Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዕሪታ!

ከአውቶቡስ ተራ ወደ መገናኛ ጉዞ ሊጀመር ነው፡፡ ታክሲ ተራው ዙሪያውን በተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎች ተወሯል። የወያሎች ጩኸት ጥርት ካለው የታኅሳስ ሰማይ፣ በውርጭ አርጩሜው ከሚጋረፈው ቀዝቃዛ አየር ተቃርኖ ሲታይ አንዳች ተስፋ በልቦና ይረጫል። እዚያ ከሸቀጣ ሸቀጡ ሠፈር ገሚሱ ዓይቶ ለማለፍ ብቻ ጊዜውን ሰውቶ ቆሟል። አንዳንዱ እንዳቅሚቲ ያለችውን እንደተሸበለለች እያወጣ ቆጥሮ ይከፍላል። ምኞትና ኑሮው ሩቅ ለሩቅ ሆነው ፍዳውን የሚያየው መንገደኛ ቀላል አልነበረም፡፡ የያዘው ዋጋ አጥቶበት የለበሰው ላዩ ላይ ነትቦ፣ የሰልባጅ ሸቀጥ የሕልም እንጀራ እየሆነበት ዓይቶ እዳላየ ሆኖ የሚያልፈው ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሲያስተውሉት ቅስም እየሰበረ ከንፈር ያስመጥጣል። የሆነው ቢሆንም ዕድል ፈንታውን የማታ የማታ እንደማያጣ ሳይጠራጠር የሚሮጠው ይኸው ሰፊው ሕዝብ ነው። ብልኃት የሌለው ሰፊነት ድል በድል ባያደርግም አዎ ዛሬም ረጅም ጎዳና ተራማጆች ነን፡፡ የግድ ነው! 

ታክሲው ቢሞላም ወያላው ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡ ተሳፋሪዎች እርስ በርስ እየተያዩ ‹ወያላው የት ቢሄድ ነው የጠፋው?› ይባባላሉ። አንዱ፣ ‹‹ጊዜን ዋጋ ከማሳጣት ቀጥሎ ሕይወት እንዴት ዋጋ እያጣች እንደምትሄድ አይገባንም…›› እያለ ትንታኔ ለማቅረብ ይሞክራል። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹አይ እኛ? እኛ እኮ በጊዜ ከቀለድነው ዘመን አንፃር እጃችን ላይ ሰዓት ማሰር የማይገባን ነን…›› ይላል፣ ይቀልዳል፡፡ ከኋላ መቀመጫ አካባቢ መነሻውን ያልሰማነው ጭውውት እንዲህ ይደመጣል። ‹‹… አንተ እሱን ትላለህ? ጊዜንና ዕድሜን ከመናቃችን የተነሳ የትውልድ ቀናችንን የምናውቅ ስንቶቻችን ነን? እንዲሁ ጀምረን እንዲሁ ስንጨርስ አይደል እንዴ የኖርነው?›› እያለ አንድ ጎልማሳ ገብስማ ፀጉሩን አጠገቡ ለተቀመጠ ተሳፋሪ ያሳየዋል። ወግ ተጀመረ ማለት ነው!

ነገርን ነገር ሲቆሰቁሰው ግሎ ሲቀጣጠል ወያላው አሁንም ብቅ ማለት አልቻለም ነበር። ‹‹ሾፌር ምንድነው የሚሻለን?›› ትጠይቃለች ጋቢና የተቀመጠች ወጣት። ‹‹እኔም እኮ ግራ ገባኝ…›› እያለ ሾፌሩ ወርዶ ለመፈለግ በሩን ከፈተ። ‹‹ይገርማል ሕይወታችን የዘገዩ ነገሮችንና ሰዎችን በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይቅር?›› ትላለች መሀል ወንበር የተቀመጠች ወይዘሮ። አጠገቧ ያለ ወጣት፣ ‹‹እንዴት?›› ብሎ ጥያቄ አቀረበላት። ‹‹በቃ ለታክሲ ወረፋ ጥበቃ፣ ጉዳይ ለማስጨረስ ወረፋ ጥበቃ፣ የትዳር አጋር ለማግኘት አመልና ፀባይ ስናጣራ ዓመታት ጥበቃ፣ ሸማችና ዳቦ ቤት ወረፋ ጥበቃ…››  እያለች ስትቀጥል በቀላሉ የማናገኘውና ዘግይቶ የሚያዘገየን ነገር ብዛቱን ማስላት ጀመርን። ‹‹በይሆናል ተስፋ ደግ ቀን ስንጠብቅ የባከነው ዕድሜስ?›› እያለ የሚቆጨው ደግሞ በአንድ ወገን ጥርሱን ነክሶ ተቀምጧል። በጥበቃ ብቻ ሳይኖሩ ያለፉ ቀናት  ስንት ይሆኑ ግን!

ያዘገየንን ሰዓት ሊክሰን ሾፌራችን ታክሲዋን ያክለፈልፋታል። መሀል መቀመጫ ከአንዲት ቀዘባ ጎን የተቀመጡ አዛውንት ስለኑሯቸው ይተርካሉ። ‹‹አሄሄ… ደከምኩ ልጄ፣ ከጎረምሳ እኩል ሮጦ መሸመት እያቃተኝ ነው…›› ይላሉ። ‹‹ኧረ ደህና ነዎት እንዲያ አይበሉ…›› ትላለች ቆንጂት ለማለት ያህል። ‹‹እንጃ ኑሮም እንደምታይው ነው…›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹…ለነገሩ ምኑን ታይዋለሽ እንዲህ አምሮብሽ?›› ሲሉ ትችት ቢጤ ጀማመሯት። ‹‹ማለት?›› አለቻቸው ክው ብላ። ‹‹ዘንድሮ እኮ የደላቸው ስለጎደለባቸው የሚያውቁት ነገር ቢኖር ለአፍ አመል የተቀነባበረ ዕውቀት ብቻ ሆኗል። ከቡና ጨዋታ ላለመገለል የሚታወቅ ዕውቀትና ነገሮችን ለመቀየር የሚታወቅ ዕውቀት ፍፁም ይለያያል…›› አሉዋት። ‹‹ቢሆንም ሁሉም ሰው እንደ ራሱ ጎጆ የራሱን ችግር ተሸካሚ ነው…›› ብላ ራሷን ለመከላከል ተናገረች። አዛውንቱ ግን ዋዛ አይመስሉም፣ ‹‹የደሃ ወዳጁ ደሃ ብቻ ነዋ። እስኪ አሁን አንቺ ስንት ደሃ ጓደኞች አሉሽ?›› ሲሏት በግርምት ትመለከታቸው ጀመር። የአዛውንቱ ጠጣርና ሰብዕናን የሚፈታተኑ ቃላት ሲቀጥሉ፣ ቆንጂት በዝምታ ከማዳመጥ በቀር ምርጫ አልነበራትም። ምን ይደረግ ታዲያ!

‹‹እስኪ ይታያችሁ ማንም ለራሱ በማያንስበት በቀደመው ጊዜ ስንረዳዳና ስንከባበር እንዳልኖርን፣ የአንዱ ላይ መውጣት ለሌሎች ቁልቁል መውረድ በሆነበት በዚህ ጊዜ ጀርባ መሳጣጣታችን አያሳዝንም? እግዚኦ ክፋት። አስታዋሽ አጥተው በየመንገዱ የወደቁትን ልናስብ ቀርቶ ዘመድ ከዘመዱ የማይፈላለግበት ዘመን ይምጣ? ፈጣሪ ምን አድርገነው ግን አንዲት እንጀራ መቁረስ ፍዳ በሆነበት ጊዜ ዕድሜያችንን ያበዛው?›› ሲሉ አማረሩ። ምሬታቸው ሥር መስደዱን እያየ ማንም ለማፅናናት አልተቻለውም። የአዛውንቱን ቃላት ከማብሰልሰልም በራሱ የኑሮ መረብ ተጠምዶ እያየ የማያየው፣ ሰምቶ የማይሰማው ጥቂት አይደለም። የሆዱ ነገር ሆዱን እየቆረጠው ለሞራል እሴቶች ሞራል ያጣውም ጥቂት አይባልም።  የአንዳንዱ መንገድ መጨረሻ ያስፈራል!

ወያላችን ሒሳቡን ሰብስቦ መልስ በመመለስ ተጠምዷል። አንዳንዱ አፍንጫውን ይዞ መልስ ሲቀበለው፣ ለአንዳንዱ መልስ ለመስጠት ራሱ ወያላው  ይለምናል። ‹‹ኧረ ተቀበለኝ ወንድሜ…›› ይላል ወያላው መጨረሻ ወንበር በጥግ በኩል በሁለቱም ጆሮዎቹ ኢርፎን ሰክቶ ስማርት ስልኩን እየጎረጎረ ዓለምን ወደ ረሳው ታዳጊ አስግጎ። በስንት ጉትጎታና አጠገቡ ባሉት ተሳፋሪዎች ጉሰማ ልጁ ጆሮውን የደፈነበትን ገመድ ነቅሎ መልሱን ተቀበለ። ‹‹ይኼ ትውልድ እኮ በዚህ ዓይነት እንኳን ለአዲስ አሠራርና ዓላማ ጥያቄ ሊያቀርብ፣ ለአሮጌው ጥያቄ መልሱ ሲመጣም ግዴለውም ማለት ነው?›› አሉ አንደኛው አዛውንት። እዚያው አካባቢ ጠየም አጠር ያለች የደስደስ ያላት፣ ‹‹ምን ይደረግ? የደጉ ዘመን ሰው ወዳጁ ከፍቶ ሲያስከፋው ፈረሱን ወይም በቅሎውን ኮርቻ ይጭናል። የአሁኑ በተራው እያየ ላለማየት እየሰማ ላለመስማት ሲመኝ በ‹ዳውንሎድ› ጥበብ ስልኩን በመጫን ይጠመዳል…›› አለች። ተረብ በሉት!

