Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ መፍጠር የሚችሉ ዜጎች አሉ›› ብሩክ ከድር (ዶ/ር)፣ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

ሟቹ የቀድሞ የናሳ ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉ (ዶ/ር) የባህር ዳር ፖሊቴክኒክ ምሩቅ እንደሆኑ በአንድ አጋጣሚ ራሳቸው ሲናገሩ ተደምጠው ያውቃሉ፡፡ ከአንጋፋው ተግባረ ዕድና ከሌሎችም የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከላት እጅግ ታላላቅ ባለ ብሩህ አዕምሮ ምሁራን መውጣታቸውን፣ የአሁኑ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በቅርቡ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ባቀረቡት የዘርፉን ታሪክ በዳሰሰ ጥናታቸው አመልክተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የሆኑት ብሩክ (ዶ/ር) ከእንግሊዝ ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፣ ቻይና ቤጂንግ አቅንተው ሦስተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በሥራ ረገድ በዋናነት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከታችኛው የአስተዳደር እርከን እስከ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አማካሪነት ለ13 ዓመታት ሠርተዋል፡፡ አሁን ወደ የሚያገለግሉበት የፌዴራል ቴክኒክና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርነት ከተዛወሩ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ የዘርፉን ዕድገትና ያሉበትን ተግዳሮቶች የተመለከተ ጥልቅ ጥናት አቅርበዋል፡፡ እሳቸው እየመሩት ካለው ከቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ጋር በተገናኘ ዮናስ አማረ ከብሩክ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የዘርፉ የፖሊሲ ክንፍ ነው የሚል ሐሳብ ታነሳላችሁ፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ቀደም ሲል ለተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተጠሪ ነበር፡፡ በዋናነት ለትምህርት ሚኒስቴር፣ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ተጠሪ ነበር፡፡ አሁን ግን ተልዕኮውን የበለጠ ሊያሳካ በሚችል መንገድ ለኢፌዴሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ ነው፡፡ ተቋሙ በዋናነት አራት ተልዕኮዎች ናቸው የተሰጡት፡፡ የመጀመሪያው ተልዕኮው ኢትዮጵያ ውስጥ የቴክኒክና ሙያ መምህራንን፣ አሠልጣኞችንና ቴክኒሻኖችን ማፍራት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ በአገራችን ብቸኛው ነው፡፡ ሌላ እንደዚህ ዓይነት ቅርጽ ያለው ተቋም በኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ በሌሎች አፍሪካ አገሮች ውስጥም ቢሆን የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞችን ለማፍራት ተብሎ የተዋቀረ ተቋም የለም፡፡

ሁለተኛው ተልዕኮ ደግሞ የዘርፉ የፖሊሲ ክንፍ (መሣሪያ) ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቅርቡ የፀደቀ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ አላት፡፡ በፖሊሲው የተቀመጠው የሥልጠና መስክ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ በሚመለከት ተቋሙ ፖሊሲው ላይ የተቀመጡ ጉዳዮችን በተግባር የመዘርዘር ሥራ ይሠራል፡፡ የፖሊሲ ጥናት ያካሂዳል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ተልዕኮ ደግሞ የኢንዱስትሪ ትስስር መፍጠር ነው፡፡ ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመተባበር በአጫጭርና በረዥም ርቀት ሥልጠናዎች የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ የሰው ኃይል ከማዘጋጀት በተጨማሪ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችንም እንሠራለን፡፡ ከዚህ ቀደም ለትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ በነበረበት ጊዜ ከብዙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማለትም ከ50ዎቹ እንደ አንዱ ብቻ ይታይ ነበር፡፡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተጠሪ በነበረበትም ጊዜ ከዘርፉ ተቋማት አንዱ ነበር፡፡ አሁን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ መሥሪያ ቤት ሲሆን ግን የቅርብ ክትትል ያገኛል፡፡ የክህሎት ዘርፉ ማስፈጸሚያ ክንፍ ሆኗል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተልዕኮውን የሚያስፈጽምበት ዘርፍ በመሆኑ የቅርብ ድጋፍና ክትትል እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ የክህሎት ልማት ሥራን የምትመራበት ሚኒስቴር አደራጅታለች፡፡ አሁን የክህሎት ልማት የራሱ ባለቤት አለው፡፡ በዚያ ሚኒስቴር ሥር መዋቀራችን የቅርብ ክትትል ለማግኘት አስችሎናል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተልዕኮ የመለየት ሥራ ማከናወኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የሚሰጡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብሎ የእናንተን ኢንስቲትዩት መመደቡ ይታወሳል፡፡ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር እንድትደራጁ መደረጉ ከትምህርት ሚኒስቴር የተነጠለ ተቋም አያደርጋችሁም? አሁንም በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ናችሁ ወይስ ከዚያ ወጥታችኋል?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- የትምህርት ሚኒስቴር ሥራ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርቶች በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለውን የትምህርት ሥራ በሙሉ ይመለከታል፡፡ የትምህርት ሥራውን የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት የትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የክህሎት ልማት ሥራ የሚመራው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው አደረጃጀት ይህ ተቋም ተጠሪነቱ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ነው፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደ አካባቢው የኢኮኖሚ ኮሪዶር ፍላጎትና ተጨባጭ ሁኔታ የጥናት፣ የአፕላይድ ሳይንስ፣ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ባህሪ ያላቸውን ተብሎ በተልዕኮ የተደራጁበት ሁኔታ አለ፡፡ በእኛ ዕሳቤ ደግሞ ቴክኒክና ሙያ የራሱ የሆነ ባህሪያት ያሉት ነው፡፡ አንደኛ ብዙ ሚሊዮኖች ሕይወታቸው የሚቀየርበት ዘርፍ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ የሚሠለጥንበት በክህሎት ልማት ማለትም በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ነው፡፡ አሠለጣጠኑ ደግሞ በደረጃ (ሌቭል) የተቀመጠ ሲሆን፣ በአዲሱ ፖሊሲ መሠረትም ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ ስምንት የሥልጠና መርሐ ግብሮች ያሉት ነው፡፡

ከአንድ እስከ አምስት ያሉትን በየክልሉና በየከተማ መስተዳድሮቹ ያሉ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኮሌጆች ናቸው የሚያዘጋጁት፡፡ ሌቭል ስድስት፣ ሰባትና ስምንትን ግን የምናዘጋጀው እኛ ነን፡፡ ከሌቭል ስድስት ጀምሮ ያለውን አሠልጣኝ የምናፈራው እኛ  ነን፡፡ ሌቭል ስድስት የመጀመሪያ ዲግሪ ሲሆን፣ ሌቭል ሰባት ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ) ሥልጠና ነው፡፡ ሌቭል ስምንት ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) ነው ማለት ነው፡፡ ከሌቭል ስድስት ጀምሮ ያለው ሥልጠና የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞችን ለማፍራት ያለመ ነው ማለት ነው፡፡ ከደረጃ ስድስት በላይ ያሉ ሠልጣኞችን የምናዘጋጀው በዘርፉ አዳዲስ የሰው ኃይል የሚያፈሩ መምህራን እንዲሆኑ፣ ወይም ወደ ኢንዱስትሪው ተቀላቅለው ኢንዱስትሪዎችን የሚመሩ ቁልፍ ቴክኒሺያኖች እንዲሆኑ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ይህን ተልዕኮ የተሸከመው ተቋም ደግሞ ይህ የእኛ ኢንስቲትዩት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆኑ ለውጦችን በትምህርት ዘርፍ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ ምዘናን በተመለከተ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ መግቢያ ብሔራዊ ፈተና ጀምሮ እስከ መውጫ ፈተና ድረስ አዳዲስ ዕርምጃዎች መወሰዳቸው ትኩረት አግኝቷል፡፡ እናንተስ ይህን ዓይነቱን መንገድ የተከተላችሁበት ሁኔታ አለ?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- በቴክኒክና ሙያም ይህ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ በቴክኒክና ሙያም ብቃት ይመዘናል፣ ይህ ደግሞ በፖሊሲውም ተቀምጧል፡፡ በፖሊሲው መሠረት 70 በመቶ የተግባር 30 በመቶ ደግሞ የቀለም ትምህርት መስጠት ተብሎ ነው የተቀመጠው፡፡ እጁን በደንብ ያፍታታ፣ ከማሽነሪዎች ጋር በደንብ የሚተዋወቅ፣ ሙያ ለምዶ የሚወጣ፣ ፋብሪካዎች ውስጥ ገብቶ የሚያገለግል፣ በኢንዱስትሪውም ሆነ በኢኮኖሚው ውስጥ አቅም የሚፈጥር ሙያተኛ ነው እኛ የምናፈራው፡፡ በፖሊሲው በተቀመጠው መሠረት ያንን ሥልጠና አግኝቶ ወጥቷል ወይ የሚለውን እንመዝናለን፡፡ ብቁ ሥልጠና አግኝቷል ወይ የሚለው ይመዘናል፡፡ ሲኦሲ እንደሚታወቀው እስከ ሌቭል አምስት ድረስ ያሉ ሠልጣኞች የሚመዘኑበት ነው፡፡ በየአካባቢው ያሉ የምዘና ማዕከላት ይህን ሥራ ይሠራሉ ማለት ነው፡፡ እኛ ከሌቭል ስድስት በላይ ያሉ ሠልጣኞች ስለሆኑ ነው የምናሠለጥነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ዕሳቤ መሠረት አንድ ሠልጣኝ ከመመረቁ በፊት የመውጫ ፈተና እንዲወስድ ከ2015 ዓ.ም. ዓ.ም. ጀምሮ የተቀመጠውን አሠራር እንተገብራለን፡፡ የእኛም ተቋም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ይዘት ያለው በመሆኑ ይህንኑ የመውጫ ፈተና (ኤግዚት ኤግዛም) አሠራርን ተግባራዊ አድርገናል፡፡ በዚህም መሠረት ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ እኛም መተግበር ጀምረናል፡፡ ባለፈው ዓመት ባደረግነው ምዘና የትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች መጥተው የመውጫ ፈተናን ተግባራዊ ያደረጉበትንና ያለፉበትን ልምድ አጋርተውናል፡፡ እንዴት የዶክመንት፣ የሰው ኃይልና የፈተና አወጣጥ ዝግጅቶችን እንዳደረጉ ተሞክሮ ወስደናል፡፡ በልምምድ ፈተና አሰጣጥ ሒደት፣ እንዲሁም በውጤት አገላለጽ የነበራቸውን ልምድ አጋርተውናል፡፡ ይህን ልምድ ወስደን ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር ሆነን የመውጫ ፈተና አዘጋጅ ቡድን አደራጅተን፣ በዚህ ቡድን አማካይነት የአስፈላጊ ዶክመንቶች ዝግጅት ተደርጎ የልምምድ ፈተና በማካሄድ ነው ወደ ምዘናው የተገባው፡፡ በ2015 ዓ.ም. ተግባራዊ ባደረግነው የመውጫ ፈተና መሠረትም ወደ 70 በመቶ ተፈታኞቻችን አልፈዋል፡፡ ውጤቱ ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ማለፊያ ነጥብ ያላገኙ ተማሪዎቻችን ደግሞ በቅርቡ በየካቲት ወር ደግመው እንዲፈተኑ እናደርጋለን፡፡ ማካካሻ ትምህርት ወስደው በድጋሚ ይፈተናሉ፡፡ የመውጫ ፈተናው ገደብ የለውም፡፡ ራስህን ለፈተና ዝግጁ ባደረግ ቁጥር ደግመህ መውሰድ እንድትችል ተደርጎ ነው የተቀረፀው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ሌቭል ስምንት ወይም ፒኤችዲ ደረጃ ነው የሚባለው የሥልጠና መርሐ ግብር ገና አልተጀመረም፡፡ በዚህ ደረጃ የሠለጠነ የሰው ኃይልን ለማሟላት ወደ ውጭ አገር ለመላክ አገሪቱ እንደምትገደድ ይሰማልና ይህንን ችግር ለመፍታት ምን እየተሠራ ነው?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- ሌቭል ስምንት ሥልጠና ለማስጀመር ኃላፊነቱን ወስደን የዝግጅት ሥራዎች እያከናወንን ነው ያለው፡፡ የመጀመሪያው ለሥልጠናው አስፈላጊው የሰው ኃይል መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከመጀመሪያ ዲግሪ በላይ ሥልጠናው የሚፈልገውን ዓይነት ተቀራራቢ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ባለሙያዎች አሉን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአጋርነት ለመሥራት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን በመፍጠር ሒደት ላይ የምንገኝ ሲሆን፣ ወደ ተለያዩ አገሮች ሄደው ከፍተኛ ሥልጠና እንዲከታተሉ የምናደርጋቸው ባለሙያዎችም ይኖራሉ፡፡ በምን መስክ ነው ይህን ሥልጠና የምንከፍተው ለሚለውም ጥናት እየተደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የትምህርትና ሥልጠና ክፍሎችን ጥናትና ክለሳ ሥራ የሚሠራ አንድ ቡድን የተዋቀረ ሲሆን፣ በዚህም የደረጃ ስምንት ሥልጠና ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆኖ ተነስቷል፡፡ ይሁን እንጂ የደረጃ ስምንት ሥልጠና አከፋፈት የገበያ ፍላጎትን የተከተለ መሆን አለበት፡፡ ለምንድነው ሥልጠናው ያስፈለገው የሚለው በግልጽ መመለስ አለበት፡፡ ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አቅም በሚገነባ መንገድ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ በዚህ በኩል በቂ ዝግጅት መደረግ አለበት ተብሎ የዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- በሌሎች አገሮች የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከል በቴክኖሎጂ ፈጠራ የዳበሩ ባለሙያዎች የሚወጡበት ቦታ ነው፡፡ የካሊፎርኒያ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (California Institute of Technology/Caltech) እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያም እንደ ባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክና ተግባረ ዕድን የመሳሰሉ የላቁ ባለሙያዎች የተገኙባቸው ተቋማት አሉ፡፡ እናንተ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ምን እየሠራችሁ ነው?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ልማት ሥራን በሚመለከት ከዚህ ቀደም ራሱን የቻለ አደረጃጀት አልነበረውም፡፡ አሁን ግን ራሱን የቻለ የቴክኖሎጂና የኢንተርፕራይዝ ልማት ሥራን የተመለከተ አደረጃጀት ፈጥረናል፡፡ በምክትል ዋና ዳይሬክተር የሚመራ ራሱን የቻለ የሥራ ክፍል አበጅተናል፡፡ ሁለተኛው እየሠራነው ያለው በአገር አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ማብቃት ነው፡፡ ብሩህ ተስፋ የተባለ የኢንተርፕረነር ልማት ኢንስቲትዩት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ሆኖ የጀመረው የሽልማት ውድድር ነበር፡፡ በዚህ ውድድር ላይ የተካፈሉና ያሸነፉ ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ በአጠቃላይ 400 የሚሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችን ሰብስበን የማብቃት ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ካለፈው ሁለት ወራት ወዲህ እነዚህ ቴክኖሎጂስቶች ያሸነፉባቸውን ፈጠራዎች ይዘው መጥተው ፈጠራውን የሚያዳብሩበት የማብቃት ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ቴክኖሎጂስቶችን የማሰባሰቡ (ቡት ካምፕ) ሥራ በመጨረሻ የፈጠራ ባለሙያዎቹ ራሱን የቻለ ኢንተርፕራይዝ እንዲገነቡ የሚያስችል ነው፡፡ የክህሎት ጉድለታቸውን የሚሞላ ብቻ ሳይሆን በቢዝነስና በዲዛይን አጫጭር ሥልጠናዎች እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡ የእርስ በርስ ግንኙነት የማጠናከሪያ ዕድልም ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ቀጥሎ የየራሳቸውን የፈጠራ ኩባንያ የሚመሠርቱበት አጋዥ ሥልጠና ያገኛሉ፡፡ ከኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ትኩረት ዘርፎች ጋር አብረው የሚሄዱ 62 ያህል ፈጠራዎች አግኝተናል፡፡ ከአምስቱ የትኩረት ዘርፎች ማለትም ከኢነርጂ፣ ከማዕድን፣ ከቱሪዝም፣ ከግብርናና ከአይሲቲ ጋር የተያያዙ አግኝተናል፡፡ ከትንንሽ የግብርና ሥራዎች ጀምሮ ድሮን ማምረት የደረሱ አስደናቂ የፈጠራ ውጤቶች አግኝተናል፡፡ ድሮን የሚያመርቱ ልጆች እዚህ ግቢ ውስጥ አሉ፡፡ ፈጠራቸውን በአካል ማየት ይቻላል፡፡ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ድጋፍ እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ በሁሉም ዘርፎች የለሙና ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ፈጠራዎችን አግኝተናል፡፡

ይህ አሠራር በየዓመቱ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡ የፈጠራ ባለሙያዎችን እንዲህ መደገፉ አንደኛ ለፈጠራ ባለሙያዎቹ ምቹ የመሥሪያ ከባቢ የሚፈጥር ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ፈጠራ ለመተካት አጋዥ ነው፡፡ ቴክኖሎጂስቶቹ ብዙ ጊዜ ሥራዎቻቸው ከውጭ ከሚገባው ምርት ጋር በተነፃፃሪነት የተሻሉ እንደሆኑ አሳይተዋል፡፡ ለምሳሌ ወደ 16 ዓይነት እህሎች መውቃት የሚችል ማሽን ፈጠራ አለ፡፡ ይህን መሰል ማሽን ከውጭ ለማስመጣት ግን ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር ነው የሚጠይቀው፡፡ ከውጭ በሚሊዮኖች ብር ተገዝተው የሚመጡትን መተካት የሚችሉ በ100፣ በ150 ወይም በ300 ሺሕ ብር ወጪ እዚሁ አገር ቤት የተሠሩ የፈጠራ ውጤቶች ብዙ አሉ፡፡ ይህ የውጭ ምርቶችን አገር ቤት መተካት እንደሚቻል ያረጋግጣል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መፍጠር የሚችሉ ዜጎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ውጭ የተመረተውን አሻሽለው የሚሠሩ ዜጎች አሉ፡፡ እኛ ወደ መፍጠር ባንሸጋገር እንኳን የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን እስካላሻሻልን ድረስ ማደግ አንችልም፡፡ ሌሎቹ አገሮች ከሌሎች አካባቢዎች የሚያገኙትን ፈጠራ ፈጥነው በመቅዳትና ለራሳቸው በሚሆን መንገድ አሻሽለው በመሥራት ነው እያደጉ ያሉት፡፡ ስለዚህ ተቋማችን እስከዚህ ድረስ ያሉ ሚናዎችን መወጣት ይችላል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከላት የዜጎችን የፈጠራና የቢዝነስ ሐሳቦች ወደ ተግባር የሚቀይሩ ማዕከላት መሆን ይችላሉ፡፡ ይህንን ለመሥራት ደግሞ እስካሁን እየተባበሩ ያሉና ወደፊትም ለማገዝ ቃል የገቡ አጋር አካላት በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የፈጠራ ሥራን ወደ ተግባር ለመቀየር አንዱና መሠረታዊ ማነቆ የገንዘብ እጥረት ነው፡፡ ይህን ለመፍታት እንደ የልማት ባንክና የዓለም ባንክ ከመሳሰሉ አጋር አካላት ጋር በጋራ መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ደግሞ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት እዚህ እኛ ዘንድ በአካል ተገኝተው የፈጠራ ሥራዎችን አይተው እንዲሄዱ አድርገናል፡፡ በዚህ ወቅትም የተመረጡ የፈጠራ ሥራዎችን በገንዘብ መደገፍ የሚቻልበት አሠራር እንደሚያስፈልግ ቃል ገብተው ነው የሄዱት፡፡ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያና የቀጣናው ዋና ዳይሬክተርም በአካል ተገኝተው ሲጎበኙ በተመሳሳይ ይህንኑ ቃል ገብተው ነው  የሄዱት፡፡ በፋይናንስ እጥረት የተነሳ የፈጠራ ሥራዎች ዳር ሳይደርሱ እንዳይቀሩ ለመደገፍ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ ሌሎችም አጋር አካላት በተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ የተስማሚነት ምዘና ኤጀንሲ ለምሳሌ እዚሁ እኛው ተቋም ውስጥ የፈጠራ ሥራዎችን የሚፈትሽበት ማዕከል አለው፡፡ የሚፈጠሩ ቴክኖሎጂዎች የተስማሚነት ችግር እንዳይገጥማቸው እዚሁ እኛ ዘንድ ባለሙያ መድበው ጭምር እየሠሩ ነው ያሉት፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ አካላት በተለያዩ ቦታዎች የፈጠራ ሥራዎች ቢሠሩም ዘርፉ የቅንጅት ችግር ስላለበት፣ የቴክኖሎጂ ልማቱን ወደ ተግባር ለመቀየር እንቅፋት አለበት ይባላል፡፡ ለምሳሌ ከእናንተ ኢንስቲትዩት በቅርብ ርቀት የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠርና ተስማሚነት የማረጋገጥ ሥራ የሚሠራው የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማት ማዕከል ይገኛል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ቴክኖሎጂ ማበልፀግ ላይ የሚሠሩ በግለሰቦች፣ በመንግሥት ወይም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚመሩ ማዕከላት አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ገበያውን የሞሉት ከውጪ የሚመጡ ወይም እንደ ምናለሽ ተራ (መርካቶ) ዓይነት ቦታዎች በሥራ ፈጣሪዎች የሚመረቱ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ ዘርፉን አስተባብሮ ቅንጅት ባለው መንገድ መምራትን የሚጠይቅ አይመስልዎትም?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- በአገራችን በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ያለው ዕሳቤ ተስፋዎችም ችግሮችም አሉበት፡፡ ትልቁና መሠረታዊው ነገር የቴክኖሎጂ ልማት አቅጣጫችን በግልጽ ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው የተበታተኑ ቢሆንም እዚህም እዚያም የቴክኖሎጂ ልማት ሙከራዎች አሉ፡፡ ሦስተኛው ጉድለት ቢኖረውም በተቋማት መካከል የመተባበር ፍላጎትም አለ፡፡ ተቋማቱ የመቀራረብ ፍላጎት እስካሳየሃቸው ድረስ ለመተባበር ዝግጁ ናቸው፡፡ ነገር ግን በተበታተነ ሁኔታ በየቦታው የሚከናወኑ የቴክኖሎጂ ልማት ሥራዎችን ማቀናጀት ካልተቻለ ሙከራዎቹ የተበታተኑ ነው የሚሆኑት፡፡ በየአካባቢው ቴክኖሎጂ ለመፍጠር የምናደርጋቸው ሙከራዎች ድግግሞሽ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ አንዱ የሚሞክረውን ሌላው በሌላ ቦታ ይሞክረዋል፡፡ በዚህ የድግግሞሽ ፈጠራ ሙከራ የተነሳ የፈጠራ ባለሙያዎች ጥረት የባከነ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህን ማቀናጀት አስፈላጊ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የፈጠራ ባለሙያዎች ምቹ ሁኔታ ለማግኘት ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ የፋይናንስ ወይም የመሥሪያ ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሮክራሲያዊ ማነቆዎች ሊፈጠርባቸው ይችላል፡፡ እነዚህን ችግሮች በማረም ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ በኩል ችግር አለ፡፡ አዳዲስ ነገር የሚያመነጩ የፈጠራ ሰዎችን በተለየ ሁኔታ መረዳትና ለፈጠራ ሥራዎቻቸው ምቹ ምኅዳር መፍጠር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የተለመደው መዋቅርም ሆነ ሥርዓተ ማኅበር ለፈጠራ ሰዎች ፈታኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ካለመፍጠርና ከቅንጅት መጓደል ጋር የተገናኘ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ሆነ አገር በመቀየር ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ለዚህ ዘርፍ እናንተ ምን ዓይነት ትኩረት ሰጥታችኋል?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- በአሁኑ ወቅት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዓለም እየተቀየረ ነው፡፡ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍም ዲጂታል ቴክኖሎጂን እንደ ባህል መቀበል ያለበት አስገዳጅ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ቴክኒክና ሙያ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ያማከለ ካልሆነ ተለምዷዊ አሠለጣጠን ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ሠልጣኞች ከሚፈጥሩት ሥራ ጋር ወይም ከማሽን ጋር በቀጥታ እጃቸው የተነካካ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ አሠለጣጠኑ ዲጂታል ቴክኖሎጂንም ያቀፈ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ሲባል አስፈላጊው የዲጂታል መሠረተ ልማት ወይም የኤሌክትሮኒክ ለርኒንግ (ኢ-ለርኒንግ) የምንለው መሟላት አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ አቅም ይጠይቃል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ይህን ለመገንባት የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅም ሊኖረን ይገባል፡፡ ወይም የአጋሮችን ድጋፍ በሚገባ መጠቀም ይጠይቃል፡፡ ሁለተኛው ማነቆ ደግሞ የሚጠይቀው የሰው ኃይል ዝግጅት የተለየ መሆኑ ነው፡፡ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ለመገንባት ዲጂታል ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ የእኛ ተቋም እነዚህን ሁለት ነገሮች ለማሟላት እየሠራ ነው የሚገኘው፡፡

በአሁኑ ወቅት ያሉን የሥልጠና ወርክሾፖች ዲጂታል ቴክኖሎጂውን የቀየጡ (ብሌንድድ ለርኒንግ) እንዲሆኑ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሠራን ነው፡፡ ካለችን ውስን የመንግሥት በጀት ተጠቅመንም የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን በተቋማችንና በቅርንጫፎቻችን ለማሟላትም እየሠራን ነው፡፡ በተከታታይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥልጠናዎችንም እንሰጣለን፡፡ የዘርፉ ፖሊሲ የ21ኛውን ክፍለ ዘመን ዕውቀቶችን (ሶፍት ስኪልን) የተከተለ መሆን አለበት ስለሚል፣ ይህንኑ ለመተግበር የዲጂታል ዕውቀት ማስጨበጥ ላይ ተከታታይ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ በአገር ደረጃ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አለ፡፡ በስትራቴጂው አንዱ ማዕቀፍ ደግሞ ቴክኒክና ሙያን ወይም እኛን ይመለከታል፡፡ ትምህርትን፣ ቴክኒክና ሙያን፣ ጤናን፣ ግብርናን ጨምሮ የተለያዩ መስኮች በዚህ ስትራቴጂ ተካተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ምን ዓይነት እንቅፋቶች አሉበት? አገሪቱ በዘርፉ የተሻለ ውጤት እንድታገኝ ዘርፉ ምን ዓይነት ድጋፍ ያስፈልገዋል ይላሉ?

ብሩክ (ዶ/ር)፡- የቴክኒክና ሙያ እየገጠሙት ያሉት ችግሮች የተደራሽነት፣ የጥራትና የተገቢነት ችግሮች ናቸው፡፡ በዘርፉ ተዋንያን መካከል የቅንጅት አሠራር ጉድለትም ሌላው ችግር ነው፡፡ እነዚህን ለመፍታት ሁሉም ተዋንያን የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ጥራት ያለው አሠለጣጠን በመገንባት፣ ኅብረተሰቡ የሚተማመንባቸው፣ ብቁ የሆኑ፣ የተሟላ ሰብዕና ያላቸው ሠልጣኞችን ለማፍራት ብዙ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ወደ ሥራ ገበያው የሚቀላቀለው ሠልጣኝ ኢኮኖሚው የሚፈልገውን ሙያና ክህሎት ብቻ ሳይሆን፣ አገሩን የሚወድ ሰብዕና ይዞ እንዲወጣ መደረግ አለበት፡፡ መፍጠር የሚችል ብቻ ሳይሆን፣ የሥራ ታታሪነትና ሥነ ምግባር ያለው ሆኖ እንዲወጣ መሠራት  አለበት፡፡ አሁን እየገጠመን ያለው ዘርፉ በአገር ደረጃ የተደራሽነት ውስንነት ያለበት ብቻ ሳይሆን ጥራት ያለው አሠለጣጠን ጉድለትም ጭምር ነው፡፡ በአገር ደረጃ በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት የሚመሩ ከ2,000 ብዙም የማይዘሉ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ናቸው ያሉት፡፡ ይህ የተደራሽነት ችግር እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ቁጥራቸው ማደግ አለበት፡፡ ቁጥራቸውን ከማሳደግ ጎን ለጎን ደግሞ አካታችነትም ሊኖረው ይገባል፡፡ ሥልጠናው ሴቶችን ከወንዶች ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ ያቀፈ፣ አካል ጉዳተኞችንና ዕድል የተነፈጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ መሆን አለበት፡፡ ዘርፉ የሚሰጣቸው ሥልጠናዎች በሌላ በኩል ኢኮኖሚው የሚፈልገውን ዓይነት አሠለጣጠን ሊሆን ይገባል፡፡ የየአካባቢውን የመልማት ፀጋ ያማከለ መሆን አለበት፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚከፈት ተቋም ሌላ አካባቢ ካለው ጋር ተመሳሳይ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ የአካባቢውን ሀብት ወደ ሥራ መቀየር የሚችል አሠለጣጠን በየቦታው መኖር አለበት፡፡

የቴክኒክና ሙያ ከፍተኛ ገንዘብ ወይም ወጪ የሚጠይቅ (ካፒታል ኢንቴንሲቭ) ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለማቃለል ደግሞ ዘርፉን ማዕከል ያደረገ የራሱ የቴክኒክና ሙያ ፋይናንስ ምንጭ መኖር አለበት፡፡ ‹‹ቲቬት ፈንድ›› የምንለው ዘርፉ የሚደጎምበት አሠራር ሊበጅ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የቴክኒክና ሙያን በተመለከተ የቆየው የተዛባ የማኅበረሰብ አመለካከት መቀረፍ አለበት፡፡ ቴክኒክና ሙያ አማራጭ ያጡ ሰዎች የሚሰባሰቡበት ነው ብሎ የማሰብ ጉዳይ መቀየር አለበት፡፡ ዜጎች ሕይወታቸውን የሚቀይሩበት የተከበረ ዘርፍ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ብዙ አገሮች የተቀየሩት ለዚህ ዘርፍ ትኩረት በመስጠታቸው መሆኑን በመረዳት፣ ለዚህ ዘርፍ የምንሰጠውን ግምት ማሳደግ ይኖርብናል፡፡              

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለኢትዮጵያ የሚበጀው ኮስተር ብሎ የባህር በር ጥያቄውን መግፋት ብቻ ነው›› ብሩክ ኃይሉ (ፕሮፌሰር)፣ አንጋፋ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ባለሙያ

ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፈረንሣይና በአሜሪካ ተመድበው በዲፕሎማትነት አገልግለዋል፡፡ ዳያስፖራው በ‹‹ኖ ሞር›› ንቅናቄ ሲያደርግ በማስተባበር ተሳትፈዋል፡፡ መንግሥትና ዳያስፖራው ለአንድ...

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...