርቦ ምላሽ በመጥፋቱ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ሲወስን፣ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ ካልታሰበበት አገር ትጎዳለች፡፡ አገር እንዳትጎዳ በጉዳዩ ላይ ምክክር ይደረግ፡፡ በአጠቃላይ ዜጎች በሕገወጦችና በሥርዓተ አልበኞች እየደረሰባቸው ያለ ችግር ሌላ ገጽታ ፈጥሮ አገር እንዳትጎዳ ጥንቃቄ ይደረግ!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...