Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጉምሩክ ኮሚሽን ቅሬታና የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ምላሽ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሪፖርተር ጋዜጣ ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትሙ ‹‹በሐሰተኛ የግዥ ሰነድና በኮንትሮባንድ የሚገባ የግንባታ ብረት የአገር ውስጥ አምራቾችን እያንኮታኮተ ነው›› በሚል ርዕስ ይዞት በወጣው ዘገባ ላይ እና በኅዳር 02 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትሙ፣ ‹‹መንግሥት በኮንትሮባንድ የሚገባውን ብረት ካላስቆመ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች በሦስት ወር ሊዘጉ ይችላሉ›› በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ ላይ፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ዘገባዎቹ የተሳሳቱና የኮሚሽኑን መልካም ስም የሚያጠፋ ናቸው በማለት ቅሬታውን አቅርቧል። 

የሪፖርተር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ቅሬታ ከተነሳባቸው ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ዘገባዎች ውስጥ ‹‹የተሳሳተና የስም ማጥፋት ድርጊት›› ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ፍሬ ነገሮች በመጥቀስ አብራሮቶ እንዲያስረዳ ጠይቋል፡፡

በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ ከሁለቱ የሪፖርተር ዘገባዎች ውስጥ ‹‹የተሳሳቱና የተቋሙን መልካም ስምና ዝና የሚጎዱ መረጃዎች ናቸው›› ያላቸውን ከታች የተዘረዘሩ ነጥቦች ለዝግጅት ክፍላችን ልኳል። እነዚህም፡-

1) ሐሰተኛ የተባለ የግዥ ሰነድ ለኮሚሽኑ ቀርቦ ተቀባይነት ባላገኘበት ሁኔታ ሰነዱ ተቀባይነት እንዳገኘና እንደተስተናገደ ተደርጎ የቀረቡ ዘገባዎች መሆናቸው።

2) የዕቃዎችን ቀረጥና ታክስ የመወሰን ብቸኛልጣን ያለው ኮሚሽኑ በአስመጪው የቀረበውን የግብይት ዋጋ ውድቅ በማድረግ ወቅታዊውን ዋጋ ለዕቃው ሰጥቶ ሊከፈል የሚገባውን ቀረጥና ታክስ አስከፍሎ እያለ በቀረበው አነስተኛ ዋጋ ምክንያት መንግሥት ቢሊዮን ብር ከቀረጥና ታክስ እንዳጣ በማስመሰል መዘገቡ ትክክል አይደለም።

3) ምንም እንኳን አስመጪው ወደ አገር እንዲያስገባ ፍቃድ ያገኘበት የብረት መጠን በሰነድ እንደታየው 300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቢሆንም ድርጅታችሁ ግን በዘገባው ይኸው መጠን ያለው ብረት ወደ አገር ውስጥ እንደገባና ለዚህም 11 ሚሊዮን ብር ብቻ ቀረጥና ታክስ በመከፈሉ መንግሥት በቢሊዮን ብር ቀረጥና ታክስ አጥቷል የሚል ዘገባ ያቀረበ

ቢሆንም ብረቱ ወደ አገር ውስጥ የገባው በክፍልፋይ ጭነት (Partial Shipment) ነው። በዚህ መሠረት በገባው የብረት መጠን ላይም መክፈል የሚገበው ቀረጥና ታክስ ተከፍሏል። ይህ አስራር ደግሞ በዓለም አቀፍም ሆነ በጉምሩክ አዋጅ ተቀባይነት ያለው ሆኖ ሳለ የሪፖርተር ዘገባ ግን የተከፈለው ቀረጥና ታክስ በዲክላራሲዮኑ ላይ ለተገለፀው ጠቅላላ የብረት መጠን እንደተከፈለ በማስመሰል ማቅረቡ ሌላው ስህተት ነው።

4) በዕታዎች ላይ ቀረጥና ታክስ የመወስን እና የመሰብሰብ ብቸኛ ስልጣን በሕግ የጉምሩክ ኮሚሽን ሆኖ እያለ የዕቃን ዋጋ ለመተመንም ሆነ በዕቃዎች ላይ ለጣል የሚገባን የቀረጥና ታክስ መጠን የመወሰን ሕጋዊ ስልጣን የሌለውን የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማህበር የተባለ ድርጅትን መግለጫ እንደ መረጃ ምንጭ በመጠቀም እና ድርጊቱ በእርግጥም የተፈፀመ በማስመሰል የቀረበው ዘገባ ሀሰተኛ ነው።

5) በጉዳዩ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ እና ማስረጃ የማቅረብ እንዲሁም የማስረዳት ብቃት እና እውቀት ያለው ጉምሩክ ኮሚሽን ስለጉዳዩ ይፋዊ በሆነ መንገድ ማብራሪያና ማስረጃ እንዲሰጥ ወይም እንዲያቀርብ ባልተጠየቀበትና ማስረጃ ባልሰጠበት ሁኔታ ዘገባው በሪፖርተር ጋዜጣ ታትሞ መሠራጨቱ ጋዜጣው ትክክለኛ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ እንዲሁም ሚዛናዊነትን ከግምት ወስጥ አስገብቶ ዘገባዎችን መሥራት እንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 የተጣለበትን ግዴታ ሆነ ብሎ ወደ ጎን በመተው የኮሚሽኑን መልካም ስምና ዝና ለመጉዳት የተሠራ ዘገባ ነው ብለን እናምናለን።

በመሆኑም ድርጅቱ በሕግ ከተጣለበት ግዴታ ፍፁም በተቃረነ አግባብ ባስተላለፈው ሀሰተኛና እዉነትነት በሌለው እንዲሁም ትክክል ባልሆነ ዘገባ የኮሚሽኑ መልካም ስምና ዝና እጅጉን የተጎዳ ስለሆነ ከላይ በተጠቀሱ እትሞች የወጣው ዘገባ የተሳሳተ ስለመሆኑ ተጠቅሶ እርማት እንዲያደርግ፣ በዚሁ አግባብ እርማት የማያደረግ ከሆነ ኮሚሽኑ ለተፈጸመበት የስም ማጥፋት ድርጊት በሕግ የምንጠይቅ መሆኑን አበክረን እንገልጻለን በማለት የኮሚሽኑ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቋል።

የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ምላሽ

ሪፖርተር ጋዜጣ፣ በጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትሙ ‹‹በሐሰተኛ የግዥ ሰነድና በኮንትሮባንድ የሚገባ የግንባታ ብረት፣ የአገር ውስጥ አምራችችን እያንኮታኮተ ነው›› በሚል ርዕስ ዘገባ አውጥቷል። በዚህ ዘገባ ውስጥ አማካኝ ከሆነ የዓለም የብረት ዋጋ በዕጅጉ ያነሰ ዋጋ መገዛቱን የሚገልጽ ሐሰተኛ የግዥ ሰነድ (under invoice) ለጉምሩክ ኮሚሽን በማቅረብ፣ 300 ሺሕ ቶን መጠን ያለው የአርማታ ብረት ወደ አገር ውስጥ መግባቱንና እንዲህ ያሉ ድርጊቶችም የአገር ውስጥ ብረት አምራች ኢንደስትሪዎችን ከህልውናቸው ባሻገር፣ መንግሥት ከቀረጥ ታክስ ማግኘት ያለበትን ከፍተኛ ገቢ እያሳጣ ስለመሆኑ ተጠቅሷል። ሪፖርተር ይህንን ዘገባ ያጠናቀረው በሰነድ ተደግፎ የቀረበለትን ጥቆማ መነሻ በማድረግ የራሱን የጋዜጠኝነት ምርመራ በማድረግ ሲሆን፣ ታትሞ በወጣው ዘገባ ውስጥ ደግሞ፣

የአገር ውስጥ ብረት አምራቾች፣ አምራቾቹን የሚወክለው የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ በጉዳዩ ላይ የሰጠው አስተያየትና የጉምሩክ ኮሚሽን ምላሽ ተካቷል።

የዝግጅት ክፍላችን የጉምሩክ ኮሚሽንን የተሟላ መረጃ ለማግኘት በወቅቱ ያደረገውን ሰፊ ጥረት ያክል ባይሳካላትም፣ በስተመጨረሻ ላይ ግን የተቋሙ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዘዘው ጫኔ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ‹‹ለጉምሩክ የሚቀርብ የግዥ ሰነድ ላይ የተቀመጠው የግብይት ዋጋ አነስተኛ ከሆነ፣ ኮሚሽኑ ሰነዱን ውድቅ በማድረግ፣ በየጊዜው በሚያደራጀው ወቅታዊ የገበያ ዋጋ መሠረት በሕግ የተቀመጠውን ቀረጥና ታክስ ይሰበስባል›› በማለት በስልክ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ምላሽ ሰጥተዋል። ይኸው የምክትል ኮሚሽነሩ ምላሽም በዘገባው ውስጥ የተካተተ ስለመሆኑ ኮሚሽኑም ሆነ የሪፖርተር አንባቢያን ዘገባውን በድጋሚ በመመልከት ማረጋገጥ እንደሚችሉ ለመግለጽ እንደወዳለን። በመሆኑም ኮሚሽኑ የሪፖርተር ዘገባ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው በማለት ያቀረበው ቅሬታና ወቀሳ ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ለዝግጅት ክፍላችን ባቀረበው የቅሬታ ደብዳቤ ላይ፣ በአስመጪው የቀረበውን የግብይት ዋጋ ውድቅ በማድረግ ወቅታዊውን ዋጋ ለዕቃው ሰጥቶ ሊከፈል የሚገባውን ቀረጥና ታክስ አስከፍሎ እያለ፣ በቀረበው አነስተኛ ዋጋ ምክንያት መንግስት ቢሊዮን ብር ከቀረጥና ታክስ እንዳጣ በማስመሰል መዘገቡ ትክክል እንዳልሆነ ገልጿል። ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ የቀረበውን ሰነድ ውድቅ በማድረግ ተገቢውን ታክስና ቀረጥ ያስከፈለው መቼ እንደሆነ ወይም ይህንን ያደረገው የሪፖርተር ዘገባ ከወጣ በኋላ ይሁን ከመውጣቱ በፊት የጠቀሰው ነገር የለም። 

ኮሚሽኑ ይህ ዘገባ ታትሞ ከወጣ በኋላ ቅሬታውን ለሪፖርተር የገለጸ ባይሆንም፣ ይህንኑ ዘገባ በተመለከተ ግን ከኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ጋር መወያየቱን የዝግጅት ክፍላችን ተረድቷል።

በኮሚሽኑና በማኅበሩ መካከል ውይይት ከተደረገ ከቀናቶች በኋላ ማኅበሩ ለመገናኛ ብዙኃን ስለ ጉዳዩ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ ሪፖርተር ጋዜጣም ይህንኑ መግለጫ እንደማንኛውም ሚዲያ ተከታትሎ፣ ‹‹መንግሥት በኮንትሮባንድ የሚገባውን ብረት ካላስቆመ፣ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች በሦስት ወር ሊዘጉ ይችላሉ›› በሚል ርዕስ ዘግቧል። በዚህ ዘገባ ውስጥም ዝቅተኛ ዋጋን የሚገልጽ የግዥ ሰነድ በማቅረብ ወደ አገር የገባው የአርማታ ብረትን በተመለከተ በኮሚሽኑና በማኅበሩ መካከል የተደረገው ውይይት ያለመግባባት (መተማመን ሳይፈጠር) እንደተጠናቀቀ ማኅበሩ ስለመግለጹ ተጠቅሷል። የጉዳዩን ዓውድ ለማስረዳትም፣ በመጀመሪያው ዘገባ የተጠቀሱ መረጃዎች በሁለተኛው ዘገባ ላይ የተካተቱ መሆናቸውንና የኮሚሽኑ አመራሮችን ምላሽ ለማካተት ተሞክሮ በወቅቱ ፈቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው ማካተት እንደልተቻለ ለማሳወቅ እንወዳለን።

ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባውን ያወጣበት አንደኛው ምክንያት፣ የጉምሩክ ኮሚሽን አነስተኛ ዋጋ የተጠቀሰበትን ሐሰተኛ የግዥ ሰነድ በመከታተል፣ የመንግሥትን ጥቅም እንዲያስከብር ጥቆማ ለመሰጠትና የአገር ውስጥ አምራቾች እሮሮ በሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲሰማና መፍትሔ እንዲያገኝ ነው። በመሆኑም ኮሚሽኑ የቀረበውን ሐሰተኛ ሰነድ ውድቅ በማድረግ፣ መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ቀረጥና ታክስ እንዳስከፈለ በዚህ ደብዳቤ የገለጸ በመሆኑ የሪፖርተር አንባቢያን ይህንን እንዲረዱ እንጠይቃለን። 

በተጨማሪም፣ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ዋጋ አሳንሶ ማቅረብ በኢትዮጵያ የተለመደና በጥናትም የተረጋገጠ ትልቅ ችግር መሆኑ ይታወቃል። ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ አፈጻጸማቸውን ያቀረቡት የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታም፣ ከውጭ የሚገባ ምርትን ‹‹ዋጋ አሳንሶ›› የማቅረብ ችግር ስለመኖሩ በይፋ ማረጋገጣቸውን ማስታወስ ተገቢ ነው። ሪፖርተር ጋዜጣም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ መረጃዎችን፣ የጋዜጠኝነትን መርህ በመከተል ሲያቀርብ እንደነበረው ሁሉ ወደፊትም በተቻለው አቅም ይህንኑ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በመሆኑም በኮሚሽኑ የተጠቀሱት ‹‹የሪፖርተር ዘገባዎች መልካም ስሙንና ዝናውን ለመጉዳት ሆነ ተብሎ የተሰሩ ናቸው›› ማለቱ፣ ለሦስት አስርት ዓመታት በሚዲያ ሥራዎቹ የሚታወቀውን ሪፖርተር ጋዜጣ እንደማይወክልና ይህንንም ታሪካችን እንደሚመሰክር ለማስገንዘብ እንወዳለን።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች