Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉማን ያቦካውን ማን ይጋግረዋል?

ማን ያቦካውን ማን ይጋግረዋል?

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

መንደርደሪያ ሐሳብ

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ‹‹ይድረስ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ›› በሚል ርዕስ በአመሐ ኃይለ ማርያም ታኅሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ በቀረበ ጽሑፍ፣ ‹‹ለውጭ ምንዛሪ እጥረት የብርን የመግዛት አቅም መቀነስ መፍትሔ ይሆናል እንዴ?›› በማለት ባስነበቡን በጣም ጠቃሚ የሆነ ጽሑፍ ላይ ተጨማሪ ግብዓት ለመስጠት ነው። አቶ አመሐ ሌላም እጅግ በጣም ትልቅ ቁምነገር ያለው ሐሳብም አስገንዝበውናል፡፡ ይኸውም ‹‹መለኪያ በሌለበት ኢኮኖሚ ሁሉም ነገር ልክ ነው›› (In an economy where there is no measure, everything is right.) የሚል ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ አመሐ በውጭ ምንዛሪ ምጣኔ የብር ዋጋ መውደቅ (Devaluation) አንድምታ አንዳንድ ጽንሰ ሐሳቦችና የኢኮኖሚውን አንዳንድ መረጃዎችን ነግረውናል፡፡ ለምሳሌ የብርን ዋጋ በማውደቅ ከኤክስፖርት ዋጋ ጭማሪ ተጠቃሚነትና ከኢምፖርት ዋጋ ጭማሪ ተጎጂነት ጥምርታ (Ratio Elasticity) ጽንሰ ሐሳብ ከአንድ በላይ ወይም በታች መሆን አለመሆንን መመዘኛ ልኬት አስረድተውናል፡፡ 

የዋጋ ንረትና የምንዛሪ ምጣኔ አንዱ የሌላው ምክንያትና ውጤት እንደሆኑ እንደሚደጋገፉም የምንዛሪ ምጣኔ መረጃዎችንና የዋጋ ንረት መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ተንትነዋል፡፡ ጥሬ መረጃን በማቀበልም ዓለም አቀፍ አወራራጅ ባንኮችን (Bank of International Settlement – BIS) እንዴት ጉዳዩን ተከታትለው እንዳላስፈጸሙ ግራ አጋቢ ቢሆንም፣ በሦስት ቀናት ውስጥ መወራረድ የሚገባውን በንግድ ባንኮች የተከፈተ ኤልሲ ሳያወራርዱ ለዓመታት በመቆየት ገና ብዙ ዕዳ እንዳለብንም ነግረውናል፡፡

የምንዛሪ ምጣኔውን በተመለከተ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ አዘውናል፣ እንታዘዛለን፣ አንታዘዝም ከማለት በቀር መሆን ያለበት ትክክለኛው የምንዛሪ ምጣኔ ይህ ነው ብሎ የነገረን አካል የለም፡፡ ለመታዘዝም ላለመታዘዝም አሳማኝ ምክንያት መኖር አለበት፡፡ አቶ አመሐ እንዳሉት መረጃ በሌለበት ኢኮኖሚ ሁሉም ነገር ልክ ነው፡፡ እኛ በምንኖርባትና በምናውቃት አገር ጽንሰ ሐሳብን በልኬት ለማረጋገጥ የሚያስችል መረጃ እንደሌለ እያወቅን ዓለም አቀፍ ተቋማት መረጃ አግኝተው በጽንሰ ሐሳብ ላይ ተመርኩዘው ተንትነው ነው ሊባል አይቻልም፡፡ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ተነስተው የሚሰጡት አስተያየት ለኢትዮጵያ ይሠራል ብለን በጭፍን ልናምንና ልንቀበልም አንችልም፡፡ ሆኖም እኛ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የተተነተነ ሳይንሳዊ መረጃ ስለሌለን ያዘዙንም ያላዘዙንም ትክክል ነው፡፡

አንድ ኢኮኖሚ ሁለት ዓይነት መረጃዎች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ አንዱ በኑሮ ታይቶ የሚታወቀው በገበያው ውስጥ ያለው መጠን (Actual Fact) ሲሆን፣ ሁለተኛው በሳይንሳዊ መንገድ ሊለካና ሊተነተን የሚችለው ጽንሰ ሐሳባዊ እውነታ (Theoretical Fact) ነው፡፡ ለምሳሌ በኑሮ ታይቶ የሚታወቀው በቋሚ የምንዛሪ ምጣኔ ሥርዓት (Fixed Exchange Rate System) የተወሰነው የኦፊሴላዊ ምንዛሪ ምጣኔ አንድ ዶላር ለሃምሳ ስድስት ብር ሲሆን፣ በተንሳፋፊ የምንዛሪ ምጣኔ ሥርዓት (Floting Exchange Rate System) የተወሰነው በትይዩ (በጥቁር) ገበያ ደግሞ አንድ ዶላር ለአንድ መቶ አሥር ብር ነው፡፡ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ግን በሒሳብ ለክተን ያወቅነው መረጃ የለንም፡፡

ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ለመግለጽ በሚያስችል ደረጃ አማርኛችን በሳይንሳዊ ቃላት ስላልዳበረ እንግሊዝኛውን በቀጥታ መተርጎም ያምታታል፡፡ ምንም ካለማለት ይሻላልና በቋሚ የምንዛሪ ምጣኔ ሥርዓት በፖሊሲ የተወሰነው ማውደቅ (Devaluation) ሲባል በተንሳፋፊ የምንዛሪ ምጣኔ በገበያው ምክንያት ራሱ ሲቀንስ መርከስ (Depreciation) ልንል እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ በምትከተለው የቋሚና የተንሳፋፊ መሀል ቤት አስተዳደራዊ ተንሳፋፊ የምንዛሪ ምጣኔ ሥርዓት (Managed Floting Exchange Rate System) የብር ዋጋ ምንዛሪ ሊወድቅም ሊረክስም ይችላል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን የተወሰነው አንድ ዶላር ለሃያ ሰባት ብር የምንዛሪ ምጣኔ የፖሊሲ ውሳኔ መውደቅ ነው፡፡ ዛሬ በኦፊሴላዊ የምንዛሪ ምጣኔ አንድ ዶላር ለሃምሳ ስድስት ብርና በትይዩ የምንዛሪ ምጣኔ አንድ ዶላር ለመቶ አሥር ብር ግን በዝግመታዊ ዕድገት ፖሊሲ አማካይነትና በገበያ ምክንያት የመጣ ስለሆነ መርከስ ነው፡፡  

አሁን እያነታረከ ያለው ጉዳይ ኦፊሴላዊ የምንዛሪ ምጣኔውን በትይዩ የምንዛሪ ምጣኔው ልክ ማውደቅ (Devalue) ማድረግ ስለማስፈለግ አለማስፈለጉ ነው፡፡ ለዚህ እንቆቅልሽ መፍትሔው ምንድነው፡፡ መልሱ በኑሮ የምናውቃቸውን የኦፊሴል ምንዛሪ የብር ዋጋና የትይዩ ገበያ ምንዛሪ የብር ዋጋ መረጃዎች በሳይንሳዊ መንገድ ከሚተነተን የጽንሰ ሐሳብ መረጃ መጠን ጋር ማቀራረብ ነው፡፡ የጽንሰ ሐሳብ መረጃን በዲያግራም የግራፍ መስመር ዝንባሌ ማየትም ይቻላል፡፡ በአልጄብራ ሒሳብ መለካትም ይቻላል፡፡ ሊለኩ የሚችሉ ሦስት ጽንሰ ሐሳቦችን ዓይተን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዚህ መልክ አለመደራጀቱን እንገልጻለን፡፡

የመግዛት አቅም እኩልነት የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ጽንሰ ሐሳብ

አንደኛው ጽንሰ ሐሳብ የመግዛት አቅም እኩልነት (Purchasing Power Parity) ጽንሰ ሐሳብ ሲሆን፣ ይህም ማለት ዶላርና ብር አንድ ለሃምሳ ስድስት እንዲመነዛዘሩ ካስፈለገ በአሜሪካ አንድ ሺሕ ዶላር ሊገዛ የሚችለውን በቅርጫት የሸማቾች ፍጆታ ሸቀጥ ዓይነትና መጠንን (Basket of Consumers Commodity) በኢትዮጵያ በሃምሳ ስድስት ሺሕ ብር መገዛት አለበት የሚል ንፅፅር ነው፡፡ ይህንን ንፅፅር ለማድረግ አስቸጋሪ የሚሆነው በቴክኖሎጂ መራራቅ ምክንያት የአሜሪካው የቅርጫት ሸቀጥ ዓይነትና ጥራት ከኢትዮጵያው የቅርጫት ሸቀጥ ዓይነትና ጥራት የተለየ መሆኑ ነው፡፡ ከቴክኖሎጂ የፋብሪካ ምርቶች መለያየት አልፎ ተርፎ የግብርና ምርቶቻችን ምግቦች እንኳ የተለያዩ ናቸው፡፡

ከዚህም ባሻገር እንደ ማንኛውም የሸቀጥ ዓይነት የውጭ ምንዛሪም በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር የሚወሰን ሲሆን፣ ውሳኔው ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ የቁሳዊ ሸቀጦች ኤክስፖርተርና ኢምፖርተር ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎች ምንዛሪውን ፈላጊዎችና አቅራቢዎች ከገቢም ከወጪም ቱሪስቶችና መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችም ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ደግሞ የቱሪዝምም ሆነ ሌሎች አገልግሎት ዓይነቶችም ሆኑ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከቁሳዊ ሸቀጦች ኤክስፖርትና ኢምፖርት ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ ስለሆነም ስለየውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲታሰብ ስለቁሰዊ ሸቀጦች ኤክስፖርትና ኢምፖርት ብቻ ማሰብ ትክክል አይደለም፡፡

የወለድ ምጣኔ እኩልነት የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ጽንሰ ሐሳብ

ሁለተኛው ጽንሰ ሐሳብ የወለድ ምጣኔ እኩልነት (Interest Rate Parity) ሲሆን ይህም የጥሬ ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦት መመጣጠን የወለድ ምጣኔን (Interest Rate) ከውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት መመጣጠን የወለድ ምጣኔ ጋር ማቀናጀት (Integrating Money Market Equilibrium with Foreign Exchange Market Equilibrium) ማለት ነው፡፡ ይህ ጽንሰ ሐሳብ የሚሠራው በአገሪቱ የካፒታል ገበያና የባንክ ተቀማጭ  ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ አገር መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችም ክፍት ሲሆን ነው፡፡ 

ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ ሰዎች ገንዘባቸውን በውጭ ምንዛሪ መንዝረው የወለድ ምጣኔ ከፍተኛ ወደ ሆነበት ማንኛውም አገር መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰነዶች ወለድ ምጣኔ ወይም በኢትዮጵያ የባንኮች ተቀማጭ የወለድ ምጣኔ ከሌሎች አገሮች የወለድ ምጣኔ ከፍ ያለ ከሆነ የውጭ አገር ሰዎች የውጭ ምንዛሪያቸውን በብር መንዝረው በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ሰነድ ለመግዛት ወይም በባንክ ለማስቀመጥ ስለሚያውሉ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ይጨምራል፡፡ የካፒታል ገበያም ሆነ የባንክ ተቀማጭ በኢትዮጵያ እስካሁን ዝግ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የጥሬ ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦት የሚገራው በወለድ ምጣኔ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠንን የምትወስነው ከወለድ ምጣኔ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ውጪ ነው፡፡ 

ገና ጥሬ ገንዘብ በሚባለው ቃል ላይ እንኳ አልተግባባንም፡፡ አሜሪካኖቹ ወይም እንግሊዞቹ ጥሬ ገንዘብ (Money) የሚሉት ብርና ሳንቲሞችን የያዘውን ምንዛሪን (Currency fiat Money) እና (Digital Money) ወይም (Credit Money) የሚሉትን የባንክ ተቀማጮችን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ገንዘብ የሚሉት በጥሬ ገንዘብ ላይ ቦንድና አክሲዮን ወይም ሌሎች ሰነዶችን የሚጨምረውን በእንግሊዝኛው (Finance) የሚባለውን ነው፡፡ የሞኒተሪ ፖሊሲ ባለቤት የሆነው ብሔራዊ ባንኩ ግን በእንግሊዝኛው ከፈረንጆቹ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት (Money Supply) ትርጉምን ቢጠቀምም በአማርኛ ምንን ጥሬ ገንዘብ፣ ምንን ገንዘብ እንደሚል ግልጽ አይደለም፡፡

ስት ገበያዎች ጣምራ ምጥጥን ጽንሰ ሳብ  

ለተቀናጀ የፊስካል፣ የሞኒተሪና የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎች (Integrated Fiscal, Monetary and Foreign Exchange Policies) በፍላጎትና በአቅርቦት እኩልነት ለየብቻ የተመጣጠኑ የምርት ገበያ እኩልነት፣ የጥሬ ገንዘብ ገበያ እኩልነትና የውጭ ኢኮኖሚ ክፍያ ሚዛን እኩልነት ገበያዎች በጥምረት መመጣጠን አለባቸው፡፡ የምርት ገበያው ለብቻው ቢመጣጠን ከጥሬ ገንዘብ ገበያው መመጣጠን ጋር ካልተጣመረ የገንዘብ ሚኒስቴርን ፊስካል ፖሊሲ ከብሔራዊ ባንክ የጥሬ ገንዘብ (ሞኒተሪ) ፖሊሲ ጋር ማቀናጀት አይቻልም፡፡ የጥሬ ገንዘብ ገበያው ለብቻው ቢመጣጠን ከምርት ገበያው መመጣጠን ጋር ካልተጣመረ የብሔራዊ ባንኩን የጥሬ ገንዘብ (ሞኒተሪ) ፖሊሲ ከገንዘብ ሚኒስቴር የፊስካል ፖሊሲ ጋር ማቀናጀት አይቻልም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ፖሊሲው ከፊስካል ፖሊሲውና ከጥሬ ገንዘብ (ሞኒተሪ) ፖሊሲው ጋር ካልተጣመረ የክፍያ ሚዛን ጉድለትን አያስወግድም፡፡

የተቀናጁ ፖሊሲዎች ለመንደፍ በመዋዕለ ንዋይ/ቁጠባ እኩልነት የምርት ገበያ መመጣጠን፣ የጥሬ ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦት እኩልነት የጥሬ ገንዘብ ገበያ መመጣጠን፣ የክፍያ ሚዛን እኩልነት፣ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት መመጣጠን የሦስት ገበያዎች መመጣጠን ቀመር (IS-LM-BP Model) የምርት፣ የጥሬ ገንዘብና የክፍያ ሚዛን ሦስት ገበያዎችን ጣምራ ተመጣጣኝነት ማጣመር (Simultaneous Equilibrium of Goods Market, Money Market, and Balance of Payment) ያስፈልጋል፡፡ ቀመሩ በቀዳሚ ተንታኞቹ ሮበርት መንዴልና ማርከስ ፍሌሚንግ ስም መንዴል ፍሌሚንግ ቀመር (Mundel Fleming Model) ተብሎም ይጠራል፡፡ ኢኮኖሚስቶች በቋሚ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ሥርዓትና በተንሳፋፊ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ሥርዓት ሊነደፉ የሚገባቸውን የፊስካልና የጥሬ ገንዘብ (የሞኒተሪ) ፖሊሲዎች ለመምረጥ አንድምታቸውንም ለመመዘን ይረዷቸዋል፡፡

መደምደሚያ

ከዚህ በላይ የቀረቡት በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ሦስት የውጭ ምንዛሪ መጣኝን ማስተካከያ ሳይንሳዊ መንገዶች ሲሆኑ፣ ከላይ እንደተገለጸው በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በሳይንሳዊ መንገድ በቀመር የተለካ መጠን የገበያ መረጃን ባይተካም የገበያ መጠኑን በፖሊሲ ለመግራት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ በሰነፍ ኢኮኖሚስቶች ተደጋግሞ የሚነገር ነገር አለ፡፡ ይኸውም መተንተን ያቃታቸውን ሐሳብ ይህ ጽንሰ ሐሳብ ስለሆነ ለአካዳማዊ ጉዳይ በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ነው የሚያስፈልገው የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ሆኖም በቀመር ተለክቶ ሊረጋገጥ የሚችል ጽንሰ ሐሳብ በፖሊሲ አማካይነት ገበያ ውስጥ ያለውን መረጃ ሊገራውና እንደሚፈለግ ሊያስተካክለው ካልቻለ ስለፖሊሲ መነጋገር ለምን ያስፈልጋል፡፡

ለሰላሳ ዓመታት ደጋግማ ሾላ በድፍን የብርን ዋጋ ብንቀንስ ኤክስፖርት ይጨምራል ኢምፖርት ይቀንሳል የምትልና በውጭ ምንዛሪ እጥረትና ዕዳ አንገቷን የተያዘች ኢትዮጵያ፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት እንዘዝሽ የምትባል ኢትዮጵያ፣ በእነዚህ ሦስት ቀመሮችም ሆነ በሌሎች መሰል ቀመሮች የውጭ ምንዛሪ እጥረቷን ችግር ለመፍታት አልሞከረችም፡፡ ኢኮኖሚውን በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ የሚተነትኑ ኢኮኖሚስቶችንም ሆነ ጽንሰ ሐሳቦቹን በቀመር ለክተው የሚያረጋግጡ የቀመር ባለሙያዎችን አላሳተፈችም፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የሞሉት ራሳቸው ኢኮኖሚውን በጽንሰ ሐሳብ ለክተው ማረጋገጥ ያልቻሉ ከአይኤምኤፍና ከዓለም ባንክ ትዕዛዝ የሚቀበሉ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ለመለካትና ለመተንተን ችሎታ ያላቸው ባለሙያዎች ማን ባቦካው ማን ይጋግራል ብለው የዳር ተመልካች ሆነዋል፡፡

በመንደርደሪያ የተጠቀሱት የቀድሞው ጽሑፍ ጸሐፊ በኢትዮጵያ ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ለብቻ አንድ መፍትሔ በመስጠት የብርን የመግዛት አቅም መቀነስ ውጤት ይመጣል ብሎ ማመን አይቻልም፣ የታመመው ሙሉ ኢኮኖሚው በመሆኑ መታከም ያለበት ሙሉ ኢኮኖሚው ነው ማለታቸው ሙሉ በሙሉ የሚታመንበት ነው፡፡ በረጅም ጊዜ የአስተዳደራዊና የአደረጃጀት ግድፈቶች ሒደት የተንኮታኮተውን ኢኮኖሚ በበሳል ባለሙያዎች ሳይተኩ የተጣመመውን ማቃናት አይቻልም፡፡ አጥፊ አልሚ ሊሆን ስለማይችልም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ብቻ ኢኮኖሚው አይቃናም፣ ማን ያቦካውን ማን ይጋግረዋል?

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...