Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አራት ባንኮች የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ ለመጀመር ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እየተጠባበቁ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በቴሌ ብር ለደንበኞቻቸው ለማቅረብ የሚያስችለውን የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ ሥርዓት ለመጠቀም፣ አራት ባንኮች የብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በቴሌ ብር ለደንበኞቻቸው ለማቅረብ የሚያስችሉ የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ (Digital Financial Market Place) እና የዲጂታል አክሲዮን ግዥና ሽያጭ (Digital Share Sell/Bay) አገልግሎቶችን፣ ታኅሳስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በይፋ አስጀምሯል፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ አገልግሎት ሁሉንም የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን፣ ባንኮች ይህንኑ እንዲያውቁ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ፕላትፎርሙን ለመጠቀም ኢትዮ ቴሌኮም ከአራት ባንኮች ጋር ውይይት አድርጎ ስምምነት ላይ መድረሱን፣ ባንኮቹም የብሔራዊ ባንክን ፈቃድ እየተጠባበቁ መሆናቸውን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል፡፡   

የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ ባንኮች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ፣ በአገር ደረጃ በብሔራዊ ባንክ በተያዘው የብሔራዊ ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ እ.ኤ.አ. በ2025 ብቻ 70 በመቶ ዜጎች በፋይናንስ እንዲካተቱ ለማስቻል፣ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ባንኮች፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን የቴክኖሎጂ አቅም ተጠቅመው የፋይናንስ አገልግሎታቸውን ተደራሽና አካታች ለማድረግ፣ ቀልጣፋ አገልግሎት በተመጣጠነ ዋጋ ማቅረብ የሚያስችልላቸውን የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ መፍትሔ ቀርቧል ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ የዲጂታል አክሲዮን የግዥና የመሸጫ ፕላትፎርም ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፣ ፈቃድ የተሰጣቸው የቢዝነስ ተቋማት የአክሲዮን ግዥም ሆነ የሽያጭ ሒደታቸውን ዲጂታል ማድረግ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የሚያከናወኑበት፣ እንዲሁም አክሲዮናቸውን ለማኅበረሰቡ በስፋትና በቀላሉ ተደራሽ የሚያደርጉበት ዕድል መመቻቸቱ ተጠቁሟል፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ አገልግሎት ለመጠቀም ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እየተጠባበቁ ያሉት አሐዱ፣ እናትና አዋሽ ባንኮች መሆናቸውንና አገልግሎቱን ሌሎች ባንኮች እንዲጠቀሙ ከባንኮች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ወ/ሪት ፍሬሕይወት አክለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከዚህ ቀደም ከዳሸን ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ በቀረፀው የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት፣ ከ3.6 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ከብድር አገልግሎት ተደራሽ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ ገበያ ሥርዓት ባንኮች ምንም ዓይነት የካፒታል ኢንቨስትመንት ማድረግ ሳይጠበቅባቸው፣ ኢትዮ ቴሌኮም በገነባው ፕላትፎርም ተጠቅመው የፋይናንስ አገልግሎቶቻቸውን ከ46 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ የቴሌ ብር ደንበኞች በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ የሚችሉበት አገልግሎት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ያዋጣናል በሚሉት መንገድ ለደንበኞቻቸው ሽያጫቸውን ወይም አገልግሎቶቻቸውን ማቅረብ የሚችሉበት ፕላትፎርም መሆኑን፣ የኢትዮ ቴሌኮም የከስተመር ኤክስፔሪየንስና ኳሊቲ ማኔጅመንት ቺፍ ኦፊሰር አቶ ሰለሞን አበራ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን እንዴት ተግባራዊ ይደረጋል የሚለውን በተመለከተ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከባንኮች ጋር የራሱ የሆነ ስምምነት እንደሚያደርግ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎቱን ይጠቀማሉ የሚለው መረጃ እንደማይታወቅ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል አገልግሎቱን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከባንኮች በተጨማሪ ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር ጭምር ውይይት እየተደረገ እንደሆነ፣ በቅርቡ በርካታ ተቋማት በዚህ ፕላትፎርም እንዲጠቀሙ የሚደረግበት አሠራር ይፈጠራል ብለዋል፡፡

የቴሌ ብር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት አስተማማኝና ቀላል መሆኑንና በተለይ የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ አገልግሎት አቅራቢንና ተጠቃሚን ለማገናኘት፣ ሥራ ፈጣሪነትን፣ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለማበረታታትና ዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት የሚያደረገውን አገራዊ ጥረት በማፋጠን ረገድ ኢትዮ ቴሌኮም ትልቁን ድርሻ እየተወጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ከ46 ሚሊዮን በላይ የቴሌ ብር ደንበኞች እንዳሉት፣ 1.6 ትሪሊዮን ብር በቴሌ ብር መሰብሰብ መቻሉ ተነግሯል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች