Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየእኛ ችግር ምን ይሆን?

የእኛ ችግር ምን ይሆን?

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

በአገራችን ኢትዮጵያ ሁሉም ነገር ሞልቶ ተርፎ ሳለ ምን ይሆን የእኛ ችግር? ሕዝባችን ምንም ነገር እንደሌለው ተርቦና ተጠምቶ ለዘመናት ሲኖር ችግራችንን በውል መገንዘብና ማስተዋል ያቃተን ለምን ይሆን? ምን ብንሆን ነው ሊገባን ያልቻለው? ወገኖቼ ተው ልብ እንግዛ፣ ተሳስበንና ተባብረን ለመሥራት እንነሳ፣ ለወገን ኩራትና አለኝታ ለመሆን እንትጋ፡፡ ሌሎች ከደረሱበት አልፈን ለመሄድ የሚያስችለን ፈጣሪ የሰጠን የተፈጥሮ ሀብቶች እያሉን ሁሌም ልመና፣ ሁሌም ቀላዋጭ ለምን እንሆናለን?

እንግዲህ በጥሞና ተከታተሉኝ ወገን ዘመዶቼ፡፡ ኢትዮጵያ ከ500 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አብልታ፣ አጠጥታ፣ አልብሳና ጤንነቱን ጠብቃ ለማኖር የሚያስችል አቅም እንዳላት የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሌም ችግረኛና ተመፅዋች ለምን እንሆናለን? በ1960ዎቹ ይመስለኛል ጊዜውን በውል ባላስታውስም የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው ከ500 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለማኖር የሚያስችሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ያላት አገር መሆኗን አረጋግጦልናል። ይሁን እንጂ ከልመናና ከምፅዋት የተሸጋገርንበት ጊዜ የለም። ለምን? የግልን ጥቅም በማስቀደም መሮጥ፣ ከራስ በላይ ሌላውን ለማየት አለመፈለግ ይሆን በማለት ራሴን ስጠይቅ፣ በእርግጥም ራስን ማስቀደም፣ አርቆ የማየት ልቦና ማጣት፣ የችሎታ እጥረትና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚል አባዜ የተተበተብን መስሎኛል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እኔ በደረስኩበትና ባደረግሁት ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ በርካታ ነገሮች አሏት፡፡ ይህንን ስንል በምኞትና ባልተረጋገጠ መረጃ ሳይሆን እንደሚከተለው በቅደም ተከተል ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡ የአንተ ሐሳብ የተሳሳተ ነው የሚል ካለም በሕዝብ ፊት በሚገባ ተከራክሬ ለማስረዳት ዝግጁ ነኝ። እኔ የከንቱ ወሬ ሰው አይደለሁም፣ የሥራ ሰው እንጂ፡፡ ራሴን አቶ ማለቴ ይሆን? ቢሆንስ እኔ አልጨነቅበትም።                                                                 በምሳሌ ነገሮችን ላስቀምጥና አይቻልም የሚሉ ካሉ ይምጡ እንነጋገርበት፣ እንወያይበት።

በአገራችን የሚመረቱ እንደ ቡና፣ ስንዴ፣ ጥራጥሬዎች፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ዝንጅብል፣ ኮሮሪማ፣ የነጠረ ማር፣ ቆዳና ሌጦ በተጨማሪ በቀላሉ ተመርተው ጥቅም ላይ በመዋል ሀብት የሚያስገኙልንን ዶሮ፣ ዕንቁላል፣ በግ፣ የቀንድ ከብቶችን በምሳሌነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከዚህ በመነሳት እንዴት ችግርንና መከራን ከወገኖቻችን ጫንቃ ላይ እንደምናወርድ ላመላክት ስለፈለግሁኝ፣ አቃቂር ከማውጣት ይልቅ ተደጋግፈን እንድንረማመድ ሐሳቤን ሳቀርብ የሁላችሁንም ድጋፍ አግኝተን ለጋራ ልማታችን አብረን እንድንሠራ ነው።

ባልደከሙበትና በሰው ትከሻ በሚገኝ ንብረት የሚገኘው ውጤት ሐሜት፣ ጥላቻ፣ ፍራቻና መለያየት ናቸው። ለትውልዱም የማይበጁ የመለያየትና የመራራቅ ተምሳሌት ነው የሚሆኑት። ስለዚህ ሁሉን የሚያስተባብርና የሚያኮራ ሥራ ሠርቶ ማለፍ ከሁሉ የበለጠ መልካም ተግባር ስለሆነ ለሥራ እንነሳ እላለሁ።

እጅግ በጣም ብዙ ማዕድናትንና ሌሎች ብዛት ያላቸው የሀብት ምንጮቻችንን በዘመኑ ቴክኖሎጂ በማምረት፣ ለምዕራባዊያንና ሌሎችም ገበያዎች ማቅረብ እንችላለን፡፡ ያሉንን የተፈጥሮ ሀብቶች በሠለጠነ መንገድ መወዳደርና ዓለም የደረሰበት ደረጃ እስክንደርስ ድረስ፣ ለምን በምንችለውና በቀላሉ ሕዝባችንን ከችግር የምንታደግበትን መንገድ አንሻም ነው ምኞቴና ሩጫዬ። ይህ ሩጫ ተሻሽሎም ሆነ ተበረታትቶ የሁላችንም የጋራ ጥረት ይታከልበት፡፡ ሁላችንም አስበንበት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተን ከተነሳሳን ምንም የሚያቅተን ነገር የለም ብዬ አምናለሁ።

አንደኛ ለዓረብ አገሮች በቅርበትም ሆነ በጥቂቱም ቢሆን በባህል ስለምንቀራረብ፣ ሁለተኛ ዋጋችንም ሆነ የተፈጥሮ ሀብታችንን ከሌላው በተሻለ መንገድ ለማቅረብ ስለምንችልና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማድረስ አቅሙም ችሎታው ስላለን፣                                                                                           ሦስተኛ ለመግባብትም ሆነ ለባህል ተቀራራቢነት ስላለን፣ ይህንና ይህንን የመሳሰሉ መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ በሙስሊሞች ፆም ወቅትና በዓላት ሲደርሱ በርካታ የሥጋ እንስሳት ማቅረብ እንችላለን፡፡ በአዘቦት ጊዜያት ደግሞ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ከእኛ የተሻለ የሚያቀርብ፣ ከእኛም የተሻለ ዋጋ የሚሰጥ ስለሌለ ዶሮ፣ ዕንቁላል፣ በግ፣ የሥጋ ከብት በማቅረብ ብቻ ዛሬ በእጅጉ የምንዋትትለትን የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ የምናገኝበትና የሰው እጅ ከማየት የምንድንበት ሁኔታ ተጠንቶ ወደ ሥራ እንድንገባ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡                                                                                                   

ለምሳሌ በየመንገዱ ሥራ በማጣት ሲዋትት የሚውለውን ወጣት ኃይል አሠልጥነን በብዛት ወደ ሥራ ማሰማራት እንችላለን፡፡ በዚህ መሠረት በቀላሉ 200 ወጣቶችን ዶሮ የማርባት ዕውቀት አስተምረን እያንዳንዱ ወጣት በትንሹ 1,500 የዕንቁላል ዶሮዎች ቢያረባና ለገበያ በዘመናዊ መንገድ ቢያዘጋጅ፣ ለምሳሌ 200 x 1,500 = 300,000 ዶሮዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ 300,000 ዶሮዎች 75 በመቶ ያህሉ ዕንቁላል ቢጥሉ 225,000 ዕንቁላሎች በየቀኑ ተገኙ ማለት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ በሳምንት ብናባዛው 225,000 X 7 = 1,575,000 ዕንቁላሎች አገኘን ማለት ነው። 1,575,000 ዕንቁላሎች ሲባዛ በ$2,00 = $3,150,000 ዶላር በሳምንት ውስጥ ይገኛል ተብሎ ይታሰባል፡፡ 150,000 የሥጋ ዶሮዎች በየሳምንቱ ብንልክ 150,000 x $5 = 750,000 x 7 = $5,250,000 በየሳንምቱ ቢገኝ በዚህ የተገኘውን አጠቃላይ የሳምንቱ ገቢ $6,825,000 ከሆነ፣ በ52 ሳምንታት ከዶሮና ከዕንቁላል ብቻ $354,900,000 (ሦስት መቶ ሃምሳ አራት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር) ተገኘ ማለት ነው።

በዚህ መሠረት ስንቀጥል ምንም እንኳ ዛሬ የነዳጅ ዘይት ሀብታም አገሮች ብዙ አማራጭ አግኝተው የእኛን አገር የከብት ሥጋ ንቀው ወደ ሌላ ቢያዘነብሉም፣ ለሰፊው ሕዝባቸው በመጠኑም ቢሆን ስለሚገዙ በሺዎች የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶችን መላክ ይቻላልና የዚያንም ግምት ለመጠቆም ይቻላል።  በጎቻችን  እጅግ ተፈላጊ በመሆናቸው በሺዎች የሚቆጠሩን ከጌሻና ከደብረ ብርሃን ማቅረብ አያቅትም፡፡ እነዚህ ምርጥ በዓለም ላይ የማይገኙ የበግ ዝርያዎች ስለሆኑ፣ በተቻለ መጠን  በሚሊዮን የሚቆጠሩ በጎችን በማቅረብ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ መገመት ይቻላል።                                                            

የዚህ ጹሑፍ ዓላማ በከንቱ የሚሰደዱትን ወገኖቻችንን በሠለጠነ አሠራር ከአገራቸው ሳይርቁ፣ በሚገባ ጥናት ተደርጎ ሁሉም በሚችሉት ዘርፍ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ነው፡፡ በተለያዩ የሙያ መስኮች ዕውቀትና ችሎታ ያላቸው በሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ መንግሥትም ፊቱን ወደ ልማት በማዞር የወገኖቻችንን ችግሮች የሚቀርፍበትን መንገድ እንዲሻ ለማሳሰብ ነው።                  

ለምሳሌ የእኛ አገር የቀንድ ከብት ቢበዛ ከ500 ኪሎ ግራም እስከ 650 ኪሎ ግራም ቢመዝን ነው፡፡ በአንፃሩ የደቡብ አፍሪካ ወይም የአውሮፓና የአሜሪካ አንድ የቀንድ ከብት ከ700 ኪሎ ግራም እስከ 1,550 ኪሎ ግራም ይደርሳል። ታዲያ የከብቱ መጠን ያን ያህል ሲሆን የሚሸጠው አንዱ ኪሎ ግራም $2.89 ነው፡፡ ይህንን እያደር በማዳቀልም ሆነ በሌላ ሁኔታ እስክናሻሽል ድረስ ባለው እየተጓዝን በተቻለን መጠን ከችግር የምንወጣበትን፣ ልጆቻችንንም ከስደት የምናስቀርበትን፣ እኛም በውጭ ምንዛሪ ሰቀቀን ባዕዳንን ከመለማመጥ እንድንወጣ በራሳችን የምንቋቋምበትን መንገድ ብንሻ ይሻላል? ወይስ ሁሌም ኮረጆ ይዘን ለልመና መዞር? ወገኖቼ ሁሉ ያለንና ሁሉ የተረፈን ሆነን ለምን እንቸገራለን? እባካችሁ ዛሬውኑ ወስኑ። ዘወትር በሁሉም ነገር ጠብና ጭቅጭቅ የሰው ባሪያ እንዳያደርገን ተባብረን እንነሳ። አገር የምትመሩም ሆናችሁ ምሁራንና ልሂቃን የምናውቀውን ሳትንቁ ምክራችንንም ተቀበሉን። አለንላችሁ ስንል እጃችሁ ከምን በሉን፡፡ ፖለቲካ ብቻ አገር ሊመራ አይችልምና ገበሬዎችንም አማክሩ፡፡ ያለማወቅ ብዙ ጥፋት እንደሚፈጥርም ተገንዛባችሁ ወደ ልቦናችን እንመለስ።                                                                                

አፍሪካን በአንድነት በማነሳሳት ሌሎች የደረሱበት ለመድረስ ከመሯሯጥ ይልቅ፣ ነባሯ ኢትዮጵያን ለዚህ ቀውጢ ጊዜ የምትዳርጓት እባካችሁን ባለን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅመን ለሌሎች ምሳሌ እንሁን። እኛ የጥቁርን ዘር ያኮራን መሆናችን ዓለም ያወቀው ታሪክ ሆኖ ሳለ በዚህ ዘመን ግን አናሰድብ። ያለንን ሊቀሙን የሚያፋጁንን በልጠን እናሳፍራቸው፡፡ እስከ መቼ ነው የእነሱ ጋሻ ጃጋሬ ሆነን የእነሱን መልዕክት ተሸክመን ወገን በወገን እየተለያየን በሽብር የምንኖረው? እባካችሁ ልብ እንግዛ፡፡

መማርና ማወቅ የፍጅት ጎዳና መሆን የለበትም፡፡ አሁን በምታደርጉት አጉል ሥራ ነገ ልጆቻችን እንዳያፍሩ አስቡበት፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ተስማምተው ሲያፋጁን ምነው ማየትና ማስተዋል አቃተን? ቋንቋቸውን ቀድተን መዘባነኑ ይሆን የእኛ ሥልጣኔ? የምንቀምሰው ጠፋ ብለን የዕለት ጉርስ መለመን ይሆን የእኛ ዘመናዊነት? እባካችሁ ያለንን በሙሉ እንኳ ባይሆን በመጠኑ ተጠቅመን ወገናችንን ከአዋራጁ ልመና እናውጣው። ለዚህ መልካም ተግባር ያልቆመ ዜጋና መሪ ነገ ምን ይል ይሆን? ልብ በሉ ታሪክ የማይረሳውን ስህተት በመሥራት ላይ ናችሁና ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ ስል ለወገኔ በሙሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ከዚህ ቀደም የሕይወት ታሪካቸውን የሚዘክር ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ያሳተሙ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል assefadefris@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...