Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሴቶች ለመማር የሚከፍሉት ዋጋ

ሴቶች ለመማር የሚከፍሉት ዋጋ

ቀን:

በሴቶች ላይ ፆታን መሠረት ያደረጉ ሥነ ልቦናዊ፣ አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቃቶች ከሌላው ማኅበረሰብ በተለየ ይፈጸማል፡፡ የጥቃቶቹ መነሻዎች ማኅበራዊ ሕግን መሠረት ያደረጉ ሲሆኑ፣ ይህም ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ልጆችን፣ ቤተሰብንና አጠቃላይ ማኅበረሰብን እየጎዳ ነው፡፡

ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከልና መብቶቻቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ በርካታ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ሕጎች፣ መመርያዎችና ፖሊሲዎች ቢኖሩም ጥቃቶቹ ሊቀሩ አልቻሉም፡፡

ሴቶች ለመማር የሚከፍሉት ዋጋ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሴቶች በቅርብ ቤተሰብ ከሚደርስባቸው ጥቃት በተጨማሪ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች በሚካሄዱ ግጭቶች፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሌሎችም ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ ይበልጥ ተጎጂ ሆነዋል፡፡ ጉዳቱ ለሁሉም ማኅበረሰብ የሚደርስ ቢሆንም፣ በሴቷ ላይ የሚደርሰው ጉዳት የተለየና ተደራራቢ ሆኖ ፆታዋን መሠረት ማድረጉ ችግሩን አባብሶታል፡፡

ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ግጭት ብቻ ሳይሆን ጦርነት ያሉባቸው ሥፍራዎች በመኖራቸው፣ ሴቶች ይበልጥ ለጥቃት ተጋልጠዋል፡፡ ይህንን እንዴት እናስቀር፣ ሥራዎች አልተሠሩም ወይ? ምን እናድርግ? በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል ኢንቨስት እናድርግ በሚል፣ በ16ቱ ፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀናት ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ይቆሙ ዘንድ የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡

ውይይት ከተደረገባቸው እንኳር አጀንዳዎች አንዱ፣ በኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራት ኅብረት ታኅሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሴቶች ትምህርት ሕግ፣ ፖሊሲና ማዕቀፎች ያሉባቸው ክፍተቶችና ዕድሎች በሚል የተዘጋጀው መድረክ ይገኝበታል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የተረቀቀው የትምህርት ምዘናና ከክፍል ክፍል ዝውውር መመርያና በአጠቃላይ የሴቶች ትምህርት ዙሪያ በተደረገው ውይይት፣ ረቂቁ የሴቶች ትምህርት የመማር ሁኔታ ዝቅ ባላለበት ሁኔታ ላይ የሴቶችን የመማር መብት የሚጥስ ሆኖ ማግኘታቸውን፣ የኅብረቱ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አዜብ ቀለመወርቅ ተናግረዋል፡፡

በዚሁ አጀንዳና አጠቃላይ በሴቶች ትምህርት ዙሪያ በትምህርት ሚኒስቴር የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ቡድን መሪ አቶ እስክንድር ላቀው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የሴቶች ትምህርትን ቁልፍ ችግሮችና ዕድሎች ይዞ እንዴት መሥራት ይቻላል? ችግሮቹ እንዴት ይፈቱ በሚሉ ሐሳቦች ዙሪያ አስተያየት የሰጡት አቶ እስክንድር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥርዓተ ፆታ አጀንዳ በተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ቢገባም፣ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት አሁንም የዓለም አጀንዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመርም የሚኒልክ አዋጅ፣ ‹‹አንድም ሰው ከትምህርት መቅረት የለበትም›› የሚል እንደነበረ፣  የቀደመው ፖሊሲም ከዓላማ ጀምሮ ለሴቶች ትምህርት አዎንታዊ ድጋፍ እንደነበረው፣ በየካቲት 2015 ዓ.ም. የወጣው አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲም ለሴቶች ትምህርት ትኩረት መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም ሴቶችን ለማስተማር ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉ፡፡ ሴቶችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት የመጀመሪያውና ትልቁ ፈተና ነው፡፡ ከፍተኛ ድህነትና ኋላቀርነት ባለበት አገር ውስጥ በተለይ ማኅበረሰቡ ለሴቶች ትምህርት ያለው ቅበላ አነስተኛ በሆነበት፣ ከ100 ሴቶች 42 ያህሉ ጎጂ ልማድ ባጠላበት በሚኖሩበት፣ ሴቶችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ይህንን ፈተና አልፋ ወደ ትምህርት ቤት የገባችን ሴት ትምህርት ቤት ማቆየትም ሌላው ፈተና ነው፡፡

የሴት ተማሪዎች ማቋረጥ ከቅድመ መደበኛ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን፣ በማስተርስና ዶክትሬት ትምህርት ደረጃ ጭምር ሴቶች በሚደርስባቸው ትንኮሳ ትምህርት ያቋርጣሉ፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ያለው ደግሞ ይበልጥ ትኩረትና ምላሽ ያላገኘ ችግር ነው፡፡

ሴቶችን ትምህርት ቤት አስገብቶና አቆይቶ በመጨረሻ ውጤታማ ማድረግ ሦስተኛው ችግር ሲሆን፣ ይህም ሴቶችን በሚፈለገው መጠን በአመራር ደረጃ እንዳናያቸው ማድረጉን አቶ እስክንድር ተናግረዋል፡፡

ሴት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት፣ ማቆየትና ውጤታማ ማድረግ ለምን ፈታኝ ሆነ?

እንደ አቶ እስክንድር፣ በኢትዮጵያ የመማር ማስተማር ሒደት የሴት ተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ ከፍተኛ ነው፡፡ ትንኮሳ፣ ጥቃት፣ ጋብቻ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት፣ የኢኮኖሚና ሌሎችም ለዚህ ምክንያት ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ የመጠነ ማቋረጥ ደረጃውም ጤናማ አገር ከሚያስመዘግበው ከአምስት እስከ ሰባት በመቶ ልቆ፣ ከ17 እስከ 20 በመቶ ነው፡፡

የመድገም ሁኔታ እየተሻሻለ ቢመጣም፣ ከፍተኛ ነው፡፡ 47 በመቶ ሴቶች ክፍል ይደግማሉ፡፡ ለአብነት አንድ ሚሊዮን ሴቶች ትምህርት ቤት ገብተው ቢሆን፣ ከስድስት ዓመት በኋላ ሲታዩ 47 ሺሕ ያህሉ የሉም ማለት ነው፡፡

የሥርዓተ ፆታ አቻነት ሲታይም፣ በቅድመ መደበኛ 100 ወንድ 91 ሴት፣ መጀመርያ ደረጃ 100 ወንድ 97 ሴት፣ መካከኛ ደረጃ 100 ወንድ 94 ሴት፣ ሁለተኛ ደረጃ 100 ወንድ 89 ሴት ነው፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲደርሱ ደግሞ በሁሉም ደረጃ ሴቶች 37 በመቶ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የሥርዓተ ፆታ አቻነት ችግርን ያሳያል፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ በጣም አባዊ የሚባል ዘርፍ መሆኑም ሌላው ለሴቶች ትምህርት ፈተና ከሆኑት ይጠቀሳል፡፡ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች ሲታይ ሴቶች በመጀመርያ ደረጃ 17 በመቶ፣ በሁለተኛ ደረጃ 11 በመቶ ሴቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ካሉት 47 ሺሕ ትምህርት ቤቶች በሱፐርቫይዘርነት ደረጃ፣ በሁለተኛ ዘጠኝ በመቶ  ደረጃና 11 በመቶ በመጀመርያ ደረጃ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያ 39 ኮሌጆች ሲኖሯት፣ በእነዚህ በዲንነት የሚያገለግሉ ሴቶች ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩ የሉም ማለት ይቻላል ያሉት አቶ እስክንድር፣ በ2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ከነበሩት 33 ዩኒቨርሲቲዎች አንድም ዋናና ምክትል ሴት ፕሬዚዳንት እንዳልነበሩ ያስታውሳሉ፡፡

በኋላ በተሰጠ ትዕዛዝ በ27 ዩኒቨርሲቲዎች ሴቶች ምክትል ፕሬዚዳንት ቢደረጉም፣ አሁን ባሉት 48 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንድም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የለችም፡፡

ትምህርት ቤት አካባቢ በየጊዜው ዓይነታቸውን እየቀያየሩ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ደግሞ ሴቶች ከመማር ጀምሮ ወደ አመራርነት እንዳይደርሱ ከሚያደርጉ ምክንያቶች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ይመደባሉ፡፡

ለአብነትም ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በውጤትና ከሌሎች ጋር ተያይዞ የሚመጡ የጥቃት መረጃዎች፣ አሁን ላይ ሁለተኛ ደረጃና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥም መከሰት ጀምረዋል፡፡ በሴቶችም በወንዶችም ላይ የሚታዩት ጥቃቶች በተለይ ለሴቶች ትምህርት ፈተናና ለኢትዮጵያም ልትሻገረው ያልቻለችው ፈተና ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ የሴቶች ትምህርት ስትራቴጂ ቢኖራትም፣ ለመተግበር የተለያዩ ፈተናዎች አሉ፡፡ አንዱና ዋነኛው የውኃና የመፀዳጃ ቤቶች ተሟልቶ አለመገኘት ነው፡፡ ውኃ ብርቅ የሆነባቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ የሚገኙ መሆኑን ያስታወሱት አቶ እስክንድር፣ በዚህም ሴቶች፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞችም  የመጀመርያ ተጎጂና ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት መሠረታዊ ጉዳይ ቢሆንም፣ አዋቂዎች ጭምር  በግልጽ የማይነጋገሩበት መሆኑ፣ በተለይ ሴት ልጆች እንዲጎዱና መረጃ እንዳያገኙ አድርጓል፡፡

የቤተ መጻሕፍትና ቤተ ሙከራዎች ደረጃቸውን የጠበቁና ለሴቶች ምቹ አለመሆንም ሴቶች በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረገ ነው፡፡ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች በአጠቃላይ ፈተና የሚገጥማቸው ቢሆንም፣ ልዩ ፍላጎት ያላት ሴት ካላት ተፈጥሮ ጋር ተያይዞ ይበልጥ የምትቸገር ሆናለች፡፡  

ከቦታ ቦታ ቢለያይም ትምህርት ቤቶች የሚገኙባቸው አካባቢዎች በራሳቸው ለሴቶች ትምህርት እንቅፋት በሚሆኑ አገልግሎቶች መከበባቸውም የሴቶችን ትምህርት ከፈተኑት ይጠቀሳል፡፡

ከዚህ ባለፈም ወንዝ እያቋረጡ የሚማሩ፣ ከመንገድ ርቀት የተነሳ ሰኞ ትምህርት ቤት መጥተው ሳምንቱን ቆይተው ዓርብ ወደ ቤተሰብ የሚመለሱና ሴት ተማሪዎችም በዚህ ሁኔታ ውስጥ እየተማሩ መሆኑ ቤት ውስጥ ካለባቸው ጫና ጋር ተዳምሮ ወደኋላ እየጎተታቸው ነው፡፡  

የጋይዳንስና ካውንስሊንግ እንዲሁም የሥነ ተዋልዶ ትምህርት አለመተግበር በተደጋጋሚ የሚነሳ ችግር ነው፡፡ የሱስ አማጭ ንጥረ ነገሮች ተጠቃሚነትም የሴት ልጆች ትምህርትን የሚያስተጓጉሉና ፈታኝ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

በሴቶች ትምህርት ዙሪያ አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ፣ በክልሎች ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ጭምር የልጅነት ጋብቻ፣ ግርዛት፣ ጠለፋ መኖሩ፣ በሴቶች ትምህርት ዙሪያ ያሉ ፖሊሲዎችና መመርያዎች በብቃት አለመተግበራቸው በተለይ ደግሞ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ችግሩ እንደጎላና የነበረው አሠራርም ወደኋላ እንዲመለስ ማድረጉ ችግሮች ተብለው ተነስተዋል፡፡

ከአንድ ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች በጦርነት ሲወድሙ የተጎዱት ሁሉም ተማሪዎች ቢሆኑም፣ ሴቶች ይበልጥ ተጎድተዋል፡፡ 6.7 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርት ሲያቋርጡ ከእነዚህ ከሦስት ሚሊዮን በላዩ ሴቶች ናቸው፡፡

የሴቶች ጉዳይ ሲነሳ ብዙዎቹ ሥራዎች በመንግሥት አለመያዛቸው፣ የሥርዓተ ፆታ ጉዳይ ሲነሳ በዘርፉ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የአጋሮቻቸውን ፍላጎት እንደሚያስፈጽሙ አድርጎ ማየትና የሴቶችን መብት፣ የኢኮኖሚ፣ አገር የመገንባት አድርጎ አለማየትም ችግር ነወ፡፡

የተማሪዎችና መምህራን ሥነ ምግባርም ከፍተኛ ችግር ነው ያሉት አቶ እስክንድር፣ አብሮ የሚጠጣ፣ ከረምቡላ የሚጫወት፣ ሴት ተማሪን ይዞ ማደር የሚፈልግ መምህር መኖር ለሴት ተማሪዎች ፈተና ነው፡፡

ሥርዓተ ፆታ ላይ ለመሥራት ሙያውን አለመረዳትም ከችግሮቹ መሀል ሲሆን፣ የሥርዓተ ፆታ ክፍሎች ተከፍተው የታጠፉበት ሁኔታም አለ፡፡ የዘርፉ አለመቀናጀት ማለትም  ትምህርት፣ ጤና፣ ፍትሕና ሌሎችም ተናበው አለመሥራታቸውም የሴት ተማሪዎችን ችግር ለመቅረፍ አላስቻለም፡፡

ምን ዓይነት ዕድሎች አሉ?

ዕድሎችን በተመለከተ የሥርዓተ ፆታ ክባብ፣ የኤችአይቪ ኤድስ መመርያዎችና ሌሎችም ሴቶችን ወደ ትምህርት ለማምጣት የሚያሠሩ ፖሊሲዎች ስላሉ፣ እነዚህን መሠረት አድርጎ ችግሮቹን መፍታት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እነዚህን መሠረት አድርገው ቢሠሩ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

እንደ አቶ እስክንድር፣ የትምህርት ሥልጠና ፍኖተ ካርታ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቀው የሚጠበቀው የትምህርት ሕግ፣ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርትና ሌሎችም በርካታ አጠቃላይ ተማሪዎችን በተለይም የሴቶችን ትምህርት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችን መተግበር ያስፈልጋል፡፡

በሴቶች ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች አንዲትን ነገር ብቻ ነጥለው ከመሥራት አጠቃላይ የችግሩ መሠረት ላይ መሥራት እንደሚገባቸው፣ ሰሞኑን ከሴት ተማሪ ወሊድ ጋር በተያያዘ በትምህርት ሚኒስቴር በወጣው ረቂቅ መመርያ ውስጥ የተካተተው ሐሳብ ቅሬታ ማስነሳቱን፣ ችግሩን ለመፍታትና አማራጭ ሐሳብ ለማግኘት በሴት ዙሪያ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር ውይይት መደረጉን አቶ እስክንድር ይገልጻሉ፡፡

በቀጣይ ድርጅቶቹ የመፍትሔ ሐሳብ ይዘው እንዲቀርቡ ቀጠሮ መያዙን፣ ሆኖም የረቂቅ መመርያውን ይዘት ከተለያየ አቅጣጫ ማየትና የመፍትሔ ሐሳቡ ሴትን ልጅ በትምህርቷ ብቁ እንድትሆን የሚያስችል እንዲሆን የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሚመጣው አማራጭ ሐሳብ አንድ ነገር ላይ ያተኮረ ሳይሆን፣ አጠቃላይ ሴት ተማሪዎች እየገጠማቸው ያለው የመማር እክል እንዴት ይፈታ፣ ምን ዓይነት አማራጭ ይቀመጥ የሚለው ላይ እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች ከተሰጡ አስተያየቶችም ሴት ልጅ ወደ ትምህርት ቤት እንድትመጣና ውጤታማ እንድትሆን፣ ሥነ ተዋልዶ ትምህርት እንድታገኝ፣ ለመማር ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ሴትን ልጅ የማስተማር ተቃርኖ ሳይፈታና በርካታ ችግሮች ባሉበት ሴትን ልጅ ከትምህርት ሊያግድ የሚችል ተጨማሪ በፖሊሲ የተደገፈ ገደብ እንዳይጣል የሚል ሐሳብ ይገኝበታል፡፡

መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ችግሩን ከሥር መሠረት መቅረፍ ባልቻሉበት፣ ቅጣቱን ወደተማሪው የሚመጣበት አሠራር ሊቆም እንደሚገባ፣ ጥራቱን ባልጠበቀ የትምህርት ሥርዓት፣ መምህር፣ የትምህርት ግብዓትና ትምህርት ቤቶች የተማሩ ተማሪዎች ፈተና ሲወድቁ ችግሩ የሁሉም ሆኖ ሳለ ተማሪዎች የሚቀጡበት ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት፣ ለዚህም ለተከታታይ ሁለት ዓመታት በተመዘገበው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወድቃችኋል የተባሉ ተማሪዎች ጥሩ ማሳያ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ሴት ልጅ መጀመርያውኑ ትምህርት ቤት እንዳትመጣ ከቤተሰብና ከማኅበረሰብ የሚደርስባትን ጫና አልፋ ትምህርት ስትገባና በሚገጥሟት የተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች ስትደናቀፍ የሚደግፋት ፖሊሲ እንዲኖርና እንዲተገበር፣ ተጎድታም መብቷን አጥታ እንዳትቀመጥ መሠራት እንዳለበትም ተገልጿል፡፡

ለሴቶች አማራጭ የትምህርት መማሪያ ስልትም ያስፈልገቸዋል፡፡ ላረገዘች፣ ለወለደች፣ ለተደፈረች፣ አገግማ እስክትመጣ ቤት ለቤት የምትማርበት፣ አንድ ላይ አድርጎ የማስተማርና ሌሎች ሥልቶችን መተግበር ያስፈልጋል፡፡

ጥቃት የደረሰባት፣ ስትሠራ ያደረች፣ የተመታች፣ ሌሎችም ችግሮችን አሳልፋ ጠዋት ትምህርት ቤት የምትመጣ ሴት ተማሪ የምክር አገልግሎት አግኝታ ክፍል እንድትገባ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋትም አለበት፡፡

ለእርስ በርስ ግጭቱ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶ ከፍተኛ በጀት በሚፈስበት አገር፣ እየተማረ ያለው ትውልድ ሊደገፍ ሲገባው፣ ወድቀሃል፣ አርግዘሻል፣ እየተባሉ ከትምህርት የሚፈናቀሉበት ሁኔታ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባልም ተብሏል፡፡

ፖሊሲዎችና መመርያዎች ሲረቀቂ ጦርነት ባለባቸውና በነበረባቸው ቦታዎች ያሉ ተማሪዎችን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን፣ በተለይ በጦርነቱ ተደራራቢ ጉዳት ያስተናገዱ ሴት ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ ሊስተናገዱና የሴት ተማሪዎችን ችግር ያገናዘበ የትምህርት ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ሐሳብ ተሰጥቷል፡፡

ረቂቅ መመርያው ላይ መሠረታዊ የሕግ ጥሰትና ችግር አለባቸው የሚባሉ ሐሳቦች እንደሚስተካከሉ የገለጹት አቶ እስክንድር፣ ረቂቅ ፖሊሲው ላይ በርካታ ነገሮች እንደተቀመጡ፣ ከረቂቁ የሚመነጩ ችግሮችን እግር በግር እየተከታተሉ ማስተካከል ላይ ተባብሮ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን የሴቶችን ትምህርት ችግር ለመፍታት ሐሳብ ይዛችሁ ኑ፣ አማራጭ አምጡ መባሉ አዎንታዊ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ አዜብ፣ ከማኅበረሰብ ጀምሮ ለሴቶች ትምህርት ያለው ቅበላ አናሳ በሆነበት፣ ሴትን እስከእነጭራሹ ከትምህርት ሊያስቀር የሚችል የእርግዝና ጉዳይ በሕግ ተደግፎ ሲመጣ ችግሩን እንደሚያባብሰው ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም እንደ ሲቪል ሶሳይቲ ያሉትን ክፍተቶች እያወጡ መነጋገር እንደሚያስፈልግ፣ መመርያው ላይ የታየው ክፍተት ከማኅበረሰቡ አመለካከት ጋር ተያይዞ የመጣ በመሆኑ መወትወት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...