Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዜጎችን ሕይወት እያናጋ ያለው ቤቲንግና ኬኖ

የዜጎችን ሕይወት እያናጋ ያለው ቤቲንግና ኬኖ

ቀን:

እዚህም እዚያም ወረቀት ይዘው ዕድላቸውን ለመሞከር የሚሯሯጡ ወጣቶችን ማየት ከተለመደ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ወጣቶቹ ከሥራ ይልቅ እንደ አቅማቸው ባላቸው ጥሪት የቆረጡት ትኬት የሚያመጣላቸውን ዕድል ለመጠቀምም በተለያዩ የቤቲንግ ማጫወቻዎች ይታያሉ፡፡

የዕድላቸውን ለማግኘት ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ የፀጥታ አካላት ሳይቀሩ ከላይ ታች እንደሚሉ ስፖርት ውርርድ የሚያጫውቱ ቤቶች ምስክር ናቸው፡፡ ውርርዱም በትንሽ ገንዘብ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ሊያስገኝ ስለሚችል፣ ከሕፃናት እስከ አረጋውያን ጨዋታው ያጓጓቸዋል፡፡ ሱስ ውስጥ የገቡም አሉ፡፡

ጨዋታው የአንዳንድ ሰዎችን ሕይወት ቀይሯል ሲባል ቢሰማም፣ ለበርካታ ሰዎች ከትዳራቸው መፈናቀል ምክንያት መሆኑም ይነገራል፡፡ በቤቲንግ ውርርድም ከሞቀ ትዳሩ የተፈናቀለው ወጣት ጥላሁን ደግፌ ይገኝበታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ወጣቱ ከባለቤቱ ጋር በትዳር ከቆየ ሁለት ዓመታት የሆነው ሲሆን፣ በየጊዜው ቤቲንግ ሲጫወት ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣቱን ለሪፖርተር ያስረዳል፡፡

በቤቲንግ ጨዋታ ሱስ ውስጥ መግባቱንና አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ ገበታ እየቀረ ቁማር ቤት እንደሚውል ይናገራል፡፡ ከባለቤቱ ጋር የመለያየቱ ምክንያት የቤቲንግ ጨዋታ መሆኑን ሲያስብ፣ ንዴት ውስጥ እንደሚገባና ከቁማር ጨዋታው በተጨማሪ ሌሎች ደባል ሱሶች ውስጥ እንዲገባ እንዳደረገው ይገልጻል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ሥራ አቁሞ የጓደኞቹን እጅ እንደሚያይ ጠቅሶ፣ ችግሩ በአብዛኛው ወጣቶች ዘንድ እንደሚያይ ያስረዳል፡፡

አሁን ላይ ከዚህ ሱስ ለመውጣት እንደከበደው፣ ከስፖርት ውርርድ በተጨማሪ ኬኖ የተባለ ጨዋታ እንደሚጫወትም ያብራራል፡፡

ቤቲንግ ሆነ ኬኖ የሚያጨውቱ ግለሰቦች በአንድ በኩል ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ቢፈጥሩም፣ የወጣቱን ሕይወት ግን እያመሰቃቀሉትና ሥራን እንዳያስብ እያደረጉት ነው ይላል፡፡

በአንድ ወቅት ለቤት ኪራይ የሚሆነውን ገንዘብ ሳይቀር መበላቱን፣ መንግሥት አፋጣኝ ዕልባት ካልሰጠ ችግሩ የሁሉንም ቤት ማንኳኳቱ እንደማይቀር ሥጋቱን ይገልጻል፡፡

የዜጎችን ሕይወት እያናጋ ያለው ቤቲንግና ኬኖ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በቁማር ሱስ እሱን ጨምሮ በርካታ ጓደኞቹ መያዛቸውን ገልጾ፣ ከዚህ በኋላ ሱሱንም ጨምሮ ይህንን ቁማር በማቆም ከባለቤቱ ጋር ለመኖር ሐሳብ እንዳለው ያስረዳል፡፡

በቤቲንግ ሱስ ወጣቱ ብቻ ሳይሆን ሕፃናትን ጨምሮ ትልልቅ ሰዎች መያዛቸውን፣ በርካቶች በቤቲንግ ውድድር ብር አግኝተው ራሳቸውን መቀየር እንደሚፈልጉ ለሪፖተር ይናገራል፡፡ ‹‹ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ የሚማርም ሆነ የሚሠራ ሰው ማግኘት ከባድ ነው፤›› የሚለው ወጣቱ፣ ማንኛውም ሰው በጉልበቱ ለፍቶ ያገኘውን ገንዘብ ቁማር ላይ እንዳያውልና ከእሱ ስህተት እንዲማር ይመክራል፡፡

ብዙ ጊዜ እሱና ጓደኞቹም ቤቲንግና ኬኖ ቤቶች ውስጥ ጊዜያቸውን እንደሚያጠፉ፣ ማንኛውም ሰው የተሻለ ሕይወት ለመኖር ከእንደዚህ ዓይነት ሱስ መውጣት እንዳለበትና መንግሥትም ሰሞኑን የወሰደው የማሸግ ዕርምጃ ተገቢ እንደሆነ ያምናል፡፡

በከተማዋም በርካታ የቤቲንግና የኬኖ ማጫወቻ ቦታዎች መኖራቸውን፣ መንግሥት የራሱን ጥቅም ከማስቀደሙ በፊት ወጣቶች ላይ ቢሠራ የተሻለ እንደሚሆን ያስረዳል፡፡  

የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው 120 የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) የሚያጫውቱ ቤቶች አሉ፡፡

ማንኛውም ባለሀብት አንድ ቤቲንግ ቤት ለመክፈት ሲፈልግ አምስት መቶ ሜትር ከእምነትና ከትምህርት ቤቶች መራቅ እንዳለበት የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከእነዚህ ተቋማት ርቀታቸውን ጠብቀው ያልተገኙ የስፖርት ውርርድ ቤቶች ሕጋዊ ዕርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር እነዚህን ተቋሞች በተመለከተ የራሱ መመርያ ማውጣቱንና ከሃያ አንድ ዓመት በታች የሚገኙ ልጆችን እያጫወተ የሚገኝ የትኛውም ቤቲንግ ቤት ዕርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን አክለዋል፡፡  

በከተማዋ በአሁኑ ወቅት ቅርንጫፋቸውን በማስፋት ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ቤቲንግ ቤቶች በሕገወጥ መንገድ እየሠሩ እንደሆነ ገልጸው፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ እነዚህን ተቋማት እያገደ ነው ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ሎቶሪ ከእነጭራሹ የማያውቃቸው ቤቲንግ ቤቶች ተከፍተው እያጫወቱ መሆኑን፣ የዚህም ችግር ዋነኛ ምክንያት ሲስተም ፕሮቫይደሮች ለቤቲንግ ቤቶች በመስጠት የስፖርት ውርርድ እንዲያጫውቱ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሲስተም ፕሮቫይደሮች የብሔራዊ ሎቶሪ ፈቃድ ለሌላቸው ቤቲንግ ቤቶች ሲስተምን እንደሚሰጧቸው የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ሲስተሙም ከተሰጣቸው በኋላ ቅርንጫፋቸውን በማስፋት ቤቲንግ ቤት እየከፈቱ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  

ብሔራዊ ሎቶሪ ፈቃድ የሰጣቸው ቤቲንግ ቤቶች በሕጋዊ መንገድ ቅርጫፋቸውን አስፍተው እየሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ በሕገወጥ መንገድ የሚሠሩ ቤቶችን ለመቆጣጠር ተቋሙ ያወጣውን መመርያ እንደ አዲስ ሊከልስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አንድ የስፖርት ውርርድ ወይም ቤቲንግ ቤት ሆነ ሌላ አካል ቤቲንግ ቤት ለመክፈት ሲፈለግ፣ ሲስተም አቅራቢ የሆኑ ተቋማት ጋር ሲሄድ፣ ተቋማቱ  የብሔራዊ ሎቶሪ ፈቃድ ማግኘቱን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው አብራርተዋል፡፡

ብሔራዊ ሎቶሪ፣ ይህንን ያካተተ አዲስ መመርያ ለማውጣት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅትም ኬኖ የሚያጫውቱ ቤቶች ላይም ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኬኖ የሚያጫወቱ ቤቶች ፈቃድ የሌላቸውና በብሔራዊ ሎቶሪ ሥር ያልሆኑ መሆናቸውን፣ አንድ ግለሰብ የስፖርት ውርርድ ወይም ቤቲንግ ቤት ለመክፈት 1.5 ሚሊዮን ብር ዋስትና ማስያዝ እንደሚኖርበት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አንድ ባለሀብት የቤቲንግ ቤት ለመክፈት ሲፈልግ የ500 ሺሕ ብር ካፒታል ፈቃድ ማውጣት እንደሚኖርበትና ይህንንም ብሔራዊ ሎቶሪ ያደረገበት ዋነኛ ምክንያት ማንኛውም ሰው እንደፈለገ ወደ ሥራው እንዳይገባና ኃላፊነት እንዲሰማው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑም የስፖርት ውርርድ ቤቶችን (ቤቲንግ) በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በመግለጫውም 3,241 የቤቲንግ ቤቶች ላይ የማሸግ ዕርምጃ መውሰዱን ጠቁሟል፡፡

የሰላምና የፀጥታ ቢሮ ወደ ዕርምጃ የገባው የቤቲንግ ጨዋታ በከተማዋ አስተዳደር እንዲሁም ቀን በቀን በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ሕይወት ዙሪያ እየፈጠረ ያለውን አሳሳቢ ችግር በመረዳት መሆኑን አስታውቋል፡፡

ቤቲንግ ከስፖርት መጫወቻነቱ ባለፈ አገር ተረካቢ ትውልድ እያጠፋ መሆኑንና ከፍተኛ የወንጀል መስፋፊያ እየሆነ መምጣቱም ለመታሸጋቸው ከምክንያቶቹ  ይጠቀሳሉ፡፡

የከተማው ወጣት ጊዜውን ያላግባብ በሥፍራው እያሳለፈ መሆኑ፣  ከተፈቀደላቸው ውጪ ሥራው በመከናወኑ፣ የሰው ልጅ ሕይወት ያላግባብ እየጠፋ በመምጣቱ፣ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን ትተው በቦታው እየተገኙ በተገቢው መንገድ እንዳይማሩ በማድረጉና የመማር ማስተማር ሒደትን እያወከ በመምጣቱ የሚሉት ነጥቦችም ለዕርምጃው መነሻ መሆናቸውን ገልጿል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...