Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግብርና ሚኒስቴር በአሲድ የተጠቃ የእርሻ መሬትን በሚፈለገው መጠን ለማከም ተቸግሬያለሁ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በጠቅላላ ከሚታረሰው 16 ሚሊዮን ሔክታር የእርሻ መሬት ውስጥ 3.7 ሚሊዮን ሔክታር በከፍተኛ አሲድ መጠቃቱን፣ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉን ለማከም መቸገሩን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ‹‹ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን›› (SAA)፣ በጅማ የታዳሽ ግብርና ፕሮጀክት ቀርፆ ለመሥራት ማሰቡን ይፋ ሲያደርግ ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ የአፈር ሀብት ልማት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሊሬ አብዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአገሪቱ ጠቅላላ መሬት 16 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው በእርሻ የሚሸፈን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሰባት ሚሊዮን ሔክታር በአሲዳማነት የተጠቃ ነው፡፡

ግብርና ሚኒስቴር በአሲዳማነት የተጠቃ መሬትን ለማከም የአሥር ዓመት ዕቅድ ይዞ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን፣ በዚህ ዓመት ከክልሎች ጋር መግባባት ላይ በመድረስ 200 ሺሕ ሔክታር መሬትን በኖራ ለማከም መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

አንድ ሔክታር መሬት ለማከም በአማካይ 30 ኩንታል ኖራ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ በአሲዳማነት የተጠቃ መሬትን ለማከም ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ሥራ አስከፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

በተለይ ኖራ የግብርና ግብዓት ሆኖ እንዲቀርብ ጥያቄ መቅረቡን ያስታወሱት አቶ ሊሬ፣ ጥያቄው ምላሽ ካገኘ በድጎማ ወይስ በብድር መልክ ነው የሚቀርበው የሚለው ላይ ውይይት እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡

በዚህ ዓመት በአሲድ የተጠቃን የእርሻ መሬት ለማከም ከትራንስፖርት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሒደት 5.2 ቢሊዮን ብር የሚጠይቅ መሆኑን፣ በአሲዳማነት የተጠቃ መሬትን ግማሽ ያህሉን ማከም እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

ከአሲዳማነት የተነሳ በርካታ ከምርት ውጪ የሆኑ መሬቶች እንደሚገኙ ያስረዱት ሥራ አስፈጻሚው፣ በችግሩ ሳቢያ ምርታማ በሆኑ አካባቢዎች ጭምር ምርት መቀነሱን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የግብርና ሚኒስቴር እንደ አንድ አማራጭ የወሰደው ለአርሶ አደሩ በቀላሉ ማከናወን የሚለውን አሠራር መዘርጋት ሲሆን፣ በዚህም የተቀናጀ የአፈር ጤንነትና ለምነትን የማሻሻል ሥራዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን አክለዋል፡፡

በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጠቃ የአሲዳማ መሬትን ለማከም በየዓመቱ እየተሠራ ቢሆንም፣ በሚፈለገው ልክ መፍትሔ ማምጣት አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡

አፍሪካ ውስጥ የአፈር ለምነት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰና በአሲዳማነት እየተጠቃ መሆኑን፣ የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፈንታሁን መንግሥቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የአፈርን ጤንነትና ለምነት አሻሽሎ ምርታማነትን ለመጨመር ታዳሽ ግብርናን መከተል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ይህም የአየር ንብረት ለወጥ የሚያመጣውን ችግር ለመቋቋም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

በዚህ መሠረት የታዳሽ ግብርና ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሚደረገው በኢትዮጵያና በናይጄሪያ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ፕሮጀክቱም በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚሆነው በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳና ሻሸመኔ በሚባል ቀበሌ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱም ለሦስት ዓመታት እንደሚቆይና ሦስት ተቋማት በጋራ ጥምረት ፈጥረው እንደሚሠሩ፣ ሥራውም ዕውን የሚሆነው ከጃፓን መንግሥት በተገኘ አንድ ሚሊዮን ዶላር ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከአምስት ሺሕ በላይ አርሶ አደሮችን ጨምሮ ከ100 ሺሕ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረጋል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ፈንታሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን ከ40 እስከ 60 በመቶ ማሳደግ የሚችሉበት ዕድል የሚፈጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የአፈር ለምነትን በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ የጥራጥሬ ሰብሎችን አርሶ አደሮች መዝራት እንዳለባቸው፣ እነዚህ ሰብሎች እንደ ማዳበሪያነት እንደሚያገለግሉ አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ በየዓመቱ በቆሎ፣ ስንዴና ጤፍ መዝራት የመሬቱ ለምነት እንዲጎዳና አሲዳማ እንዲሆን እንደሚያደርገውና ምርቶቹ ደርሰው ከታጨዱ በኋላ የሚቀረውን ተረፈ ምርት ለከብቶች መኖነት አርሶ አደሩ ስለሚወስደው፣ የመሬቱ ለምነት በከፍተኛ መጠን ሊቀንስ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች