Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትሁሉም ነገር ሕግና ሥርዓት አለው

ሁሉም ነገር ሕግና ሥርዓት አለው

ቀን:

በገነት ዓለሙ

እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ በአገራችን የሕዝብ በዓላት ዝርዝር ውስጥ የካቲት 12/የሰማዕታት ቀን የሚባል የበዓል ቀን ነበር፡፡ የሠራተኛ ሕግ፣ የንግድ ሕግ፣ የንግድ ሰነዶች ሕግ ሁሉ ተፈጻሚ የሚሆንበት የበዓል ቀን ነበር፡፡ ደርግ ይህንን በአንድ ወቅት የሕዝብ በዓል የነበረ ቀን ተራ ቀን ሲያደርገው፣ ወይም ‹‹ታስቦ›› የሚውል ተራ ቀን ሲያደርገው ቢያንስ ቢያንስ ሕግ አውጥቶ ነው፡፡ አሁን ሥራ ላይ ባለው የሕዝብ በዓልና የሳምንት ዕረፍት ቀን አዋጅ አማካይነት ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ያልኩት ከሌሎች መካከል ለምሳሌ ‹‹ታስቦ ይውላል›› ያለውን የበዓል ‹‹አከባበር›› ዓይነት ራሱን ሳይደነባ ማለትም ‹‹ሬጉሌት›› ያላደረገ መሆኑ መጀመሪያ ውዥንብር፣ ከዚያም በኋላም ብዥታ በመፍጠሩ ነው፡፡ የዛሬ ምሳ ታስቦ ይውላል ማለት ዓይነት አባባል ቋንቋው ውስጥ የገባው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ለምን ይህንን የመሰለ ቀን ይህ ቀን የተሸከመውን ታሪክ፣ የሚያከብረውንና የሚዘክረውን ግፍና ሥቃይ የሕዝብ በዓል ከሚያከብራቸው ዝርዝሮች ውጪ አደረገው? ውሳኔውን በሕግ የገለጸው ዕርምጃ ሲታሰብ፣ ሲፀነስ፣ ሲወሰን፣ ሕጉ ሲወጣ ሳይሆን፣ ከዚያ በፊት ፍቀዱልኝ የሚባል፣ የሕዝብ ፈቃድን ይዤ ተልኬ ነው ማለት የነበረበት ጉዳይ ነበር፡፡ ለዛሬና ለነገ እንዲጠቅምና እንዲረዳ፣ ደርግ እንኳን እንዲህ ከሃምሳ ዓመት በኋላ ሲታማ ‹‹ለእኔ ብለህ ስማ›› ለማለት እንጂ የዛሬ ጉዳዬ የደርግ ሥራና ውሳኔ አይደለም፡፡

ጥያቄው አሁን ለጊዜው ለምን የሰማዕታት ቀን ከሕዝብ በዓላት ዝርዝር ውስጥ ተሰረዘ የሚለው ሳይሆን፣ የሕግ አወጣጡ የተከተለውን መንገድ ነው፡፡ ሕጉ የወጣው ዕርምጃ የተወሰደው ‹‹በዝግታና በጥልቅ ታስቦ፣ በለዘብታ ክርክር ተጠርቶ፣ በትዕግሥት እየተመላለሰ ተመክሮ የተቆረጠ ነገር እንዲሆን ተደርጎ›› ነው ወይ? ዋናው ጉዳይና አጀንዳዬ የዚህ ጽሑፍም ጭብጥ የሰማዕት ቀን አይደለም እንጂ፣ የ1967 ዓ.ም. የሕዝብ በዓላት ሕግ ዕለቱን የአዘቦት ቀን ቢያደርገውም የካቲት አሥራ ሁለት የሚባል፣ በእሱ ስም የቆመ፣ የተሰየመ አደባባይ ሐውልት፣ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል አሉ፡፡ የሚገርመው ግን (በዚህም አማካይነት ወደ ዋናው ጉዳዬ እየተጠጋሁ መምጣቴን ለማመላከት)፣ የስም አሰጣጣችን የመልክዓ ምድር አሰያየም ተግባራችን ሕግና ደንብ፣ እንዲሁም ‹‹አውጪ ባለሥልጣን›› ባለቤት አለኝ የሚል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም. አዲስ አበባና አገርን እንደተቆጣጠረ መጀመሪያ የወሰደው ‹ኦፊሺያል›› ዕርምጃ ከሌሎች መካከል በመዝገብ ስሙ፣ በይፋ ወይም በተሰጠ ስሙ ሳይሆን በሕዝብ ስሙ የደብረ ዘይት መንገድ የሚባለውን መንገድ፣ ግንቦት 20 መንገድ ብሎ የሰየመበት ዕርምጃ ነው፡፡ ግንቦት 20 መንገድ ቢሰየምለትም፣ ወዲያውኑና ያንኑ ጊዜ የስም ታፔላ (ኔምፕሌት) ቢቆምለትም አንድም ሰው በዚያ ስም ሳይጠራው፣ ሳያውቀው፣ እንኳን ሌላው ሰው የዜና ሰዎችም፣ ‹‹የዕለቱ የመድኃኒት ቤት ተረኛ›› የግዴታ የሚያስተዋውቁ ባለሥልጣናትም በዚህ ስም ሳይጠሩት፣ ‹‹አሁን›› ደግሞ (አሁን ማለት ከ2010 በፊት ነው!) በአንድ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገር ስም ተሰይሟል፡፡ መንገድ የተሰየመለት ግንቦት 20 ‹‹ዕውቅና›› ማጣቱ ሲገርም፣ ይበልጥ የሚደንቀው ደግሞ ይህንኑ ዕለት የሕዝብ በዓል ያደረገ፣ ብሎ የጠራ፣ ደጋግሞም ያከበረ የመንግሥት ተግባር ዛሬም ድረስ፣ ቢያንስ ቢያንስ እስከ 2010 ዓ.ም. ጊዜ በነበረው ጊዜ ይህ ቀን በሕዝብ በዓላትና በዕረፍት ቀን ሕግ ውስጥ ሳይጨመር መቅረቱ ነው፡፡ ‹‹ሥራዬ›› ብሎ ሕግ ማውጣት ቢቀር በ1988 ዓ.ም. የካቲት ውስጥ የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀን አዋጅ 16/67 የማሻሻያ አጋጣሚ በተገኘበት ጊዜ እግረ መንገዳዊ ሥራ እንኳን አልተደረገም፡፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሕግ ማውጣት ባለቤት አለው፡፡ ዋናው ሕግ አውጪ የተወካዮች ምክር ቤት ነው፣ የተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ያወጣል፡፡ በእነዚህ ሕጎች መሠረት ደግሞ ‹‹መመርያ›› የሚባል በተለይም ደግሞ ከአስተዳደር አዋጅ መውጣት ወዲህ ሙሉ በሙሉም ባይሆን፣ ትንሽ መላ ማግኘት የጀመረ (ቢያንስ ቢያንስ መኖሩ የሚመዘገብ) የሕግ ዓይነት አለ፡፡ ስያሜም፣ ስም ማውጣትም ሕግ አለው (የሕግ ማዕቀፍ አለው/ሊኖረው ይገባል) ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አቅሚቲ ሕግ የማውጣት ባህርይ አለው፣ ሕግ የማውጣት ሥራ ነው፡፡ እሱም ሕግ የማውጣት ሥራና ተግባር ነውና አውጪው ባለሥልጣን ማነው?  ብቻ ሳይሆን በምን ሥልጣኑስ አወጣው? የሚሉትን ጥያቀዎች የመመለስ ግዴታ ጭምር ያለበት ሥራ ነው፡፡ ዋናው ሕግ የማውጣት ሥልጣንና ተግባር እንደሚታወቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ከእሱ በታች ያሉ ሕግ አውጪዎች ደግሞ ሕግ የማውጣት ሥልጣናቸው ሲበዛ ተመጥኖ በውክልና የተሰጠ መሆኑ በየጊዜው የሚጮህ ማስጠንቀቂያ ሆኖ መታወቅና መኖር አለበት፡፡

‹‹ስም ማውጣት ያውቃሉ›› እየተባለ ቢዘፈንና ‹‹ቢዘመርልን››ም ስም ማውጣት ሕግና ሥርዓት እንዳለው አናውቅም፣ ወይም ለማወቅ ግድ የለንም፡፡ ለምሳሌ በመላው ዓለም ከታወቁ ስም ካላቸው የአውሮፕላን ማረፊያዎቻችን መካከል አዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት/አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አንዱ ነው፡፡ አያታ (IATA ወይም ኢንተርናሽናል ኤር ትራንስፖርት አሶሴሽን ADD፣ ኢንተርናሽናል ሲቪል አቪዬሽን ኦርጋናይዜሽን (ICAO) ደግሞ HAAB በሚል ኮድ ይጠሩታል፣ ያውቁታል፡፡ ዓለም ዙሪያ የሚታወቀውም በዚህ ስሙ ነው፡፡ እያንዳንዱ ይህ የአውሮፕላን ማረፊያ ያገለገለው/አገልግሎት የሰጠው ወይም እዚያ የሚያርፍ አውሮፕላን የጫነው ሻንጣ የሚለጥፈው ምልክት ‹‹ADD›› የሚለው አዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ነው፡፡ ዛሬ (ይህንን በምጽፍበት ሰዓት) በሰማያዊ መደብ ላይ በነጭ ፊደል ተጽፈው የተተከሉትን የአዲስ አበባ የመንገድ ምልክቶች የዚህን አውሮፕላን ማረፊያ ስም ንገረን ብንለው/ስንለው ቦሌ አየር መንገድ ይለናል፣ በጽሑፍ ሚሊዮኖች በተከሰከሱት የመንገድ ምልክት ጽሑፉ፡፡ በዚህ ባለቤት በሌለው፣ ከዚህም የተነሳ የሚገራው በጠፋ (ሬጉሌትድ ባልተደረገ) ወድቆ የተገኘ፣ የማንም ሥራ በሆነ የአላዋቂ ሳሚ ያበላሸው ጥፋት ምክንያት ቋንቋው ራሱ ተበላሽቶ ኤርፖርት ማለት አየር መንገድ ሆኗል፡፡ በቋንቋው ላይ የደረሰው ስብራት መጠነ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ወደ አማርኛ የተመለሱ የውጭ አገር ፊልሞች ውስጥ ‹‹…ሪዮዲጄኔሮ አየር መንገድ›› ጠብቂኝ ዓይነት ትርጉም ሰምተናል፡፡ አንድ የከተማ አስተዳደር የከተማ መንገዶችን ስያሜና ምልክት ሲያቆም/ሲተክል የሠራው ስህተትና ጥፋት አራሚ አጥቶ፣ ሳይጠየቁ መቅረት የሚባል ነገር ሠፍኖና ገንግኖ ቋንቋውና የሕዝብ ግንዛቤ ውስጥ የፈጠረውና አየር መንገድን አውሮፕላን ማረፊያ ያደረገው ብልሽት ተራዎቹ ውይይቶች፣ የግል ጭውውቶች፣ የኤፍኤም ‹‹መዝናኛ›› መድረኮች ብቻ ሳይሆን፣ ትልልቅ ዜናዎችና ቁምነገሮች ውስጥም በሽታው ተጋብቶ ስናይ ያሳስበናል፡፡ የታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋናን ዜና እዩልኝ ስሙልኝ፡፡  

አዲስ አበባ ታኅሳስ 2፣ 2016 (ኤፍቢሲ) የኢትዮጵያ የአየር መንገድ አዲሱን ‹የአየር መንገድ ከተማ› ግንባታ በአራት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡

አየር መንገዱ ‹‹ኤርፖርት ሲቲ›› ብሎ የሚጠራውን ግንባታ ለመጀመር ከጫፍ የደረሰው፣ እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ለማርካት መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለማ ያደቻ ተናግረዋል፡፡

የ‹አየር መንገድ ከተማው› ካልተገነባ አየር መንገዱ በዘርፉ እያስመዘገበ ካለው ፈጣን ዕድገት አንፃር እንደሚፈተን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፕሮጀክቱ መታቀዱን አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 5 ቢሊዮን ብር ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፣ በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አሁን ላይ አየር መንገዱ በኦሮሚያ ክልል ከቢሾፍቱ ከተማ ጥቂት ወጣ ብሎ በሚገኝ ሥፍራ የመጀመሪያውን የአየር መንገድ ከተማ ግንባታ ለማስመር በዝግጅት ላይ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ ከቀረጥ ነፃ የግብይት ሥፍራና የካርጎ ሎጂስቲክስ ማዕከል እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡ የአዋጭነት ጥናቱን በማጠናቀቅም ለዓለም አቀፍ ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ይህንን ‹‹ማንም እየተነሳ›› የሚያበላሸውንና ‹‹ያላዋቂ ሳሚ›› የሚጫወትበተን ሥራ፣ እንዲህ ባለበት ቢቆይ፣ እንዳለ ቢተው የሚያጎድለውን፣ የሚያስከትለውን ጉዳት ለማሳየት ጭምር በአገርም በዓለም አቀፋዊ ደረጃም ባለቤትና ባለአደራ እንዳለው ማመላከት ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ጋር፣ በዚህ አጋጣሚ አገራችን ውስጥ ‹‹ስለፊደል አጻጻፍ፣ ስለቃላት አገባብ፣ ስለሰዋሰው ሥርዓትና ስለሐሳብ አገላለጽ የቋንቋ ደንብን በመከተል ውሳኔ የመስጠት›› ሥልጣንና ተግባር የተሰጠው በሕግ የተቋቋመ የመንግሥት ተቋም እንደነበር አስታውሳለሁ፣ ወይም ላስታውስ፡፡ በ1964 ዓ.ም. በሕግ የተቋቋመው ይህ የመንግሥት የሥልጣን አካል ብሔራዊ የአማርኛ መርሐ ልሳን (አካዴሚ) ይባል ነበር፡፡ በወታደራዊ መንግሥት ዘመን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ ተብሎ ተሰየመ፡፡ እኔ በግል እንደ ሸማች በማውቀው ልክ ‹‹የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት›› (እንግሊዝኛ – አማርኛ)  የመሳሰሉትን ድንቅ ሥራዎች ያሳተመው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ በ1990ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተወሰደው፣ ወይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሆነው በሚያሳዝን ሁኔታ (አሳዛኙ ነገር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ አይደለም) የሕግ አወጣጥ ሥርዓቱ ራዳር ሳያውቀው/እንዲያውቀው ሳይደረግ ዝም ብሎ ‹‹ሹክክ›› ብሎ፣ ዱካውን አጥፍቶ ነው፡፡ የየትኛውንም በሕግ የተቋቋመ የመንግሥት ተቋም አስፈላጊነት ለማስቀረትም ሆነ፣ ተጠሪነቱን ወይም ቦታውንም ለመለወጥና ስያሜውን ለመቀየር የተለመደውና ተገቢም አሠራር ሕግ በማውጣት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽንን ያፈረሰው በአዋጅ ቁጥር 151/91 ነው፡፡ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ተሃድሶና ልማት ፈንድ የሚባል ተቋም ነበር፡፡ የዚህ ተቋም መብትና ግዴታዎች የተላለፉት፣ የተላለፉትም ወዴት እንደሆነ የተገለጸው በሕግ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 521/99 ነው፡፡ አሁን በቅርቡ በ2009 ዓ.ም. የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የሚባል ቀርቶ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የተባለ የተቋቋመው ሁሉምና እያንዳንዱም በሕግ ነው፡፡ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን ያቋቋመው ደንብ ቁጥር 398/2009 ነው፡፡ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ይባል የነበረውን ተቋም ያፈረሰውና የዚህንም ኤጀንሲ መብትና ግዴታዎች ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ያስተላለፈው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ማፍረሻ አዋጅ ቁጥር 1022/2009 ነው፡፡

ለምሳሌ የገለጽኩት ዓይነት የማፍረሻም ‹‹የዝውውር››ም ክብርና ማዕረግ ሳያገኝ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲያው እንደ ዘበት፣ እንደ ዋዛ ‹‹ሹክክ ብሎ›› የገባው (Unceremoniously የተሸኘው፣ የተሰናበተው) ይህ ተቋም ከሌሎች መካከል ቅድም እንደጠቀስኩት በፊደል አጻጻፍ፣ በቃላት አገባብ፣ በሰዋሰው ሥርዓትና በሐሳብ አገላለጽ ላይ የቋንቋ ደንብን በመከተል ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ነበረው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግም ይህንን ሥልጣንና ተግባር የመንግሥት መሥሪያ ቤት አድርጎ ላቋቋመው ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ የሰጠው ሕግ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች ግዴታ አድርጎ የሚያዘው ሌላም የሚገርም ድንጋጌ ነበር፣ እንዲህ ይላል፡፡

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የግል ድርቶች ግዴታ፣

  1. የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የድርጅቶች፣ የትምህርት፣ የምርምርና የሐሳብ ማሠራጫ ድርጅቶች ጭምር በፊደል አጻጻፍ፣ በቃላት አገባብ ፣ በሰዋሰው ሥርዓት፣ በኪነ ጥበብ ቃላት ስያሜና አማርኛ ከሌላ ቋንቋ ቃላት ስለሚቀበልበት ሁኔታ መርሐ ልሳን የሚሰጠውን ውሳኔ አክብረው ይሠሩበታል፡፡
  2. የግል የትምህርት፣ የጥናት፣ የምርምርና የሐሳብ ማሠራጫ ድርጅቶች በሕጉ መሠረት ሲጠየቁ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተውን ውሳኔ አክብረው ይሠሩበታል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች እንዲሠሩባቸው የሚፈለጉ ውሳኔዎች ሁሉ በመርሐ ልሳን መጽሔት ይወጣሉ፡፡

አንድ ነገር ማጥራትና ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ጭብጤ፣ ችግሬ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች  አካዴሚ ‹‹ተጠሪነት› ለምን መጀመሪያ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ኋላም ከባህል ሚኒስቴር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሄደ የሚል በጭራሽ አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (ከአንቀጽ 13 ጋር ተቀናጅቶ) መሠረት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ማለትም፣ እንዲሁም በተለይ ደግሞ የቅድሚያ ምርመራ በማናቸውም መልኩ የተከለከለ ነው ማለት የምገልጸውን ሐሳብ ይዘት ብቻ ሳይሆን፣ ሐሳቤን የምገልጽበትን ፎርም/መልክ መንገድ ይጨምራልና ይህ ነፃነት የቋንቋዎች  አካዴሚ ከሚሰጠው/እሰጠዋለሁ ከሚለው ውሳኔ ጋር ሊጣላ፣ ሊወዛገብ ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት የቋንቋዎች አካዴሚ ሕግ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች ላይ የጣለው ግዴታ ሐሳብን ከመግለጽ ነፃነት ጋር ይጋጫልና ግልግል ነው የሚል መከራከሪያና መቃወመሚያ ተገላገልን አይባል ነገር፣ ‹‹ግልግሉን› ዕፎይታውን ያመጣው ነገር ሕግን የተከተለ ባለመሆኑ እሰይታችን እውነት አይደለም፡፡ ጥፋትን በጥፋት ማረም ነው (የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች የሐሳብ ማሠራጫ ድርጅቶች ጭምር የፊደል አጻጻፍ፣ የቃላት አገባብ፣ የሰዋሰው ሥርዓት የቃላት ስያሜን በተመለከተ አካዴሚው የሚሰጠውን ውሳኔ የማክበር ግዴታ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ ነፃነትን ይጋፋል፣ ይቃረናል፣ ይረጋግጣል ማለት፣ ሙሉ በሙሉ እውነትና ትክክል ቢሆን እንኳን ይህንን የተገላገልነው በትክክለኛው መንገድ ሳይሆን ስህተትና ጥፋት ሠርተን፣ ሕግ ረግጠን ነውና እዚህ ውስጥ እሰይታና ዕፎይታ የለም)፣ እንዲያም ቢሆን አየር መንገድንና አውሮፕላን ማረፊያን አንድ ናቸው፣ ምን ለያቸው፣ አንድ ስያሜ ይበቃቸዋል ማለት ዱባና ቅልን ማምታታት ብቻ ሳይሆን፣ የሁለቱም መጠሪያ አንድ ነው ማለትን ያህል ጅልነትና ድንቁርና ነው፡፡

በዚህ ላይ መነጋገር፣ በአጠቃላይ መነጋገርን ማወቅ፣ ስያሜም (የቃላት፣ የቦታም፣ የበዓልም) ሕግና ደንብ ባለቤትም እንዳለው እንደሚያስፈልገው መግባባትና መረዳት የትልቁ፣ ሥርዓት የመገንባት አሠራር የማቋቋም ሥራችንና ግዴታችን አካል ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ በያዝነው ዓመት ውስጥ የተለያዩ በዓላትን፣ ወይም ቀናትን አክብረናል፡፡ ታኅሳስ 15 ቀን 116ኛው የመከላከያ ቀን ሆኖ ተከብሯል፡፡ ኅዳር 29 ለ18ኛ ዓመት እንደተለመደው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ተብሎ ተከብሯል፡፡ ታኅሳስ መጀመሪያ ላይ ደግሞ የአየር ኃይል ቀን ማጠቃለያን አክብረናል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁና በዚሁ በተመሳሳይ ምክንያት የተከበሩ፣ የሚከበሩና መከበር ያለባቸው ቀናት ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ቀናት የምናከብርበትና የምናነግሥበት ምክንያቶች የታወቁ ናቸው፡፡ ለመሥሪያ ቤቱ፣ መሥሪያ ቤቱ/ተቋሙ ለሚያከናውነው ተግባርና አደራ፣ እንዲሁም ለባለሙያዎቹ ለአስተዋጽኦዋቸው ክብር መስጠት ምሥጋና ማቅረብ፣ ባለውለታነታችንን መግለጽ፣ መስዋዕትነታቸውን ማሰብ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ማኅበራዊ አስፈላጊነታቸው የግዴታ የሆነ ምክንያቶችና ፋይዳዎች አሉ፡፡ አከራካሪውና አነጋጋሪው ይህ አይደለም፡፡ ወይም አንዳንድ ጊዜ የሚገርም ነገር ስለሚያጋጥም አይደለም፡፡ ሐሳቤን በደንብ ስላልገለጽኩት አንድ ምሳሌ ላቅረብ፡፡ ለምሳሌ ኦገስት 19 በየዓመቱ የሚከበር የተመድ የዓለም የሰብዓዊነት ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን በየዓመቱ እንዲከበር መነሻ የሆነው ከሃያ ዓመት በፊት በዚሁ ቀን አሜሪካ ኢራቅን ወርራ በያዘችበት (ከ2003 – 2011) ወቅት፣ ባግዳድ ውስጥ አንድ ሆቴል ላይ በደረሰ ጥቃት የተመድ ዋና ጸሐፊውን ተወካይ ጨምሮ በ22 የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ላይ የሞት አደጋ በመድረሱ፣ አደጋው ከደረሰ ከአምስት ዓመት በኋላም የተመድ ጠቅላለ ጉባዔ ይህ ቀን በዚህ ስም እንዲጠራና እንዲከበር ውሳኔ በማስተላለፉ ነው፡፡ ቀኑ የሚከበረው አደጋና ቀውስ ውስጥ የገቡትን፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ የግድ የሚያስፈልጋቸውን፣ ለዚህ ችግር የተጋጡትን፣ እንዲሁም ለእነሱ ዕርዳታ ለማድረግ የተሰማሩትን፣ ወዘተ ነው፡፡ ሃያ ሁለት ሰዎች በአደጋ ሞቱብኝ ብሎ ደንግጦ፣ ይህንን ቀን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውንና ለችግር የተጋጡትን ሕዝቦች፣ እንዲሁም ዕርዳታ አድራሽ ሠራተኞችን ማሰብ በአጠቃላይ፣ እንዲህ ያለ ሥራና ግዳጅ እንዳለ ማስታወስ፣ እያስታወሱም በጎ ሥራውንም የግዴታ ተግባራቸውንም እያሰቡ የዚህን የሥር የመሠረት ምክንያት ነቅሎ መጣልን የሚያከብረው ይህ የተቀደሰ የተመድ ተግባር፣ ዘንድሮ ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአንድ መቶ በላይ ሠራተኞች ቢያልቁበትም፣ ድንጋጤው ባህርይው ሲሆን አላየንም፡፡ ጉልበተኛ ከሚፈቅደው በላይ መራመድ የማይችል ‹‹ከንቱ›› እና መሳቂያም ሲሆንም ዓይተናል፡፡

እኛም በዓል ስናከብር፣ ቀን ሰይመን ስናነግሥ፣ እውነታችንን ነው? ዕውን የምናከብረውን ቀን ትርጉምና ፋይዳ ይገባናል? ከማለት ጋር ይህንን ውሳኔያችንን የሚመራው ሕግና ሥርዓት መኖሩን ማረጋገጥ አለብን፡፡ መጀመሪያ ነገር በሕዝብ በዓላትና በእነዚህ ‹‹ቀናት›› መካከል ያለውን ልዩነት በትክክልና በእርግጠኛነት የሚደነባ፣ ትርጉምና ጥያቄ ቢነሳ፣ ብዥታና ውዥንብር ቢፈጠር ወደ ‹‹ጠንቋይ ቀላቢ›› ሂዱ የማይል አሠራር ሊኖረን ይገባል፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ባለቤትም ሊኖረው ይገባል፡፡ በየቦታው፣ በየዘርፉ እየተነሱ የ… ቀን ማለት ቢያንስ ቢያንስ ሌላው ቢቀር የበጀት፣ የወጪ አንድምታ አለውና (ለምሳሌ ከአንድ የውጭ አርዕስት ወደ ሌላ ማዛወር የማይቻለውን ያህል) ቀን ማክበርን የመውሰን ጉዳይ ወሳኙ/አውጪው ባለሥልጣን የሚባል ባለቤት በሕግ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ባለቤት እንዲኖረው ማድረግ በቅርቡ የተለያዩ ቀናት ሲከበሩና ከዚህ በፊት ለተለያየ ጊዜ ይከበሩ እንደነበር ማብራሪያ ሲሰጥ የተገለጸው ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር፣ መጠበቂያና ሌላው ቢቀር የተመዘገበ ማስረጃ ያስቀምጣል፡፡ ባለቤት መሰየምና በሕግ የሚመራ ውሳኔ ማድረግ፣ በሕግም እንዲመራ መወሰን ተጠያቂነትን ያስከትላል፣ ሳይጠየቁ መቅረትን ይከላከላል፣ ሌለው ቢቀር ኅዳር 29 አሰያየም ላይ የደረሰውን ውዥቀት የመሰለ ችግር ያስቀራል፡፡

ኅዳር 29 ሕገ መንግሥቱ የፀደቀበት ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ከዋለበት ከነሐሴ 15 የተለየ ቀን ነው፡፡ ኅዳር 29 ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ አንድ ብለን የሕገ መንግሥት ቀን ብለን ስናከብር ከቆየን በኋላ፣ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መጥቶ ጦርነቱም ፍፃሜ አግኝቶ ብዙ ከቆየ በኋላ፣ አሥራ አንድ ዓመት ያህል ቆይተን ኅዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ብለን ለዚያውም እንደገና አንድ ብለን መቁጠር ጀመርን፡፡ ለምን? እንዲህ ያለ የቢሻን ውሳኔን ‹‹እንዳሻህ ተራመድ››ን፣ ያፈቀደውን መሥራትን የሚከለክል ነገር ስለሌለ፡፡

እንዲህ ያለ ውዝግብ የሚፈጥር፣ መረን የሚለቅ፣ ሳይጠየቁ መቅረት የሚመርቅና የሚያበረታታ ነገር የቦታ ስያሜዎች ላይም ነግሷል፡፡ ቤታችን፣ ውስጣችን ከነገሠው ዝብርቅርቅነት አንዳንዴም ውዝግብና ፍልሚያ አልኖ በቅርቡ አዲስ አበባ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ጭምር ጠልፎ ሲጥል ያሳየ ችግር አለው፡፡ እዚህም ላይ ጭብጤ የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አዲስ አበባ ነው? ወይስ ፊንፊኔ? የሚለው አይደለም፡፡ አስፈላጊ ከሆነ በአገር ሰፊውና ትልቁ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ይባል ወይስ ፊንፊኔ የሕዝብ ፈቃድ አግኝቶ ሊፀና ሊለወጥ ይችላል፡፡ ይህ የሕግ ማዕቀፍ ዓለም አቀፋዊ አንድምታ ያለው ነው፡፡ አስፈላጊ ያደረገውም ከውስጥ ጥያቄ ይልቅ የውጭ ግንኙነት ነው፡፡ የጋዛ ምድር በጦርነት ምክያት እንዲህ እንደ እንቅብ በምትንቀረቀብበት ወቅት፣ በአንድ መልክዓ ምድራዊ ቦታ ስም ላይ ዓለም በአንድ አፍ ካልተስማማና ካልተነጋገረ ለምሳሌ ኻንዩንስን ፍልስጤሞች በአንድ ስም፣ እስራኤሎች በሌላ ስም ፈረንሣይኛና እንግሊዝኛ በተለያዩ ሆሄ ነው የምጽፈው ቢሉ ያን ቦታ መድረስ አይቻልም፡፡ የመልክዓ ምድራዊ ቦታዎች ስያሜ ሕግጋትን መሠረት ያስያዘው ዓለም አቀፋዊ ማዕቀፍ የሆነበት ምክንያት አንዱ ይህ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አምስት ዋና ዋና የሥልጣን አካላት መካከል አንዱ (ከጠቅላላ ጉባዔው፣ ከፀጥታ ምክር ቤቱ እኩልና አቻ አቋም ያለው) የኢኮኖሚና የሶሻል ካውንስል በሚባለው አካል ውስጥ ‹‹UNGTGN›› (United Nations Group of Experts on Geographicl Names) የሚባል መሥሪያ ቤት አለ፡፡ ተመድ በዚህ መሥሪያ ቤት አማካይነት መልክዓ ምድራዊ ስያሜዎች ባለቤት፣ ደረጃ (ስታንዳርዳይዝድ እንዲደረጉ) እንዲኖራቸው ይጠይቃል፡፡ እያንዳንዱ አገርም ብሔራዊ የስያሜ ባለሥልጣን እንዲኖረው ይሻል፣ ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለ ‹‹ብሔራዊ ወይም አገራዊ የመልክዓ ምድር ስሞች ባለሥልጣን›› የሚባል በዚህ ስም የሚጠራ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የላትም፡፡ የ‹‹UNGEGN›› መረጃም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው፡፡ ሆኖም ግን የመንግሥታቱ ድርጅት የዚህ ጉዳይ ባለቤት የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ይህንን አደራ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሲሠራ የኖረው የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ኤጀንሲ ነው፡፡ በተለያየ አደረጃጀትን በሚወስኑ የማሻሻያ/መልሶ የማደራጃ ሕጎች አማካይነት ቀድሞ የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ኤጀንሲ ይባል የነበረውን ሥራ ጭምር ተረክቦ በተቋቋመበት ሕግ ተጨማሪ ሥራዎችን የሚሠራው፣ የ‹‹ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት›› የሚባለው፣ ተጠሪነቱም ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሆነው ተቋም ነው፡፡

ሕግ ማክበርና ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የወጣውን ሕግ የማክበር/የማስከበር ሥራ የማንም ግዴታ እንዲሆን ትንሽና ትልቅ ሳይባል፣ የዘወትር ወይም የአዘቦትና የልዩ ጊዜ ችግር ተብሎ ሳይለይ፣ ሁሉም ነገር በሕግ ሊገዛ ይገባዋል፡፡ ሥርዓት የመገንባት ትልቁ አደራ ይህንን ሁሉ ከቁጥር ማስገባት ይሻል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...