Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርለኢትዮጵያ  ፓርላማዊ  ወይስ  ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት? ለምን?

ለኢትዮጵያ  ፓርላማዊ  ወይስ  ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት? ለምን?

ቀን:

በዳዊት  አባተ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታ አገራዊ ጉዳዮችን እንድንመረምር፣ እንድንወስንና በተግባር እንድናውል የሚጠይቅ ነው፡፡ አንዱ መሠረታዊ ጉዳይ ለኢትዮጵያ  ፓርላማዊ  ወይስ  ፕሬዚዳንታዊ  ዴሞክራሲ ሥርዓት ይሻላል የሚለው ነው፡፡ ይህን አጀንዳ ብዙ አገር ወዳድ ዴሞክራቶች ለረጅም ጊዜ ሲያነሱት ቆይተዋል፡፡ የፖለቲካ ሊቃውንትም ስለሁለቱ ሥርዓቶች ደካማና ጠንካራ ጎኖች በሰፊው ጽፈዋል፡፡ የዚህች ጽሑፍ ዋና ዓላማ ለዴሞክራሲና ለአገራችን አንድነት መጠናከር የትኛው ሥርዓት ይበጀናል ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅና ለወደፊት ጉዟችንን እንድናስተካክል ለመገፋፋት ነው፡፡ ስለሁለቱ ሥርዓቶች ጠንቅቀን ማወቅ አገራችን ለ30 ዓመታት ያህል በመከተል ላይ ያለችውን ፓርላማዊ ሥርዓት መቀጠል ይገባል? ወይስ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት መለወጥ ይበጀናል? የሚለውን ለመወሰን ይረዳል፡፡

በዓለም ላይ ያሉት ሁለት የዴሞክራሲ ሥርዓቶች ሲሆኑ፣ ፓርላማዊና ፕሬዚዳንታዊ ናቸው፡፡ ፓርላማዊ የሚባለው ሥርዓት በሕዝብ ተወካዮች (በፓርላማ አባላት) የሚመረጥ አባል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት መሥርቶ አስፈጻሚ አካሉን (መንግሥትን) ይመራል፡፡ በዚህ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለቱም ምክር ቤቶች አባል በመሆኑ ሁለቱ ክፍሎች በተግባር የተያያዙና የተጣመሩ ናቸው፡፡ ይህ ጥምረት ሕግና ደንብ ለማውጣትና ለማስፈጸም ቀላል ስለሚሆን ደጋፊዎቹ ትልቁ ጠንካራ ጎን አድርገው ሲቆጥሩት፣ ሌሎች ደግሞ የሥርዓቱ ዋና ድክመት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህም ማለት የተወካዮች ምክር ቤት (ሕግ አውጪው) እና አስፈጻሚው አካል በቅርበትና በመግባባት ስለሚሠሩ ቀልጣፋ ነው ማለታቸው ነው፡፡ በፓርላማዊ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሚመለምሉት ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ብቻ ስለሚሆን፣ ብቃትና ተገቢው ልምድ ያላቸውን ግለሰቦች ማግኘት ቀላል ስላልሆነ የሥርዓቱ አንዱ ጠንካራ ድክመት ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ግን ፕሬዚዳንቱ (የአገሪቱ መሪ) በቀጥታ በሕዝብ ይመረጣል፡፡ ይህም በግልጽ ውድድር ተመሥርቶ በመላው አገሪቱ በድምፅ ብልጫ ያሸነፈው ዕጩ ተወዳዳሪ የአገሪቱ መሪ (ፕሬዚዳንት) ይሆናል፡፡ በዚህ ሥርዓት ፕሬዚዳንቱ በራሱ ውሳኔ ሚኒስትሮችን (ካቢኔውን) እና ሌሎችንም የመንግሥት ባለሥልጣናት ያለምንም ጫና በነፃነት ይመርጣል፣ ይሾማል፡፡ በሕዝብ በቀጥታ መመረጡ ብቻ ሳይሆን የሚሾሙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከፓርላማ አባላት ውጪ ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ ለኃላፊነት ብቃት ያላቸውን ዜጎች ለመመልመል ሰፊ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ የሥርዓቱ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ በአጠቃላይ ሥልጣን (ኃላፊነት በሕግ አውጭው (ተወካዮች ምክር ቤት) እና በሥራ አስፈጻሚው አካል መለያየት የፓርላማዊና የፕሬዚዳንታዊ ሥርዓቶች ዋናው ልዩነት ነው፡፡

ሁለቱም ሥርዓቶች ደጋፊና ተቃዋሚ አላቸው፡፡ የፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ከሚከተሉት መካከል አሜሪካ፣ ፈረንሣይና ኬንያን ከፓርላማዊ ሥርዓት ደግሞ እንግሊዝ፣ ካናዳና ጃፓንን መጥቀስ ይበቃል፡፡ ፓርላማዊ ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች በቁጥር ከፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በእጀጉ ያንሳሉ፡፡ የተለያዩ አገሮች የሕዝባቸውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ከአንዱ ሥርዓት ወደ ሌላው ሥርዓት እንደሚለውጡ ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ከፓርላማዊ ወደ ፕሬዚዳንታዊ የሚለውጡ የበለጡ ሆነው እናገኛለን፣ ይህም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በቅርብ ጊዜ አርማኒያ ከፕሬዚዳንታዊ ወደ ፓርላማዊ ለውጣለች፡፡ የጎረቤታችን ሶማሊያ ደግሞ ከፓርላማዊ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የለወጠችበት ዋናው ምክንያት የዘውግ (Clan) ፖለቲካ ያስከተለውን አገራዊ ችግር ለመቅረፍ በመሆኑ እኛ ከዚህ መማር ይጠበቅብናል፡፡ አገራችን ፓርላማዊ ሥርዓትን ከፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት እንዴት ልትመርጥ እንደበቃች ለብዙዎቻችን ግልጽ ባይሆንም፣ ለእንደዚህ ዓይነት መሠረታዊ ጉዳይ ሰፊ የምክክር መድረክና ሕዝበ ውሳኔ ሊኖር ይገባ ነበር የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡  

አሁን ኢትዮጵያ የምትመራበት ሥርዓት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 56፣ ‹‹በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ  ያደራጃል፣ ይመራል፤›› የሚለውን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሕወሓት/ኢሕአዴግን ወክለው በትግራይ ከአንድ ወረዳ ተመርጠው የምክር ቤት አባል ሆኑ፡፡ ከዚያም የኢሕአዴግ ተመራጮች የምክር ቤቱን አብላጫ መቀመጫ ስለያዙ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን፣ የፓርላማዊው ሥርዓት የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ተጀመረ፡፡

ይህም ማለት ከየወረዳው ተመርጠው የመጡ ተወካዮች ከመካከላቸው አንዱን አባል ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው በመምረጥ የአስፈጻሚ አካሉን (ካቢኔ/የሚኒስትሮች ምክር ቤት) እንዲያደራጁና አገሪቱን እንዲመሩ ሥልጣን ተሰጣቸው ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ትኩረት መስጠት ያለብን ዋና ነጥብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ የተመረጡት በአንድ ወረዳው ሕዝብና በተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንጂ፣ በቀጥታ በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳልሆነ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ለኢትዮጵያ የሰነቁትን ራዕይና ዓላማ ለሕዝብ አላሳወቁም ነበር ማለት ነው፡፡ 

የፓርላማዊ ሥርዓት ደጋፊዎች ዋና መከራከሪያ ነጥብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወካዮች የተመረጠ በመሆኑ፣ የምክር ቤት ድጋፍ ስለማይለየው ሥራ አስፈጻሚው አካል (ካቢኔው/መንግሥት) በቀላሉ ሕጎችና ደንቦችን አቅርቦ የማፅደቅ ዕድሉ ከፍተኛ ነው የሚለው ነው፡፡ የሥርዓቱ ተቃዋሚዎች ደግሞ ሕግና ደንቦችን ሕዝብ  ሳያውቃቸው የሚፀድቁበት ሁኔታ ስለሚፈጥር የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል እንዳይደለ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመረጡት የፓርላማ አባላት ስለሆኑ ከሥልጣን ሊያወርዱት፣ ሊሽሩትም ስለሚችሉ ትኩረቱም ሆነ ሥጋቱ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባን አጠቃላይ ጉዳይ ግን ይህ ሥርዓት በቆየንበት 30 ዓመታት ለኢትዮጵያ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል ወይ የሚለው ነው፡፡

በዚህ ሥርዓት አገሪቱ በግጭትና ጦርነት እየታመሰች በመሆኗ የአንድነት እሴቶች በእጅጉ ተሸርሽረዋል፡፡ ከዚህም በላይ ድህነት፣ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል፡፡ በአገሪቱ የሚካሄደው ብሔር ተኮር የፖለቲካ ዘይቤና በዚያም ምክንያት የተፈጠሩትን ችግሮች ፓርላማዊ ሥርዓት አይፈታውም እንዲያውም እንዳያባብሰው ያሠጋል፡፡ በብሔር (ነገድ) በተደራጁ የምክር ቤት አባላት በመጡ መሪዎች ከአድልኦ ነፃ የሆነ መልካም አስተዳደር በአገሪቱ ይሰፍናል ብሎ የማያምነው ሕዝብ ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ ይህም ማለት ከመጣበት (ከመረጠው) ብሔር/ክልል የሚገኙ ሰዎችንና ቡድኖችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ሥርዓቱ ክፍተት ይሰጣል፣ ሙስናን ከመጋበዙ በላይ የአንድነት ስሜትንም ይሸረሽራል ብለው የሚጠራጠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ያለችበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሥርዓቱ ስለማይመልስ ለአገራችን ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ያስፈልጋል የሚሉ የፖለቲካ ባለሙያዎች ብዙ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በቀጥታ በሕዝብ ድምፅ የሚመረጥ በመሆኑ፣ ለኢትዮጵያ በጎ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር አያጠራጥርም፡፡ ለምሳሌ ሦስት ግለሰቦች ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለመሆን ቢወዳደሩ፣ መጀመሪያ ለአገሪቱ ያላቸውን ራዕይና ዓላማ ለሕዝብ በዝርዝር ያሳውቃሉ፣ የአገሪቱን አንገብጋቢ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች እንዴት እንደሚፈቱና የሕዝቡን ፍላጎት እንዴት እንደሚያሟሉ ያስረዳሉ፡፡ መራጩ ሕዝብም የተወዳዳሪውን ዓላማ፣ ብቃታና ከዚህ በፊት ያበረከቱትን በጎ ነገር፣ ወዘተ. መሠረት በማድረግ ላመነበት ዕጩ ተወዳዳሪ ድምፁን በቀጥታ ይሰጣል፡፡ የሚበዛውን ድምፅ የሚያገኘው ዕጩ ተወዳዳሪ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ይሆናል፡፡

ለምሳሌ ከ60 ሚሊዮን መራጭ ዜጎች ውስጥ ከግማሽ በላይ ማለትም ቢያንስ 30 ሚሊዮን ዜጎች በቀጥታ የመረጡት ሰው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ከተለያየ ብሔረሰብና የእምነት ተከታዮች እንደመረጡት ግልጽ ነው፡፡ ከደገኛውም ከቆለኛውም ድምፅ አግኝቷል፡፡ ከከተማና ከገጠር ነዋሪዎችም ወጣትና ሽማግሌ፣ ሴቶችም ወንዶችም ይፈልጉታል፡፡ ከተማረውም ከማይሙም ድምፅ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት መላው የአገሪቱን ሕዝብ በቀጥታ ከመሪው፣ መሪውንም ከሕዝቡ ጋር የሚያቀራርብ ቀጥተኛ ኃላፊነትና የተጠያቂነት ስሜት ስለሚሰጥ ሥርዓቱ  አገራዊ የመተማመን እሴቶችን ይፈጥራል፡፡

በሌላ በኩል የፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ዋና ችግር ተብሎ የሚጠቀሰው ፕሬዚዳንቱ ሕግና ደንቦችን በሕግ አውጭዎች በቀላሉ ለማፅደቅ አለመቻል፣ እንዲሁም በፓርላማው የሚወጡ ደንቦችን ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ሊያስቆሙት/ሊያግዱት ስለሚችሉ በዚህ በኩል ቅልጥፍና ይጎለዋል ይላሉ፡፡ ይህ ችግር የጎላ የሚሆነው ግን ፕሬዚዳንቱ የተመረጡበት ፓርቲ አብዛኛውን የፓርላማ መቀመጫ ያልያዘ እንደሆነ ነው፡፡ በአጠቃላይ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ከጥቅሞቹ ጉዳቶቹ ስለሚያንሱ ዛሬ የሚበዙት የዓለም አገሮች የሚከተሉት ይህን ሥርዓት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ብዝኃነት በሚበዛባቸው የአፍሪካ አገሮች የፓርላማዊ ሥርዓት ተመራጭ እንዳልሆነም በደንብ እንገነዘባለን፡፡

 ለኢትዮጵያ የፓርላማዊ ሥርዓት እንዴት እንደተመረጠ ለብዙዎቻችን ግልጽ ባይሆንም፣ ለሕዝቡ “እናውቅለታለን” በሚሉ ሥልጣን ፈለጊ ግለሰቦችና ጥቂት ድርጅቶች የተወሰነ ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ወደፊት ግን የሚሻለውን ሥርዓት መምረጥ የዜጎች መብት ስለሆነ ሁኔታዎች ሊመቻቹና መድረኮች ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ ለአገሪቱ የሚሻለውን ሥርዓት መምረጥ የአገሪቱ ዜጎች መብት መሆኑ የበለጠ ግለጽ ሊሆን ይገባል፡፡ አሁን ካለንበት ውስብስብ ችግር ወጥተን ለነገይቱ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም፣ አንድነትና ዴሞክራሲ በማስፈን ለትውልድ የሚተላለፍ የተረጋጋ የመንግሥት ሥርዓት እንዲኖር ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የተሻለ አማራጭ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው dawitabatetassew@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...