Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሔሊኮፕተር የፈጠራ ሥራው የተሸለመው ወጣት

በሔሊኮፕተር የፈጠራ ሥራው የተሸለመው ወጣት

ቀን:

ባለፈው ሳምንት ለአምስት ቀናት በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው በ‹‹ፈጠራ ለአቪዬሽን ልህቀት›› ኤክስፖ፣ በአቪዬሽን ኢኖቬሽን ውድድር ሔሊኮፕተር ሠርቶ በማቅረብ አንደኛ የወጣው ዕበ ለገሠ የ100 ሺሕ ብር ተሸላሚ ሆነ፡፡

የሠራት ሔሊኮፕተር ለሦስት ደቂቃ ያህል መብረር እንደምትችል የተናገረው ዕበ፣ የልጅነት ህልሙን ዕውን ለማድረግ ለዓመታት እልህ አስጨራሽ ሙከራ አድርጓል።

በሔሊኮፕተር የፈጠራ ሥራው የተሸለመው ወጣት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ዕበ ለገሠ የሠራት ሔሊኮፕተር

ሔሊኮፕተሯ ተሻሽላ ገበያ ላይ መዋል የምትችልና የተሠራችበት ቁሳቁስ ሙሉ በሙሉ በአካባቢ የሚገኙ መሆናቸውም ወጣቱን ለአሸናፊነት አብቅቶታል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፈጠራውን ለማገዝ ቃል እንደገባለት የገለጸው ዕበ፣ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ነገር ይዞ ለመቅረብ እንደሚሠራ ተናግሯል፡፡

በወቅቱ ለውድድር ከቀረቡት 90 የፈጠራ ሥራዎች በአንደኝነት አጠናቆ የተሸለመውን 100 ሺሕ ብር፣ በትግራይ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንደሰጠ ወጣቱ ጠቁሟል፡፡

ዕበ ነዋሪነቱ በሽረ እንደሥላሴ ከተማ ሲሆን፣ የልጅነት ህልሙ ብዙዎች እንደሚሉት አውሮፕላን ማብረር አሊያም በአውሮፕላን መሄድ አልነበረም፡፡ ይልቁንስ ሐሳቡ ከዚህም ከፍ ያለ ነበር፡፡ የግሉን አውሮፕላን ሠርቶ በሰማይ ላይ መንሳፈፍ ምኞቱ እንደነበር  የሚናገረው ወጣቱ፣ ሐሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ እልህ አስጨራሽ ጉዞ አድርጓል።

በትምህርት ደረጃው ከአሥረኛ ክፍል ባይሻገርም፣ በሰማይ መብረር የምትችል ሔሊኮፕተርን ከመሥራት አላገደውም።

በሔሊኮፕተር የፈጠራ ሥራው የተሸለመው ወጣት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ዕበ ለገሠ

የፈጠራ ሥራውን በ1991 ዓ.ም. እንደወጠነው፣ ከአንድም አምስት ጊዜ ሰው አልባ ሔሊኮፕተሮችን ሠርቶ፣ ሁለቱ ምንም ዓይነት የመብረር ሙከራ ሳያደርጉ እንደቀሩ፣ ሦስተኛዋ ደግሞ ወደ ሰማይ እንደሄደች መዳረሻዋ ሳይታወቅ በወጣችበት ደብዛዋ ጠፍቶ የቀረች ሲሆን፣ አራተኛዋ ከፍታዋ ዝቅ ያለ ስለነበር ከተራራ ጋር ተላትማ ሙከራዋ ሳይሳካ እንደቀረ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ዕበ ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልሳካ ያለው ሰው አልባ በመሆናቸው ይሆን እንዴ? በማለት ደጋግሞ ካሰበ በኋላ ‹‹ለምን በሰው የምትበር ሔሊኮፕተር አልሠራም?›› የሚል አምስተኛ ሐሳብ እንደመጣለት ይናገራል።

ሐሳቡንም ሳይውል ሳያድር ወደ ተግባር በመለወጥ በፋይበር ግላስና በአሉሙኒየም የተሠራች ከዚህ ቀደም ከተሠሩት በመጠንም ሆነ በጥራት ለየት ያለችና አብራሪዋን ብቻ የምትይዝ ሔሊኮፕተር በአራት ዓመት ሠርቶ በማጠናቀቅ በራሱ አብራሪነት መካከለኛ ሙከራን አድርጎ ነበር፡፡

ካለፈው ተደጋጋሚ ሙከራዎች በመነሳት በስምንት ወራት ወስጥ ሠርቶ ያጠናቀቃትና ለሽልማት ያበቃችው ሔሊኮፕተር፣ ከመገናኛ ራዲዮና ከጥቃቅን የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ውጭ በአብራሪ ታግዛ ሙሉ በረራ የማድረግ ሙከራ ማድረጓን ወጣቱ ተናግሯል። ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይም ጨርሳለች፡፡

የአውሮፕላን ማምረቻ ቁሳቁሶችን በመጠቀም እንደሠራት የተናገረው ወጣቱ፣ ለአብራሪው ብቻ የሚሆን ቦታ ቢኖራትም፣ እስከ አራት ሰው ወይም አራት ኩንታል ጭነትን ተሸክማ መብረር እንደምትችል ተናግሯል፡፡

ዕበ እንደሚለው፣ ሔሊኮፕተሯ ተጠናቃ ወደ ሥራ ስትገባ በከተሞችና በጥብቅ ደኖች አካባቢ ለሚነሱ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎዎችን ለማጥፋት፣ የአንበጣ መንጋን ለመከላከልና ቅኝት ለማድረግ ታገለግላለች፡፡ ሰዎች ገዝተው ለትራንስፖርት ሊጠቀሙበትም ይችላሉ፡፡

ወጣት ዕበንና መሰል የፈጠራ ባለሙያዎችን በአንድ መድረክ ያገናኘ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የተባለለት ኤክስፖ ከታኅሳስ 1 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።

ኤክስፖው ‹‹ፈጠራ ለአቪዬሽን ልህቀት›› በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ሥራ ፈጣሪዎች በአንድ የተሰባሰቡበት ነበር፡፡

እነዚህና መሰል የፈጠራ ባለሙያዎችን በአንድ መድረክ ያገናኘው ኤክስፖ ዓላማ፣ ያለ በቂ የመንግሥት ድጋፍ በራሳቸው ተነሳሽነት በአቪዬሽን መስክ በፈጠራ ሥራ ላይ የተሰማሩና የወደፊቱን የአገሪቱን የአቪዬሽን ገጽታ በመቀየር ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ አቅም ያላቸውን ወጣቶች  በማበረታታትና በመደገፍ በዘርፉ ቴክኖሎጂና ኢኖቬዬሽን እንዲስፋፋ ለማድረግ ነው፡፡

በኤክስፖው 95 ወጣቶች በጋራና በተናጠል ሆነው 90 የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ 34 የግልና የመንግሥት ተቋማትም በአቪዬሽን ዘርፍ የሚያከናውኑትን ሥራ አቅርበዋል።

ለዕይታ ከቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች ውስጥም 90 በመቶ የሚሆኑት ድሮኖች ነበሩ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...