Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ተቋም  አባል  አገሮች  በአዲሱ ዓመት እንዲፈጽሙ  ያሳሰባቸው ጉዳዮች

ዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ተቋም  አባል  አገሮች  በአዲሱ ዓመት እንዲፈጽሙ  ያሳሰባቸው ጉዳዮች

ቀን:

‹‹ስፖርት እንደ ቀድሞው ዘመን ለስሜት ብቻ ተብሎ የሚዘወተር አይደለም፤›› ብለው የሚከራከሩ እየተበራከቱ ነው፡፡ ቀድሞ ለስሜቴ ስፖርትን ስለምወድ፣ ወይም ለአገሬ ሰንደቅ ዓላማ ብዬ ነው ወደ ስፖርቱ የገባሁት የሚሉ በርካቶች ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ተጫዋች ሌላ ክለብ  ለመቀላቀል  የጠየቀው  የዝውውር ክፍያና ወርኃዊ ደመወዝ፣ በጊዜው እንደ ‹ኃጢዓት› ታይቶ ነበር።

በአትሌቲክሱም አትሌቶች በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተካፍለው የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከማውለብለብ በዘለለ፣ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከዚህም  በላይ  በሩጫው ከሚያገኙት ክፍያ ይልቅ በአገር ቤት የሚሰጣቸው ሽልማት ሚዛኑ የደፋ ነበር፡፡

በቅርቡ በተደረገ ጥናት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ስፖርት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኢንዱስትሪ፣ ንግድ፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እየሆኑ ከመምጣታቸው በዘለለ ለአገር ኩራት መገለጫ  መሆናቸውን ይጠቅሳል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ተቋም  አባል  አገሮች  በአዲሱ ዓመት እንዲፈጽሙ  ያሳሰባቸው ጉዳዮች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በዚህም ምክንያት እነዚህን እውነታዎች ለማሳካትና ድል ለማድረግ ሕግ ወደ መጣስ የሚገቡ መበራከታቸው ይወሳል፡፡  ከዚህ ጋር ተያይዞም የተለያዩ ስፖርተኞች በማወቅም ሆነ ባለማወቅም እንደማይደርስባቸው በማሰብ፣  ራሳቸውን አደጋ ውስጥ ሲከቱ መስተዋሉ ጥናቱ ያሳያል፡፡

 እንደ ገፊ ምክንያት የሚያነሱት ከስፖርቱ ጀርባ ያሉት ረብጣ ገንዘብ የሚያቀርቡ ግዙፍ የትጥቅ አምራቾችና አጓጊ ሽልማቶች መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡

በአንፃሩ በአጭር ጊዜ ለመበልፀግ አቋራጭ መንገድ ለመከተል የሚዳዱት በርካታ አትሌቶች ምንም እንኳ ተሳክቶላቸው የተወሰነ ጊዜ በአበረታች ቅመሞች ተጠቅመው የፈለጉትን ቢያሳኩም፣ በጤናቸው  ላይ የከፋ ጉዳት እንደሚደርስባቸውና ለሥነ ልቦናዊ ቀውስ ሊዳርጋቸው እንደሚችል ጥናቱ ያመላክታል።

በዓለም የዶፒንግ ክስተት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚያው መጠን ውስብስብነቱም መጨመሩም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በጊዜ ሒደት  የአበረታች ንጥረ ነገር ተጨማሪ ትርጓሜዎች ሲኖሩት፣ እንደ ቤክማን መዝገበ ቃላት አተረጓጐም ዶፒንግ ማለት አትሌቶች በተለምዶ ከሚያገኙት የላቀ አቅም የሚጨምር ያደርገዋል፡፡

በውድድሮች ውስጥ ከበርካታ አጋጣሚዎች በኋላ እ.ኤ.አ. በ1928 የዓለም  አትሌቲክስ ፌዴሬሽን (አይኤኤፍ)፣ በአትሌቲክስ ውድድር ዶፒንግን ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የከለከለ ነው፡፡ ከዚያም ከ32 ዓመት በኋላ የፀረ ዶፒንግ ምርመራ መተግበር ችሏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1972 በሙኒክ ኦሊምፒክ የመጀመሪያው የዶፒንግ ቁጥጥር የተደረገ ሲሆን፣ በ1976 የሞንትሪያል ኦሊምፒክ በርካታ አትሌቶች በመጠቀማቸው ሜዳሊያቸውን ተነጥቀዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የዶፒንግ ምርመራ ውጤት በውድድር ወቅት ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበት ደነገገ፡፡

ሆኖም እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ በኋላ አበረታች ንጥረ ነገር የሆኑትንና ያልሆኑትን ቅመሞች  ለመለየትና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ለማጭበርበር ፍላጎት ለነበራቸው ዕድል ከፍቶ እንደነበር መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

ዘመናዊ ስፖርት ከተጀመረ በኋላ በርካታ አትሌቶች ንጥረ ነገሩን ተጠቅመው በመገኘታቸው፣ ከሁለት ዓመት ቅጣት ጀምሮ ከስፖርት ዓለም እንዲታገዱ ተደርገዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅሞ የተገኘ አትሌት በዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ)  ያስቀመጣቸውን ሕጎች እንደጣሰ ይቆጠራል፡፡ እነዚህም የተከለከሉ ንጥረ ነገሮች መጠቀም ወይም ለመጠቀም መሞከር፣ ለምርመራ ፈቃደኛ አለመሆን፣  ናሙና ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን፣ ናሙናውን ማስወገድ፣ እንዲሁም መዋሸትና ማጭበርበር እንደማንኛውም የሕግ ጥሰት እንደሚወሰዱ ያስቀምጣል፡፡

በዓለም ላይ ሁሉም አገሮች ከፀረ አበረታች ጋር በተያያዘ የተለያየ ሕግ ያላቸው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ተጠቅሞ የተገኘ አትሌት በወንጀል ሕግ እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡

ዋዳ በየዓመቱ የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን ዝርዝር ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2024 ከጃንዋሪ 1 ቀን  (ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም.) ጀምሮ የስፖርቱ ማኅበረሰብ መጠቀም የማይገባውን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡ አያይዞም አትሌቶች፣ ማናጀሮች፣ አሠልጣኞች፣ እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትራማዶልን በተመለከተ ትልቅ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

እነዚህን በውድድር ወቅትና ከውድድር ውጪ መጠቀም የማይቻል ሲሆን፣ ከሆርሞን መጨመር ጋር የተያያዙ ለሕመም የሚወሰዱ እንክብሎች፣ አነቃቂ፣ እንዲሁም ናሮቲክ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል። በተለይ በአብዛኛዎቹ አትሌቶች ዘንድ እየተለመደ የመጣው ኢፒኦ (EPO) እና ስቴሮይድ (Steroid) የተባሉ አበረታች ንጥረ ነገሮች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ዋዳ አስምሮበታል።

እንደ ዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ ዝርዝሩ ከስምንት ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ይህም ለሁሉም የዓለም የፀረ አበረታች መድኃኒት ባለሥልጣኖች፣ አትሌቶች በውድድርም ሆነ ከውድድር ውጪ የተከለከሉ ንጥረ ነገሮችን  ሊገነዘቡ እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን፣ ዋዳ  በ2024 ባሠራጨው የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞች ዝርዝር ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡

በዓለም በተለያዩ ስፖርቶች አበረታች ንጥረ ነገሮች የተጠቀሙ  ከማንኛውም ውድድሮች የታገዱ ሲሆን፣ ከ2020 ጀምሮ አራት አገሮች በርካታ አትሌቶች ተገኝተውባቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሩሲያ 41 አትሌቶች፣ ኬንያ 12፣ ህንድ 12፣ እንዲሁም አሜሪካ 11 አትሌቶች አበረታች ንጥረ ነገሮችን የተጠቀሙ አትሌቶች በመያዝ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

በቅርቡም በኢትዮጵያ ስምንት አትሌቶች በ2023 አበረታች ንጥረ ነገር መጠቀማቸው ይፋ ሲሆን፣ በተጨማሪ ምርመራ የሚያሻቸው መኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ እያንዣበበ የመጣው የዶፒንግ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ጫናው

ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ደማቅ ተሳትፎና ውጤት ጥያቄ ውስጥ እየገባ መምጣቱ እየተነሳ ነው። ይህም ቀድሞውንም ኢትዮጵያ በተለይ በረዥም ርቀቱ ከኬንያውያን አትሌቶች በጋራ በመሆን በበላይነት መቆጣጠራቸውን ተከትሎ፣ በምዕራቡ ዓለም ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቅ አስችሎታል። በተለይ በተደጋጋሚ የሚሻሻሉና የሚሰበሩ ክብረ ወሰኖች ጥርጣሬውን የጎላ አድርገውታል። አትሌቶች በማራቶን እና በትራክ ውድድሮች የሚያስመዘገቡት አዲስ ክብረ ወሰንን ትከትሎ፣ ዶፒንግ የሚል ቅፀላን በትንታኔዎች ላይ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። በዚህም መሠረት በ2023 በርካታ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅመው መገኘታቸው ጥርጣሬው እንዲያይልና የዓለም አቀፉ የስፖርት ማኅበረሰብ ትኩረት እንዲስብ አስችሎታል።

በቅርቡም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስለጉዳዩ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኗል በማለት ተናግሯል። በኢትዮጵያ የዶፒንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የገለጸው ፌዴሬሽኑ በተለይ ከዕውቅናው ውጪ በተለያዩ አገሮች የጎዳና ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ቁጥር መጨመሩን አስረድቷል።

እንደ ፌዴሬሽኑ ማብራሪያ ከሆነ በርካታ አትሌቶች የቱሪስት ቪዛ በመያዝ፣ በቻይና፣ በዓረብ አገሮችና  በሰሜን አሜሪካ ውድድሮች ላይ እየተሳተፉ ነው። ከዚህም በላይ አበረታች ንጥረ ነገሩን በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር አስገብተው በልምምድ ሥፍራዎች እየቸበቸቡ የሚገኙ ግለሰቦች መኖራቸውን አመልክቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከኬንያ የተባረሩ 170 ማናጀሮች አብዛኛዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የፌዴሬሽኑ የሕክምና ባለሙያዎች አስረድተዋል።

 ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ  በ2023 ስምንት ኢትዮጵያውያን አበረታች ቅመም መጠቀማቸው የገለጸ ሲሆን፣ ሁለት አትሌቶች ጊዜያዊ ዕገዳ ጥሎባቸዋል። ሁለቱ አትሌቶች በዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተካፈሉ መሆናቸው ጉዳዮን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎታል። በተጠቀሰው ዓመት አበረታች ቅመም የተጠቀሙ ስምንት አትሌቶች ከየትኛውም ውድድር ሲታገዱ፣ በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮን በ3000 ሜትር መሰናክል የተወዳደረችው ዘርፌ ወንድምአገኝና በማራቶን የተወዳደረችው ፀሐይ ገመቹ በጊዜያዊነት ታግደዋል፡፡ ዘርፌ ኢፒዮ የተባለ ንጥረ ነገር መጠቀሟ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ፀሐይ በአትሌት ባዮሎጂካል ፓስፖርት (Athletes Biological Passport) በመጠርጠሯ ተጨማሪ ምርመራዎች እንደሚቀሯት ተገልጿል።

የአትሌት ባዮሎጂካል ፓስፖርት መሠረታዊ መርሆ የዶፒንግ ንጥረ ነገሩን ወይም ዘዴን በራሱ ለማወቅ ከመሞከር ይልቅ የዶፒንግን ተፅዕኖ በተዘዋዋሪ የሚያሳዩ የተመረጡ ሥነ ሕይወታዊ ተለዋዋጮችን በጊዜ ሒደት መከታተል ነው።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕክምና ባለሙያዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት፣ ዘርፌ በቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮን  ከውድድር ውጪ በኦገስት ወር በተደረገላት ምርመራ ኢፒዮ (EPO) መጠቀሟ፣ እንዲሁም ከውድድር መልስ በተደረገላት ምርመራ (Steroid) መጠቀሟ ተረጋግጧል፡፡

ሌላዋ አትሌት ፀሐይ  ገመቹ ስትሆን አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅማለች በሚል በመጠርጠሯ ተጨማሪ ምርመራዎች ይጠብቃታል ተብሏል።  እንደ ባለሙያዎቹ ማብራሪያ አትሌቶች በምርመራ ቋት ሁለት ዓይነት ምርመራ የደምና የሽንት  ይደረግላቸዋል።

በሽንት ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር ወዲያው የሚታወቅ ሲሆን፣ በአንፃሩ በደም ውስጥ የሚደረገው ምርመራ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይፈልጋል። በአትሌት ባይሎጂካል ፓስፖርት የተጠረጠሩ አትሌቶች፣ በሕክምና ምክንያት የተጠቀሙት ነገር  ካለ፣ በቂ መረጃ ማቅረብ እስኪችሉ ድረስ ታግደው የሚቆዩ ይሆናል።

የፀሐይም ጉዳይ በቂ መረጃ እስኪቀርብ ድረስ ክትትሉ የሚደረግ ሲሆን፣ ነፃ ሆና ከተገኘች ወደ ውድድር የመግባት ዕድል ይኖራታል።

በሌላ በኩል ‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አደጋ ተጋርጦበታል፣ ችግር ውስጥ ነው›› በማለት ጉርድ ሾላ በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ መግለጫ የሰጠው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ ዋነኛው መንስዔ ያደረገው በጎዳና ውድድሮች ላይ የሚገኙት አጓጊ ሽልማቶች፣ እንዲሁም አትሌቶች ሕመም ሲገጥማቸው ቶሎ ለማገገም በሚል ንጥረ ነገሮችን መጠቀም እያዘወተሩ በመምጣታቸው መሆኑን ጠቅሷል።

በዚህም አበረታች ንጥረ ነገሩን የሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቁጥር መጨመሩ ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን በበኩሉ፣ በመላ አገሪቷ ለሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ሥልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጿል። ባለሥልጣኑ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለሚሳተፉ አትሌቶች በቅርቡ ምርመራ እንደሚያደርግም አስታውቋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቋት ውስጥ ያሉ 400 አዋቂ አትሌቶች ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተገልጿል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...