አዛውንቱ እኛ የገባን የገባቸው አይመስሉም። ሒደት ቀለሟን ስትቀያይር በቋንቋም ታደንቋቁረን ይዛለች። ታዳጊው በተራው ነገሩን በዝምታ ሊያልፈው አልፈልግ ብሎ፣ ‹‹ታዲያ የሰው ልጅ በማሰብ ችሎታዬ በሥልጣኔ እዚህ አደረስኳት የሚላት ዓለም እያደር የጦርነት፣ የሽብርና የክፋት አውድማ ከሆነች ምን ማድረግ አለብን?›› ብሎ ጠይቆ ሲያበቃ በአካባቢው ያሉትን ተሳፋሪዎች ገላመጣቸው፡፡ ‹‹እውነት ነው ቲክቶክና ዩቲዩብ ባይኖሩን ኖሮ ምን እንሆን ነበር? ዓለም እንደሆነች ይኼን ያህል ሺሕ ዘመን ፍትሕ የማታውቅ፣ በፖለቲካ ቁማር የሕዝቦችን ሰላማዊ ኑሮ ማመስ ያልሰለቻት ሆነች። ደግሞስ እንኳን ፍትሕን የዓለም ዋንጫን አራት ዓመት እየጠበቅን መሳተፍ ሕልም የሆነብን ከዚህ በላይ ብንዘጋጋ ይገርማል?›› አለች ጠይሟ ወጣት። እንደኖሩት ኖረው እንደሚሰነብቱት እየሰነበቱ ያሉት አዛውንት በበኩላቸው ዝምታን መርጠዋል። እንዲህ እንዲህ ያለው ሰዓት ላይ ዝምታ ብዙ ይላል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ቀበና አካባቢ የጫንናት አንዲት ተሳፋሪ ድንገት፣ ‹‹ወይኔ… ወይኔ… ወንድሜን…›› ብላ ማልቀስ ጀመረች። ‹‹ምን ነካት? አሁን ደህና አልነበረችም እንዴ?›› ይለኛል ከፊት። ‹‹አንድ የእናቴን ልጅ… ወይኔ ወንድሜን…›› ቀጥላለች። ወያላው፣ ‹‹ምን ሆኖብሽ ነው?›› ብሎ ሲጠይቃት እንዳልሰማችው ሁሉ መሬት መሬቱን እያየች እንባዋን ታዘረው ቀጠለች። በኋላ አዛውንቱ ቆጣ ብለው፣ ‹‹ምንድነው ተናገሪ እንጂ? በሽታውን ያልተናገረ መድኃኒቱን ምን ብሎ ያገኘዋል?›› አሏት። በለቅሶ ብዛት ዓይኗ ደም የመሰለው ሴት፣ ‹‹ምን ብዬ እናገረዋለሁ አባቴ? ጠዋት እኮ ደውሎልኝ ነበር፡፡ አሁን እኮ ነው ‹ይህች ዓለም ጥቅም ስለሌላት ደህና ሁኝ እህቴ ብሎ ቴክስት አደረገልኝ› ብላ በድንገት ታሪኩን አቋርጣ ዕሪታዋን አቀለጠችው። የሰሞኑ ራስን ማጥፋት አባዜ ነው መሰል!

 ‹‹እና ዓለምን መናቁ ነው የሚያስለቅስሽ? ድሮስ ይህች ከንቱ ዓለም ምን ታስደስታለች?  እሱም እኮ ይኼ ገብቶት አይደለም ወይ ምክር ጣል ያደረገልሽ?›› እያሏት ገና ሳይጨርሱ አዛውንቱ፣ ‹‹የገዛ ሕይወቱን በራሱ አጥፍቶ ነው አሉኝ እኮ አባባ። እኔን በስልክ አናግሮ ለካ እሱ በራሱ ላይ ፈርዷል፡፡ ይኼ ቤቲንግ የሚባል ቁማር ነው ምክንያቱ፣ ኧረ ምን ልሁነው? ወይኔ የእናቴ ልጅ…›› እያለች ዕሪታዋን ስታቀልጠው አንድ የሚተነፍስ ሰው ጠፍቶ ታክሲያችን በድንጋጤ መንፈስ የፈረሰች ጎጆ መሰለች። ወያላችን በተሰበረ ቅስም በተዳከመ ድምፅ፣ ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ ሲያወርደን ምስኪኗ ሴት ዕንባዋን እያዘራች ተለየችን። ይህ አደገኛ ቁማር ስንቱን ይዞት እየጠፋ እንደሆነ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እንደ አዲስ ፋሽን እየተስፋፋ ያለው ራስን ማጥፋትስ ስንቶችን እያስነባ እንደሆነም አሁንም ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ዕሪታ ሲበዛ ደግ አይደለምና እስቲ እናስብበት፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት