Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳ ባንክ የሰሜኑ ጦርነት ካደረሰበት ተፅዕኖ በመውጣት የተጣራ 489 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰሜን ጦርነት ምክንያት ለተከታታይ ዓመታት በባንኩ አጠቃላይ አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ ያረፈበት አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት የትርፍ ምጣኔውን በማሳደግ ከታክስ በኋላ 489.5 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡ 

ባንኩ የ2015 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ጦርነቱ ያሳረፈበት ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም የተለያዩ የማሻሻያ ዕርምጃዎች በመውሰድ አጠቃላይ አፈጻጸሙን በማሻሻል በ2015 የሒሳብ ዓመት የትርፍ ምጣኔውን ማሳደግ ችሏል፡፡ ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 747.1 ሚሊዮን ብር ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ140 በመቶ ብልጫ እንዳለው የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዓለም አስፋው ለጠቅላላ ጉባዔው ባቀረቡት ሪፖርት አሳውቀዋል፡፡ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 311 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በኋላ ያገኘው ትርፍም ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ከ221 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ 

የስሜኑ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 781 ሚሊዮን ብር አትርፎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት ግን ይህ የትርፍ መጠን ወደ 414 ሚሊዮን ወርደ ሲሆን በ2014 የሒሳብ ዓመት ደግሞ የበለጠ በማሽቆልቆል 311 ሚሊዮን ብር ሚሊዮን ብር ደርሶ ነበር። የባንኩ ትርፍ በዚህን ያህል ደረጃ ዝቅ ለማለቱ ዋነኛ ምክንያት የባንኩ አብላጫ ተበዳሪዎች በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ የነበሩ በመሆናቸው ብድሩን ለማስመለስ ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመግባቱ ነው፡፡ 

በዚህም ምክንያት ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት ካገኘው ትርፍ ላይ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው የባንኩ አንድ አክሲዮን ያገኘው የትርፍ ድርሻ 2.6 ብር ብቻ ነበር፡፡ በ2015 የሒሳብ ዓመት ግን የባንኩ ትርፋማነት በመሻሻሉ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን 187 ብር የትርፍ ድርሻ ማግኘት ችሏል።

የባንኩ ጠቅላላ ሀብት በ2015 መጨረሻ ላይ 35.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን የሚገልጸው ባንኩ ከዚህም ውስጥ ለደንበኞች የተሰጡ ብድሮች ከጠቅላላው ሀብት 75 በመቶውን ሲይዝ፣ የብሔራዊ ባንክ ሰነድ ግዥ፣ ጥሬ ገንዘብና ገንዘብ አከል ሀብቶቹ ደግሞ 7.9 እና 11.0 በመቶውን ድርሻ መያዛቸው ታውቋል።

ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ማሳደግ እንደቻለም የሥራ አፈጻፈም ሪፖርቱ ያስረዳል። በዚህም መሠረት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 27.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ1.3 ቢሊዮን ብር ወይም የ5.3 በመቶ  ብልጫ እንዳለው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

የባንኩን ጠቅላላ የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም 1.6 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉን የሚያመለክተው ይኸው ሪፖርት ይህም ዓመት በ11 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ 

የባንኩ የብድር ክምችቱም 26.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ12 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ባንኩ የታመሙ ብድሮችን ወደ ጤነኛ ብድር ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን፣ በዚህም የተበላሸ ብድር መጠኑን ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ባንኩ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የረዥምና የአጭር ጊዜ ዕቅዶችን በመንደፍ የታመሙ ብድሮችን ወደ መደበኛ ብድር ለመመለስ አሁንም ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። በግጭቱ ምክንያት የባንኩ ተበዳሪዎች ከፍተኛ ጉዳት ያጋጠማቸው መሆኑን፣ በዚህም ምክንያት ብድራቸውን መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ባንኩ የሰጠውን ብድር ለማስመለስም ሆነ ተጨማሪ ሀብት ለማሰባሰብ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ መቆየቱን የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አስረድተዋል።

‹‹በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል አንፃራዊ መረጋጋት መፈጠሩን ተከትሎ ተዘግተው የቆዩት የባንኩ ቅርንጫፎችን መልሶ በማቋቋም ወደ ሥራ ለማስገባት የተደረገው ጥረት በባንካችን ላይ ከፍተኛ ወጪ አስከትሏል›› ያሉት ቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ከዚህም በላይ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የቆዩት የባንኩ አስቀማጭ ደንበኞች የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ምክንያት ባንኩ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወጪ እንደሆነበት ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እስኪያጋጥመው ድረስ ፈተና ላይ ወድቆ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ የብድር ተመላሽ ገንዘብ በወቅቱ ማሰባሰብ ባለመቻሉ ምክንያትም የባንኩ ጤነኛ ያልሆኑ ብድሮች መጠን በከፍተኛ ደረጃ የጨመረበት ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 4.7 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ መሰብሰብ የቻለ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸሙ ጋር ሲነፃፀር የ35 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከተገኘው ጠቅላላ ገቢ ውስጥ ከብድር ወለድ የተገኘው ገቢ የ89 በመቶ ድርሻ በመያዝ ለዕድገቱ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን፣ ቀሪው ወለድ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች የተገኘ ነው።

የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ማጠናቀቂያ ላይ የባንኩ አጠቃላይ የሠራተኞች ቁጥር 5,667 የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 50 በመቶ (2,846) ቋሚ ሠራተኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 50 በመቶ (2,821) ጊዜያዊ ሠራተኞች ናቸው፡፡ 

ባንኩ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በ2015 የሒሳብ ዓመት አሥር ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 288 አድርሷል፡፡ የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ወቅት የተከለ ካፒታሉ 2.62 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች