Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፈጠራ ሐሳብን ዕውን የማድረግ ጉዞ

የፈጠራ ሐሳብን ዕውን የማድረግ ጉዞ

ቀን:

አቅም የለኝም፣ ጊዜና ገንዘብ አይበቃኝም፣ ዕውቀትም ሆነ የሚረዳኝ ሰው ከጎኔ የለም፣ ልከስር እችላለሁ፣ ዕድሜዬ አይፈቅድም የሚሉትና የመሳሰሉት ምክንያቶች ብዙዎችን ከልጅነት ህልማቸው ጋር እስከወዲያኛው የሚያለያዩ ሰበቦች ናቸው፡፡

‹‹እነዚህ ሁሉ ሰበቦች ከዓላማዬ አንድ ስንዝር እንኳን ወደ ኃላ አያስቀሩኝም›› ይላል ወጣት ኢበ ለገሠ።

ወጣቱ የልጅነት ህልሙን ዕውን ለማድረግ ለዓመታት እልህ አስጨራሽ ጉዞን አድርጓል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፈጠራ ሐሳብን ዕውን የማድረግ ጉዞ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ተቆጥረው የማያልቁ ፈተናዎች ተስፋ አስቆራጭና ያልተሳኩ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርጓል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁሉ ሙከራዎች ምንም ያህል ጊዜና ጉልበት ቢፈጁም በአሁኑ ወቅት የልጅነት ህልሙ ዕውን ሊሆን ሽርፍራፊ ጊዜያት እንደቀሩት ተናግሯል።

ኢበ ነዋሪነቱ በሽሬ ከተማ ሲሆን፣ የልጅነት ህልሙ ብዙዎች እንደሚሉት አውሮፕላን ማብረር አልያም በአውሮፕላን መሄድ አልነበረም፡፡ ይልቁንስ ሐሳቡ ከዚህም ከፍ ያለ ነበር፡፡ የግሉን አውሮፕላን ሠርቶ በሰማይ ላይ መንሳፈፍ ምኞቱ እንደነበር  የሚናገረው ወጣቱ፣ ሐሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ እልህ አስጨራሽ ጉዞን አድርጓል።

ኢበ ምንም እንኳን በትምህርት ደረጃው ከአሥረኛ ክፍል ባይሻገርም፣ በሰማይ መብረር የምትችል ሔሊኮፕተርን ከመሥራት አላገደውም።

የፈጠራ ሥራውን በ1991 ዓ.ም. እንደወጠነው የሚናገረው ወጣቱ፣ ከአንድም  አምስት ጊዜ ሰው አልባ ሄሊኮፕተሮችን ሠርቶ፣ ሁለቱ ምንም ዓይነት የመብረር ሙከራ ሳያደርጉ እንደቀሩ ተናግሯል፡፡ ሦስተኛዋ ደግሞ ወደ ሰማይ እንደሄደች መዳረሻዋ ሳይታወቅ በወጣችበት ደብዛዋ ጠፍቶ የቀረች ሲሆን፣ አራተኛዋ ደግሞ ከፍታዋ ዝቅ ያለ ስለነበር ከተራራ ጋር ተላትማ ሙከራዋ ሳይሳካ እንደቀረ ያስታውሳል፡፡

ከብዙ ድካም በኋላ ከመሬት አንላቀቅም ብለው የመብረር ሙከራ ያላደረጉት ሄሊኮፕተሮች፣ መመለሻዋ ጠፍቶ እንደወጣች የቀረችውም ሆነ ከፍ ብላ መብረር ባለመቻሏ ከተራራ ጋር ተጋጭታ የተሰባበረችው ሔሊኮፕተር፣ ወጣቱን ተስፋ አላስቆረጡትም፡፡ ይልቁንስ ለሌላ ምዕራፍ እንዲዘጋጅና በእያንዳንዱ ምዕራፍ አዲስና የተሻለ ሐሳብ እየፈጠረና የጎደለውን እየሞላ እንዲመጣ እንደረዳው ተናግሯል።

ኢበ ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ምን አልባት አልሳካ ያለው ሰው አልባ በመሆናቸው ይሆን እንዴ? በማለት ደጋግሞ ካሰበ በኋላ ‹‹ለምን በሰው የምትበር  ሔሊኮፕተር አልሠራም›› የሚል አምስተኛ ሐሳብ እንደመጣለት ይናገራል።

ሐሳቡንም ሳይውል ሳያድር ወደ ተግባር በመለወጥ በፋይበር ግላስና በአሉሙኒየም የተሠራች ከዚህ ቀደም ከተሠሩት በመጠንም ሆነ በጥራት ለየት ያለችና አብራሪዋን ብቻ የምትይዝ ሔሊኮፕተር በአራት ዓመት ሠርቶ እንዳጠናቀቀና በራሱ አብራሪነት መካከለኛ ሙከራን እንዳደረገ የሚያወሳው ወጣቱ፣ የረዥም ጊዜ ድካሙ ፍሬያማ ሊሆን ዳር እንደደረሰና ከስኬት ጫፍ ለመድረስ መቃረቡን ተናግሯል።

ታዲያ ይህች ለሙከራ ተብላ የተሠራችው ሔሊኮፕተር እንዲሁ በቀላሉ አይደለም፡፡ አንዱ ሲበላሽ፣ ሌላው ሲተካ አብሮ የሚወጣው ገንዘብ ቀላል አይደለም። ምንም እንኳን ከሌላው የተሻለ ሙከራ ብታደርግም፣ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ጨርሳለች፡፡

ይህንን ሁሉ ገንዘብና ጊዜ ፈጅታ እንደታሰበው ባትሆንም ባሳየችው የተሻለ ውጤት ወደ ቀጣዩ የስኬት ጉዞ በፍጥነት እንዲሸጋገር ትልቅ በር እንደከፈተችለትና ስድስተኛውን ሙከራ ለማድረግ ረድታዋለች።

ካለፈው ተደጋጋሚ ሙከራዎች በመነሳት በስምንት ወር ወስጥ ሠርቶ ያጠናቀቃት ሔሊኮፕተር፣ ከመገናኛ ራዲዮና ከጥቃቅን የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ውጭ በአብራሪ ታግዛ  ሙሉ በረራ የማድረግ ሙከራ ማድረጓን ወጣቱ ተናግሯል።

ሔሊኮፕተርሯን ከሁሉም ለየት የሚያደርጋት ጥሩ የበረራ ሙከራ ማድረጓ ብቻ አይደለም የሚለው ኢበ፣ በተፋፋመ ጦርነት ወቅት የመድፍ ጮኸት ከሩቅም ከቅርብም እየተሰማ በሞትና በሕይወት መካከል በነበረበት ወቅት መሥራቱም ጭምር መሆኑን ያስታውሳል፡፡

በዚያን ወቅት ዘረፋና ቅሚያ የበዛበት ስለነበር ብዙ የመለዋወጫ ዕቃዎች  እንደተዘረፉበትም ገልጿል።

የአውሮፕላን ማምረቻ ቁሳቁሶችን በመጠቀም እንደሠራት የተናገረው ወጣቱ፣ ምንም እንኳን ለአብራሪው ብቻ የሚሆን ቦታ ቢኖራትም፣ እስከ አራት ሰው ወይም አራት ኩንታል ጭነትን ተሸክማ መብረር የምትችል መሆኑን ሙሉ በሙሉ ተጠናቃና በባለ ሙያ ተገምግማ ለሽያጭ ስትቀርብ የመሸጫ ዋጋ እንደሚተመንላት ተናግሯል።

ሔሊኮፕተርሯ ተጠናቃ ወደ ሥራ ስትገባ በከተሞችና በጥብቅ ደኖች አካባቢ ለሚነሱ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎዎች ሰፊ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ደርሳ ለማጥፋት፣ የአንበጣ መንጋን ለመከላከልና ቅኝት ለማድረግ እንደምታገለግል፣ ሰዎች ገዝተው  ለትራንስፖርት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም አክሏል።

‹‹እስካሁን ካለፈው ይልቅ መጪው ብዙ ሥራንና ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል፤›› ያለው ኢበ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ዕገዛ እንዲያደርጉለት ጥሪ አቅርቧል።

 ወጣት ኢበንና መሰል የፈጠራ ባለሙያዎችን በአንድ መድረክ ያገናኘ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የተባለለት ኤክስፖ ከታኅሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።

ኤክስፖው ‹‹ፈጠራ ለአቪዬሽን ልህቀት›› በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ሥራ ፈጣሪዎች በአንድ ተሰባስበው የሠሩትን፣ የለፉበትንና የደከሙበትን እንዲሁም ከኪሳቸው አውጥተው ገንዘብ ያፈሰሱበት የፈጠራ ውጤት በሳይንስ ሙዚየም ለዕይታ አብቅተዋል፡፡ እንደ ወጣት ኢበን ሁሉ ወጣት ንጉሥ ፍፁምና ወጣት ማቲያስ ሙሉጌታ ከመቀሌ ከተማ ለአንበጣ መንጋ መድኃኒት መርጫ፣ ለእሳት ማጥፊያ፣ ለመድኃኒት አቅርቦት እንዲሁም ለካርታ ቅኝት የሚያገለግሉ ድሮኖችን ሠርተው ለዕይታ አቅርበዋል።

ወጣት ንጉሥ ድሮን ለመሥራት ምን እንዳነሳሳው ሲናገር፣ ከሦስት ዓመት በፊት በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ እንደነበር  ያስታውሳል።

ወጣቱ የሠራት ድሮን አንበጣ ቢከሰት የተባይ መርጫ መድኃኒትን በመሸከም   በ14 ኪሎ ሜትር ከፍታ ከክልል ወደ ክልል በመብረር የታለመላትን ግብ ማሳካት እንደምትችል ተናግሯል።

የባትሪ ችግር ካልገጠማት እስከ ተፈለገው ርቀት መጓዝ እንደምትችል የተናገረው ንጉሥ፣ ከ14 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ በመሆን እስከ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት መብረሯን ማረጋገጡን ተናግሯል።

ወጣት ብስራት አበበ ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋፋት ሄሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ዴቨሎፕመንት ሴንተር የመጣ ሲሆን፣ ከሦስት ተማሪ ጓደኞቹ እንዲሁም ከአራት መምህራን ጋር በመጣመር ይዞት የቀረበው የስፔስ ሳይንሱን ያግዛል ያሉትን ሮኬት ነው።

የፈጠራ ሥራቸው መነሻም የመመረቂያ ጽሑፋቸው እንደሆነ የተናገረው ብስራት፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታትም ከመሬት ኦርቢት መውጣት፣ ህዋ ላይ መድረስና  በዘርፉ ዕቅዳቸው እንደሆነ፣ ሥራው ብዙ ገንዘብና ውስብስብ ሒደትን የሚጠይቅ በመሆኑ የዘርፉ ባለድርሻዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲረዷቸው ጠይቋል፡፡  

እነዚህና መሰል የፈጠራ ባለሙያዎችን በአንድ መድረክ ያገናኘው ይህ ኤክስፖ ዓላማ፣ ያለበቂ የመንግሥት ድጋፍ በራሳቸው ተነሳሽነት በአቪዬሽን መስክ በፈጠራ ሥራ ላይ የተሰማሩና የወደፊቱን የአገሪቱን የአቪዬሽን ገፅታ በመቀየር ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ አቅም ያላቸውን ወጣቶች  በማበረታታትና በመደገፍ በዘርፉ ቴክኖሎጂና ኢኖቬዬሽን እንዲስፋፋ ለማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።

በኤክስፖው 95 ወጣቶች በጋራና በተናጠል ሆነው 90 የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ 34 የግልና የመንግሥት ተቋማትም በአቪዬሽን ዘርፍ የሚያከናውኑትን ሥራ አቅርበዋል።

ለዕይታ ከቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች ውስጥም 90 በመቶ የሚሆኑት ድሮኖች ናቸው።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...