Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቢጂአይ ኢትዮጵያ ምርት አከፋፋዮች በሌሎች አከፋፋዮች ሊተኩ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ምርቱን በእጥፍ እንደሚያሳድግ አስታወቀ

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ባዘጋጀው አዲሱ ስትራቴጂ መሠረት በአሁኑ ጊዜ በገበያ ተወዳዳሪነት የተሻለ ለመሆን፣ የሥርጭት ሥርዓቱን በማዘመን ከውጭ ሆነው የሚሠሩ አከፋፋዮችን (outsource distributer agents) በራሱ ባዘጋጃቸው ለመተካት ማቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናገሩ፡፡

ኩባንያው በነደፈው አዲስ ስትራቴጂ መሠረት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ምርቱን በእጥፍ እንደሚያሳድግና በአሁን ጊዜ አምስት ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ቢራ እንደሚያመርትና በእጥፍ በማሳደግ አሥር ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር እንደሚያሳድግም ገልጿል፡፡

የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሄርቬ ሚልሃድ ማክሰኞ ታኅሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኩባንያው ስድስት የተለያዩ ግቦችን የያዘ ስትራቴጂ ለመተግበር አቅዷል ብለዋል፡፡ የመጀመሪያው ስትራቴጂ ‹አንድ የሆነ› ቢጂአይ ፋብሪካ መመሥረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቢጂአይ የተለያዩ የቢራ ፋብሪካዎችን በመግዛት ሲሠራ የቆየ በመሆኑ፣ የተለያዩ ፋብሪካዎቹን በአንድ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በማድረግ ትልቅ ብቃት መፍጠር ዕቅዱ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን በቢጂአይ ሥር ለማጠቃለል፣ አዲስ አበባ የሚገኘውን ፋብሪካ ሰበታና ማይጨው የራያ ቢራ ፋብሪካዎች የማዘዋወር ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ በውኃ አቅርቦት ውስንነትና በሎጂስቲክስ ተግዳሮቶች ምክንያት በአዲስ አበባ መሀል ከተማ የሚገኘውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካውን ለማንሳት መገደዱን አስረድተዋል፡፡

አዲስ አበባ የሚገኘውን ፋብሪካ ለማንሳት ሰባት ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ መሆኑንና ወደ ራያ የሚሄደው የጠርሙስ ማምረቻ፣ እንዲሁም ወደ ሰበታ የሚሄዱት የፋብሪካ ዕቃዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሠራተኞችን ጥቅም በሚያስከብር መንገድ የሰው ኃይልን ማዘመን የሥራ ሒደት ለማከናወን፣ እንዲሁም የተሻለ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን ለመቅጠር መታቀዱ ሌላው ስትራቴጂ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት የቢጂአይ ሠራተኞች ለሪፖርተር የተናገሩት ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ዕቅድ ጋር የተለያየ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሠራተኞቹ ለሪፖርተር በሰጡት መረጃ መሠረት አሁን ያሉት ሠራተኞች ያለ ፍላጎታቸው ከጊዜያቸው በፊት ቀድመው ጡረታ (early retirement) እንዲወጡ እየተገደዱ መሆኑን፣ የጡረታ ክፍያቸው የ18 ወራት እንደሆነ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ኩባንያው ከጊዜያቸው ቀድመው ጡረታ የወጡ (early retirement) እና ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ ሠራተኞች እንዳገለገሉባቸው ዓመታት መጠን፣ እስከ 48 ወራት የሚጠጋ ደመወዝ መክፈሉን አስታውቋል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከተመሠረተ 25 ዓመታት ቢሆኑም፣ አሁን በሥሩ ያሉት ፋብሪካዎች ከ50 እና ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የቢጂአይ ኢትዮጵያን አዲሱ ስትራቴጂካ መተግበር ያስፈለገው በኢትዮጵያ ከተፈጠረው የገበያ ለውጥ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን፣ እንዲሁም የኩባንያውን ዕድገት ለማፋጠን መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያው በዓመት 7.4 ቢሊዮን ብር ግብር በመክፈል ከፍተኛ ግብር ከፋይ በመሆኑ ለማኅበረሰቡ መልሶ የመስጠት ሥራ አንዱ ስትራቴጂ በማድረግ የትምህርት፣ የጤናና የአካባቢያዊ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ሰባት ፋብሪካዎቹ 3,500 ቋሚ ሠራተኞችና 2,000 ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዳሉት አስታወቋል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ የሜታ አቦ ፋብሪካን ጨምሮ የተለያዩ ፋብሪካዎችን በመግዛት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም በማይጨው (ራያ)፣ በኮምቦልቻ፣ በሐዋሳ፣ በዘቢዳርና በዝዋይ በሚገኙት ፋብሪካዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ካስቴል፣ ሜታ ቢራና ድራፍት፣ የሪፍት ቫሊ የወይን ምርቶች፣ እንዲሁም ስንቅ ከአልኮል ነፃ መጠጥ በማምረት ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች