Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ለበርካታ ጉዳዮቻችን ሊጠቅሙን የሚችሉት ዘመን አፈራሾቹ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላልተፈለገ ዓላማ ሲውሉ ያናድደኛል፡፡ ምንም እንኳ ሙያዬ ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ቢሆንም፣ ለፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ልዩ ዝንባሌ ስላለኝ ከአገሬ እስከ ዓለም አቀፍ ድረስ በርካታ ጉዳዮችን እከታተላለሁ፡፡ ለዚህ ስልም የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውልድ የሆኑትን ትዊተር፣ ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ፣ ወዘተ ቻናሎችን በሚገባ እጠቀምባቸዋለሁ፡፡ ከመደበኛው ትምህርት ባልተናነሰም በርካታ ዕውቀቶች ገብይቼባቸዋለሁ፡፡ ሁሉም ነገር በጎነቱና ክፋቱ የሚለየው እንደ አጠቃቀማችን ስለሆነ፣ ብዙዎቹ የአገሬ ወጣቶች ከተጠቃሚነት ይልቅ ለተጎጂነት ራሳቸውን ያጋለጡ ስለመሰለኝ ነው ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ የተነሳሳሁት፡፡

ተዓማኒነት የጎደላቸው መረጃዎች እንደ ሰደድ እሳት በተስፋፉበት በዚህ ዘመን ሰዎች በጣም እየተቸገሩ ነው፡፡ መረጃ ኃይል ነው ሲባል በአገር ላይም ሆነ በግለሰብ ሕይወት ላይ ሁነኛ ተፅዕኖ ስላለው ነው፡፡ በአግባቡ የተቀናበረ መረጃ የሚፈለገውን ውጤት ለማስገኘት ሲረዳ፣ በሐሰት የሚነዛ መረጃ ግን ከባድ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተደጋጋሚም ታይቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አማካይነት በተለቀቁ አደገኛ ቅስቀሳዎችና የተዛቡ መረጃዎች ምክንያት በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ለዓመታት ለፍተው ያፈሩት ንብረትም ወድሞባቸዋል፡፡ በሥልጣኔ ወደ ፊት የገፉ አገሮች ለመረጃ የሚሰጡት ዋጋ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ፣ የተትረፈረፈ ሀብት በማግኘታቸው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ይተርፋሉ፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የተሻለ መረጃ ማግኘት የቻለ አሸናፊ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በተዛባ መረጃ ምክንያት ደግሞ የከሰሩ ብዙ ናቸው፡፡

በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመ አንድ ድርጊት አሁን ከምነግራችሁ አንድ ወግ ጋር ተገጣጠመብኝ፡፡ ለዚህም ስል እንዲህ ጻፍኩት፡፡ አፄ ቴዎድሮስ የአንድ ደጃዝማች አገር ተቆጣጥረው ለማስገበር የጦር ዝግጅት ሲያደርጉ፣ በደጃዝማቹ ላይ ያኮረፉ አንድ ሹም ቴዎድሮስ ሠፈር ይመጣሉ፡፡ የደጃዝማቹ የጦርነት ቀጣና እንዴት በቀላሉ እንደሚጣስ ምክር ይሰጣሉ፡፡ በእሳቸው ጠቋሚነት በደጃዝማቹ ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት ይፈጸምና አፄ ቴዎድሮስ ድል ያገኛሉ፣ ደጃዝማቹንም ይማርካሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተገኘው ድል የተደሰቱት አፄ ቴዎድሮስ ለሠራዊታቸው መሪዎችና ጀብዱ ለፈጸሙ ወታደሮቻቸው የማዕረግ ዕድገትና የተለያዩ ሽልማቶችን ይሰጣሉ፡፡ ደጃዝማቹን ከድተው ለድሉ መገኘት ቁልፍ የሆነ አስተዋጽኦ ያደረጉት ሰው ግን ሽልማት ሳያገኙ ይቀራሉ፡፡ በዚህ የተከፉት የደጃዝማች ሹም ለአፄ ቴዎድሮስ በመከፋት አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ‹‹በአጭር ጊዜ ወሳኝ ድል እንዲጎናፀፉ ማድረግ በመቻሌ እንዴት ሽልማት እነፈጋለሁ?›› በማለት ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ አፄ ቴዎድሮስ አንዱን ሹም በስም ጠርተው፣ ‹‹ይህንን ሰውዬ እስር ቤት ክተትልኝ፡፡ እኔ ጌታውን ከከዳ አሽከር ጋር ውል የለኝም…›› ማለታቸው በአቶ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ‹‹ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› መጽሐፍ ላይ ሠፍሯል፡፡

በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት የሚያነጋግር ጉዳይ ባይኖረንም፣ ዘመኑ መረጃ በፍጥነትና በጥልቀት የሚተላለፍበት በመሆኑ አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ፈጣን የቴክኖሎጂ ዘመን መረጃ በጥራት ሊደርሰን የሚገባው በማንኛውም የሥራ መስክ ላይ የተሰማራን ሰዎች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መወሰን እንድንችል ነው፡፡ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ዣንጥላና ካፖርት መያዝ ሲገባን፣ ፀሐያማና ሞቃታማ ስለሆነ ቀላል ልብስ ልበሱ ብሎ በዶፍ ዝናብ ቢያስደበድበን ለኒሞኒያና ለመሰል በሽታዎች ያጋልጠናል፡፡ ማንም የማይፈልገው ጥራቱ የወደቀ ምርት በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ተኳኩሎ ቀርቦ ሕይወታችንን ለአደጋ ይዳርገዋል፡፡ ለዚህም ሲባል የሚተላለፍልን መረጃ እውነተኛ ብቻ መሆን አለበት፡፡ መረጃ በትክልል መተላለፍ ካልቻለ አገሮችን ጦር ሊያማዝዝ ይችላል፡፡ ውጤቱም ዕልቂትና ውድመት ይሆናል፡፡

በዚህ ዘመን የሚተላለፉልን መረጃዎች ምን ያህል ጥራት አላቸው ስንል ተከድኖ ይብሰል ማለት ይቀላል፡፡ ለሕይወታችን ወሳኝ ከሆኑ ዜናዎች እስከተለያዩ ምርቶች ማስተዋወቅ ድረስ የተዛቡ መረጃዎች ናቸው የሚደርሱን፡፡ የግለሰቦችን ፍቅረ ነዋይና ውስጣዊ ስሜት የሚያረኩ ነገሮች ላይ ተመሥርተው የሚደርሱን መረጃዎች ትክክለኛ ውሳኔ ላይ እንዳንደርስ እያደረጉን ናቸው፡፡ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በጋዜጣ፣ በመጽሔትና በማኅበራዊ ድረ ገጾች የምንሰማቸው ብዙዎቹ መረጃዎች ጥራት የላቸውም፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ በፕሮፓጋንዳ የተሞሉ ናቸው፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦችን ጥቅምና ፍላጎት የሚያቀነቅኑ፡፡

ከዓመታት በፊት ከአንድ ወዳጄ ጋር አንድ ሆቴል ውስጥ ቢራ እየቀማመስን ነበር፡፡ በዚህ መሀል አንዱ፣ ‹‹በፌስቡክ የተለቀቀውን ወሬ ሰማችሁ?›› አለን፡፡ ጓደኞቼ ሰምተዋል፡፡ እኔ ምን እንደሆነ ስለማላውቅ፣ ‹‹ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ ‹‹የመንግሥት ባለሥልጣናት ስዊድን ውስጥ ባለው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተወሰነባቸው…›› አለኝ አንዱ፡፡ ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ? በይፋ መከሰሳቸውን ያልሰማን ሰዎች እንዴት ፍርዱን አመንን? ዘ ሔግ የሚገኘው ፍርድ ቤትስ መቼ ነው ስዊድን የሄደው? ይህንን ወሬ አምነው ከዳር እስከ ዳር ሲነዙ የነበሩትስ ይህንን ቀላል ጥያቄ እንዴት ዘነጉት? የወሬ ጫፍ ይዘው ሲያናፍሱ የሚውሉ ብዙ ሰዎች አውቃለሁ፣ ያውም የተማሩ፡፡ ነገር ግን ‹‹ለምን? እንዴት? መቼ? የት?…›› ብለው አይጠይቁም፡፡ እኔ ደግሞ በእንዲህ ዓይነቶቹ ‹‹የጋን ውስጥ መብራቶች›› ስበግን እኖራለሁ፣ ፈርዶብኝ፡፡

አንድ ጊዜ ደግሞ አንዱ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በኢቦላ ወረርሽኝ ሁለት ሺሕ ሰዎች አልቀዋል…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፣ ደንግጬ ግን ዝም አላልኩም፡፡ ‹‹ወሬውን ከየት አገኘህ?›› አልኩት፡፡ በጣም ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹ከአስተማማኝ ምንጭ ነው…›› ብሎኝ፣ ‹‹ይህንን መረጃ የነገረኝ እዚህ አገር ውስጥ ያለ ማንኛውንም ሚስጥር ያውቃል፡፡ መንግሥት አፍኖት ነው እንጂ እውነት ነው…›› እያለ ወሬውን ሲያሟሙቅ ለአታላይ ይዳርግህ እንዳልለው ጡር መስሎኝ ተውኩት፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር መከርኩት፡፡ ‹‹ለፕሮፓጋንዳ የሚወራ ከንቱ ወሬና ትክክለኛ መረጃ ለይተህ ዕወቅ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ገብተህ የተማርከው እኮ እንድትጠይቅና እንድትመራመር እንጂ፣ የሰማኸውን ሁሉ እንደ ቧንቧ እንድታስተላልፍ አይደለም…›› ብዬው በቆመበት ጥዬው ሄድኩ፡፡ እውነት ቢሆን ኖሮ እሱ ከአስተማማኝ ምንጭ አገኘሁት ያለውን ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አልጄዚራ፣ ወዘተ ላይ እንሰማው ነበር፡፡

ነፍሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በአንድ ወቅት በሸገር ሬዲዮ ጣቢያ በተከታታይ በቀረበው አስደናቂ ቃለ ምልልሳቸው፣ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል የድሮውን እሳቸውን የተመለከቱ አሉበት፡፡ እሳቸው በአፅንኦት ሲናገሩ የነበሩት ይህንኑ ነበር፡፡ መጠየቅና መመርመር ባለመኖሩ ምክንያት አንዴ ‹ፀረ ሴት ናቸው፣ ሌላ ጊዜ አባታቸው እከሌ ነው፣ ያለ በቂ ማስረጃ ክፉ ድርጊት ፈጽመዋል፣ ወዘተ› መባላቸውን እንደተናገሩ ይታወሰኛል፡፡ ሰዎች ዝም ብለው ማውራት እንጂ ትንሽ ማጣራት ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት በጣም አናሳ በመሆኑ እንደሚገረሙ በሐዘኔታ መናገራቸውን አልዘነጋም፡፡ መጠየቅና መመርመር በሌለበት አሉባልታ እውነት ይሆናል፡፡ የመልካም ሰዎች ስም ይጎድፋል፡፡ ወሬኞችና አሉባልተኞች ደግሞ ከየትም እያመጡ እንደ ጭቃ ይለጥፋሉ፡፡ ግልጽነት በጎደለው ኅብረተሰብ ውስጥ ወሬ ይነግሣል፡፡ ‹‹ሳያጣሩ ወሬ ሳይገሉ ጎፈሬ›› እየበዛ ነው፡፡ በአሉባልታ ምክንያት ትዳር ይፈርሳል፣ ሕፃናት ይበተናሉ፡፡ የት ይደርሳል የተባለ ቢዝነስ ይቀዘቅዛል፡፡ አገር በወሬ ይፈታል፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ ሁኔታው አደገኛ ደረጃ የደረሰ ይመስላል፡፡ ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት በመብዛቱ ለመረጃ ጥራት መጨነቅ ስለሌለ አገር የአሉባልተኞች መጫወቻ እየሆነች ነው፡፡

(ሥዩም አሰፋ፣ ከወይራ ሠፈር)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...