Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከቁጥጥር ውጭ እየሆነ የመጣው ሕገወጥ የእንስሳት ዕርድ

ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ የመጣው ሕገወጥ የእንስሳት ዕርድ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ እስከ 30 በመቶ ያህል የዳልጋ ከብቶች ወይም ሠንጋዎች፣ እንዲሁም ከ95 በመቶ በላይ በጎችና ፍየሎች (በኮንትሮባንድ) በሕገወጥ መንገድ እየታረዱ ለንግድ እንደሚቀርቡ በጥናት መረጋገጡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ እንድሪስ እንደገለጹት፣ ጨለማን ተገን በማድረግና በልዩ ልዩ አሳቻ ሥፍራዎች በሕገወጥ መንገድ የሚታረዱ የእነዚሁ እንስሳት የሥጋ ምርት ለንግድ የሚቀርበውም በየልኳንዳ ቤቱ፣ በየሬስቶራንትና በተለያዩ ምግብ ቤቶች ነው፡፡

በከተማው ከሚገኙ ባለ አራትና አምስት ኮከብ ሆቴል ቤቶች ውስጥም በሕገወጥ መንገድ ታርዶ የቀረበላቸውን የበግና የፍየል ሥጋ የሚጠቀሙ እንዳሉ አክለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሥጋዎች ጤንነታቸው ያልተመረመረ ሲሆን፣ ጤንነቱ ያልተረጋገጠን ሥጋ መመገብ ደግሞ ከእንስሳት ወደ ሰው ለሚተላለፉ በሽታዎች ይዳርጋል፡፡ እነዚሁም በሽታዎች ጥገኛ ከሆኑ ትላትል ጋር ተያይዞ የሚመጣና በተለይ ገዳይነቱ የታወቀው አባሠንጋ የመሳሰሉት እንደሚገኝበት፣ ለአካባቢ ብክለት መንስዔ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ2009 ዓ.ም. በሕገወጥ ዕርድ ምክንያት ብቻ ከሥጋ ግብር ማግኘት የነበረበትን 1.53 ቢሊዮን ብር እንዳጣም አስታውሰዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በአዲስ አበባ ያሉት ሁለት ቄራዎች ተደራሽ አለመሆናቸው፣ የግንዛቤ ችግር፣ ግብር ላለመክፈል የሚደረግ መፍጨርጨር፣ የቄራዎችና የእንስሳቱ የገበያ ማዕከላት ተራርቀው መቋቋማቸው ለሕገወጥ ዕርድ መስፋፋት መንስዔ ሆነዋል፡፡

በሕገወጥ ዕርድ ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ጥናት በ2009 ዓ.ም. መካሄዱን፣ ጥናቱንም ያከናወነው ከፈረንሣይ የእንስሳት ሕክምና ተቋም የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን መሆኑን አቶ ሰይድ ገልጸው፣ ቡድኑ ጥናቱን ያከናወነውም ከፈረንሣይ የልማት ድርጅት በተገኘ ብድር የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅትን ለማዘመን የተዘጋጀውን ፕሮጀክት አዋጭነት በዳሰሰበት ወቅት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በጥናቱ የአዲስ አበባ ሕዝብ የሥጋ ፍላጎት ምን ያህል ነው? ለዚህም ሲባል በሕጋዊ መንገድና ከሕግ ውጪ በሆነ አካሄድ ምን ያህል የዳልጋ ከብት፣ በግና ፍየል ይታረድ ይሆናል? ኮንትሮባንዲስቶችን ወደ ሕጋዊ መስመር ማምጣት ቢቻል ድርጅቱ የመሸከም አቅሙ እስከምን ድረስ ነው? የሚሉት ነጥቦች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የዳሰሳ ጥናትና የተጠቀሰው የኮንትሮባንድ ዕርድ በመንፈሳዊ በዓላትም ሆነ በአዘቦት ቀናት በየቤቱ ለግል ፍጆታ የሚታረዱትንና በቅርጫ መልክ የሚከናወኑትን እንደማይመለከትም ሥራ አስኪያጅ ጠቁመዋል፡፡

ጥናቱ የተከናወነው ከስድስት ዓመታት በፊት ቢሆንም፣ ሕገወጥነቱ አሁንም እንዳልተገታ፣ ይልቁንስ ተባብሶ እንደቀጠለ፣ ሕገወጦችም ትስስር እንዳላቸው፣ እየተደራጁና አቅማቸውንም እያፈረጠሙ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ሕገወጥ ዕርድን የመቆጣጠር ሥልጣን ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ሲቋቋም አጠቃላይ የደንብ ጥሰቶችን የመቆጣጠር ተግባር እንደተሰጠው አቶ ሰዒድ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ የመቆጣጠሩን ሥራ ባከናወነበት ወቅት የተሟላ መረጃ ይዞ ሲንቀሳቀስ፣ ክትትልና ቁጥጥር ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው፣ መረጃውም የትኞቹ ልኳንዳ ቤቶችና ሬስቶራንቶች ናቸው በሕገወጥ የታረዱትን የእንስሳት ሥጋ የሚያስገቡት የሚልና ሌሎችም ለሥራው ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ነጥቦችን ማካተቱን አስረድተዋል፡፡

የደንብ ማስከበር በሕገወጥ የታረደ እንስሳት ሲጓጓዝ አግኝቶ ከመያዝ ባለፈ ጥልቀት ያለው ክትትል የማካሄድ ክፍተት እንዳለበት፣ የአዲስ አበባ አስተዳደርም ይህንን በመገንዘብ ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትን ያሳተፈና እኩል ኃላፊነትና ተጠያቂነትን ያካተተ የቁጥጥር ዘዴ ለመዘርጋት የሚያስችል እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ መሆኑንና በቅርቡ ይተገበራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ‹‹የኢትዮጵያ ቄራዎች ባለአክሲዮን ማኅበር›› በሚል መጠሪያ በ1.36 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው ኅዳር 12 ቀን 1949 ዓ.ም. ሲሆን፣ የሥራው አቅጣጫ በክፍያ የዕርድ አገልግሎት መስጠት ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከባለ አክሲዮኖቹም መካከል የንጉሣውያን ቤተሰቦች 12 በመቶ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት 42 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች 48 በመቶ፣ የውጭ ባለሀብቶች አራት በመቶ የአክሲዮን ድርሻ እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡

የደርግ መንግሥት በሚያራምደው የዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት መሠረት የግል ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅቶች ወደ መንግሥት ይዞታ ሥር እንዲሆኑ ባወጣው አዋጅ መሠረት፣ ድርጅቱ ተወርሶ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሥር እንዲተዳደር መደረጉን፣ ከኢሕአዴግ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ድርጅት ሆኖ በማገልገል ላይ እንደሚገኝና የልማት ድርጅት ከሆነ ወዲህ ከዕርድ አገልግሎት ባሻገር ከአገልግሎቱ የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን የማቀነባበር ሥራ ደርቦ እንደሚያከናውን አመልክተዋል፡፡

አንድ የቁም ሠንጋ ከታረደ በኋላ ከሚገኘው የሥጋ ምርት ውስጥ 52 ከመቶ ያህሉ ብቻ ለምግብነት ሲውል፣ የቀረው ተረፈ ምርት በመሆኑ የሚወገድ ወይም ለምግብነት የማይውል መሆኑን የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር በጥናት መረጋገጡን ይገልጻል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...