Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በርቱ ተበረታቱ!

ሰላም! ሰላም! ያኔ በደጉ ጊዜ ብዬ እንዳልጀምር እዚህ አገር መቼ ነው ደግ ዘመን የነበረው የሚል ተቃውሞ አይጠፋም፡፡ ድሮ ቀረ ሲባል አልቀረብህም ተብሎ እንደሚተረበው ማለት ነው፡፡ ለነገሩ እውነት እኮ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ አብዛኛው ክፍል የሚነግረን የጦርነት ውሎዎችን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማንንም ምስክር መጥራት የሚያስፈልገን አይመስለኝም፡፡ ሌላው ቀርቶ የታሪክ ባለሙያው አቶ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ‹‹ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› የተባለውን መጽሐፋቸውን ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አውሶኝ እንዳነበብኩት ታሪካችን በሙሉ እስኪባል ጦርነት ነው፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ ከዚያም በፊት የነበረው ታሪካችን በሙሉ የጦርነት ነው፡፡ ‹‹ተስፋፊዎችንና ወራሪዎችን መክተን ከመለስንባቸው ዓውደ ግንባሮች እስከ እርስ በርስ ፍጅታችን ድረስ፣ ትውልዱ በሙሉ ሲዋጋ መኖሩን ታሪክ ከበቂ በላይ ከትቦታል፡፡ አሁንም ቢሆን አልለቅ ብሎ የሚታገለን ይኸው አበሳችን ነው…›› እያለ በተደጋጋሚ ሲናገር ሰምቸዋለሁ፡፡ እንዲያው ለነገሩ ግን ከዚህ አባዜ የሚገላግለን ምን ይሆን ብዬ ስጠይቀው፣ ‹‹ለዘመኑ የሚመጥን አስተሳሰብ ተላብሰን ችግሮቻችንን ለመፍታት ሥልጡን መሆን ነው የሚጠበቅብን…›› ይለኛል፡፡ የሚለው ሁሉ ቢገባኝም የእሱን ሥልጡን አባባል ማን ነው ለመቀበል የሚፈልገው ብዬ ሳስብ ጭንቅ ይለኛል፡፡ መላ ያጣ ነገር!

እስቲ ውሎዬንና አዳሬን ደግሞ ልንገራችሁ፡፡ ያው እንደምታውቁት እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ነኝ፡፡ ምን ሆነ መሰላችሁ? እኔ አንድ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ አሻሽጬ ገዥና ሻጭ ከሰዓት በኋላ የድለላ ኮሚሽኔን ሊሰጡኝ ቀጠሮ ይዤ ምሳዬን ለመብላት ወደ ቤት ስሄድ ሠፈርተኛው ተሰብስቧል። ደጋግሜ እንዳጫወቱኳችሁ የመንደራችን ነዋሪ የመሰብሰብም የመበተንም ችግር የለበትም። ባሰባሰበው ተገናኝቶ ተበተን ሲባልም በሰላም መለያየት ያውቅበታል። እኔ እንደ ሠፈሬ ሰው የማመሠግነው ምስኪን ነዋሪ የለም። ወደ ቤተ ክርስቲያን ወይም ወደ መስጊድ ለፀሎት የሚሄድበትን ጊዜ አትንኩበት እንጂ፣ ለአካባቢ ልማትና ለሚያጋጥሙ ችግሮች ተሰባስቦ በሥርዓት ለመነጋገር ፈቃደኝነቱ ያስደንቀኛል፡፡ ከወጣት እስከ አረጋዊ የሠፈሩን የቀበሌ አዳራሽ ግጥግጥ ብሎ ሞልቶ ሥርዓት ባለው መንገድ ሲነጋገር፣ የአሜሪካና የእንግሊዝ ፓርላማዎችን ያስንቃል ስላችሁ የደላላ ቧልት እንዳይመስላችሁ፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል ብትሉኝ እነ አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው ስብሰባውን ፈር አስይዘው የሚመሩት፡፡ አዛውንቱ ሰብስቤም ሆነ እማማ ደብሪቱ፣ አቶ ባይሳም ሆኑ እትዬ ስርጉት፣ አቶ ሶርሳም ሆኑ ወ/ሮ ትርሃስ፣ አባባ አብዱም ሆኑ ወጣቱ ኡመድ ሁሉም በእኩልነትና በመከባበር ሲነጋገሩና እነ ባሻዬ ሥርዓት ሲያስከብሩ ለሚያይ ያስደንቃል፡፡ ዕፁብ ድንቅ ያሰኛል!

በቅርቡ ሠፈራችን ተከራይቶ የገባው አቶ ዘይኑ፣ ‹‹ወገኖቼ አካባቢያችንን በንቃት መጠበቅ አለብን፡፡ ጊዜው ስለከፋ ሰላማችን ህልውናችን መሆኑን እንገንዘብ። እርግጥ ነው እዚህ ሠፈር ነዋሪው ለገዛ ሰላሙ ተባባሪ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን በዚህ ተዘናግቶ መቀመጥ አይገባም፡፡ ሰላም አደፍራሾችን፣ ሌቦችንና እኛን መጠቀሚያ ለማድረግ በደካማ ጎናችን ለመግባት የሚያደቡትን በጥንቃቄ መከታተል አለብን፡፡ አጉል የዋህነት ለበግም አልበጃት…›› እያለ ብዙ ተናገረ። በዚህ መሀል አንዱ ነዋሪ እጁን አውጥቶ ሲፈቀድለት፣ ‹‹እስቲ ሥጋትህን በአጭሩ አስረዳን?›› ሲለው፣ ‹‹በአጭሩ ምን መሰለህ፣ እኛ ለፍቶ አዳሪ ዜጎች ስለሆንን የማንንም አጀንዳ እንደወረደ እየተቀባበልን ሰላማችንን ማጣት የለብንም ነው…›› አለው። አዛውንቱ ባሻዬ ያው እንደሚታወቀው ሰብሳቢ በመሆናቸው፣ ‹‹ከቅንነት የመነጨ ሥጋት ከሆነ እንቀበለዋለን፡፡ ነገር ግን እኛን አሁን የቸገረን የምንናገረውና የምናደርገው አልገጥም ማለቱ ስለሆነ፣ አዲሱ መንደርተኛችን እውነተኛ ባህሪህንም እንድታሳየን በዚሁ ጥሪዬን እያቀርብኩልህ የዛሬው ስብሰባ በዚህ ያብቃ…›› ሲሉ ትንሹ አዳራሽ በጭብጨባ አስተጋባ፡፡ እስቲ እንተዋወቅ ማለታቸው እኮ ነው!

ከስብሰባው በኋላ ቤት ምሳ ለመብላት ስደርስ ሌላ ስብሰባ ገጠመኝ። የት አትሉም? ቤት ነዋ፡፡ ‹‹እኔና አንተ…›› አለች ገና ከመግባቴ ውዷ ማንጠግቦሽ። ‹እኔና አንተ› ካለች ነገር አለ ማለት ነው። ‹‹…መነጋገር አለብን…›› ብላ ፊት ለፊቴ ወንበር ስባ ተቀመተች። ‹‹ምሳ ከበላን በኋላ አይደርስም?›› ብልስ እኔ። አላልኩም ቀላል ጉዳይ መስሎኝ ነበር። ግን የነገር ቀላል አለው እንዴ? አቅለን አቅለን የት እንደ ደረስን ይኼው እየታዘባችሁ መሰለኝ። ማንጠግቦሽ ቀጠለች። ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ተቻችለንና ተከባብረን ኖረናል። ማን ከሚችለው በላይ እንደቻለ እሱ ያውቀዋል። አሁን ግን በቃኝ…›› አትል መሰላችሁ? እስኪ እናንተ ፍረዱ። ማን ነው ባልበላ ሆዱ የመገንጠል፣ የመገነጣጠልና የመለያየት ጥያቄ መስማት የሚፈልገው? ‹‹እና?›› ብዬ አፌን ከፍቼ ስቀር በሁኔታዬ ደነገጠች። ‹‹በቃኝ ምን?›› ብዬ ስጮህ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ዝም አልልህም ነው የምልህ። እኔ ጥያቄዬን በሰላማዊ መንገድ የማቅረብ መብት፣ አንተም ‹እህ?› ብለህ የመስማት ግዴታ አለብህ…›› ካለች በኋላ፣ ለእኔ ጥቃቅን የሚመስሉ እሷን ግን እንቅልፍ ሲያሳጧት የሚያድሩ የቤት ለቤት እንከኖቼን ዘከዘከች። እኔ ደግሞ ልሄድ ነው የምትል መስሎኝ ክው ብያለሁ እኮ። በኋላ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ የደረሰብኝን ሳጫውተው፣ ‹‹እንዴ ይኼን ያህል ጊዜ አብራችሁ ኖራችሁ እንዲህ እንደ ዋዛ ልሂድ ትላለች ብለህ ታስባለህ?›› ሲለኝ የራሴ ነገር አስገረመኝ። ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅድላትን፣ የሴቶች መብት የሚያግዛትን እኔ በጉልበት ላኖራት ይታሰባል እንዴ? ያኔ ‹ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ሥር እናውላለን› ብለው ራሳቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ ስንል የነበረው፣ ይኼው እኛስ ራሳችንን መቆጣጠር  የተሳነን ጊዜ ላይ መስሎኝ ያለነው። ወይ ሰውና ተፈጥሮ!

ውድ ማንጠግቦሽ የምትለኝን ሁሉ እሺ ብዬ ምሳዬን ጥርግ አድርጌ በልቼ፣ የይቅርታና የምሥጋና አፀፋ ሰጥቻት ስወጣ ስልኬ አንዴ ጮሃ ዝም አለች። ‹‹የሙዚቃ ድምፅ ማሳመሪያ ገዝተው አሸንፈው ይሸለሙ›› የሚል ማሳሰቢያ መሰል የቴሌብር የጽሑፍ መልዕክት ነው። እኔ ዕድሌን መቼ አጣሁት? ደጋግሜ እንዳጫወትኳችሁ እኔና አዳም ዕጣችንን የጣልነው፣ የወጣልንም እኩል ይመስለኛል። ‹ተሸልመህ ብላ› ብሎ ነገር አይገባኝም። እኔን የሚገባኝ ‹አዳም ሆይ በላብህ ወዝ ጥረህ ግረህ ብላ› የሚለው የፈጣሪ ቃል ነው፡፡ ስለዚህ የመልዕክት መስጫ ሳጥኔ እንዳይሞላ ‹ዴሊት› ልጫን ስል፣ ከአውሎ ንፋስ በላይ የተዋከበ ‹ሚስድ ኮል› ጥሪ ደረሰኝ። ኮሚሽኔን ከሚሰጡኝ ሰዎች አንደኛው ነው። እንዴት ቢሳሳ ነው መደወል የከበደው? እያልኩ መልሼ ስደውል፣ ‹ይቅርታ ያለዎት ቀሪ ሒሳብ አነስተኛ ነው…›› አለች የቴሌዋ፡፡ ትንሽ ትልቁን አንቱ ማለት የማይሰለቻት መልካም ሴት ናት። አንዳንዴ ታዲያ ይገርመኛል። ምኑ መሰላችሁ? አሥር ሳንቲም ሳይኖረው ስልካችን ‹አነስተኛ ሒሳብ አለዎ› መባላችን ማለቴ ነው። ‹‹ቴሌ እግዜር አሁንም ያሰበውን ያሳካለትና የዋለልን ትልቅ ውለታ ስናጣና ስናገኝ እኩል እያስተናገደ ዱቤ መስጠቱ ነው…›› የሚለኝ አንድ የእኔ ቢጤ ደላላ ነው። ድሮም ሆነ አሁን ዱቤ የሚሰጡን ምሥጉን የሱቅ ነጋዴ ጎረቤቶቻችንም እዚህ ላይ እንዳይዘነጉ አደራ እላለሁ፡፡ እኔ በበኩሌ የሽኩርን፣ የደንድርን፣ የሙሰማንና የወልቀሮን ውለታ አልረሳም፡፡ ደመወዝ እስኪደርስ ድረስ ያኖረን የእነሱ የዱቤ መዝገብ እንደሆነ የብዙዎቻችን ታሪክ ነው ብዬ ብናገር ዋሸህ አልባልም፡፡ ዕድሜና ጤና ይስጥልን ማለት ተገቢ ነውና ሁላችሁም አመሥግኑ፡፡ እንዲህ ነው ደስ የሚለው!

ወደ ሌላ ጉዳዬ ከመሄዴ በፊት አንድ የሚከራይ ቪላ ነበርና ወደ እዚያው ገሰገስኩ። አፈላልገው ያገኙኝ ተከራዮች ናቸው። ቪላውን ዓይተው የኪራይ ዋጋውን ተነጋግረው ሲያበቁ፣ ‹‹በቃ ተስማምቶናል፣ ነገ መጥተን የስድስት ወራት እንከፍላለን…›› አሉ። ‹‹እንዳላችሁት ይሁን…›› ብዬ ሸኘኋቸው። ‹‹ዘንድሮ በቃሉ የሚገኘው ዕብድ ብቻ ነው…›› ይላሉ  አዛውንቱ ባሻዬ በእንደወረደ ንግግራቸው። ‹‹እንዴት?›› ስላቸው ሁሌም የሚሰጡኝ መልስ ተመሳሳይ ነው። ‹‹ያው አንዴ አብዷልና የሚያወራውን አያውቀውም፣ ቢያውቀውም አይገደውም። አንተም የሚናገረውን እንጂ ፍፃሜውን አትጠብቅም። ስለዚህ ቃሉን በከንቱ በመዝራት እንደ ቃሉ በየሥፍራው በከንቱ የሚገኘው እሱ ብቻ ነው…›› ይሉኛል። እሱ ቃሉ ከሚያልፍ ሰማይና ምድርን ማሳለፍ የሚቀለው አምላክ ይሁነን እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም። ባሻዬ እንዲህ ቢሉኝም እኔ ግን በጣም ብዙ ቃላቸውን የሚጠብቁ ሰዎች አውቅ ነበር፡፡ እርግጥ ነው ብዙዎች በሞት ከዚህ ዓለም ተለይተዋል፡፡ ቢሆንም ጥቂት የቀሩ ግን አሉ፡፡ እነዚህ ዕድሜና የኑሮ ልምድ ያካበቱ ሰዎች ዛሬም በቃላቸው አሉ፡፡ እኔም ሲፈልጉኝ አላሳፍራቸውም፡፡ ቃሉን ለሚጠብቅ ሸብረክ ብሎ መታዘዝ ልማዴ ነው፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ እንደ አረም የበቀሉ እኩዮች መብዛታቸውን ሳስብ ያጥወለውለኛል፡፡ እነሱ ገንዘቡን ከየትም ያምጡት አያገባኝም፡፡ ይህንን መላ ያጣ የገንዘብ አሰባሰብ ከተካኑበት ውስጥ ብዙዎቹ ግን ያሳዝኑኛል፡፡ አንድም ከባህሪ ብልሽት እስከ ስስታምነት፣ ሌላም ከዕውቀት አልባነት እስከ ሆዳምነትና ሰካራምነት ድረስ የሚገለጹበት መሆኑ ድንቅ ይለኛል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ሴሰኝነታቸው ሲታከልበት፣ ለሥራ ሳይፈጠሩ በአቋራጭ ሀብት ቆጥ ላይ መሥፈራቸው ያስገርመኛል፡፡ አራሙቻ ሁላ!

እንሰነባበት መሰል፡፡ የታኅሳስ መጀመሪያ ሳምንት ውስጥ ጆሮ ሊበጥስ የሚደርሰውን የምሽት ቅዝቃዜ ሞቅ ለማድረግ ግሮሰሪ ታድመናል፡፡ እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ዘግይተን ደርሰን ነው መሰል ግሮሰሪው በደንበኞች ጢም ብሎ ሞልቷል፡፡ መምህራን፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የባንክ ባለሙያዎች፣ ነጋዴዎች፣ ፖለቲከኞች፣ አነቃቂዎች፣ ደላሎች፣ ወዘተ የተሰባሰቡበት ግሮሰሪ ሁሉም ከቢጤው ጋር እየተጎነጨ ወጉን ይሰልቃል፡፡ ከእኛ አለፍ ብሎ ያለውን ጠረጴዛ የከበቡ ሦስት ሰዎች የጦፈ ወግ ይዘዋል፡፡ በዕድሜው ገፋ ያለው አንደኛው፣ ‹‹ምናለበት በዚህ ዘመን ወጣት ብሆን ኖሮ…›› እያለ በፀፀት ሲናገር ጆሮአችን ውስጥ ገባ፡፡ ይህ ጉዳይ የእኔም የሁልጊዜ ቁጭት ስለነበር፣ ‹‹እኔም እኮ ምናለበት ወጣት በሆንኩ እያልኩ እቆጫለሁ…›› ብዬ ወደ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሐሳቤን ስሰነዝር ፈገግ ብሎ እያየኝ፣ ‹‹ኖሮ ብሎ ነገር አይገባኝም…›› ብሎ ወሽመጤን በጠሰው፡፡ ‹‹… አንበርብር ለላፈ ነገር ከመቆጨት ይልቅ ስለዛሬህና ስለነገህ አጥብቀህ አስብ፡፡ ትናንት ላይመለስ የሄደ ባቡር ነው፡፡ ላይመለስ የሄደን ባቡር ለመሳፈር ማሰብ የዛሬውንና የነገውን ያሳጣሃል…›› ሲለኝ መለስ አልኩ፡፡ ይሻላል!

‹‹…በጉብዝናህ ወራት እግዚአብሔርን አስብ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል መቼም አትዘነጋውም፡፡ እኛ በልጅነታችን ተኮትኩተን ብናድግ ኖሮ እኮ ዛሬ የሚያተራምሱን ከንቱ ነገሮች እስረኛ አንሆንም ነበር፡፡ ምን ልልህ መሰለህ፣ በከንቱ ፖለቲከኞች አጉል አጀንዳ ስንባዝን ኖረን ሁሉም ነገር ከንቱ ሲሆንብን፣ ፊታችንን ወደ ፈጣሪ ስንመልስ ብዙ ነገሮች አምልጠውን ይሄዳሉ፡፡ የፈጣሪን ነገር ቀርበን ስንመረምርና ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም የሚለው ምክር ዘንድ ስንደርስ እኛ ግን በዕድሜ ገፍተናል፡፡ ያኔ በጉብዝናችን ጊዜ ይህንን ወርቃማ ምክር ዓይተን መመርመር ብንችል ግን በከንቱ ነገሮች ያባከናቸው ጊዜያት እያስቆጩን፣ ምነው አሁን ወጣት በሆንን ኖሮ… ኖሮ… ኖሮ… እያልን አናላዝንም ነበር…›› እያለኝ ከምጎነጨው በላይ ንግግሩ ሙቀት ለቀቀብኝ፡፡ የእሱ ንግግር ብዙ የባከኑ ጊዜያትን አስታወሰኝ፡፡ ማንም ከየትም እየቃረመ ከያዘው የማይረባ ሁለትና ሦስት ዲግሪ እኔም አንድ የረባ አላጣም ስልም ተቆጨሁ፡፡ ግና መቆጨት ምንም ፋይዳ ስለሌለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንዳለው የዛሬውና የነገው ጉዞዬ ላይ ማተኮርን መምረጥ ይኖርብኛል፡፡ ‹‹ታሪክ ማንበብ ብቻ ሳይሆን መሥራት የሚቻለው እንዲህ ሰከን ብሎ ሲታሰብ ነው…›› ብሎ ሲያበረታታኝ የበለጠ ልቤ ተነሳሳ፡፡ እናንተም በርቱ፣ ሁላችንም እንበርታ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት