Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመንግሥት ግፊት በተካሄደው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተሰሙ ድምጾች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔያውን አካሂዷል፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ወቅቱን ጠብቀው ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫ ማካሄድ ያልቻሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጣልቃ ገብነት ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ማካሄዳቸው ግድ ሆኗል፡፡   

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ምክር ቤቶቹ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን እንዲያደርጉ ባያስገድድ ኖሮ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጨምሮ ሁሉም ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ለማካሄድ ፕሮግራም እንዳልነበራቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

ሆኖም ከሁለት ሳምንታት ወዲህ ሚኒስቴሩ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔያቸውን እንዲያካሂዱ ቀነ ገደብ ያስቀመጠ ማሳሰቢያ መስጠቱን ተከትሎ፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ ይህ ጠቅላላ ጉባዔ በመደረጉም የንግድ ማኅበረሰብ ያሉበትን ችግሮች በአጋጣሚው ለመተንፈስ ተጠቅሞበታል። ከዚህም ሌላ በንግድ ምክር ቤቱ አሠራሮች ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ለመጠየቅም ዕድል ሰጥቷል፡፡ 

በዚህ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱን ዓመታዊ ክዋኔ የሒሳብ አጠቃቀም የተመለከተ ሪፖርት በምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ቀርቧል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው ላይ በአብዛኛው ንግድ ምክር ቤቱ አከናውናቸዋለሁ ያላቸውን የተለያዩ ተግባራት በመልካም የተወሰዱ ቢሆንም፣ የንግድ ምክር ቤቱ ዋነኛ ክዋኔ መሆን የነበረባቸው ጉዳዮች ላይ መሥራት የነበረባቸው ተግባራት እንዳልተከናወኑ አባላቱ አመልክተዋል፡፡

በተለይ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለንግድ ምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በሰጠው ቦታ ግንባታ ላይ ፕሮጀክቱን መፈጸም ባለመቻሉ ቦታውን መነጠቁን የጠቀሱ አንዳንድ የገባዔው ተሳታፊዎች፣ የምክር ቤቱ አባል የሆኑ የንግድ ማኅበረሰቡ ተወካዮች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በማድረግ ግንባታውን ማከናወን ይቻል እንደነበር ሲገልጹ ተደምጠዋል። 

አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር በጋራ ለማልማት ከምክር ቤቱ ጋር የተገባው ውል መቋረጡን በተመለከተ፣ ከጠቅላላ ጉባዔው አባላት ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከሉ በጋራ ለማልማት አሁንም የአባላት ዕገዛ የሚያሻ እንደሆነ የቦርድ አባላቱ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ውሉን ያቋረጠው ከተማዋን በሚመጠን መልኩ ማዕከል ለመገንባት በመሆኑ፣ ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን ማድረግ ካልቻለ ከሌላ አልሚ ጋር እንደሚገነባ ለምክር ቤቱ ማስታወቁንም ተናግረዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ መገንቢያ ቦታ መነጠቁ ሀቅ ቢሆንም፣ ቦታውን የተነጠቀው ምክር ቤቱ ግንባታውን ባለመፈጸሙ ሳይሆን የከተማ አስተዳደሩ ቦታውን ለሌላ አገልግሎት ለማዋል በመፈለጉ ነው የሚል ምላሽ ከምክር ቤቱ አመራሮች ተሰጥቷል።

የንግድ ምክር ቤቱ ሕንፃ ግንባታ በበጀት እጥረት በወቅቱ ባለመከናወኑ የቦታው የሊዝ ውል ቢቋረጥም ሌላ ምትክ ለማግኘት ቦርዱ ክትትል እያደረገ መሆኑንም የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች ተናግረዋል፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን ቦታ ተረክቦ በእጁ ከስምንት ዓመታት በላይ የቆየና በቀድሞ አመራር ግንባታዎችን ለማካሄድ ብዙ ጥረቶችን አድርጎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ቦርዱ ግንባታ ያልተጀመረበትን ምክንያትና ለቦታው መወሰድ የበጀት እጥረትን ምክንያት ማቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነ ሲገለጽ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የቀድሞ ቦርድ አሁን ላለው ቦርድ ኃላፊነቱን ሲያስረክብ የሚገነባውን ሕንፃና ለግንባታ ማስጀመሪያ የሚሆን ገንዘብ ጭምር ያስተላለፈ ቢሆንም፣ አሁን ያለው አመራር ግንበታውን ለማካሄድ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳያደርግ መቆየቱ የተፈጠረ ችግር እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ በዕለቱ ከአንድ የጠቅላላ ጉባዔ አባል የቀረበው ሐሳብ ደግሞ ንግድ ምክር ቤቱ የሕንፃው ግንባታ በርብርብ እንዲሠራ አለማድረጉ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ምክር ቤቱ የቢሮ ሕንፃ ለመገንባትና የኮንቬንሽን ማዕከል ለመገንባት ሰፊ ቦታ መውሰዱን በማስታወስ፣ ግንባታዎቹን ረዥም ዓመታት ማከናወን ባለመቻሉ የሊዝ ዋጋው ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

ወ/ሮ መሰንበት በበኩላቸው ለሕንፃ ግንባታ የሚሆነው ቦታ ቢወሰድም ተለዋጭ ቦታ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ቦታው የት እንደሆነ ያልገለጹ ሲሆን፣ ከቀድሞው ቦታ የተሻለና ከከተማ መሀል ወጣ ያለ ቦታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

ሌሎች የጉባዔው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ የምክር ቤቱ ዋና ተልዕኮ የንግድ ኅብረተሰቡን ዓላማ ከመንግሥት ጋር ድልድይ ሆኖ ማገናኘት ቢሆንም፣ በቀረበው ሪፖርት ላይ ይህንን አለመመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር እየሠራ አይደለም የሚል አስተያየት የሰጡት ተሳታፊ ደግሞ፣ የምክር ቤቱ ሌላው አባል ብዙ የመንግሥት ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች ባለው አዋጅ፣ ደንብና መመርያ መፈጸም የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን፣ በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን የሚሞግት ተቋም መሆን ሲገባው ‹‹አለ ከማለት የለም ወደሚባልበት ደረጃ ደርሷል›› ሲሉ ተችተዋል፡፡ በማሳያነትም አንድ ነጋዴ በግል ያጋጠማቸውን ችግር እንዲፈታላቸው ለንግድ ምክር ቤቱ ያስገቡት ማመልከቻ መልስ አለማግኘቱን በመጥቀስ፣ ንግድ ምክር ቤቱ የአባላቱን ችግር እየፈታ አይደለም ሲሉ ተሟግተዋል።

ንግድ ምክር ቤቱ ከመንግሥት ጋር እየሠራ ያለው ሥራ አለ ለማለት አይችልም በማለት የገለጹት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ ለአብነትም በዕለቱ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተወካይ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር እየሠሩ ስለመሆናቸው ያነሱት ነገር ቢኖር፣ እየተዘጋጀ ያለውን የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የተመለከተ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህም ሌላ ግንኙነት እንደሌላቸው የሚያመለክት ነው በማለት ቦርዱን ተችተዋል፡፡ ስለዚህ ንግድ ምክር ቤቱ ነጋዴውን ሊወክልና ችግሮቹ ላይ አብሮ ሊቆም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ 

አሁን ያለው የንግድ ኅብረተሰቡ ችግር ከፍተኛ ስለመሆኑ አጽንኦት የሰጡት የንግድ ምክር ቤቱ አባል ችግሩን ለመፍታት ንግድ ምክር ቤቱ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎችንም በጥናት ላይ የተመሠረተ እንዲሆንና ነጋዴውን በቅርበት የሚመለከት መሆን እንዳለበት አሳስበው በዕለቱ የቀረበላቸውን ግን ከዚህ የተለየ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ተብሎ ከአባላቱ የተነሳው ሌላው ጥያቄ፣ የ2015 የግብር አጣጣል ፍትሐዊ ካለመሆን ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ንግድ ምክር ቤቱ ሊሞግትልን አልቻለም የሚል ነው፡፡ ብዙ ነጋዴዎች በዚህ ምክንያት እየተቸገሩ በመሆኑ ንግድ ምክር ቤቱ ድምፁን እንዲያሰማ ተጠይቋል፡፡

ችግርን ለመፍታት ደግሞ የንግድ ምክር ቤቱ ከገቢዎችም ሆነ ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መመካከር ነበረበት ይህ አልሆነም፡፡ እናንተ እኛን የወከላችሁ እንደመሆናችው እንዲህ ያለውን ችግር መፍታት ካልቻላችሁ በጣም አስቸጋሪ ነው በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ 

ጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎች በቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ቦርድ አባላትንና ዋና ጸሐፊው ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ በተለይ ከንግድ ምክር ቤቱ ሕንፃ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሊቀረበ ጥያቄ ከዚህ በኋላ በተሻለ ሁኔታ ፕሮጀክት ቀርፀው ለተግባራዊነቱ እንደሚሠሩ አመልክተዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸው፣ የ2015 በጀት ዓመት ንግድ ምክር ቤቱን ለተሻለ አገልግሎት ሲጠናከር ነበር ብለው፣ ተቋማዊ የአቅም ግንባታዎች ላይ ሲሠሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ከገቢዎችና ከጉምሩክ ጋር በተያያዘ በተነሱ ጉዳዮችና እየፈረሱ ያሉትን የንግድ ድርጅቶች ጉዳይ የሚመለከቱት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የንግድ ሥራን ሕልውናን ይፈታተናሉ፣ እንዲሁም ሊጠኑና ሊፈተሹ ይገባል የተባሉ ጉዳዮችን እንደ የቤት ሥራ ወስደው እንደሚመለከቷቸው ገልጸዋል።

እንዲህ ያሉ ጉዳዮች የንግድ ምክር ቤቱ ሥራዎች መሆናቸውን ያስታወሱት ዋናው ጸሐፊ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ 105 ጥናቶች ተካሂደዋል ብለዋል፡፡ በአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽናል ማዕከል ላይ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ያለው የአክሲዮን ድርሻ አንድ አራት ሺሕኛ ነው፡፡ ይህንን ኮንቬንሽን ማዕከል ለመገንባት ዋነኛ ጠንሳሽና መሥራች ቢሆንም የማዕከሉ ካፒታል አሁን ላይ አራት ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 

ሌላው ቦርድ አባል ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል፣ ንግድ ምክር ቤቱ ሊሠራባቸው ይገባል የተባሉ ጉዳዮች ላይ በመሥራት አፈጻጸማቸው በሚቀጥለው ዓመት በሪፖርት ተካተው የሚቀርቡ ይሆናል ብለዋል፡፡ በንግድ ምክር ቤቶቹ ማቋቋሚያ አዋጅ ዙሪያ ለተነሳ ጥያቄም ንግድ ምክር ቤቱ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት ያስፈልጋል ያላቸውን ምክረ ሐሳቦች ማቅረቡም ተገልጿል፡፡ በጽሑፍ ጭምር ያቀረበ መሆኑን የቦርድ አባሉ ሁለቱም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ የንግድ ኅብረተሰቡን የሚመጥን አዋጅ ያወጣሉ ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡ 

‹‹አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽንም ሆነ ሕንፃውን ለመገንባት አቅቶን አይደለም፡፡ ነገር ግን ብቻችንን ምንም ማድረግ አንችልም፤›› ያሉት የቦርድ አባሉ፣ ከዚህ በፊት አባላት የአቅማችሁን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ሐሳብ የቀረበ ቢሆንም፣ ተሳትፎው አነስተኛ ነበር በማለት ከዚህ በኋላ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ላይ አባላት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡ 

ከአባላት የቀረቡትን ጥያቄዎች ይዞ የሚሠራባቸው መሆኑን የገለጹት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት በበኩላቸው፣ በተለይ በሕንፃው ግንባታ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች