Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበትግራይ ክልል ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ ለደረሰ ውድመት የካሳ ጥያቄ ሊቀርብ ነው

በትግራይ ክልል ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ ለደረሰ ውድመት የካሳ ጥያቄ ሊቀርብ ነው

ቀን:

በናርዶስ ዮሴፍ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያቋቋመው ‹‹በትግራይ የተፈጸመ ዘር ማፅዳት አጣሪ ኮሚሽን››፣ በክልሉ የማይክሮ ፋይናንስ ላይ ለደረሰ ውድመት የካሳ ጥያቄ ሊያቀርብ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ የካሳ ጥያቄ ያቀረበላቸው ደደቢትና አደዳይ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ናቸው፡፡

በትግራይ ክልል 86 ወረዳዎች በ112 ንዑስ ቅርንጫፎችና በ12 ዋና ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ሕንፃዎች ላይ ከደረሰው ውድመት፣ 52 በመቶው በኤርትራ ሠራዊት እንደሆነ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኮምፒዩተሮችንና የቢሮ ማተሚያ ማሽኖችን ጨምሮ በዋናነት ደግሞ ተቋማቱን የሚያስተሳስረው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ላይ ከደረሰው ውድመት 40 በመቶው በኤርትራ ሠራዊት፣ እንዲሁም 30 በመቶ ደግሞ በፌዴራል መንግሥት ኃይሎች የተፈጸመ ነው ሲል፣ ኮሚሽኑ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ባቀረበው ጥናት ማስታወቁን አስረድቷል።

በኮሚሽኑ የፋይናንስ ጉዳዩች ጥናት ክፍል አባልና የመቐለ ዮኒቨርሲቲ መምህር አረጋዊ ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ‹‹ስናጠና ማነው ጉዳት ያደረሰባችሁ? ሕንፃዎቻችሁን ማን አወደመ ብለን እያንዳንዳቸውን ጠይቀናል። አልፎ አልፎ ‹‹የከተማ ወንበዴ ነው ንብረቴን ያወደመው የሚል ምላሽም አግኝተናል። በሌላ በኩል ንብረቴን ያወደመው የኤርትራ ሠራዊት ነው፣ የፌዴራል ሠራዊት ነው ያሉ አሉ። አላውቅም ያሉንም ነበሩ፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

በመቐለ፣ በአዲግራት፣ በአክሱም፣ በሽራሮ፣ በዓድዋ፣ በማይጨው፣ በአላማጣ ከሚገኙ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጽሕፈት ቤቶች 86 በመቶ ያህሉ ‹‹አሉ ብሎ ለመጥቀስ በሚከብድ ሁኔታ ወድመዋል፤›› ብለው፣ ‹‹ከተፈጸሙ ዝርፊያዎች 66 በመቶ በመሣሪያ ጥቃት የታገዙ፣ 17 በመቶው ሆን ተብለው በተፈጸሙ ቃጠሎዎች ወድመዋል፤›› ብለዋል።

ጦርነቱ በተከሰተበት ወቅት በሕንፃዎቻቸው፣ በንብረቶቻቸው፣ ተቀምጦ በነበረ ገንዘብና በሰነዶቻቸው ላይ ሙሉ ለሙሉ ውድመት የደረሰባቸው በተምቤን፣ በአዲግራት ፋፂ፣ በሽራሮና በአዲአሮ በሚገኙ ዋና ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ላይ ነው በማለት አረጋዊ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

በባድመ፣ በዛላምበሳ፣ በደደቢትና በሽረ በሚገኙ ቅርንጫፍና ንዑስ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች 74 በመቶ የሚሆኑት ከግማሽ በላይ የቃጠሎ ውድመት እንደደረሰባቸው አክለዋል።

በሁሉም የተቋማቱ ጽሕፈት ቤቶች በነበሩ አላቂና አላቂ ያልሆኑ የቢሮ መገልገያ ዕቃዎች ላይ ተፈጽሟል በተባለው ውድመት 74 በመቶው በስርቆት፣ አሥር በመቶው በቃጠሎ፣ እንዲሁም ስምንት በመቶ ሆን ተብሎ ባልተፈጸመ ጥቃት የወደመ (Collateral Damage) ነው ሲሉ አረጋዊ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ በአጠቃላይ ከደረሰው ውድመት 43 በመቶው ሆን ተብሎ በከባድ የጦር መሣሪያ ድብደባ፣ 38 በመቶው ደግሞ ሆን ተብሎ በተፈጸመ ዝርፊያ የተፈጸመ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የፋይናንስ ተቋማት ላይ በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት በተመለከተ ባደረገው ጥናት መረጃ ስብሰባ ሒደት የመጀመሪያው ዙር እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ድረስ እንደነበረ፣ በወቅቱ ጦርነት እንደ አዲስ በመቀስቀሱ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማግሥት በመቀጠል በሁለተኛ ዙር እስከ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. በተሰበሰበ መረጃ ውጤት የተጠናቀረ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በጥናቱ ሁለተኛ ክፍል በፋይናንስ ተቋማቱ ላይ በጦርነቱ በቀጥታ በንብረቶች ላይ ከደረሰ ውድመት ባሻገር፣ አገልግሎት ባለመሰጠቱ ሊገኝ ይችል የነበረ ገቢንና አሁን የወደመውን ለመተካትና ሥራ ለማስጀመር የሚያስፈልገውን ወጪ ጉዳዮችን ለመመርመር የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱን 6,500 ተበዳሪዎች በማነጋገር መረጃ መሰብሰቡን ኮሚሽኑ ገልጿል።

አረጋዊ (ዶ/ር)፣ ‹‹ተቋማቱ ገቢያቸው ከብድር የሚያገኙት ወለድ እንደመሆኑ፣ ቀደም ሲል ያበደሩትን ብድር አሁን መልሰው ማግኘት ይችላሉ ወይ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ወሳኝ ነው፤›› ብለዋል።

በዚህም በደንበኞች በኩል ‹ተቋማቱ ያበደሩን ገንዘብ የራሳቸው እንዳልሆነና ከማኅበረሰቡ በቁጠባ የሰበሰቡት እንደሆነ ስለምናውቅ መመለስ እንዳለብን እንገነዘባለን፡፡ ነገር ግን አሁን ተፈናቅለን በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የተጠለልን አለን፡፡ ለ17 ወራት ደመወዝ ያልተከፈለን አለን፡፡ እኛም ያለፉትን ዓመታት እንደ እናንተ በኪሳራ ስላሳለፍን መክፈል አንችልም› በማለት ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅድሚያ በጦርነቱ ጊዜ የተሰበሰበ የብድር ወለድ መጠን ክፍያ እንዲቀርላቸው፣ በማስከተልም ንግዳቸውን ለመጀመር የሚያስችል ሥራ እንደ ገና የሚጀምሩበት አዲስ ተጨማሪ ብድር እንዲቀርብላቸው፣ እንዲሁም ያለባቸውን ብድር የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው መጠየቃቸው ተገልጿል።

ኮሚሽኑ በጥናቱ መደምደሚያ ሁለቱ የፋይናንስ ተቋማት እንዲያገግሙና የደንበኞቻቸውን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል ሁኔታ ላይ እንዲገኙ ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል ብሏል።

‹‹ማን ይክሳል? የሚለው በሕግም የሚወሰን መሆኑ እንዳለ ሆኖ በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩ የፌዴራል መንግሥት ሠራዊት፣ የኤርትራ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ኃይሎችና ሌሎች በትግራይ ክልል ፋይናንስ ተቋማት ላይ በተፈጸሙ ውድመቶች ድርሻቸው ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ጥናት አጠናቀን ለጊዜያዊ አስተዳደሩ አቅርበናል፤›› ሲሉ አረጋዊ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

እንዲሁም በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቱ ላይ የደረሰውን ውድመት መጠን በገንዘብ ሲገመትና ካሳ መክፈል ያለባቸው አካላት እያንዳንዳቸው ምን ያህል ይፈለግባቸዋል ተብሎ ተጠያቂ እንደሚደረጉ በጥናቱ ተካቶ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ መቅረቡን ገልጸው፣ ለመገናኛ ብዙኃን ለማሳወቅ ኃላፊነት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡

በኮሚሽኑ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል ደረሱ ስለተባሉ ውድመቶች ከሚደረጉ ጥናቶች፣ በፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተደረገው ጥናት እስከ ታኅሳስ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ቀርቧል ብለዋል።

ሪፖርተር ይህን መረጃ ለማጣራት ለጊዜያዊ አስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ረዳዲ ሃለፎም በተደጋጋሚ በስልክ ጥሪና በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ስልካቸውን ዝግ በማድረግ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...