Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ተስፋዬን ፍለጋ ከ፬ ኪሎ እስከ ቬሮና››

በተክለጻድቅ በላቸው

የመጽሐፉ ርዕስ፡ ተስፋዬን ፍለጋ ከ፬ ኪሎ እስከ ቬሮና

ደራሲ፡ ማርቆስ ተግይበሉ

ኅትመት፡ በአሜሪካ በ2015 ዓ.ም.፣ በአዲስ አበባ በ2016 ዓ.ም.

የገጽ ብዛት፡ 327 ከ25 ፎቶዎችና ሰነዶች፡፡ በርካታ የዘፈን ዝርዝሮችና

ግጥሞች፡ ዲስኮግራፊ (የሙዚቃ ኅትመቶቹና ውጥን ሥራዎቹ መረጃችን

ዝርዝር) በጽሑፉ ውስጥ ያካተተ ነው፡፡

‹‹ተስፋዬን ፍለጋ ከ፬ ኪሎ እስከ ቬሮና›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ርዕሱ ‹‹ተስፋዬን ፍለጋ ከ፬ ኪሎ እስከ ቬሮና›› ሰምና ወርቅ ያለበት፣ ማርቆስ ተግይበሉ ከልጅነቱ አንስቶ ተስፋዬ ማን ነው? እውነተኛው መጨረሻውስ? እና መሰል ጥያቄዎችን አዝሎ፣ ፍለጋውን ቦግ ጭልም እያለ ግን ጨርሶ ተስፋ ሳይቆርጥ የጉዞ ታሪኩን አካትቶ ስለገጣሚ ድምጻዊ አርቲስት ተስፋዬ ገብሬ (ቴስ) ያጠናውን፣ የታዘበውን በግልጽነትና በቁጥብነት ከአዲስ አበባ አንስቶ እስከ ቬሮና (ሌሎች የተጓዘባቸውን ሥፍራዎችን ጨምሮ) ያለውን የሕይወት ስንክሳር የሚተርክ ውብ መጽሐፍ አበርክቶልናል። ልክ በመጽሐፉ መግቢያ እንዳለው በጭውውት መልክ የቀረበ ግሩም ትረካና በውስጡ ብዙ ታሪኮች የታጨቁበት ድርሰት ነው። መታሰቢያውን በርካታ ታሪኮችና መዝገቦችን ቅርስ አድርጋ ላቆየችውና በቸርነት ላጋራችው ለተስፋዬ የቀድሞ ባለቤት ለአንጀሊና ነው። ‹‹የምትወደውን ባሏን በሞት ከተነጠቀች ከአራት አሠርታት በኋላም ጋቢውን ለብሳ ለምታነባው አንጄላ ፒዚጌላ ይሁን›› ይላል። ተገቢ መታሰቢያ።

ማርቆስ ለመጻፍ ሲነሳሳ ከአገር ርቆ በሙያም ከአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ንባብ ርቆ በአሜሪካ አገር መኖር ከጀመረ ስለከራረመ ብቃት የለኝም የሚል ጥርጣሬ የተሰማው ቢሆንም፣ በወዳጆቹ አበረታችነትና የልጅነቱ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ስንቁ የሆኑትን የአማርኛ መምህራኑን እንዲሁም ከአያቱ ጥልያን ሠራሽ የጥይት ሳጥን ውስጥ ተከማችተው ይገኙ የነበሩትን የተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሰፈራቸው ከነበረው የኤፒኤን (APN) ቢሮ በነጻ ስጦታ እየተቀበሉ ያነቧቸው የነበሩ ክላሲካል ልብ ወለዶችና የግጥም መጻሕፍት ማንነቱን ከመቅረጽ አልፈው የደራሲነት ክህሎቱን አበጃጅተውት ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም ምናቡ (የኢማጅኔሽኑ) ጥልቀት አሌ አይባል። ለምሳሌ መጽሐፉንም ተስፋዬን ፍለጋ አንብቤ ስጨርስ ከሥዕላዊ ትረካነቱ የተነሳ it is a movie!  ‹‹ፊልም ይመስላል›› ነበር ያልኩት።

የማርቆስ ተስፋዬን ፍለጋ በማለት ያዘጋጀልን መጽሐፍ በእኔ አተያይ የሚከተሉት ጉልህ ገጽታዎች አስተውዬበታለሁ። (ስድስት የሚሆኑ እንዲሁም ቢበልጥ እንጂ በርካታ ፋይዳዎች ይስተዋልበታል።) 

‹‹ተስፋዬን ፍለጋ ከ፬ ኪሎ እስከ ቬሮና›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር   

. እንደ ጥበብ ታሪክ ቀዳሚ ነው

ይህ ሥራ እንደ ሥነ ጥበብ ታሪክ ቀዳሚ ሥራ በመሆን (as Art  and social history) ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎች ጥሩ ግብዓት ብቻ ሳይሆን ቀዳሚ ምንጭ ወይም primary source ሥራ ነው። በተለያየ ዲሲፕሊን ለሚገኙ አጥኚዎችም እንደ ቀዳሚ ሥራ ሆኖ ማገልገል ይችላል። ምንጮቹም የቅርብ ሰዎች ከሆኑት የታተሙና ያልታተሙ ሰነዶች፣ በቃለ መጠይቅ ላይ የተመረኮዘ፣ በጉብኝት (ተስፋዬ ይኖርበት ከነበረው አገር እስከ ባለቤቱ ድረስ በመሄድ) ethnographic field research እና በሌሎች ሰዎች የማይገኙ እንዲሁም ያልተጠኑ መረጃዎችን አካትቷል።

እንደ ምሳሌ የሚሆነን የፎቶግራፍ ክምችቶቹ፣ የዲስኮግራፊ (የአልበሞቹ ዝርዝር)፣ በተለያዩ ቋንቋዎች በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በጣሊያንኛ የተሠሩትን ሙዚቃዎች፣ የዜማው ስልትና ግጥሞችን በትርጉም (በኢንተርኔት ተርጉሞ የአማርኛ የግጥም ለዛ እንዲኖረው በማድረግ) ጭምር አስቀምጧቸዋል (ይኼ ጅምር ሥራ ሌሎች ቋንቋዎቹን የበለጠ የተካኑ አሻሽለው ሊሠሩትና ሊያጠኑት ይችላሉ)፣ የተለያዩ ሰነዶች፣ በተስፋዬ ገብሬ የእጅ ጽሑፎች (ይህ በፊሎሎጂ ጥናትም ሊጠና ይችላል) ባጭሩ መጽሐፉ እኒህና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል።  

ስለአብዮቱ በሚናገርበት ምዕራፍ ‹‹አብዮታዊት ኢትዮጵያ›› (ገጽ 183-193) ዜማዎችና ግጥሞችን የምናውቃቸውንና የማናውቃቸውንም ከነዓውዳቸው በጣፋጭ ትረካ ያስቃኘናል። ይህን መሰል በጽሑፍ ከተለያዩ የሥነ ጥበብ (አርት) ፎርሞች ወደ ጽሑፍ ተመልሰው በታሪክ ምሁራን የተተየቡ ጥቂት ናቸው። እንደ ዓለሜ እሸቴ (ፕሮፌሰር) Aleme Eshete, Songs of the Ethiopian Revolution Chansons de La Revolution Ethiopienne (Addis Ababa: Ministry of Culture, September 1979) በሚል በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች (አማርኛ፣ አፋርኛ፣ ጉራግኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አኝዋ፣ በኤርትራ ትግርኛ፣ ሶማልኛ፣ ወላይትኛ) የተደረሱ መዝሙሮችን አነስ ባለችና በባለሁለት ቋንቋ (እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ) መጽሐፍ ከመግቢያና ከግርጌ ማስታዎሻዎች ጋር የሠሩልን ተጠቃሹ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ በዩኔስኮ ስለባህል የታተመ  አነስ ያለች መጽሐፋቸውና ስለ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የጻፉት ሥራዎች ይገኙባቸዋል። ይህ የተስፋዬ ገብሬ ‹አብዮታዊት ኢትዮጵያ› ምዕራፍ በቁጥብነት በአሥር ገጾች አስቀመጠው እንጂ አስፋፍቶ የዘመኑን መንፈስ ከሌሎች አርቲስቶች ከተሠሩት ጋር በማነጻጸር ሊሠራቸው ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ለሌሎች አጥኚዎችም እንደ ግብዓት በር ከፋች ሥራ ይሆናል።  

‹‹ተስፋዬን ፍለጋ ከ፬ ኪሎ እስከ ቬሮና›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

፪. በግለሰብ የማበረሰብ ትውስታ  

ትውስታው የግለሰብ ብቻ ባዮግራፊ አይደለም የማኅበረሰብ ማያ ሊሆንም ይችላል። መስኮቱ ተስፋዬ ገብሬ ቢሆንም የትውልዶች ዘመን ለውጦች ተከትቦበታል። በሰይፉ መታፈሪያ አተረጓጐም ተስፋዬን ፍለጋ በንተሱ ልንለው እንችላለን። ግን የግለሰብ ብቻም አይደለም። የበርካታ ግለሰቦችን የቡድንን፣ የማበረሰብን ትውስታ ይዟል ማለት ይቻላል። Collective Biography የምንለው ዓይነት። በተስፋዬ ፍለጋ ውስጥ ቤተሰቦቹ፣ አብሮ አደግ ጓደኞቹ፣ የሙያ ባልደረባዎቹ፣ ሰፈሩ፣ የአዲስ አበባና የቬሮና ከተሞች ይዳሰሱበታል። እንደ ባዮግራፊ በአንድ ግለሰብ በኩል የከተሞች፣ የትውልድ፣ የክፍለ ዘመን እኩሌታ ተቃኝቷል፡፡ ይህን መሰል ሥራ የአይዳ ዕደማርያም ተጠቃሽ ነው (Aida Edemariam, The Wife’s Tale – a personal history, London: HarperCollins, 2018)። በአያትዬው ታሪክ መነጽር የአንድ ክፍለ ዘመን የአገር ታሪክ ታስቃኛለች። ማርቆስም በቴስ በኩል ለክፍለ ዘመን ሩብ ጉዳይ አለፍ ያለ ትዝታን ለውጦችን ያስቃኘናል።

፫. የከተማና የዳያስፖራ ሙዚቃ አርት

ይህ ርዕሰ ጉዳይ ብዙ አልተሠራበትም ማለት ይቻላል። በኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ርቀው ከሄዱ በኋላ የሠሩት ሥራዎች ተጠንቷል ለማለት አያስደፍርም። እንደ ሰሎሞን አዲስ ስለኢትዮጵያውያን በአሜሪካ በስደት የመቶ ዓመት ታሪክ የሚያስቃኝና በሠዓሊያን ዙሪያ የሚያተኩረው የኤልዛቤት ሥራዎች ውጪ ስለኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሥነ ጥበብ አልተሠራም ማለትም ይቻላል። ጌታቸው ኃይሌም (ፕሮፌሰር) በአንድ መጣጥፋቸው በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የአማርኛ ገጣሚዎች በማለት ያሰናዷት ተጠቃሽ ናት።

ይህ የማርቆስን ሥራ ከእነዚህ ለየት የሚያደርገው በአንድ አርቲስት የሕይወትና የሙያ ጉዞ ላይ በማተኮሩ፣ ቀዳሚና ፈር ቀዳጅ ነው። በአንድ አርቲስት ወይም ምሁር ዙሪያ የሚያተኩር ሥራ ላይ የሚያጠነጥን ሥራ መሠራቱ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ። ሌሎቹ ጠቀሜታ ቢኖራቸውም ይኼን ዓይነቱ ደግሞ ትኩረቱና ጥልቀቱ የበለጠ ይሆናል የሚል ዕይታ አለኝ፡፡ እኔም በራሴ የጥናት መጽሐፍ የተከተልኩት ስለሆነ ይህንን ሳላወድስ ባልፍ ‹‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ›› ያስብልብኛል።

ተስፋዬ አዲስ አበባ አራት ኪሎ ተወልዶ ያደገ ከመሆኑ የተነሳ ሙዚቃው ከአገርኛው የዜማ ስልት አፈንግጦ ከውጪው የተቀዳ ነው፡፡ በሥራው ከአገሩ ወደ ጣሊያን፣ ከዚያም በአሜሪካ በቆየበት ጊዜያት የተለያዩ የሙዚቃ ስልቶችን አቀንቅኗል። የአፍሪካ አሜሪካውያንን የጃዝን ሙዚቃ በማቀንቀኑ የልዩ ልዩ ባህሎችን ልውውጥና መስተጋብር ፈጥሯል።

ስለዚህ ጉዳይ አሸናፊ ከበደ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹የሙዚቃ ለውጥ music change በአፍሪካ የሚመጣው በሦስት ምክንያቶች ነው። ይኼውም ከmusical adoption, acculturation and innovation ነው›› ይላሉ። የመጀመሪያው አዶፕሽን ከቅኝ ግዛት ኮሎኒያሊዝም አስተሳሰብ የተነሳ የራስ የሆነውንና ራስን ከመጥላት እንዲሁም ቅኝ ገዥዎችን ከመውደድ ሥነ ልቦናዊ ዝቅተኛነት ስሜት የሚፈጠር ነው ሲሉ፣ ሁለተኛውና ሦስተኛው የጥገና ወይም የፈጠራ ሁናቴ የተካተተበት ነው በማለት ከከተሜነት ባህልም ጋር ያያይዙታል።

የሙዚቃው ሊቅ እንዳሉት ተስፋዬ ገብሬ አዲስ አበባ ያውም መሀል ፬ ኪሎ እንደመወለዱ፣ የተማረበት ትምህርት ቤት መምህራንና ሥርዓተ ትምህርቱ፣ በወወክማ (ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር) ያገኛቸው የነበሩ የውጭ አገር መምህራን ሳቢያና በሆሊውድ ፊልም ካለው ጫና አንጻርም ወደ ውጪው የሙዚቃ ስልት ሳይሳብ አልቀረም። በዘመኑ ሁለቱንም (ባህላዊውንና ዘመናዊ) የሙዚቃ ስልት የሚከተሉ እንደነበሩ ቴስ የዘመናዊው ሙዚቃ ስልት የሚሳብ ቢሆንም (በአዲስና በተሻሻለ መልክ) ‹‹የፍቅር ምግብ››ን የመሰሉ ሙዚቃዎች ሠርቶ አበርክቶልናል።

፬. ስለተዘክሮ ስለትውስታ

ይኼ የትውስታ፣ የትዝታ ጉዳይ (popular memory as history) ለዳያስፖራ አርቲስቶች ወይም ነዋሪዎች ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ነው። በሌላ አባባል በስደት ኗሪዎች ደራሲውም፣ ባለታሪኩም እንዲሁም የተደራስያኑ (አንባብያኑ) ዓብይ ርዕሰ ጉዳይ ይመስለኛል። ይህንን የተስፋዬ ገብሬ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም አርቲስቶች ይጋሩታል። ከዘፈን ውጭ ብናስብ የኃይሌ ገሪማ (ፕሮፌሰር) ፊልሞችንና ጽሑፎች እንዲሁም የፊልም ቲዮሪስቱን የተሾመ ኃይለ ገብርኤል (ፕሮፌሰር) ሥራዎች መጥቀስ ይቻላል።

ስለ ተዘክሮ፣ ስለ ትውስታ ለመመለስ ናፍቆትና የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ለመመለስና ለማስታወስ ባሉ ውጣ ውረዶች ከባድ ተግዳሮቶች የዳያስፖራ አርት በእጅጉ ያስቃኛል። ይህንን ተዘክሮና ትውስታን የኃይሌ ገሪማም ሆነ የተስፋዬ ገብሬ ሥራዎች ይገልጡልናል። ኃይሌ በጤዛ ፊልም ላይ ዋናው ገጸ ባህርይ የሆነው ዶክተሩ አንበርብር የአፍሪካ ምሁራንን ሲወክል ወደ ተዘክሮውና ትውስታው ለመመለስ ያለውን ተግዳሮት፣ የደረሰበትን ጉዳት እንዴትና ለምን እንደሆነ በመፈለግ የሚያጠነጥን ድራማዊ ፊልም ነው።

ከዚህ አንጻር ደራሲው ማርቆስም የልጅነት ተዘክሮውና ትውስታው ውስጥ፣ ያልጠፋው ግዙፉ የተስፋዬ ገብሬ ማንነት ራሱን ፍለጋ ሥራውና  ከጉዞ ማስታወሻዎቹ ጋር በውብ ቋንቋና ምስል ከታላቅ ምናብ ጋር ያስቃኘናል። 

፭. ጽሑፉ ጋባዥ ነው ያሳትፋል

ማርቆስ ለመማር ዝግጁነቱ (ተማሪነቱን)፣ የማያባራ ተመራማሪነቱን እንዲሁም ትህትናውን የሚያሳየን ሥራ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የደራሲው ‹Intellectual Curiosity› እናይበታለን። ይህ ለደራስያን በተለይም ለተመራማሪዎች ትልቅ ብቃት ወይም ቨርቹ ነው ማለት ይቻላል። ማርቆስ በታሪክ ቆፋሪነቱ ‹‹የትውስታ አርኪዮሎጂስት›› ቢባል የተመቸ ነው። ምክንያቱም በሞት ከተለየን አርባ የሆነውን ተስፋዬ ገብሬን ከውልደቱና ዕድገቱ ወደ 80 ዓመታት ተመልሶ በ327 ገጾች ሰንዶ አቅርቦልናል። ብዙ ውጣ ውረድ ማድረጉን ስናይ የታሪክ ቆፋሪነቱን እንድንዘክር አርኣያ ሆኖልናል። ጸሐፊው ማርቆስ በሥራው ሒደት ያጋጠሙትን ክፍተቶች መሞላት አለበት የሚል ሐሳብ ከሰዎች ሲደርሰው፣ እሱ ካገኛቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች የተሻሉ ሆነው ካገኛቸው ለማረምና ለመታረም ያለው ዝግጁነት እጅግ ደስ የሚል በመሆኑ ወደፊት ምናልባት መጽሐፉ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ዕትም ከታተመ ሊያሻሽለው ‹‹ስህተት›› ቢኖርም ሊያርመው ይችላል ብዬ እገምታለሁ። (በተጨማሪ ተከታይ ሥራ ወይም የፊልም ስክሪፕት ሆኖ በፊልም መልክ ቢሠራበት መልካም ነው እላለሁ።) በሌላ ቃለመጠይቅ፣ እትም ወይም ከኅትመት ውጭ እንደፊልም ባለ መልኩ ቢሠራው ብዙ ነገሮችን ለማካተትና ለማበጃጀት አቅምና ፈቃደኝነት ያለው ደራሲ ነው።  በተጨማሪም የተስፋዬ ሙዚቃዎች ሃይማኖት ሰባኪ (ካቶሊክን ለማለት ነው) የሚሉ ሐሳቦች ተደጋግመው ተጠቅሰዋል። ይህ ሐሳብ ከመሬት ተነስቶ አይደለምና ይህንን ያሉት ከየትኞቹ ሙዚቃዎች ተነስተው ነው?  በየትኛው ቋንቋ የተዜሙት? እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎችን በማከል ሰፋ ያለ ማብራሪያ በማርቆስ ወይም በሌሎች አጥኚዎች ተጠንተው  ትንተናን ያቀርቡልናል የሚል እምነት አለኝ።

፮. ውልት ራው ምጋና

የመታሰቢያ ሐውልት ወይም ምንም ዓይነት ተቋም ሆነ ፕሮግራም ላልተሠራለት አርቲስት ገጣሚና ድምጻዊ ተስፋዬ ገብሬ፣ ትውልድና የታሪክ ምዕራፍ እንዲሆነን ለኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ከተማም ትውስታ ይሆነን ዘንድ ሐውልት የሆነ ሥራ ማርቆስ ሰጥቶናል። ቴስ በግጥምና ዜማው፣ ማርቆስ ደግሞ በጥልቅ ምርምር ምናብ ሁለቱም በፍቅር የአገር ፍቅርን፣ የሕዝባችንን ውበትና ክብር ድል አድራጊነት እንዲሁም የመዲናችንን ውበት በተለያዩ ሁኔታዎች ቢደበዝዝም ትዝታውን አስቀርተውልናል።

‹‹የአዲስ አበባ ነገር›› በሚለው የመዝጊያ ምዕራፉ፣ ‹‹አበባ! አዲስ አበባ (ከሀገር ፍቅር ማኅበር ጋር)፣ አዲስ አበባ ውብ ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማና እዚህ ነው የተወለድኩት›› የሚሉት መዘርዝርና በቴስ የእጅ ጽሑፍ ‹‹አዲስ አበባ ውብ ከተማ›› በምናብና በትውስታ የአገርና የከተማን የቀደመ ውበት በፍቅር ያበረከትልናል።  

ለዓመታት ድካሙ፣ ለከፈለው ዋጋ (በጊዜ፣ በገንዘብና በስሜት) ከፍ ያለ ምሥጋና ይገባዋል። ቅርስ ሲናድ፣ ታሪክ ሲፋቅ፣ ትውስታ ወይም ተዘክሮ ሲደለዝ፣ መጻሕፍት ሲዘረፉ፣ ቤተ መጻሕፍት ሲቃጠሉ፣ ቤተ መጻሕፍት የሚያህሉ ታሪክ ነጋሪዎቻችን ሲያልፉ፣ ሐውልቶች ሲፈርሱ እያየ ይህ ነገር ተስፋ ሳያስቆርጠው በብዙ መሥዋዕትነትና ትጋት የተስፋዬ ገብሬን ሥራዎች ጥንቅቅ ባለ ሁኔታ ሠርቶልናልና አሁንም በድጋሚ ምሥጋና ይቸረዋል። ለእኛ በሰበብና ባስባቡ የባለታሪኮቻችንን የታሪክ ምዕራፎች ከዓይናችን ሥር ሲጠፉብን እያየን፣ ባላየ ዝምን ማለታችንንና ያለመሥራታችንን ይኮንነናል። በይቻላል መንፈስም ተነሳስተን እንሠራ ዘንድ ድንቅ ሥራውን አበርክቶልናል። ይህን የፍቅር ስጦታ labor of love ነው!።

በዚህ ጽሑፍ ለተካተቱ ምስሎች ማርቆስ ተግይበሉን ዕውቅና ስንሰጥ ከልባዊ ምሥጋና ጋር ነው።

ከአዘጋጁ ጽሑፉ በጣሊያን ካልቸራል ኢንስቲትዩት ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ለመጽሐፉ ምርቃት የቀረበና የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው tekletsadikbelachew@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles