Friday, March 1, 2024

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምና ያለ መከሰስ መብት ጥያቄ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአስከቿይ ጊዜ አዋጅ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እንዳስፈላጊነቱ በመላ አገሪቱ ሊተገበር ይችላል ተብሎ በአማራ ክልል በሥራ ላይ ውሏል፡፡ ባለፉት አራት ወራት የአዋጁን ትግበራ ተከትሎ በአማራ ክልልና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

አዋጁ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ ክልል ከተሞች የእንቅስቃሴ ገደቦችና የሰዓት እላፊ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥሰት ወንጀል ተከሰው ብዙዎች ከመታሰራቸው በተጨማሪ፣ በሕገወጥ እንቅስቃሴ ተሳትፈዋል ተብለው ብዙዎች ታስረዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የመንግሥት ኃይሎች በክልሉ ይንቀሳቀሳሉ በሚባሉ ታጣቂዎች ላይ የተጠናከረ ኦፕሬሽን ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ የክልሉን ፀጥታ የማስከበሩ ሥራ በመደበኛው የሕግ ማስከበር አሠራር ማከናወን ባለመቻሉ ተብሎ ሥራ ላይ የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ጠንከር ያሉ ኦፕሬሽኖችና የፀጥታ ኃይሎች ዕርምጃዎችን ያስከተለ ቢሆንም የክልሉ ሁኔታ ስለመሻሻሉ ግን ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች አሁንም ቢሆን ጠንካራ የተኩስ ልውውጦችና ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸው ይነገራል፡፡ የእነዚህ ግጭቶች መቀጠል ደግሞ የክልሉን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚያደፈርስ ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን በሕይወት የመኖር መሠረታዊ መብትም አደጋ ላይ የጣለ መሆኑ ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት በአማራ ክልል ለወራት የቀጠለው የትጥቅ ግጭት ያደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ በሰፊው ዳሶታል፡፡ ተፋላሚ ኃይሎች ሲቪል ሰዎችንና ንብረቶችን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችንና መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ከማድረግ ሊቆጠቡ እንደሚገባ ያሳሰበው ሪፖርቱ፣ መንግሥትም የማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለበት አሳስቦ ነበር፡፡

ሪፖርቱ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች ግጭት መከሰቱን ገልጾ ነበር፡፡ በመንግሥት ኃይሎች በአየር ወይም ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ውጊያ በታጣቂዎች ላይ መክፈታቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ መጥተህ ብላ ከተማ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ ሲቪሎችን መግደሉን አመልክቷል፡፡ በደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ ጥቃት ደግሞ ስምንት ሲቪሎች መሞታቸውን ነው የገለጸው፡፡

እነዚህንና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸሙ በከባድ መሣሪያ የታገዙ ጥቃቶችን የሚዘረዝረው ሪፖርቱ፣ በክልሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላም ቢሆን ግጭቱ ባለመብረዱ የተነሳ የዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

የኢሰመኮ ሪፖርት ከወጣ በኋላም በአማራ ክልል ግጭቱ መቀጠሉ ይሰማል፡፡ በቅርቡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአማራ ክልል የተጀመረው ታጣቂዎችን የመደምሰስ ዘመቻ እንደሚቀጥል የጠቆመ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ከኦነግ ሸኔ ቡድን ጋር ተጀምሮ የነበረው የድርድር ጥረት ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በአማራ ክልል ይንቀሳቀሳሉ ከሚባሉ የታጠቁ ኃይሎች ጋር ደግሞ አንዳችም የድርድር ፍንጭ እስካሁን አልታየም፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የሁለቱ ትልልቅ ክልሎች የኦሮሚያና የአማራ ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ በቀላሉ ይሻሻላል የሚል ግምት እንዳይፈጠር ያደረገ ነው የሆነው፡፡

በአማራ ክልል መንግሥት ሥር የሚታተመው በኩር ጋዜጣ ከሰሞኑ ‹‹ሰላም የታጣባቸው ፈታኝ ወቅቶች›› በሚል ርዕስ ባስነበበው አንድ ሀተታ፣ ክልሉ የተሟላ ሰላም እንደሌለው በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ‹‹በክልሉ አስተማማኝና ነፃ እንቅስቃሴ የለም፡፡ ከአንድ ከተማ ወደሌላ ከተማ የሚደረግ የመጓጓዣ እንቅስቃሴ አሁንም ገና መፍትሔ አላገኘም፡፡ አርሶ አደሩ ያመረተውን ለገበያ ማቅረብ አልቻለም፡፡ ጤና ተቋማት የተሟላ የሕክምና አገልግሎት ወደ መስጠት አልተሸጋገሩም፡፡ የመጀመርያው ወሰነ ትምህርት ተጠናቆ መመዘኛ ፈተናዎች በሚሰጡበት በዚህ ወቅት በመማር ማስተማር ቢጀመርም እንኳን፣ ሁሉም ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ገና አልተገኙም፡፡ በአጠቃላይ የፀጥታ መደፍረሱ ክልሉን ብሎም አገሪቱን ለከፋ ማኅበራዊ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት እየዳረገ መሆኑን በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ፤›› በማለት ነው በኩር ሀተታውን ያቀረበው፡፡

የክልሉ መንግሥት ግን ሰሞኑን ባካሄደው የሰላም ጥሪ መሠረት፣ በርካታ ወጣቶችና ታጣቂዎች ከሕገወጥ እንቅስቃሴ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን በመግለጽ ላይ ነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያትና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ የአማራ ክልል ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለውም ገና አለየለትም፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን በማድረግ እየተወሰዱ ያሉ አንዳንድ ዕርምጃዎች መነጋገሪያ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በተለይ ካለመከሰስ መብት ጋር በተያያዘ ጥያቄ እያስነሳ ያለው በተለያዩ እርከኖች ያሉ ምክር ቤቶች እንደራሴዎች የሚታሰሩበት አሠራር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥያቄዎች እየተነሱበት ነው፡፡

ያለ መከሰስ መብት በማንሳት በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎች ጉዳይ በኢትዮጵያ አዲስ አይደለም፡፡ ከእነ አቶ ታምራት ላይኔ እስራት ጀምሮ በ1993 ዓ.ም. እስከ ተፈጠረው የኢሕአዴግ መከፋፈል ያለ መከሰስ መብታቸው በምክር ቤቶች የተነሳ ሰዎች በርካታ መሆናቸው ይነገራል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ የፖለቲካ ለውጥ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሰዎች ያለ መከሰስ መብታቸው ተነስቶ ለሕግ ሲቀርቡ ታይቷል፡፡ የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ አሌ) ይህ ዕጣ ከገጠማቸው አንዱ ናቸው፡፡ የትግራይ ክልል ጦርነት በተቀሰቀሰ ማግሥት ደግሞ የተወካዮች ምክር ቤት የደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) እና የ38 የትግራይ ክልል አመራሮችን ያለ መከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወሳል፡፡

ባለፈው ዓመት ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ተጠያቂ ለማድረግ፣ የተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳቱ አይዘነጋም፡፡

ይሁን እንጂ ከዚያ በፊትና ከዚያ ወዲህ በተፈጠሩ አንዳንድ አጋጣሚዎች ያለ መከሰስ መብታቸው በተለመደው መንገድና አሠራር ሳይነሳ የሚታሰሩ ሰዎች መኖራቸው፣ ጉዳዩ የሕግ ክርክር እንዲነሳ የሚጋብዝ እየሆነ ነው፡፡

ያለ መከሰስ መብታቸው በምክር ቤት ሳይነሳ ሰዎች የሚታሰሩበት የሕግ አግባብ ወይም አሠራር እንዳለ የተጠየቁት የሕግ ባለሙያው አቶ መሱድ ገበየሁ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

‹‹በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወይም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ላይ ከአራት መብቶች ውጪ ሌሎች በሙሉ ተፈጻሚ እንደማይደረጉ ተቀምጧል፡፡ ያለ መከሰስ መብትን ጨምሮ ሌሎች ብዙ የመብት ዓይነቶች ተፈጻሚ አይሆኑም፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተገናኘ የተጠረጠሩ ናቸው በሚል ግለሰቦች ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ሊታሰሩ ይችላሉ፤›› ሲሉ ነው ያስረዱት፡፡

ከሰሞኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አቶ ታረቀኝ ደግፌ የተባሉ የጉራጌ ዞን ተወካይን ያለ መከሰስ መብት ማንሳቱን እንደ ምሳሌ የጠቀሱት አቶ መሱድ፣ የተወካዩ ያለ መከሰስ መብት ሊነሳ የቻለው የተጠረጠሩበት ጉዳይ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የተያያዘ ላይሆን እንደሚችል ገምተዋል፡፡

‹‹ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዙ የወንጀል ጥርጣሬዎች ጊዜ ግን ይህን ቅደም ተከተል የመጠበቅ ግዴታ አይኖርም፡፡ አዋጁን ለማስፈጸም የሚቋቋመው ኃይል (ኮማንድ ፖስት) የት ላቆየውና ፍርድ ቤት ላቅርበው የሚሉ ጉዳዮችን የሚመለከተው እሱ ነው፡፡ ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጋር በተገናኘ በፓርላማው የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መከታተያ ቦርዱ ስለሚመለከተው፣ በሰዎቹ አያያዝ ላይ መልስ የሚሰጠው እሱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የእነዚህ አካላት አሠራር የእርስ በርስ ቁጥጥር ያሰፈነ (ቼክ ኤንድ ባላንስ) ነው ወይ የሚለው ጉዳይ መጠየቅ ይኖርበታል፤›› በማለት አቶ መሱድ የሕግ ተጠያቂነት ወሰኑ እስከየት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በኋላ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ተወካይ አቶ አማኒያስ ጉሸና መታሰራቸውን ፓርቲው ይፋ አድርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ካሳ ተሻገር (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ዮሐንስ ቧያሌውን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ክርስቲያን ታደለ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ መታሰራቸው ታውቋል፡፡

በቅርቡ የኦሮሚያ ምክር ቤት (ጨፌ) አባል አቶ ታዬ ደንደአ ያለ መከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ አቶ ታዬን በተመለከተ ደግሞ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በሰጠው መግለጫ መሠረት፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋረ በመተሳሰር ለጥፋት ተልዕኮ በኅቡዕ ሲሠሩ ተደርሶባቸዋል በሚል ጥርጣሬ መያዛቸው ነው የተነገረው፡፡ ከዚህ አንፃር የአቶ ታዬ ጉዳይ በቀጥታ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የተገናኘ አለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

ያለ መከሰስ መብት ስለሚጣስባቸው ሁኔታዎች የተጠየቁት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው አበበ በበኩላቸው፣ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ የሕገ መንግሥት መብት ለጥቂት ሰዎች ማለትም ለዲፕሎማቶች፣ ለምክር ቤት አባላት፣ ለፍርድ ቤት ዳኞችና ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹በሕገ መንግሥቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ኃላፊነት በተቀመጠበት አንቀጽ 63 ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ እስካልተያዘ ድረስ ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ በወንጀል አይጠየቅም ተብሎ ተደንግጓል፡፡ ይህ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ይህ ለጥቂት ሰዎች ብቻ ተብሎ የተቀመጠ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በሕግ በተቀመጠው አግባብ ሳይነሳ ሰዎች መታሰራቸው ምን ዓይነት ምሳሌ ያለው ነው የሚለው ለእያንዳንዱ ግለሰብ አስተያየት የሚተው ጉዳይ ይሆናል፤›› በማለት ነው የገለጹት፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀ ጊዜ ላይነኩ ስለሚችሉ መብቶች የተጠየቁት አቶ አበባው አንቀጽ አንድ፣ 88፣ 25፣ 39 ተብሎ መዘርዘሩን ያወሳሉ፡፡

‹‹አንቀጽ 25 ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡ የትኛውም ሰው ወንጀል ከሠራ ይጠየቃል፡፡ ይህን የሕገ መንግሥት ዓላማ ግን የሚሽሩ አንዳንድ አሠራሮች አሉ፡፡ ሕፃናት ሰው ቢገድሉ በወንጀል አይጠየቁም፡፡ ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው ቢባልም ነገር ግን በዕድሜ ለጋነት የተነሳ ይህ ተጣሰ፡፡ ሁለተኛው በአዕምሮ ሕመም የተነሳ በሕግ አለመጠየቅም ይኖራል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በልዩ ሁኔታ (በሕግ አግባብ) ያለ መጠየቅ መብት የተሰጣቸው ዜጎች ጉዳይ ይመጣል፡፡ ዜጎች በሕግ አግባብ እኩል ናቸው ወንጀል ከሠሩ ይቀጣሉ ቢባልም እንኳ፣ በእነዚህ ሦስት ሕገ መንግሥታዊ አሠራሮች የተነሳ ከሕግ ተጠያቂነት ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ድንጋጌ እያለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል በሚል ብቻ ያለ መከሰስ መብት በሕግ ሳያነሱ ዜጎችን ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል ወይ የሚለው ጉዳይ መጠየቅ ይኖርበታል፤›› ሲሉ ነው የሕግ ሙግቱ የት ድረስ እንደሚሄድ ያስረዳሉ፡፡

ስለዚህ ሁኔታ አስተያየት ያጋሩት አቶ መሱድ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁሉንም መብቶች አካልን ነፃ የማውጣት (ሀቢየስ ኮርፐስን) ጨምሮ የሚከለክል በመሆኑ፣ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ተያዙ ተብሎ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጠርጥረዋል የተባሉ ሰዎችን ጉዳይን ማንሳት እንደማይቻል ነው የገለጹት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -