Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየቀነጨረው ዴሞክራሲና የትውልዱ ዕዳ

የቀነጨረው ዴሞክራሲና የትውልዱ ዕዳ

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

ትውልድ የታሪክ ባለ ዕዳ ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድም በአገራችን እየተፈጸመ  ላለው በጎም ሆነ ክፉ ሁነት ተጠቃሽ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድ ወደ አንድ መንደርነት የተቀየረው የዓለም ተፅዕኖ ተጨምሮበት ከበፊቱ ትውልድ በተሻለ የነቃ፣ የተማረና የሠለጠነ ሊባል ይችላል፡፡ በዚያው ልክ በብሔርተኝነት የደደረ፣ በታሪክ ቁርሾና በጥላቻ ፖለቲካ የተሳከረ፣ ራስ ወዳድነት ያየለበት፣ እርስ በርሱ የሚጨካከን፣ ወዘተ. እየመሰለ መምጣቱን መካድ አይቻልም፡፡

የእኛ ትውልድ ምሁራንና የፖለቲካ ተዋንያንን ጨምሮ በርከት ባሉ አገሮች ራስ ወዳድነትና አርቆ አለማሰብ እየበረከቱ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መጎልበት ይልቅ፣ ሁከትና ትርምስ አየሩን ሞልቶት ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ መከራና የኋላቀርነት መንገድ አለመሻሻል ዋነኛ ተጠያቂዎች ምሁራንና አገር ተረካቢዎች መሆናቸውን የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመሠረቱ የአሁኑ ትውልድ አመነውም ካደውም ዴሞክራሲ ማለት የሕዝብ፣ ለሕዝብ፣ በሕዝብ የቆመ ሥርዓት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የአማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ደግሞ በሕዝባዊ ምርጫ በመሆኑ ምርጫም የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫ የሚካሄደው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድን በመረጡ የፖለቲካ ታጋዮችና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ነው እንጂ፣ በኃይል በተፋጠጡ ተፋላሚዎች መካከል አይደለም፡፡

ለአብነት ያህል ብናነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ በምንገኝበት ደረጃ ያጋጠመው የፖለቲካ ፍጥጫ በአሀዳዊ (ጠንካራ አገራዊ ብሔርተኝነት) እና በነጣጣይ ብሔርተኝነት (የዘውግ ፌዴራሊዝም መጠናከር) መካከል ያለው አለመቀራረብ ነው የሚሉ ተንታኞች አሉ፡፡ ይህን ሐሳብ ከሚያነሱት ምሁራን መካከል አቶ አንዳርጋቸው አሰግድን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ምሁሩ “ቅን ፍላጎት እስካለ መንገድ አለ” በሚል ርዕስ የለውጡ ጅማሬ ሰሞን ባቀረቡት መጽሐፍ፣ ነገሮችን በሚዛንና በቅንነት ዓይቶ ማስተካከል ካልተቻለ ተቃርኖ በእነዚህ ሁለት መደወሪያዎች ውስጥ የተሸጎጠ ይሆናል ብለዋል፡፡ እንደ መፍትሔ ፈታኙን ችግር ሲዳስሱ ግን እንዲህ በማለት ነው፡፡

‹‹የብሔሮች ጥያቄ የሚፈታው በአሃዳዊ አስተዳደር ብቻ ነው የሚል ወንጌል የለም። በፌዴራል አስተዳደር ብቻ ነው የሚል ወንጌልም የለም። የብሔሮች መብት ዴሞክራሲያዊ በሆነ አሃዳዊም ሆነ ፌዴራላዊ አስተዳደር ውስጥ ሊስተናገድና ሊጠበቅ ይችላል። ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ስዊዲን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ኢጣሊያ፣ ሆላንድ፣ ኢስቶኒያ… በሰፊ የራስ ገዝ አስተዳደር የብሔሮችን መብቶች አውቀውና አስተዳድረው የሚያስተዳድሩ አሀዳዊ አገሮች ናቸው። በሌላ በኩል በዚች ምድር ላይ ከሺሕ በላይ ብሔሮች አሉ። ከመካከላቸው በፌዴራል አስተዳደር የሚተዳደሩት 25 አገሮችና ከዓለም ሕዝብ 40 በመቶ ናቸው። ከ198 የዓለም አገሮች መካከል የአንድ ብሔር መንግሥት ብቻ ተብለው የሚዘረዘሩት 14 አገሮች ውስጥ እንኳን (ሌሴቶ፣ ጃፓን፣ አርሜኒያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ አልባኒያ፣ ሃንጋሪ፣ ባንግላዲሽ፣ ሞንጎሊያ፣ ታይላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ቼክ፣ አይስላንድ፣ ግሪክ) ሌሎች ብሔሮች አሏቸው፤›› አንዳርጋቸው አሰግድ “ቅን ፍላጎት እስካለ መንገድ አለ”  (2013፣ 78)

የእኛ አገር ፖለቲከኞች ግን በቅን ፍላጎት አዲስ መንገድና ከታለፉባቸው ፈተናዎች የሚያወጡ የፖለቲካ ዘይቤዎችን ፈልጎና ከነባራዊው አገረ መንግሥት ጋር አዋህዶ ከመተግበር ይልቅ፣ ተቃርኖውን በማባባስ የአሸናፊነትና የጠላት ወዳጅ ፍረጃን ገፍተውበታል፡፡ የጦርነትና የእርስ በርስ ትርምስ ሰርክሉ ላይበጠስ እንዲመላለስም ዳግም ፈቅደውለታል፡፡ ግን ለምን የሚለው የቁጭት ጥያቄ መነሳት ያለበት እዚህ ላይ ነው፡፡

በሠለጠነው ዓለም እንደምንመለከተው ፓርቲዎች ‹‹ቆመንለታል›› የሚሉትን ሕዝብ (ቡድን) መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል አማራጭ ሐሳቦችን ያመነጫሉ፡፡ በዘላቂነት ርዕዮተ ዓለም ለይተው ቢታገሉም፣ በጋራ ለመኖር የሰላማዊ የጋራ ፖለቲካ ሥልትን ለአገረ መንግሥት መቆሚያ ምሰሶ ከማድረግም አይቦዝኑም፡፡ ግጭትና ጦርነትን በርካታ ዋጋ ከፍለውም ቢሆን ስለተሻገሩት ዳግም ላይመለሱበት በዴሞክራሲ መርሆዎች ተማምለው ዘግተውታል፡፡

ሐሳቦቻቸው ለቆሙለት ኅብረተሰብ (ቡድን) እና በጠቅላላው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይታገላሉ፣ ሐሳቦች በዴሞክራሲያዊ አኳኋን ተግባራዊ እንዲሆን የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ የፖለቲካ መሪ አስተማሪ በመሆን ከፍተኛ የአመራር ሚናም ይጫወታሉ፡፡ እንጂ በእኛ አገር እንደሚታየው ለጥቅም ሲራኮቱም ሆነ በትርምስ ሥልጣን ለማግኘት እዚያና እዚህ ሲረግጡ ወይም እንመራዋለን ከሚሉት ሕዝብ ኋላ ሲሞዳሞዱ ዓይታዩም፡፡

ዜጎቻቸውም በዝርዝር የተተነተኑ ሐሳቦችን ይዘው መብትና ጥቅማቸውን የሚያስከብርላቸውን ፓርቲ ካሉት ፓርቲዎች መካከል የግራ ቀኙን ሰምተውና መዝነው፣ ይበጀናል የሚሉትን በራሳቸው ፈቃድ በነፃ ምርጫ ይመርጣሉ፡፡ በፖለቲካ ልዩነት ለመመረጥ ተወዳድረው ያሸነፉትም ሆኑ የተሸነፉት የአገረ መንግሥት ምሰሶዎቻቸውን ጠብቀውና አገረ መንግሥቱ የሚተዳደርበትን የፖለቲካ ሥልት (አሀዳዊ፣ ፌዴራላዊ ወይም ከሁለቱም ዕሳቤዎች የተውጣጡ የአስተዳደር ሥልቶችን) ጠብቀው ይታገላሉ፡፡ በእኛ አገር ግን ይህ መንፈስ ባለመዳበሩ እነሆ አሁንም መንግሥትን በኃይል ጥሎ ፍላጎትን ዕውን ለማድረግ ሆኗል ፍትጊያው፡፡ መንግሥትም አገር ለመጠበቅ ያሰናዳውን ጦር በፀጥታ ስም የፖለቲካ መሣሪያ እያደረገው ቀጥሏል፡፡

በእኛ ሁኔታ ካለፉት አራትና አምስት አሥርት ዓመታት አንስቶ የፖለቲካ ትግሉ ሴራ፣ መጠላለፍ፣ ቡድንተኝነት፣ አሉባልታ፣ አቃቂርና ጥላቻ የተላበሰ መሆኑ ሲታይ ምሁርነትና ሥልጡን ፖለቲካ ማራመድ ብሎም ምክንያታዊነት ውኃ እንደበላቸው መረዳት አይከብድም፡፡ አሁን አሁን እንደሚታየው በታሪክ አጋጣሚ የተያዘ ሥልጣንንም ለራስና ለቡድን ጥቅም ለማዋል ቀፍድዶ ከመጠቀም አልፎ፣ ለአገርና ለመላው ወገን በሚጠቅም መንገድ የመጠቀሙ ብልህነትና ወኔ አለመታየቱም የሚያስተዛዝብ ወራዳ ተግባር ሆኗል፡፡ ይህም በመሆኑ ነው መፍትሔ የሚያማትር ዕውቀትና ብልህነት ያስፈለገው፡፡

በዓለም ታሪክ በትጥቅ ትግል ውስጥም ሆነ በኃይል የፖለቲካ አማራጭ ውስጥ ምሁራን የሉም ባይባሉም፣ የአመፃ መንገድ አንድ ቦታ ላይ ቆሞ እንደ አገር መነጋገርና ሁሉን አሳታፊ በሆነ መንገድ ወደ ዴሞክራሲያዊ መንገድ መሄድ ካልተቻለ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው፡፡ ለዚህም ነው ትናንት በትግራይ፣ አሁን ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች መንግሥትና አጠቃላይ ሥርዓቱን ተቃውመው እየተፋለሙ ያሉ ኃይሎች ሁሉ ወደ ክብ ጠረጴዛ መጥተው፣ የመንግሥት ሆደ ሰፊነትም ኖሮ መነጋገርና ለትውልድ መፍትሔ የሚሆን የሰላም አየር መተንፈስ ይኖርበታል የሚባለው፡፡

ለዚህ ደግሞ በመንግሥትም ውስጥ ሆነ በተፎካካሪ ኃይሎች በኩል በየትኛውም መስክ ቢሆን ዓላማቸውን በሚገባ የተረዱና ያወቁ፣ የተነሱለትን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመተንተን፣ ለማቀናበርና ለሕዝብ ለማቅረብ ፍላጎትና አቅም ያላቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ሊኖሩ ይገባል፡፡ አብዛኛው በሌላው ተታሎ የሚነዳበት፣ ኑሮውን በአድርባይነት ለመግፋት የሚልመጠመጥ በበረከተበት ለፖለቲካና ለዴሞክራሲ ትግል አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል ማለት አይቻልም፡፡ እናም ፈጣን የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡

ትውልዱ ከወደቀበት ታሪካዊ ዕዳ ለመላቀቅ ግን ተወደደም ተጠላ፣ በየትኛውም ደረጃ የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉ ወገኖች የአገሪቱን ሕገ መንግሥት አክብረውና የሕግ ማዕቀፉን ጠብቀው፣ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህ አመቺ የሆነ ንፍቀ ክበብ ከሌለ እንኳን ትግሉ መሆን ያለበት ሥርዓተ መንግሥቱን በመናድ ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን፣ ሕዝብን በማሳመን ብልሽቱን አጋልጦ እንዲሻሻል ሰላማዊ የትግል ሥልቶችን በማስቀደም መሆን አለበት፡፡

በእርግጥ ገንዝብ፣ ወታደርና የተከማቸ መዋቅር ያለው መንግሥት፣ ከሕዝብም ሆነ ከሚቃወሙት ወገኖች የሚደርስበትን ሂስና ወቀሳ ችላ ብሎ በጉልበት እየተፋለምኩ እቀጥላለሁ ሲል የትግሉ አቅጣጫ መቀየሩ አይቀርም፡፡ ያም ቢሆን ግን በተናጠልና በሚያደናግር የጥላቻና የመጠፋፋት መንገድ ሳይሆን፣ ከውስጥ እስከ ውጭ ጠንካራ ጫና ማሳደር ይቻላል፡፡ መደማመጥ ቀርቶ ሁሉም በራሱ ጎሳ እየተሰባሰበ የሚደረግ ፍልሚያ ግን ሄዶ ሄዶ የሚያስከትለው ትውልድ ተሻጋሪ ጥፋት ብቻ ነው፡፡

በእርግጥ በእኛ አገር የታሪክ ተቃርኖ ምክንያት ብቻ ሳይሆን ባለመታደል ጭምር፣ ሕዝቡ አይደለም የፖለቲካ ልሂቃኑም ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም፣ ዓላማና ግብ ባላቸው ፓርቲዎች የመሰባሰብ ሃሞት እንደሌላቸው እየታየ ነው፡፡ እንደ ፖለቲካ ተዋናይ በመሀላቸው ያሉትን አነስተኛና መለስተኛ ልዩነቶች በውይይት በማጥበብና በመቻቻል፣ ወደ አንድ ወይም ወደ ሁለትና ሦስት ፓርቲ ተሰባስበው ድምፃቸው ሰሚ እንዲያገኝ መሥራት የቻሉ ኃይሎችም እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ ይህን ካልተሻገርን ደግሞ ከውድቀት አንወጣም፡፡

በፖለቲካ ትግሉ ውስጥ አልፎ አልፎ የሚታየው መሰባሰብም በተፋላሚ ኃይሎች መካከል በዓላማቸው ውስጣዊ አንድነት ከመሆን ይልቅ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› በሚለው ብሂል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ውድቀት እንጂ ስኬትና የዴሞክራሲ መጎልበት እየታየ አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መሰባሰብ ሕዝባዊ አመኔታን ካለማስገኘቱም በላይ በድቡሽት ላይ እንደተሠራ ቤት የሚፈራርስ አንድነት እየሆነ በርካታ ኪሳራ ማድረሱም የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን በየጎራው እየተፋለመ ያለው ኃይል ቢሳካላት በምን ቋንቋ ተግባብቶ አገር ሊያቆም ይችላል የሚለው ሥጋት የበርካቶች የሆነውም፣ መሠረቱ ከላይ የተጠቀሰው ስለሆነ ነው፡፡

እውነት ለመናገር አነሰም በዛም ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ የሆነ ሥርዓት እያለ፣ እንኳንስ ተበታትኖ ተሰባስቦም ቢሆን የኃይል አማራጭን እንደ ሥርዓት መለወጫ ሥልት መውሰድ የተሻለ ዕድል የሚያስገኝ እንዳልሆነ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ በዘያ ላይ አሁን እየታየ ባለው መገዳደል፣ የደሃ አገር ሀብትን ማጥፋትና በጦርነት መማገድ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሰበዓዊ መብት ጥሰትና የንፁኃን ዕልቂት እየደረሰ ከታሪካዊ ውርደትም መዳን የሚችል የፖለቲካ ኃይል ሊኖር አይችልም፡፡

በተመሳሳይ አገር እየመራ ያለውም ፓርቲ መንግሥት በመሆኑ የጨበጠውን ወታደርና የፀጥታ ኃይል፣ ገንዘብና የአገር ሀብት፣ እንዲሁም መንግሥታዊ መዋቅርና መሰል ሀብቶች ይዞ የሰላም አማራጭን አንድ ዕርምጃ እየሄደ ጭምር ዕውን ማድረግ ካልቻለ በሕግም ሆነ በታሪክ መጠየቁ አይቀርም፡፡

እንግዲህ በግራም ሆነ በቀኝ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ ተግባራትን የሚያውኩት እንዲህ ያሉ ከራስ ወዳድነትና ሕዝብን መናቅ የሚመነጩ ስግብግብነቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ምንኛ ከታሪክ የማንማር፣ ሰፊ አገር ይዘን በጠባብና በጨፍጋጋ ምኅዳር የምንዳክር ልክፍተኞች ነን የሚያስብለውም ችግሩ በሁሉም አካባቢ የሚታይ በመሆኑ ነው፡፡ ይህን ኋላቀር አስተሳሰብ በአዲስ መንፈስ ሰባብሮ ለመሻገር ደግሞ በዋናነት ምሁራን፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የመገናኛ ብዝኃን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የእምነት ተቋማትና ነፃ አደራጃጀቶች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ መንግሥትና ሕዝብም የየድርሻቸውን ትግል ማድረግ ግድ ይላቸዋል፡፡ በአፍ ሳይሆን በተግባር፡፡

አሁን ከምንገኝበት አገራዊ የፖለቲካ ቅርቃር አንፃር ደግሞ ገና ከጅምሩ መጠራጠርን አስወግዶ በተግባር እየፈተኑና እያረሙ መሄድ የሚቻልበትን የብሔራዊ ምክክር ተቋም መቀበል፣ ማጠናከርና መደገፍ ብቸኛ መፍትሔ ነው፡፡ በተለይ ዋና ዋና የሕዝብ ጥያቄዎችንና የማያግባቡ ድንጋጌዎችና ዕሳቤዎችን ተቀራርቦ ለመፍታትም ሆነ የጋራ ለማድረግ፣ አገራዊ ምክክርና ድርድርን ከመጀመርና ማጠናከር የተሻለ መፍትሔ ሊኖር አይችልም፡፡ የፓርቲዎች የፖለቲካ አቋም ክርክርና ውይይትም ቢሆን፣ ለአገሪቱና ለሕዝቡ ጠቀሜታ ሲባል በመሀል ዳኛና አወያይ መከናወን አለበት፡፡

በየትኛውም ደረጃ በሚካሄድ ውይይትና ድርድር ውስጥ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ የሕዝብ ወኪሎች የመደራደሪያ ነጥባቸው ከራሳቸው መነሻ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ፍላጎቶች የሚመነጩ፣ በየትኛውም አኳኋን የሚነሱ መከራከሪያዎች ለአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ያደሉ፣ የሚጠቀሙባቸው ቃላት ጨዋነት የተሞሉባቸው፣ አቀራረባቸውም በመከባበርና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለውም በሕግና ሥርዓት ብሎም በጋራ ተቋም የትኛውንም ምክክርና ድርድር መምራት ሲቻል ብቻ ነው፡፡

በእንዲህ ያለ ወደ ብሔራዊ ዕርቅና ብሔራዊ መግባባት የሚያደርስ የዴሞክራሲ ቁልፍ መድረክ ስኬት ውስጥ ሚዲያዎችም ያላቸው ቁልፍ ሚና ከልብ ተፈትሾ መስተካከል አለበት፡፡ በተለይ የመንግሥት ሚዲያዎች በምርጫ ወቅት ሲያደርጉ እንደነበሩት የፓርቲዎች የክርክር ነጥብና አቋምን ሚዛናዊ ባልሆነ ሙያዊ አሠራር በማስኬድ፣ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎች ጭምር በመካድ ያለውን ሥርዓት ለማገልገል ከሞከሩ ከጭቃው ውስጥ መውጣት አይቻልም፡፡ ይልቁንም ትክክለኛና ሚዛናዊ የሆነ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሐሳብና መረጃዎችን ለሕዝቡ ማድረስ አለባቸው፡፡ የሚበጀውን መወሰን ደግሞ የሕዝብ ድርሻ ይሆናል፡፡

እንኳንስ በሕዝብ ሀብት የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኃን፣ የግል ሚዲያዎችና  የማኅበራዊ አንቂዎች የአንዱን ብሔር/ፓርቲ ሐሳብ ሙሉውን አስተላልፎ የሌላውን መልዕክት ቆራርጦ ማቅረብ፣ ወይም አሳስቶና አወናብዶ ማስተላለፍ ሙያዊም ፍትሐዊም አለመሆኑን ከግምት ማስገባት አለባቸው፡፡ የሞራልና የሕግ ተጠያቂነት እንዳለ ሊረዱ ግድ ነው፡፡ ታሪካዊ ኃላፊነትን እንዳለመወጣትም መቆጠሩም አይቀርም፡፡ እባካችሁ ከኖረው በሽታችን ተላቀን የመፍትሔው አካል እንሁን ብሎ በጋራ መነሳትም ለሁሉም ባለድርሻዎች የሚሰጥ የአገር ጥሪ ሊሆን ይገባል፡፡

በመሠረታዊ ልዩነቶችና አከራካሪ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና አገረ መንግሥቱን የሚያስከብር፣ በፌዴራል መርሆዎች ላይ የተመሠረተ፣ በነፃ ምርጫና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር፣ በእምነትና በፆታ እኩልነት የሚሠራ የሕግ የበላይነት፣ ወዘተ ለመሳሰሉት እሴቶች ዘብ ቆሞ የተለያዩ አመለካከቶችን ከማቀራረብና አገርን ከማረጋጋት በላይ ትልቅ ክብር የሚያሰጥ ተግባር ስለሌለ ቸል አይባል፡፡ እናም ሚዲያና ተዋናዩ በአገራችን ሰላም ይሰፍን ዘንድ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲ እንዲዋለድም ትልቁን ድርሻ መወጣት ግድ ይላቸዋል፡፡

የዕለቱን ጽሑፍ የምቋጨው በአቶ አንዳርጋቸው አሰግድ ሐሳብ ነው፡፡ ‹‹…አሉታዊ የታሪክ ሸክሞችን በሚመለከት ያለው ብቸኛ የሰላምና የአብሮነት መንገድ በአንድ ወገን የሩቁን አከራካሪ ታሪኮች ለታሪክ ተመራማሪዎች እውነትን ፍለጋ፣ ለፍትሕና ዕርቅ መንገዶች መተው ነው፡፡ በሌላው ወገን የቅርብ ጊዜ (የድኅረ 1983) ግጭቶችን በሚመለከት ግን ያለው ብቸኛ የሰላምና የአብሮነት መንገድ የጋራ ወደፊትን በጋራ መራመድ ነው፡፡ ለዚህም በድርድር፣ በፍትሕና በዕርቅ መንገዶች ተቃርኖዎችን ለመፍታት መጣር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰዎች በዚህ ላይ ርዕዮተ ዓለማዊ አቋምንና ፖለቲካዊ መንገዶችን በአግባቡ ቢለዩ፣ ብዙ ርቀቶች አብሮ ለመሄድ ይቻላቸዋል፡፡››  (2013፣ 73)

ስለሆነም ጦርነት፣ መገዳደልና መበጣበጥ ይብቃ እንላለን፡፡ በቃ ካላልን ደግሞ እንደ ሚያጠፋፋን አንዘንጋ፡፡ እናም በየመስኩ የተሰማራችሁ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የመንግሥት አካላትና ኃላፊነት የሚሰማችሁ የሰው ልጆች ሁሉ ከወዲሁ የሰላም ጥሪ አሰሙ፣ ለዕርቅና ለሰላም ሥሩ፡፡ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች/ተፋላሚዎችም ብትሆኑ ከመንግሥት ጋር የማያግባቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በሰበብነት በመደርደር ሳይሆን፣ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ሚዛናዊ ጥያቄዎችን በማቅረብ የመፍትሔው አካል ለመሆን ተሰናዱ፡፡

ሕዝቡም የእርስ በርስ ጥላቻን ሳይሆን ችግሮችን ለመፍታት፣ የመነጋገርና የመቻቻል አካሄድን ባህሉ እንዲያደርግ ለማስተማርና የራሱን ግንዛቤ ወስዶ በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሰላማዊ ውሳኔውን እንዲሰጥ ለማስቻል ይሥራ፡፡ ሕዝብንና የደሃ አገርን ሀብት እየማገዱ፣ ‹‹እልህ ምላጭ ያስውጣል›› በሚል አስተሳሰብ መቀጠል ግን ፍፃሜው ተያይዞ መውደቅ መሆኑን ለመናገር ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን  እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...