Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከቲክቶክ የተቀዳው ሽልማት

ከቲክቶክ የተቀዳው ሽልማት

ቀን:

በዳንኤል ንጉሤ

ቲክ-ቶክ በሴብቴምበር 2016 በቻይና መተግበሪያ ፈልሳፊዎች ነበር ‹‹ዶዪን›› በሚል ስያሜ የቪዲዮ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ሆኖ ለገበያ የቀረበው። ይህ መተግበሪያ በቻይና ተወዳጅነቱና ተቀባይነቱ በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ የመተግበሪያው ፈልሳፊዎች መልካሙን አጋጣሚ በመጠቀም ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በመወሰን ቲክቶክ በሚል ስያሜ ይፋ አደረጉት።

ከቲክቶክ የተቀዳው ሽልማት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ተሸላሚው ሙሴ ሰለሞን

ይህ መተግበሪያ በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ በከፍተኛ ደረጃ በማደጉ ከ1.6 ቢሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚገለገሉበት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለያዩ የአፕሊኬሽን ማውረጃዎች ላይ ከሦስት ቢሊዮን በላይ ጊዜ በመውረድ (ዳውንሎድ በመደረግ) ከሌሎች የማኅበራዊ ሚድያ መተግበሪያዎች በመብለጥ ቀዳሚነቱን ይዟል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከመቶ ሃምሳ በላይ አገሮች ተጠቃሚዎች የሆኑበት ቲክቶክ ከመቶ ሃያ በላይ ቋንቋዎችም እንዲሠራ ተደርጎ የተመረተ መተግበሪያ ነው፡፡ በኢትዮጵያም በከፍተኛ ደረጃ ከሚዘወተሩ የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተሠልፏል። 

ቲክቶክ በኢትዮጵያ በስፋት መዘውተር የጀመረው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ ሲሆን፣ ወረርሽኙም በሰዎች ላይ ከፍተኛ ድብርት በማምጣቱ ምክንያት ሰዎች እንደ ቀዳሚ መረጃ ማግኛና እንደ መዝናኛ በማገልገል ያን ከባድ ጊዜ እንዳሳለፉበት ይነገራል።

በመተግበሪያው ወጣቶች በብዛት የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ ከመዝናኛነት አልፎ የሥራ ዕድልን በመፍጠር  የገቢ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

በዚህ መተግበሪያ ላይ ከአንድ ሚሊየን በላይ ተከታይ ያላቸው ወጣቶች በመኖራቸው የተለያዩ ድርጅቶች ማስታወቂያ በማሠራታቸው ለራሳቸው ብሎም ለቤተሰቦቻቸው የገቢ ምንጭ በመሆን ሕይወታቸውን እየቀየሩበት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ቲክቶክ በውስጡ የተለያዩ ይዘቶች ሲኖሩት መረጃ መስጠት፣ ኮሜዲ፣ የበጎ አድራጎት ሥራ፣ የዳንስ ጥበብ እንዲሁም የተለያዩ ትርዒቶች ይስተናገዱበታል።

በኢትዮጵያ የመተግበሪያውን ተፅዕኖ የተመለከቱት የሚልኪ ሚዲያና ኤቨንት ባለቤት የሆኑት አቶ አላሙዲ ሙስጠፋ፣ ከዩኒየን ኤቨንት ጋር በመሆን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን በቲክቶክ ላይ በጎ ተፅዕኖ ያደረጉ ሰዎችን ለማበረታታት ያሰበ ሽልማት ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል አካሂደዋል።

‹‹ከሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ ቲክ ቶክን መምረጥ ያስፈለገው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘ ስለሆነ ነው፤›› ያሉት አቶ አላሙዲ፣ በተጨማሪም ‹‹መተግበሪያውን ለበጎ ዓላማ የተጠቀሙትን ሰዎች መሸለምና ማበረታታት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው ነው፤›› ሲሉ ያስረዳል። 

በ2015 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የመሸለም ሐሳቡን እንዳመጡት የተናገሩት አቶ አላሙዲ በቲክ ቶክ ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ተከታይ ያላቸውን ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ቲክ ቶከሮችን ጠርተው ስለጉዳዩ በማወያየትና የእነሱን ገንቢ ሐሳብ በመስማት የሽልማት ዝግጅቱን ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

ስለምርጫው አካሄድም ሲያስረዱ ‹‹ወደ ሰባ በመቶ የሚሆነውን ድምፅ ለሕዝብ ነው የሰጠነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ሠላሳ በመቶ የሆነው ድምፅ ደግሞ በዳኝነት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው  ለአብነት እንደ ሠርፀ ፍሬስብሐት የመሳሰሉ ዳኞች ተሳትፈውበታል›› ሲሉ አክለዋል።

ለሽልማቱ እንደ መሥፈርት የቀረቡት፣ መተግበሪያውን በመጠቀም የሥራ ዕድል የፈጠሩ፣ በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ያመጡ፣ ሰዎችን በመርዳት አንቱታን ያተረፉ፣ መልካም መረጃዎችን ለሰዎች ማድረስ የቻሉና በሌሎች ጥሩ ምግባራት የኢትዮጵያን ባህልና እሴትን በማይሸረሽሩ መልኩ የተሳተፉ ናቸው።

ከ12ቱ የሽልማት ዘርፎቹ፣ ምርጥ መረጃ ሰጪ፣ ምርጥ የዓመቱ በጎ ሰው፣ ምርጥ ኮሜዲ፣ ምርጥ ኤዲቲንግና ምርጥ ቀጥታ ሥርጭትና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በየዘርፉ ያሸነፉት የቲክ ቶክ ዓርማ ያለበት ዋንጫና የመቶ ሺሕ ብር ሽልማት ሲያገኙ፣ በአጠቃላይ ዘርፍ አሸናፊ ለሆነው ደግሞ ሦስት መቶ ሺሕ ብር  ከቲክ ቶክን ዋንጫ ጋር ተበርክቶለታል።

የምርጥ መረጃ ሰጪ አሸናፊ የሆነው ወጣት ሙሴ ሰለሞን  ቲክ ቶክን እንዴት እንደጀመረ እንዲህ ያስታውሳል።

‹‹ቲክ ቶክን የጀመርኩት የኮረና ሰሞን ሲሆን፣ ሁሉም ሰው እቤቱ በነበረበት ሰዓት እኔም እንደ ትርፍ ጊዜ ማሳለፊያነት እጠቀምበት ነበር፡፡ ከዚያም የራሴን ቪዲዮዎች በመልቀቅ ቀስ በቀስ ዕውቅናንን አገኘሁ፤›› ሲል ያስረዳል። ትልቅ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብሎ አለመጀመሩ ኮሮናው ሲያልፍ በዚያውም ያልፋል ብሎ ያስብ እንደነበርም ገልጿል።

 ሰዎች እንደመዝናኛ ቲክ ቶክን በሚጠቀሙበት ወቅት መረጃዎችን ለሕዝቡ በማቅረቡ እንዲታወቅና እንዲታይ፣ እንዲሁም ብዙ ተከታይ እንዲያገኝ እንደረዳው የሚናገረው ወጣት ሙሴ፣ ከቲክ ቶክ ሕይወቱ በፊት ከቀልዶች ይልቅ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ ነገሮችን የማወቅ ፍላጎት እንደነበረው ይናገራል። ይኼ ልምዱም አሁን ለደረሰበት ዕውቅና መሠረት እንደሆነ ያምናል።

የዛሬ ሦስት ዓመት ቲክ ቶክ እንደ ቀልድ የጀመረው ሙሴ አሁን ላይ በቲክ ቶክ አካውንቱ ከስድስት መቶ ሺሕ በላይ ተከታዮች እንዳሉት ይናገራል።

ከሁለት ወር በፊት፣ ‹‹ሰዎች የምትወዷቸውን ቲክ ቶከሮች ምረጡ›› ተብሎ በወጣው ማስታወቂያ መሠረት ዕጩ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ሙሴ፣ በዳኞች ውሳኔ አሸናፊ ሆኖ እንደተመረጠ ገልጿል።

‹‹መረጃን በመስጠት ዘርፍ ላይ በመሰማራቴ ይህ ሽልማት ለእኔ የበለጠ ዕውቅናና አመኔታ እንዳገኝ ይረዳኛል፤›› ያለው ሙሴ፣ ‹‹ሕዝቡ የማምነው እሱ ነው ብሎ ሲመርጠኝ ትልቅ ኃላፊነት ስላሸከመኝ እምነቱን ማጉደል እንደሌለብኝ ተሰምቶኛል፤›› ሲል ያስረዳል።

የወደፊት ጊዜ ዕቅዱ የራሱ የሆነ የሚዲያ ተቋም መክፈት እንደሚፈልግ ተናግሯል።

አቶ አላሙዲ ስለ ቲክ ቶክ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያስረዱ፣ ‹‹የቲክ ቶክ መድረክ ማንም ሰው ተነስቶ መጠቀም ስለሚችል የተለያዩ አላስፈላጊ ነገሮች ይንሸራሸሩበታል፤›› ያሉ ሲሆን፣ ለምሳሌነትም ብሔርንም፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩና ሰላም የሚያውኩ ይዘቶችን የያዙ ሐሳቦች እንደሚተላለፉበትና ተገቢ እንዳልሆነም ይጠቅሳሉ።

በኢትዮጵያም እንደዚህ ዓይነት ይዘቶች ቁጥጥር ስለማይደረግባቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ብዙዎች ይናገራሉ።

‹‹መንግሥት ከሌሎች አገሮች ልምድ በመውሰድ ቁጥጥር ማድረግ አለበት፤›› ያሉት አቶ አላሙዲ፣ በምሳሌነትም እንደ ቻይና በየምድቡ በመመደብ ማለትም የሕፃናት፣ ወጣቶች፣ የተማሪዎች፣ የአዋቂዎች ብሎ በመከፋፈል የቪዲዮ ይዘቶችን መቆጣጠር እንደሚቻል ያስረዳሉ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...