Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአንድ ወር ዕድሜ የቀረው የአፍሪካ ዋንጫና ዝግጅቱ

የአንድ ወር ዕድሜ የቀረው የአፍሪካ ዋንጫና ዝግጅቱ

ቀን:

በአፍሪካ ትልቁና አንጋፋው የእግር ኳስ ውድድር በአይቮሪኮስት ሊስተናገድ የአንድ ወር ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡

በአብዛኛው አፍሪካውያን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ለማሰናዳት የምዕራብ አፍሪካዋ አገር አይቮሪኮት ዝግጅቷ አጠናቃ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡

እ.ኤ.አ. በ1984 ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ማሰናዳት የቻለችው አይቮሪኮስት፣ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ታስተናግዳለች፡፡ 34ኛ ምዕራፍ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ከጥር 4 እስከ የካቲት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ይከናወናል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ማግሥት በሚከናወነው የዋንጫ ጨዋታ 24 ቡድኖች ይሳተፋሉ፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ስማቸውን የተከሉ ተጫዋቾች ውድድሩን እንደሚያደምቁት ይጠበቃል፡፡

በመጪው ሐምሌ ወር ለማድረግ መርሐ ግብር ተይዞለት የነበረው ውድድሩ፣ በአይቮሪኮስት ከፍተኛ የዝናብ ወቅት ስለሚሆን በጥር ወር እንዲደረግ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

አይቮሪኮስት የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማሰናዳት ኃላፊነቱን ብትረከብም፣ በአንፃሩ በቂ ዝግጅት ባለማድረጓና የስታዲየም ግንባታዎች ባለመጠናቀቃቸው ለካሜሮን መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በመክፈቻው ቀን አዘጋጇ አይቮሪኮስት ከጊኒ ቢሳዎ ጋር አቢጃን በሚገኘው አሊሳጌ አውታራ ስታዲየም በመጠጋጠም የአፍሪካ ዋንጫው በይፋ ይጀምራል፡፡

በመክፈቻው ቀን መርሐ ግብር የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ግብፅ በምድብ ‹‹ለ›› ሞዛምቢክን የካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ሴኔጋል በምድብ ‹‹ሐ›› ጋምቢያን ይገጥማሉ፡፡

በኳታር የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ የገባው የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በዓለም 13ኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ ሆኖም ብሔራዊ ቡድኑ ኢትዮጵያ በ1968 ዓ.ም. ባዘጋጀችው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ካገኘ በኋላ ማሸነፍ አልቻለም፡፡  ሞሮኮ በምድብ ስድስት፣ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ዛምቢያና ታንዛኒያ ጋር ተደልድሏል፡፡

ከመክፈቻው ቀን ጨዋታ በኋላ በየቀኑ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች እንደሚደረጉ ተገልጿል፡፡

ከየምድቡ ሁለት ቡድኖች በቀጥታ ሲያልፉ አራት ምርጥ ሦስተኛ ብሔራዊ ቡድኖች ወደ 16 ውስጥ ይካተታሉ፡፡

ከ12 ዓመት በፊት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የነበረችው አይቮሪኮስት የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋቾችን ታሰባስባለች፡፡ ስድስት ስታዲየሞች ለውድድር ተሰናድተዋል፡፡ ስታዲየሞች እድሳት የተደረገላቸው እንዲሁም እንደ አዲስ የተገነቡ ናቸው፡፡

የአይቮሪኮስት መንግሥት ለስታዲየሞቹ ግንባታ እንዲሁም የተለያዩ መሠረተ ልማቶች አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጓል፡፡ 20 ሺሕ ተመልካቾች የመያዝ አቅም ያላቸውን ሦስት ስታዲየሞች እንደ አዲስ ገንብቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሁሉም ስታዲየም አቅራቢያዎች 12 የልምምድ ሜዳዎች ተገንብተዋል፡፡ አዲስ ከተገነቡት ስታዲየሞች ውጪ ያሉ እድሳት የተደረገላቸው ስታዲየሞች አሊሳጌ አውታራ 60,000 ተመልካቾች መያዝ አቅም ሲኖረው፣ ቀሪዎቹ ሁለት ስታዲየሞች 33,000 እና 40,000 ተመልካቾች የመያዝ አቅም አላቸው፡፡

ሌላው የውድድር መጫወቻ ‹‹ፓኩ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህም የቀድሞ አይቮሪኮስት ተጫዋቾች የነበረውን ሎረንታ ፓኩ ለመዘከር በማሰብ ስያሜ መሰጠቱ ተነስቷል፡፡

ፓኩ እ.ኤ.አ. 1970 አይቮሪኮስት ከኢትዮጵያ ባደረገችው ጨዋታ 6ለ1 ስታሸንፍ አምስት ጎሎችን ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡

የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያዊው በአምላክ ተሰማን ጨምሮ በአጠቃላይ 32 ዋና ዳኞች፣ 33 ረዳት ዳኞች፣ አራት የቪዲዮ ዳኞች፣ ስድስት የቴክኒክና የአካል ብቃት ባለሙያዎች ይመሩታል፡፡

ከአይቮሪኮስት የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት በዘለለ ማን ዋንጫው ያነሳል? የሚለው የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ የተገናኙት የሴኔጋልና የግብፅ ብሔራዊ ቡድኖች ከፍተኛ ግምት አግኝተዋል፡፡

በ2019 አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮናዋ አልጄሪያ በካሜሮን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ደካማ አቅም ብታሳይም በአይቮሪኮስት ልታሳካው እንደምትችል ከወዲሁ ግምት ካገኙ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ተጠቅሳለች፡፡

ሞሮኮ የአይቮሪኮስት አፍሪካ ዋንጫን እንደምታሳካ ከፍተኛ ግምት ካገኙ ብሔራዊ ቡድኖች ቀዳሚዋ ናት፡፡

አዘጋጇ አይቮሪኮስት ሌላዋ ግምት ያገኘችው ብሔራዊ ቡድኖችን ስትሆን ከዲዲየር ድሮግባና ያያ ቶሬ በኋላ ስመጥር ተጫዋቾች ማፍራት አለመቻሏ ግን ተወስቷል፡፡ በካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ በመለያ ምት የተረታችው ግብፅ በአጥቂዋ መሐመድ ሳላህ ተስፋ መሰነቋ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የናይጄሪያ፣ ጋና እንዲሁም ካሜሮን ብሔራዊ ቡድኖች በውድድሩ ከፍተኛ ግምት ካገኙ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በአውሮፓ በተለያዩ ክለቦች እየተጫወቱ የሚገኙ  ወጣት አፍሪካውያን ተጫዋቾችና ልምድ ያካበቱ ተጫዋቾች በአይቮሪኮስት ይጠበቃሉ፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...