Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ብቻ 1.42 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ብቻ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ነው የተባለ የተጣራ 1.42 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡ ታወቀ፡፡ 

ከባንኩ የ2015 ሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ የተጣራ 1.42 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ90.5 በመቶ ብልጫ እንዳለው ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ 

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከታክስ በኋላ የተገኘው ትርፍ 746.7 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ግን ከወለድና ነፃ ባንክ አገልግሎቱ ብቻ ያገኘው ትርፍ በአገሪቱ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት በአንድ ዓመት ውስጥ የተገኘ ከፍተኛ ትርፍ በመሆን የሚጠቀስ ነው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት አራት ሙሉ ለሙሉና ከ12 በላይ በመስኮት ደረጃ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ያሉ ቢሆንም፣ እስካሁን በዚህ ደረጃ በአንድ ዓመት ያተረፈ ባንክ እንደሌለ ሪፖርተር ካሰባሰበው መረጃ ለመረዳት ችሏል፡፡ 

ባንኩ በ2015 ሒሳብ ዓመት ላገኘው አጠቃላይ ትርፍም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ 19 በመቶ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ይህንን ያህል መጠን ያለው ትርፍ ማስመዝገብ የቻለው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚያሰባስበውን ተቀማጭ ገንዘብ በቶሎ ለብድር በማዋሉ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

ከባንኩ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለውም፣ በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ የሰጠው ብድር አጠቃላይ መጠን 16.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በ2015 ሒሳብ ዓመት ብቻ በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ሦስት ቢሊዮን ብር ብድር አቅርቧል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ በየዓመቱ ለብድር የሚውለው የገንዘብ መጠን እያደገ መሄዱ ከዘርፉ የሚያገኘውን ትርፍ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ባንኩ በ2015 ሒሳብ ዓመት ያገኘው አጠቃላይ ትርፍ በ19 በመቶ ዕድገት የታየበት ለዚህም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ደግሞ 19.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ ሪፖርት ያመለክታል። ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ውጤታማ የሚባል አፈጻጸም ሊያስመዘግብ የቻለበት ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ከወለድ ነፃ አስቀማጮችን ብዛት በማሳደግ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ በመጨመሩ ነው፡፡ የባንኩ 2015 የሒሳብ ዓመት ሪፖርት እንደሚሳየውም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ 740 ሺሕ አዲስ ቆጣቢዎችን በማፍራት አጠቃላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ብዛት 3.03 ሚሊዮን ማድረስ ችሏል።

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ባንኩ የደረሰበት የቆጣቢዎች ቁጥርም ባንኩ ካሉት ጠቅላላ አስቀማጮች ቁጥር 27 በመቶ ድርሻ ይዟል። ይህም ባንኩን በመደበኛውም ሆነ በአጠቃላይ ከወለድ ነፃ የአስቀማጮች ቁጥር ከግል ባንኮች በመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ እንደሚያደርገው ከባንኩ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡ 

በ2015 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡን በ20.13 በመቶ ማሳደግ የቻለውን የኦሮሚያ የኅበረት ሥራ ባንክ፣ በዓመቱ መጨረሻ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 116.2 ቢሊዮን ብር አድርሷል። በሒሳብ ዓመቱ ብቻ ያሰባሰበው አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ 19.48 ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ፍቅሩ ደክሲሳ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ 

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ የባንኩን ሀብት ከማጠናከር አኳያ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በቅርቡ በ633 ሚሊዮን ብር ገንብቶ ያስመረቀው የመሸጋገሪያ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስም አጠቃላይ የሀብት መጠኑን በ22.4 በመቶ በማሳደግ 140.3 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ባንኩ በአዲስ አበባ በሰንጋ ተራ፣ በካሳንቺስ፣ በሻሸመኔ የሕንፃ ግንባታ ለማከናወን ቦታ መረከቡን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል አካባቢ በተረከበው 46 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ 65 ወለሎች የሚኖሩት ሕንፃ ለመገንባት ማቀዱ ታውቋል።

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከ17.17 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህ የገቢ መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ47 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው፡፡ የባንኩ ወጪ ደግሞ በ55.5 በመቶ በመጨመር በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 14.32 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም ታውቋል፡፡ 

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በ2015 መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉን በ2.2 ቢሊዮን ብር በመጨመር 10.02 ብር አደርሷል፡፡ ባንኩ ከሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ 34.4 በመቶ ለአገር ውስጥ ንግድ፣ 27.4 በመቶ ለዓለም አቀፍ ንግድ 17 በመቶ ለማኑፋክቸሪንግ ነው፡፡ 

ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይቷል ተብሎ የሚጠቀሰው፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 377.75 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት በ13.8 በመቶ ዝቅ ያለ መሆኑም ታውቋል፡፡ ለውጭ ምንዛሪ ገቢ መቀነስ በዓለም የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በተለይም የቡና ዋጋ አለመረጋጋት በሒሳብ ዓመቱ የወጪ ንግድ ገቢ መቀነሱ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ በተለይ ባንኩ ከፍተኛ መጠን ያለውን ቡና በመላክ መታወኩ ከኮፕሬቲቮችና ሌሎች ላኪዎችን በደንበኛነት ከመያዙ አንፃር፣ በቡና ዋጋ ላይ የታየው ያለመረጋጋት ወይም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች