Monday, June 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በትግራይ ክልል ይጠበቅ ከነበረው የመኸር ምርት የተገኘው 35 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በትግራይ ክልል በ2015/16 ዓ.ም. የምርት ዘመን ከመኸር ይገኛል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረው የሰብል ምርት ማግኘት የተቻለው 35 በመቶ ብቻ መሆኑን፣ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ምሩፅ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በትግራይ ክልል በየዓመቱ 1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በክረምት እርሻ ይሸፈን እንደነበርና 23 ሚሊዮን ኩንታል ያህል ምርት ይጠበቅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈጸም ባለመቻሉ በዚህ ዓመት የመኸር ወቅት መሸፈን የተቻለው 48 በመቶ የሚሆነውን የእርሻ መሬት መሆኑን፣ በተጨማሪም ከ630 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት በትግራይ ክልል አስተዳደር ውስጥ አይደለም ብለዋል፡፡

የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነገሮች ወደ ነበሩበት ይመለሳሉ የሚል ዕቅድ ተይዞ እንደነበር፣ በዚህም በአጠቃላይ 1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በማረስ 23 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ እንደነበር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ባለመሆኑና አብዛኛው የሚታረስ የክልሉ መሬት ከክልሉ ይዞታ ውጪ በመሆኑ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር የሚገኘው 646 ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ የታረሰ መሬት 15.5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በተፈጥሮአዊና በሰው ሠራሽ ክስተቶች ምክንያት ሊገኝ የቻለው ግን አምስት ሚሊዮን ኩንታል ብቻ እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ሥር በሚገኘው 646 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ በደረሰው የአንበጣ መንጋ፣ ወቅቱን ያልጠበቀና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ፣ ተምችና ሌሎች የሰብል ተባዮች፣ እንዲሁም ግብዓት በወቅቱ ካለመድረስ ጋር ተዳምሮ ይጠበቅ የነበረውን ውጤት ማግኘት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ 512 ሺሕ ሔክታር መሬት ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ምክንያች ጉዳት ደርሶቦታል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የመኸር ምርት መሰብሰቡን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ መሠረት ይጠበቅ ከነበረው የተገኘው ምርት 35 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የተገኘው ምርት ዝቅተኛ በመሆኑ የግብርናና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ አደጋ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ ስለጉዳዩ በመነጋገር በምርት ላይ የደረሰውን ጉዳትና ድርቁን ለማካካስ በበጋ መስኖ፣ በከተማ ግብርና እርጥበት ባለባቸው ቦታዎች ቶሎ ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎች ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ክልሉ የተለየ ዕገዛ ያስፈልገዋል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከቀዬው ውጪ ስለሚኖር ለተረጂነት መዳረጉን ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳ የፌዴራል መንግሥት የውጭ ምንዛሪና መሰል ችግሮች ቢኖሩበትም በተቻለ አቅም ለክልሉ ዕገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ በትግራይ ጊዜያዊ ክልል አስተዳደር ሥር ነበሩ ያሏቸው ምዕራባዊ ዞኖች በአማራ ክልል ውስጥ መጠቃለላቸውና በኤርትራ ድንበር በኩል የሥጋት ቀጣና የሆኑ እርሻ ቦታዎች በመኖራቸው፣ የእርሻ ሥራ በሚፈለገው መጠን እየተከናወነ አይደለም ብለዋል፡፡

ክልሉ አቅሙን በሙሉ እየተጠቀመ ቢሆንም በራሱ አቅም ብቻ ያሉትን ችግሮች ሊፈታ ስለማይችል፣ የፌዴራል መንግሥት በተቻለው አቅም ድርቁን ጨምሮ ካሉት ችገሮች ጋር ሊጣጣም የሚችል ድጋፍ እንዲያደርግ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች