Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች››

‹‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች››

ቀን:

ጥንታዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ፣ በተለያዩ ጥናቶች እንደሚገለጸውም ከአራት እስከ አምስት ሺሕ ዓመታት ይዘልቃል፡፡ ይህም በሥነ ጥንት (አርኪዮሎጂ) ምርምር የተደገፈ ነው፡፡

‹‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ባለ ብዙ ባህሎችና ቅርሶች መድበል ከሆነችው ኢትዮጵያ ከጥንታዊም ሆነ ከመካከለኛው  ብሎም ከዘመናዊ ታሪኳ የሚቀዱ ዘርፈ ብዙ ፍሬ ነገሮች አሏት፡፡ ይህም በአገሪቱ ብቻ ሳይወሰን በተለይ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚዘልቅ ሀብቶች ጭምር ባለቤት ናት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ኢትዮጵያችን ሀብታም አገር ናት፡፡ ሀብትዋም በያይነቱ ነው፡፡ በመሬቷ ሆድ ውስጥ ብዙ ማዕድኖች በያይነቱ ብረቶችና ነዳጅ ዘይቶች ይገኙበታል፡፡ በምድረ ገጽዋ ላይ ደግሞ የሚበቅልበት እህልም፣ የሚለማበት ተክልም ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ የሚሠማሩባት እንስሳዎችስ ማን ቆጥሮና ዘርዝሮ ሊጨርሳቸው? ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በላይም አንድ ልዩ ሀብት አላት፡፡ እሱም የተፈጥሮ ውበቷ፣ ታሪኳ፣ ኪነ ጥበቧ፣ ባህሏ ሥነ ሥርዓቷ፣ መጻሕፍቷ፣ አድባራቷ፣ ገዳማቷ በማለት አንዳንዱን ለማስታወስ ያህል እምንገልጸው፣ ለእኛ ምሥጢር ሆኖ የተደበቀን የወርቅ ማዕድንን ነው፡፡››

ይህ ዓቢይ ጥቅስ፣ ከሃምሳ አምስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያን ቱሪዝም በበላይነት ይመራ ከነበረው የማስታወቂያና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የሥራ ትስስር የነበራቸው ሊቁ አባ ገብረ ኢየሱስ ኃይሉ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለቱሪስት መስህብነት፣ መዳረሻነት ትልቅ ገበታ መሆኗን በገለጹበት መጽሐፋቸው ውስጥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹የማያልቅ የወርቅ ማዕድን (የኢትዮጵያ ውበት)›› በሚለው መጽሐፋቸው ሊቁ እንዳመለከቱት፣ በወርቅ ማዕድን የተመሰለው ቱሪዝም የማያልቅ ሀብት የማይደርቅ ምንጭ መሆኑን መላው ዓለም ተገንዝቦታል፡፡

‹‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የመጽሐፉ አዘጋጅ አቶ ሞገስ ጌትነት
ፎቶ ሔኖክ ያሬድ

ይህን ሀብት ትውልዱ በቅጡ ያውቀዋልን፣ በተለይ አዳጊ ወጣቶች የሚለው በየጊዜው የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡ የአገሪቱን ዘርፈ ብዙ ሀብቶች ለማስተዋወቅ በተለያዩ ተቋማትም ሆነ በግለሰቦች ደረጃቸውም ሆነ ይዘታቸው ይለያይ እንጂ በመጽሐፍም ሆነ በመጽሔት መልክ ሲቀርቡ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአገራዊ ቋንቋዎች ከተዘጋጁት ይልቅ በባህር ማዶ ልሳኖች የተሠራጩት በርከት ይላሉ፡፡

መሰንበቻውን ‹‹ልጆች በቀላሉ አካባቢያቸውን እና አገራቸውን መገንዘብ እንዲችሉ በምስልና መጠነኛ በሆነ ገለጻ የተዘጋጀ›› የሚል መክፈቻ ያለው አንድ መጽሐፍ ገበያ ላይ ቀርቧል፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ ‹‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች›› የሚል ሲሆን አዘጋጁ አቶ ሞገስ ጌትነት ናቸው፡፡

አቶ ሞገስ ቀደም ሲል በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በሕግ አማካሪነት እየሠሩ ይገኛሉ። በልጆች ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መጻሕፍትን እያዘጋጁ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ቅርሶቹንና ባህሉን የሚያውቅና በግብረገብ የታነፀ ትውልድ ለማፍራት፣ ልጆች በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ መጽሐፍ ማዘጋጀት አስፈላጊነቱን በማመናቸው ‹‹ውቢቷ ኢትዮጵያ ለልጆች›› የሚል መጽሐፍ አዘጋጅተዋል፡፡

ይዘቱም በአራት ክፍሎች የተቀነበበ ሁኖ ቀዳሚው፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅባቸው ነገሮችን ማለትም የዓድዋ ድል፣ የቡና መገኛነቷን፣ ድምቀቷ የሆኑ አትሌቶቿ፣ የራሷ የዘመን አቆጣጠርና የአጻጻፍ ሥርዓት ያላት፣ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው ኢትዮጵያውያንን የሚያሳይበት፣ የቅድመ ሰው ዘር መገኛነቷ የተገለጸበት ነው፡፡

ሁለተኛው ክፍል ስለ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ታሪኳን ከመስህቦቿ ሐውልቶቿና ሙዚየሞቿ ጋር ተያይዞ ቀርቦበታል፡፡ ሦስተኛው ዓብይ ክፍል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት ስድስት ታሪካዊ መስህቦች (አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ሐረር፣ ኮንሶ፣ ጥያ) እና ሰባት የተፈጥሮ መስህቦችን (የስሜን ተራሮች፣ ጢስ ዓባይ፣ የባሌ ተራሮች፣ ሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ፣ ኤርታሌና የደናኪል ዝቅተኛ ስፍራዎች፣ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች) ይዟል፡፡

የመጨረሻው ክፍል የመስቀል፣ የጥምቀት፣ የኢሬቻ፣ የፊቼ ጫምባላላ ክብረ በዓላት፣ የገዳ ሥርዓት ያሉበት የማይዳሰሱ ባህላዊ መስህቦችን አቅፏል፡፡

በተወሰነ ደረጃ የማየት  እክል  ያለባቸው አቶ ሞገስ፣ መጽሐፉ ልጆች አካባቢያቸውንና የአገራቸውን ባህል እንዲያውቁ በማሰብ ያዘጋጁት መሆኑን ገልጸዋል።

 የልጆች መጻሕፍት ሲፃፉ በአመዛኙ ተረቶች ላይ ያዘነበሉ በመሆናቸው ታሪካቸውንና ባህላቸውን የሚያስገነዝቡ መጻሕፍትም አስፈላጊ በመሆናቸው እነሱ ላይ ለማተኮር መፍቀዳቸውን ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ወላጆች ልጆቻቸው ከመደበኛ ትምህርት በዘለለ ሁለንተናዊ ዕውቀት እንዲገበዩ መጻሕፍትን ለልጆቻቸው ማስነበብ እንዳለባቸውም በማስገንዘብ ጭምር፡፡

አዘጋጁ ታሪካዊውን መጽሐፍ ለዓይነ ሥውራንም ሆነ የዕይታ እክል ላለባቸው ተደራሽ ለማድረግ በብሬል ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...