Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሕጎች ላይ የሚታየው የጥራት ችግር ፍትሕ ለማስፈን ተግዳሮት መፍጠሩ ተነገረ

በሕጎች ላይ የሚታየው የጥራት ችግር ፍትሕ ለማስፈን ተግዳሮት መፍጠሩ ተነገረ

ቀን:

በኢትዮጵያ የሚወጡ ሕጎች የጥራት ችግርና ለመንግሥት ያደሉ መሆናቸው፣ ለፍትሕ ሥርዓቱ ተግዳሮትና ለዜጎች ፍትሕ ማጣት ምክንያት እንደሆነ ተገለጸ፡፡

‹‹መልካም አስተዳደር በአፍሪካ›› የሚባለው ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ቢሮ ‹‹ተቋማዊ ልማት አደረጃጀትና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ›› ባዘጋጀው መድረክ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት መምህር ዘካርያስ ቀንዓ (ፕሮፌሰር) የፍትሕ አካላት አደረጃጀት፣ የሕግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ጹሑፍ አቅርበው ነበር፡፡

ዘካርያስ (ፕሮፌሰር) በጹሑፋቸው የሕጎች ግልጽ አለመሆንና ለመተግበር አስቸጋሪ መሆን፣ ለዜጎች የፍትሕ ዕርካታ ማጣት ቁልፍ ምክንያት ከመሆኑም በላይ፣ የተወሰኑ ሕጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ከዜጎች ይልቅ ለመንግሥት የሚያደሉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ሕጎች በመኖራቸው ዳኞች በሕጉ መሠረት ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሲቸገሩ እንደሚታዩ፣ ፍርድ ቤቶች ሕጎቹ ሲወጡ የነበሩ ቃለ ጉባዔዎች፣ ዝርዝር ውይይቶችና ክርክሮችን የሚያመላክቱ የዳራ ሰነዶች ለማግኘትም እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡

ሕጎች በሚተረጎሙበት ወቅት በአማርኛውና በእንግሊዚኛው መካከል ያለውን አለመጣጣም ሲያብራሩ፣ ከአማርኛ ወደ እንግሊዚኛ ሲቀየር በፓርላማው የታሰበው የሕግ ይዘት ሲተረጎም ከመጀመሪያው ዕሳቤ ውጪ የሆነ ትርጉም መስጠት እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚሰማው የዓቃቤ ሕግ ድምፅ እንጂ ጠበቆች ቢናገሩም ሐሳባቸው እንደማይደመጥ፣ በዚህም ሳቢያ ‹‹ዳኞች አስፈጻሚውን በሚወክለው ዓቃቤ ሕግ እንጂ በሕጉ አይመሩም›› የሚል አቤቱታ ይሰማል ብለዋል፡፡ ከፍትሐ ብሔር ሕግ አንፃር በተለይም የግብር አፈጻጸምን በተመለከተ ለሚቀርቡ ክሶች፣ ዳኞች ለመንግሥት ያደላሉ የሚል ተደጋጋሚ ትችት እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡

ከሕጎች ጥራትና ግልጽነት ማነስ በተጨማሪ፣ በፍርድ ቤቶች የሚወሰኑ ውሳኔዎች አለመፈጸም፣ አንዳንዴም ‹‹ያንተን የፍርድ ቤት ውሳኔ ይዘህ ሂድ፣ ዞር በል፣ ያዝና ጥፋ…›› የሚመስሉ ምላሾች አሉ ብለዋል፡፡

በምክር ቤት ፀድቀው የሚወጡ ሕጎች ለረዥም ጊዜ ያለ መቆየት ችግር፣ የፍርድ ቤቶች ተደራሽ አለመሆን፣ በክልሎችና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች መካከል የጠነከረ ትስስር አለመኖር፣ የዳኝነት ሥራ እንደ መሸጋገሪያ እንጂ እንደ ሙያ አለመቆጠርና ሠራተኞች ልምድ እየያዙ ወደ ጥብቅና ሲሄዱ ልምድ የሌላቸው ዳኝነት ውስጥ እንደሚቀሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቶች የሥልጠና አቅምና የልምድ ማፈላለጊያ እንጂ፣ ለረዥም ጊዜ መቆየት የማይችሉባቸው የሥራ ዘርፎች ናቸው ብለዋል፡፡

‹‹ዳኞችንና ፍርድ ቤቶችን አንበሳ ማድረግ አለብን፣ አስፈጻሚው ከሕግ ውጪ የሚሠራውን ካልተወና ልክ አይደለም ካልተባለ በስተቀር የዳኝነት ሥራ በጣም ችግር ውስጥ ነው፣ ገለልተኛ ልናደርገው ይገባል፤›› በማለት፣ አስፈጻሚው አካል ለሕግ ተጠያቂ ካልሆነ ፍርድ ቤቶች ከጫና ሊለወጡ የማይችሉ በመሆናቸው መንግሥት ቆም ብሎ ሊያስበብት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ለዳኞች ሥልጠና በሚሰጥበት ወቅት የርዕዮተ ዓለም ሳይሆን ለፍርድ ቤት ሥራ የሚረዳቸውን ክህሎት ለማስታጠቅ የሚያግዝ የአቅም መፍጠሪያ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ዘካርያስ (ፕሮፌሰር) ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ከፍርድ ቤት አውጥቶ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መስጠት ሕገ መንግሥቱ ችግር እንዳለበት ማሳያ በመሆኑ፣ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት መመለስ ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በጣም ይቸገርበታል፤ በልኩ እየሄደበትም አይደለም ብለዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ወንጀል በፈጸሙና በተፈጸመባቸው ወገኖች መካከል በሚኖር ክስ፣ በባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት ውሳኔ ካገኘ በኋላ፣ በሌላ ጊዜ ወይም ከተወሰነ ዓመት በኋላ በዘመናዊ ፍርድ ቤት ወንጀል ፈጸመ የተባለው ግለሰብ ላይ እንደ አዲስ ክስ መሥርቶ በወንጀል ለማስጠየቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ይህ የሕግ ክፍተት ለባህላዊና ለዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ተገቢውን ዕውቅና ካለመስጠት የመጣ በመሆኑ፣ በመካከላቸው መተላለፍና መጠላለፍ እንዳይኖር በተገቢው መንገድ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡

የመልካም አስተዳዳር ለአፍሪካና ምሥራቃዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ዘሪሁን  መሐመድ (ዶ/ር)፣ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች አሠራር ግልጽ ባለመሆኑ ምክንያት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የባህላዊ ፍትሕ ሥርዓትን እየተሸረሸረ ነው፡፡ በተወሰኑ ቦታዎች የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ከዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት መስጫ ተቋማት የባሰ ውድ መሆናቸውን፣ አልፎ አልፎም ለሽማግሌ አበል ተብሎ ከፍ ያለ ገንዘብ እንደሚጠየቅ አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ዘካሪያስ ኤርኮላ፣ ለአስፈጻሚው አካል ማድላት የሚለው ዕሳቤ በግልጽ በጥናት አለመብራራቱንና በፍርድ ቤቶች የአሠራር ችግር መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በጥናቱ የተነሱት ጉዳዮች ብዙዎቹ ወደፊት ሰፊ ጥናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፣ የተወሰኑት እንደ ቅሬታ ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...