Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የአዲስ አበባ ከተማ ቄራዎች ድርጅትን የማዘመን ጅማሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቄራዎች ድርጅት ከተቋቋመ 67 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ድርጅቱ በፊት ከነበረበት አሮጌው ቄራ ተነስቶ አሁን የሚገኝበት ቄራ ሊቋቋም የቻለው የቄራዎች ድርጅት ከከተማው ውጪ መሆን አለበት ከሚል ዕሳቤ ነው፡፡ አሁን የሚገኝበት ቦታ ደግሞ ከከተማው መስፋፋትና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ከተማ ሆኗል፡፡ ከስድስት አሠርታት በላይ ያስቆጠረው ድርጅቱ ዘመኑን በዋጀ መልኩ መሻሻል ይኖርበታል፡፡ የማሻሻያው ሥራ አሁን ባለበት ቦታ ላይ ይሁን? ወይስ እንደተለመደው ከከተማ ወጣ ባለ ቦታ ይቋቋም? የሚለውን በጥናት ለማየት ተሞክሯል፡፡ አቶ ሠዒድ እንድሪስ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በድርጅቱ እንቅስቃሴ፣ በማስፋፋቱ ሥራና ተያየዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅትን ተልዕኮ፣ የሥራ ትኩረት፣ የአሠራርና አደረጃጀቱን ቢያብራሩት?

አቶ ሠዒድ፡- የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የሥራ ድርሻ ለምግብ የሚውሉ እንስሳትን የዕርድ አገልግሎት መስጠትና ከዚህም የሚገኘውን ተረፈ ምርቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ተጠቃሚዎች ማቅረብ ነው፡፡ አገልግሎት የሚሰጠው ለ24 ሰዓታት ሲሆን፣ ሥራውም የሚከናወነው በሦስት ፈረቃዎች በመደራጀት ነው፡፡ ይህም አደረጃጀት እንዲኖር ያስፈለገው ማንኛውም ደንበኛ ወይም ልኳንዳ ነጋዴ በፈለገበትና በሚያመቸው ጊዜ ወይም ሰዓት አገልግሎቱን ያለምንም ውጣ ውረድና ችግር በቀላሉ እንዲያገኝ ለማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለልኳንዳ ነጋዴዎች የምትሰጡት ለአገልግሎት ምን ይመስላል?

አቶ ሠዒድ፡- ድርጅቱ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ 16 የሥርጭት መስመሮች አሉት፡፡ በእነዚህ መስመሮች የሚገኙ ልኳንዳ ነጋዴዎችና ደንበኞች የየራሳቸው ኮድና አካውንት ቁጥር አላቸው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ነጋዴ ለንርድ የሚውሉ እንስሳትን ሲያቀርብ በመጀመሪያ የዕግድ ፈቃዱን ይዞ መምጣት አለበት፡፡ ነጋዴው የማይመቸው ከሆነ ደግሞ ‹‹በቄራ አመቻች ማኅበር›› አማካይነት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ማኅበሩ ሕጋዊ ዕውቅናና በድርጅቱም ዘንድ ተቀባይነት አለው፡፡ እንስሳት ወደ ድርጅቱ እንደገቡ ወገባቸው ወይም ጀርባቸው ላይ የደንበኛው ኮድ ይጻፍበታል፡፡ በየሥርጭት መስመሮችም እንዲደረደሩ ይደረጋል፡፡ ከዚያም በቁም የጤንነት ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ ጤና ከሆኑ ለዕርድ ይዘጋጃሉ፡፡ ብቁ ያልሆነው ደግሞ ወደ ማቆያ በረት ይወሰዳል፡፡ የጤንነቱ ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላ በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖት አባቶች እንስሳቱ ተባርከው ወደ ዕርድ እንዲገቡና እንዲታረዱ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ብቁ ያልሆኑት እንስሳት ለምንድነው ወደ ማቆያ በረት የሚሄዱት?

አቶ ሠዒድ፡- ወደ ማቆያ በረት እንዲወሰዱ የሚደረገውም ተጨማሪ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ወደ ፊት የሚታይበት ሒደት ስላለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምርመራ የሚያደርጉ ሐኪሞችንና የሃይማኖት አባቶችን በተመለከተ በዝርዝር ቢያስረዱን?

አቶ ሠዒድ፡- የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የምርመራና የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችሉ 43 የእንስሳት ሐኮሞች አሉት፡፡ ከሚባርኩትም አባቶች መካከል የክርስቲያኑን አባት የሚመድበው የአዲስ አበባ ቤተ ክህነት ሲሆን፣ የሙስሊሙን አባት የሚመድበው የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ቤተ ክህነቱና ጽሕፈት ቤቱ አባቶችን የሚመድቡት ለሥራቸው ብቁና ችሎታ ያላቸው መሆናቸውን በማስረገጥ ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚላኩት አባቶች ደግሞ የድርጅቱ ቋሚ ሠራተኛ ይሆናሉ፡፡ በደመወዝ መክፈያ ሰነድ (ፔሮልም) ይመዘገባሉ፡፡   

ሪፖርተር፡- በቀን ወይም በዓመት ስንት እንስሳት ይታረዳሉ?

አቶ ሠዒድ፡- በቀን በአማካይ ወደ 800፣ በዓመት ደግሞ ከ250,000 በላይ የዳልጋ ከብቶችና ከ200,000 በላይ በግና ፍየሎች ይታረዳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- እንስሳቱ ከታረዱ በኋላ ለየልኳንዳ ቤቱ የሚዳረሰው እንዴት ነው? የጤንነት ምርመራ የሚደረግላቸው በቁመናቸው ሳሉ ብቻ ነው? ወይስ ሥጋውም ይመረመራል?

አቶ ሠዒድ፡- እንስሳቱ የጤንነት ምርመራ የሚደረግላቸው በቁመናቸውና ከታረዱም በኋላ ነው፡፡ በቁም ከዚያም ከታረደ በኋላ እያንዳነዱ የሥጋ ብልት ምርመራ የተደረገበት መሆኑንና በሁለቱም ሃይማኖቶች እምነት መሠረት መባረኩ ከተረጋገጠ በኋላ፣ በየሥርጭት መስመሮች ለሥምሪት በተዘጋጁ ተሽከርካሪዎች ላይ የሥጋ ምርቱ እየተጫነ ይጓጓዛል፡፡  

ሪፖርተር፡- በድርጅቱ ውስጥ የሚታረዱት እንስሳት ምን ዓይነት ናቸው? በቀን ብዙ እንስሳት እንደሚታረድ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንድ የድርጅቱ ተሽከርሪዎች የማጓጓዝ አቅማቸው እንዴት ይታያል?

አቶ ሠዒድ፡- በድርጅቱ ውስጥ የሚታረዱት እንስሳት በሁለቱም ሃይማኖቶች እምነት መሠረት ሊበሉ የሚችሉ ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነ ዕርድ ፈጽሞ አይከናወንም፡፡ የሥጋው ምርት ወደ ልኳንዳ ቤቶች የሚጓጓዘው በሁለት ዓይነት ተሽከርከሪዎች ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ዓይነት ትልልቅና የድርጅቱ ንብረት የሆኑ ተሽከርካሪዎች ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ዓይነት ተሽከርካሪዎች ደግሞ አነስተኛና የግል ናቸው፡፡ ሦስት፣ አራትና ከዚያም በላይ የሆኑ የእንስሳት ምርት በትልልቁ፣ ከዚህ በታች የሆኑ ደግም በትንንሾቹ ተሽከርካሪዎች ይጓጓዛሉ፡፡ የግል ተሽከርካሪዎቹ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው፣ በድርጅቱ ዕውቅና የተቸራቸውና በየጊዜውም ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግላቸው ናቸው፡፡ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ለዚህ ሥራ ያስፈለጉበት ምክንያት ሰዓት ሳይገድባቸው በፍጥነት የማጓጓዝ አቅም ስላላቸው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከዕርድ አገልግሎት የሚገኙ ተረፈ ምርቶች በምን ጥቅም ላይ ይውላሉ?

አቶ ሠዒድ፡- ከዕርድ አገልግሎት ከሚገኙ ተረፈ ምርቶች መካከል አንዳንዶቹ ፕሮሰስ ይደረጋሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በጥሬያቸው ይዘጋጃሉ፡፡ ፐሮሰስ ከሚደረጉና በጥሬያቸው ከሚዘጋጁትም ውስጥ የተወሰኑት ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ፡፡ የተወሰኑ ደግሞ የውጭ ምንዛሪን በሚተካ መልክ ይውላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ልብና ሐሞት ወደ ውጭ ይላካሉ፡፡ አብዛኛው የውጭ ገበያው ቻይና ናት፡፡ ሥጋና አጥነት ተፈጭተው ለዶሮና ለውሻ መኖ ይውላሉ፡፡ መኖ በዚህ መልኩ ባይዘጋጅ ኖሮ ከውጭ አገር ማስመጣት ግድ ይሆን ነበር፡፡ ሞራው ደግሞ በደንብ ከተነጠረ በኋላ ለሳሙና ማምረቻ ይውላል፡፡   

ሪፖርተር፡- ለድርጅታችሁ ማስፋፊያ እንዲውል የተዘጋጀው ቦታ አሁን በምን ደረጃ ይገኛል? የማስፋፊያ ሥራው የተጓተተ ይመስላል፡፡ ሊያብራሩልን ይችላሉ?

አቶ ሠዒድ፡- ሃና ማሪያም አካባቢ መሬት ተረክበን አበዳሪና አማካሪ ድርጅቶች መረጣ ከተከናወነ በኋላ ወደ ቀጣይ ሥራ ከመግባቱ አስቀድሞ አሁን ያለው የለውጥ መንግሥት መጣ፡፡ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ሌሎች ችግሮች መጀመሪያ እንፍታ በሚል አመለካከት የተነሳ ይህኛው እንዲዘገይ ተደረገ፡፡ በዚህ መካከል ቀደም ሲል በቦታው ላይ የነበሩና እንዲነሱም ተደርገው የነበሩ ወገኖች እንደገና ተመልሰው ሠፍረዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ በዚህ ቦታ ላይ ለሚያካሂደው የማስፈፊያ ሥራ የሚውል ገንዘብ ከየት ያገኛል ተብሎ ይታሰባል? በቦታው ያሉትን ሰዎች የማስነሳቱ ሁኔታ በምን መልኩ ነው የሚከናወነው?

አቶ ሠዒድ፡- ድርጅቱ በተጠቀሰው ቦታ ላይ ዘመናዊነቱን በጠበቀ መልክ የሚገነባው ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች በሚገኝ ብድር ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ ደግሞ ብድሩን የሚሰጡት በቦታው ላይ የሠፈሩትን ሰዎች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአግባቡ አስነስቶ በሌላ ቦታ በማሥፈር ነው፡፡ ቄራን ማዘመን እንጂ ከከተማ ውጪ ማውጣት ብቻ መፍትሔ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የትም ቦታ ቢኬድ ሽታ መፍጠርና አካባቢን መበከል የለበትም፡፡ ስለዚህም ለማዘመን የትም ቦታ ችግር የለም፡፡   

ሪፖርተር፡- ከአነጋገርዎ እንደተረዳሁት ድርጅቱን አሁን ባለበት ሥፍራ ላይ ማዘመን ይቻላል፡፡ ማዘመኑ እንዴት እንደሚከናወን ቢያብራሩት?

አቶ ሠዒድ፡- ድርጀቱ አሁን ባለበት ሥፍራ ሆኖ ለማዘመን የሚያስችል ጥናት አስጠንተናል፡፡ ማስተር ፕላንም (ዲዛይን) አሠርተናል፡፡ የሕንፃው ዲዛይም እንደሚያመላክተው ከሆነ ለዋናው መሥሪያ ቤት ወይም ለድርጅቱ የሚውሉ ልዩ ልዩ ቢሮዎች፣ ለንግድ አገልግሎት የሚውል የሥጋ መደብር (ሚት ሞል)፣ ሰው እየተመገበ የሚዝናናበት፣ የተለያዩ የሥጋ ማቀነባበሪዎች፣ ወዘተ ይኖረዋል፡፡ ለዚህም ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ የተወሰነውን ከራሳችን፣ ቀሪውን ፋይናንስ ደግሞ በብድር ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በድርጅቱ ቦርድ ፀድቋል፡፡ ይህ ሲታሰብ ደግሞ ቄራ ብቻ ሳይሆን የእንስሳት መሸጫ በረቶችም አብረው መታየት አለባቸው፡፡ በዚህ መልኩ ድርጅቱን አሁን ባለበት ቦታ ማዘመን ይቻላል፡፡ ይቀየራል ከተባለ ግን የእንስሳት መሸጫ ማዕከላትን ያማከለ መሆን አለበት፡፡   

ሪፖርተር፡- ሃና ማሪያም ያለው ቦታ ይዞታውንና አሁን በማን እጅ እንዳለ ቢገልጹልን?

አቶ ሠዒድ፡- ቦታው 20 ሔክታር መሬት ሲሆን፣ በድርጅቱ ስም ካርታ አለው፡፡ አጠገቡም ለእንስሳት መሸጫ ማዕከል የሚሆን ስድስት ሔክታር መሬት ተይዞለታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በቦታው ላይ 52 አርሶ አደሮች ሠፍረውበታል፡፡ ወደ ፊት በሕጉና በአግባቡ መሠረት ተነስተው ወደ ሚዘጋጅላቸው ቦታ ይዛወራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱን የማዘመን ጅማሮ አለ ለማለት ይቻላል?

አቶ ሠዒድ፡- አዎ! አለ፡፡ ለዚህም በ62 ሚሊዮን ብር ወጪ የተረፈ ምርት ማቀነባሪያውን ዘመናዊ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ማቀነባበሪያው አጥንት የሚፈጭና መኖዎችን የሚቀቅል ማሽን ነው፡፡ ማሽኑ ወደ ውጭ የሚተነውን መጥፎ ጠረን የሚያጠፋ መሣሪያ ተገጥሞለታል፡፡ ለዚህም የሚውሉ ልዩ ልዩ መለዋወጫዎች ቀርበው አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓል፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...