Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በጨረታ የማስወገድ ሒደት የንግድ ውድድርን እንዳይጎዳ ይፈተሽ!

ከዚህ ቀደም በዚሁ ዓምድ ሥር የኮንትሮባንድ ንግድ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ እያናጋ ስለመሆኑ የሚያመላክት ጽሑፍ በወፍ በረር ቀርቦ ነበር፡፡ በሌላ ተያያዥ ጉዳይም መንግሥት በቁጥጥር ሥር አዋልኳቸው የሚላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በዓይነትም ሆነ በመጠን እየጨመረ መሆናቸውን የሚያሳዩ አኃዛዊ መረጃዎች በአስረጂነት ቀርበውም ነበር፡፡ የሚያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በመንግሥት እጅ ከገቡ በኋላ ምን ይደረጋሉ? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ብዥታ ስለመኖሩም ተመላክቷል፡፡ በተለይ የሚያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መጠን እየጨመረ ከመምጣቱ አንፃር እነዚህ ዕቃዎች መጨረሻቸው ምንድነው? ምንስ እየተደረጉ ነው የሚለውን ጥያቄ ደግመን ደጋግመን ለማንሳት የሚያስገድዱ ብዙ ምክንያቶች እየቀረቡ ነው፡፡ የሚያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ግምት ሲነገር አኃዙ አስደንጋጭ ከመሆኑም በላይ ሒሳቡ ሲሰላ በዓመት የሚያዘው ዕቃ ግምት የአንዳንድ ክላላዊ መንግሥታትን ዓመታዊ በጀት ያክላል ማለት ይችላል፡፡ 

ስለዚህ ይህንን ያህል መጠን ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች አወጋገድ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ እየተሠራበት ካልሆነ ጉዳዩ አደጋ እንደሚያስከትል መገመት ይቻላል። ለሌብነትም በር የሚከፍት መሆኑ አያጣራጥርም፡፡ በመንግሥት እጅ የገቡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የሚያዙት ወይም የሚወረሱት በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ያልገቡ በመሆናቸው ነው፡፡ ወይም በሕጋዊ መንገድ ለውጭ ገበያ መቅረብ ሲገባቸው ከዚህ አፈንግጠው በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሊወጡ ሲሉ የተያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በሕገወጥ መንገድ የተያዘ ምርት ወይም ዕቃ ለሕጋዊ መንገድ ሥራ ላይ መዋል ወይም መወገድ አለበት ማለት ነው፡፡ 

እንዲህ ባለው መንገድ ሲንቀሳቀሱ የተያዙ የተለያዩ ምርቶችና ሸቀጦች መንግሥት የሚወርሳቸው ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል ጭምር መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በተለይ በሕጋዊ መንገድ የሚገቡ ምርትና ሸቀጣ ሸቀጦች የጥራት ደረጃቸው ተዓማኒ ስለማይሆን ኅብረተሰቡ ላይ አደጋ እንዳያደርሱም በማሰብ ዕርምጃው የሚወሰድ መሆኑን ሁሉም ይገነዘበዋል፡፡ ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሆነው ሆኖ የተወረሱ የኮንትሮባንድ ምርቶች አወጋገድ በሕጋዊው የግብይት ሥርዓትንና በፍትሐዊ ውድድር ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ለብቻው ሊታይና ሊፈተሽ ይገባል። 

በኮንትሮባንድ የሚገቡ ዕቃዎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳታቸው በአገር ደረጃ የሚገለጽ ቢሆንም የኮንትሮባንድ ዕቃዎች አምልጠው በገበያ ውስጥ ሲገቡ የመጀመርያ ተጎጂ የሚሆነው ተመሳሳይ ምርቶችን ለመነገድ ሕጋዊ ፈቃድ ወስደው የሚሠሩ ነጋዴዎችን ነው፡፡ 

እነርሱ ቀረጥ ከፍለው የሚያስገቡትን ዕቃ ሲሸጡም የመንግሥት ግብር የሚከፍሉ ናቸው፡፡ በጎን ቀረጥ የማይከፈልበት የትርፍ ግብር የማይጠየቅባቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ገበያውን ከያዙት ሕጋዊ ነጋዴው ከሰረ የመንግሥትም ገቢ ቀነሰ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኮንትሮባንድ ዕቃ በሕገወጥ መንገድ ገብቶ ገበያውን እንዳይረብሽ ታሳቢ ተደርጎ ጭምር ነው ኮንትሮባንድን ለመከላከል የሚሠራው፡፡ 

በመሆኑም በኮንትሮባንድ የሚያዙ ዕቃዎች መልሰው የሚሸጡ ከሆነ ለሕገወጥ ድርጊት ሕጋዊ መፍትሔ እንደመፈለግ ይቆጠራል ወደ ሚባለው ድምዳሜ ይወስዳል፡፡ 

የብዙዎችን ብዥታና ጥያቄም ይህ ነው፡፡ በኮንትሮባንድ የተያዙ ዕቃዎች በአደባባይ ወይም በይፋ መሸጣቸው እንዴት አግባብ ይሆናል? በኮንትሮባንድ የገባ ዕቃ ገበያ ውስጥ ከገባ አንዱ ጉዳት ሕጋዊ ነጋዴውን መጉዳት ከሆነ በኮንትሮባንድ የተያዘ ዕቃን መንግሥት መልሶ ከሸጠ በዚህ ዕርምጃ እነዚያን ምርቶች የሚሸጡ ነጋዴዎች ሥራን ማበላሸት አይሆንም? ስለዚህ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ወደ ገበያ እንዳይገቡ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች መልካም የመሆናቸውን ያህል የእነዚህ ዕቃዎች የመጨረሻ አድራሻም በሕግና በሥርዓት ተገቢውን ቦታ እንዳይዙ ማድረግ ካልተቻለ የግብይት ሥርዓት ውስጥ መዛባት ይፈጥራል፡፡ ያልተገባ የንግድ ውድድርን ከማስከተሉም በላይ ሕጋዊ ነጋዴዎችን ቢዝነስ ሊጎዳ እንደሚችል ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ 

እንዲህ ያለውን አስተያየት ለመስጠት የወደድኩበት ያለምክንያት አይደለም የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በአደባባይ እየቸበቸቡ መሄድ ከተለመደ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚፈጠረው መዛባት እየሰፋ ይሄዳል ከሚል ሥጋት ነው፡፡ 

የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ከመሸጥ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ እየሰማን ያለው ማስታወቂያ ግን መንግሥት የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በጨረታ ለመሸጥ መወሰኑ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሕጋዊነቱ ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡ ሕጋዊ መሠረት ካለውም ጉዳዩ መፈተሽ እንደሚገባው የሚጠቁም ነው፡፡ ለማንኛውም ሰሞኑን የገቢዎች ሚኒስቴር በኮንትሮባንድ ከያዛቸው ዕቃዎች ውስጥ የሞባይል ቀፎዎችን ለመሸጥ ያወጣው ማስታወቂያ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር ባወጣው ማስታወቂያ፣ ‹‹እንዳያመልጥዎ! በኮንትሮባንድ የተያዙና የተወረሱ ስማርት የሞባይል ቀፎዎች እስክሪኖችና ቻርጀሮችን ይጫረቱ!›› ይላል፡፡ 

ከዚሁ ማስታወቂያ ጋር ተያይዞ በድምጽ የተላለፈው መልዕክት ደግሞ ‹‹በጉምሩክ ኮሚሽን የአዋሽ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በኮንትሮባንድ ሲዘዋወሩ ተይዘው የተወረሱ ስማርት የሞባይል ቀፎዎች እስክሪኖችና ቻርጀሮችን በግልጽ ጨረታ አወዳድሮ መሸጥ ይፈልጋል›› በማለት መሥፈርቱን የሚያሟሉ ተጫራቾች በማስታወቂያው ላይ በተገለጸው ቀንና ሰዓት የተዘጋጀውን የጨረታ ሰነድ እንዲገዙ ጥሪ የሚያቀርብ ነው፡፡ የጨረታ መክፈቻ ቀኑም በዚሁ ማስታወቂያ ተገልጿል፡፡ ይህንን ማስታወቂያ እንዳወጣ የተገለጸው ደግሞ የአዋሽ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ይህ ማስታወቂያ በድምጽም በጽሑፍም በገቢዎች ሚኒስቴር የመረጃ ገፆች ላይ በግል እንዲቀመጥም ተደርጓል፡፡

ስለዚህ በኮንትሮባንድ የተያዙ ዕቃዎችን እንዲህ ባለው መንግድ መሸጥ በተመሳሳይ ንግድ ላይ የተሰማሩ ቢዝነሶችን የሚጎዳ መሆኑ ሳይታወቅ ቀርቶ ከሆነ ሊታረም ይገባል፡፡ ስለሆነም በኮንትሮባንድ የተያዙ ዕቃዎች አወጋገድ ዙሪያ ያለው ብዥታ ሊጠራ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሕገወጥ የተባለ ማንኛውም ምርትና ሸቀጥ በሕጋዊ መንገድ መሸጥ ሕጋዊ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ላይም የሚመለከታቸው ሐሳብ ይሰጡበት፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት