Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፀደይ ባንክ አጠቃላይ ሀብቱን 55 ቢሊዮን ብር ማድረሱን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከብድርና ቁጠባ ተቋምነት ወደ ባንክ እንዲያድጉ ከተፈቀደላቸው ስድስት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ፀደይ ባንክ፣ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን ከ55 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉንና የደንበኞቹም ቁጥርም ከ13 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡

ባንኩ የሞባይል ባንክ አገልግሎቱን በይፋ መጀመሩን ባስታወቀበት ዝግጅት ላይ እንዳመለከተው፣ የባንኩ የሀብት መጠን ዕድገት በማሳየት 55 ቢሊዮን ብር ለመድረስ ካስቻሉት፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለይ በአማራ ክልል በራሱ ባለቤነት የተመዘገቡ 246 ሕንፃዎችና ቤቶች ያሉት መሆኑን ነው፡፡ ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት የነበረው ጠቅላላ የሀብት መጠን 38.8 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ከተጠቀሱት ሕንፃዎቹ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ከምድር በላይ 37 ወለሎች ያሉት የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በአማራ ክልልም የራሱ የሆኑ ሕንፃዎችና ቤቶች እንዳሉት ታውቋል፡፡

ይህም በመሆኑ ባንኩ ከሌሎች ባንኮች በተለየ አሁን ላይ አገልግሎት ከሚሰጡት 530 ቅርንጨፎች ውስጥ 246 የሚሆኑት ቅርንጫፎች በራሱ ሕንፃዎችና ቤቶች የሚገለገልባቸው ናቸው፡፡

ፀደይ ባንክ በቅርቡ ወደ ባንክ ከተሸጋገሩ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት መካከል አንዱ በመሆኑ፣ የማክሮ ፋይናንስ ተቋም ሆኖ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ያፈራቸውን ደንበኞች ይዞ በመጓዝ፣ አሁን ላይ የደንበኞቹ ቁጥር 13 ሚሊዮን መድረሱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ወደ ባንክ ከተሻገረ በኋላ፣ በመደበኛና የማክሮ ፋይናንስ የባንክ አገልግሎት ያፈራቸው ደንበኞች ከ1.6 ሚሊዮን በላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት የነበሩት ደንበኞች ቁጥር 11 ሚሊዮን፣ ከእነዚህ ደንበኞች ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት የባንኩ ተበዳሪዎች ስለመሆናቸው መጠቀሱ አይዘነጋም፡፡  

ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ ያደጉ ስድስቱ የብድርና የቁጠባ ተቋማት፣ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት መደበኛውን የባንክ አገልግሎትና የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት አጣምረው መሥራት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ፣ የደንበኞቻቸው ቁጥርም ከሌሎች መደበኛ ባንኮች የተለየ በቁጥር ከፍ ሊል ችሏል፡፡

ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አድጎ ሥራ የጀመረው መስከረም 2015 ዓ.ም. እንደነበር አይዘነጋም፡፡  

ፀደይ ባንክ አሁን በጣምራ የሚሠራውን የባንክ አገልግሎት ለማስፋት፣ ለደንበኞች ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት፣ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይም ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የሞባይል ባንክ አገልግሎት በይፋ ማስጀመሩ እንደ ምሳሌ ተጠቅሰዋል፡፡ ተወዳዳሪና አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ቴክኖሎጂ አስፈላጊ ስለመሆኑ የጠቀሱት የባንኩ ፐሬዚዳንት አቶ መኮንን የለውምወሰን፣ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ለማስፋት ተጨማሪ አገልግሎቶችን በማከል የሚቀጥል ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡   

ፀደይ ባንክ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በሚል መጠሪያ ስም የጀመረው ከ20 ዓመታት በፊት ሲሆን፣ በወቅቱ ሥራውን ሲጀምር በሦስት ሚሊዮን ብር ካፒታል፣ በ40 ሠራተኞች፣ በስድስት ቅርንጫፎችና 1,200 ደንበኞችን በመያዝ እንደነበር በባንኩ ምሥረታ ላይ የተጠቀሰው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሰሞኑን ባስታወቀው መረጃ ደግሞ ካፒታሉን ወደ 12 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉንና የተከፈለ ካፒታሉን ደግሞ 9.83 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 7.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የሠራተኞቹም ቁጥር ከሦስት ሺሕ በላይ ማድረስ መቻሉ ተገልጿል፡፡.       

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች