Monday, February 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ስም ማጥፋትና ስም ማጉደፍ በ“ቁራጯ ክር” ተምሳሌት

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ስም ማጥፋት ምን ማለት ነው? ስም ማጥፋት ማለት አንዳች ለማግኘት ሲባል አንድ ሰው ምንም ባልፈጸመው ወይም የፈጸመውን አነስተኛ ጉድለት በማጋነንና በመወንጀል፣ ወይም በድብቅ የሠራውን ምሲጢር አውቆ ያ ሚስጥር የሰውየውን ስብእና በሚነካ መልኩ በማናፈስ ከቤተሰቡ፣ ከጓደኞቹ፣ ከሚያምኑበት ሰዎች ጋር ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ ወይም ተደብቆ በሠራው ነገር እንዲያፍር ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሠረቱ ስም ማጠፋት ወንጀል ቢሆንም ስሙ የጠፋበት ሰው ንፅህናውን እስኪያረጋግጥ ድረስ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተሸማቅቆ ሊቆይ ይችላል፡፡ ሆኖም ስም ማጥፋት የሰውን ስም ማጉደፍ የወንጀል ደረጃውን እንደ መስረቅ ወይም ነፍስ እንደ ማጥፋት መመዘን በእጅጉ አስቸጋሪ ሲሆን፣ ስሙ በጎደፈው ሰው ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖም ከሁለቱ ይለያል፡፡  ስም ማጥፋት በሚጠሉት ሰው ወይም ቡድን፣ ወይም ድርጅት አንዳች አቃቂር ፈጥሮ የማነወር ወሬ መንዛትም ሊሆን ይችላል፡፡ ስም ማጥፈት የሚፈለገው ሰው፣ ድርጅት፣ ቡድን፣ ፓርቲ መንፋሳዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዲያድርበት፣ ወይም ስሙ ከሚጎድፈው ሰው ገንዘብ ወይም ሹመት ሌላ ነገር በመፈለግም ሊሆን ይችላል፡፡  ስም አጥፊው የስም ማጉደፉን የሚያከናውነው በግልጽ ባደባባይ፣ በጋዜጣ፣ ወይም ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው እንዲተላለፍ በማድረግ ሊከናወን ይችላል፡፡

ስም ማጥፋት ዋነኛው የፖለቲካ መሣሪያ ሲሆን ይህም በአገር ውስጥ ሥልጣን ለመያዝና በሥልጣንም ተደላድሎ ለመቀመጥ፣ በውጭ አገር በተፃራሪ መስመር የቆሙ አገሮችን የሠሩትንም ሆነ ያልሠሩትን አጋነው በማቅረብ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሊያካሂዱ ይችላሉ፡ ምዕራባውያን በሰሎች፣ ‹‹በመሠረቱ ሕጎች በሕዝብ ውይይት ምክንያታዊ ሒደት ሳይሆን፣ ስም ማጥፋትና በማስፈራራት ሒደት የተሠሩ ሲሆኑና በተመሳሳይ ሁኔታ ይፈጸማሉ፤›› በማለት አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ፡፡ኢዳ ታርቤል የተባሉ ጸሐፊ፣ ‹‹ሮክፌለርና አጋሮቹ በዎልስትሪት ባንኮች የቦርድ ክፍሎች ውስጥ በቅናሽና በችግር፣ በጉቦና በስም ማጥፋት፣ በስለላና በዋጋ ቅነሳ፣ በአደረጃጀትና ርኅራኄ በሌለው ቅልጥፍና እንጂ በባዶ ሜዳ ስታንዳርድ ኦይል ኩባንያን አልገነቡም…›› ብለው ነበር።

ስም ማጥፋት በብዙ መንገዶች የሚገለጽ መሆኑን ዕውቁ ፈረንሣዊ ጸሐፊ ገደ ሞፓሳ እ.ኤ.አ. በ1876 ‹‹ቁራጯ ክር›› በሚል ርዕስ በጻፈው ዝነኛ ሥራው አሳይቶ ነበር፡፡ ይህ ጽሑፍ ለንባብ የበቃው ከ147 ዓመታት በፊት ቢሆንም ዛሬም እንደ አዲስ ሥራ ይነበባል፡፡ ስለአስተማሪነቱ አስተያየትም ይሰጥበታል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ይህን ጽሑፍ የተረጎመው በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜም ወቅታዊና አስፈላጊ በመሆኑ ከላይ የቀረበውን የመንደርደሪያ ሐሳብ በማዘጋጀት እንደሚከተለው ይተርከዋል፡፡

ቁራጯ ክር

ዕለቱ የገበያ ቀን ሲሆን በዚህ ቀን ገበሬዎችና ሚስቶቻቸው የጎርደርሺል መንገዶችን በሙሉ አጣበው ወደ ከተማ ይሄዱ ነበር፡፡ አቶ አውትኮርንም ከነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚያ መንገድ ላይ ወንዶቹ የሚጓዙት በቀላሉ ቢሆንም እንኳን እግራቸውን ባነሱና ወደፊት ተራምደው ባስቀመጡ ቁጥር እንደ ግመል የሚጎተቱ ይመስላሉ፡፡ የእግራቸው ጡንቻ እንደ አገር ቤቱ ለግብርና ሥራ እንደ ተጎነጎነ ገመድ ተጠማሏል፡፡ ትከሻቸው ቀጥ ያለ ቢመስልም መላ አቋማቸው ሲስተዋል የተሽመደመደ ነው፡፡ በቁምጣ ሱሪዎቻቸው ሾልከው የወጡት እግሮቻቸው እንኳን ከመጉበጣቸው የተነሳ ተራርቀው የወጡ የዛፍ ግንዶች ይመስላሉ፡፡

ከመንገዱ ላይ ጥጃ በገመድ ይጎትታሉ፡፡ ከተሸከሙት ቅርጫት ላይ ዳክዬ ወይም ዶሮ ያስቀመጡ ሚስቶቻቸውም ባሎቻቸው የሚጎትቷቸውን እንስሳት በአርጩሜ እየመቱ ይነዳሉ፡፡ የሴቶቹ ዕርምጃ አጫጭር ሲሆን ጥድፊያቸው ከወንዶቹ ጉዞ የሚፈጥን ይመስላል፡፡ ከፀጉራቸው ላይ ሸብ ያደረጉት ነጭ ሻሽና ከሻሻቸው ላይ ጣል ያደረጉት ኮፍያ አማምረው ወደ ገበያ እንደወጡ ይመሰክራል፡፡

በዚያ ሞቃት የአየር ሁኔታ ካፖርቱን ተጀቡኖ በሐሳቡ ልዩ ልዩ ነገሮችን የሚያወጣና የሚወርደው ሀውቸኮረን ነው፡፡ ወደ ገበያ ከሚሄዱት ሰዎች መካከል በመጋጃ ፈረሶች በሚሳብ ጋሪ ላይ ተቀምጠው የሚጓዙም ነበሩ፡፡ መጋጃዎቹ ፈረሶች ለጭነት እንጂ ጋሪ ለመጎተት ስላልሠለጠኑ መንገድ አይመርጡም፡፡ በዚህ ምክንያት በጋሪዎቹ ላይ የተሳፈሩት ሰዎች በእግራቸው ከሚጓዙት የበለጠ መቆሳሰላቸውና መጎሳቆላቸው አይቀርም፡፡ በዚህ ዓይነት ጉዞም ሀውቸኮረን ከገበያተኞቹ ጋር ጎርድቫል ከተማ ደረሰ፡፡

ጎደርቫል ከተማ የሚገኘው የገበያ ቦታ በሰዎችና በእንስሳት ተሞልቷል፡፡ የቀንድ ከብቶች ወደ ላይ ከፍ ብለው የተንሿጠጡ ኮፍያዎችን ያደረጉ ሀብታም ገበሬዎችና ጋቢን ያህል ሻሽ ራሳቸው ላይ ያሰሩ ሴቶች ገበያውን ሲያስጨንቁት ላስተዋለ እንደ ጉንዳን በአንድ ጊዜ ከመሬት የፈሉ ሊመስለው ይችላል፡፡ ቀጭንና ወፍራም ድምፅ ቅጥ አምላኩ ተለይቶ የማይታወቅ ጫጫታ ሰፍኗል፡፡ ከሁሉም በላይ አንዳንድ ሳንባቸው ያስቻላቸው ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ሳቅ ሲስቁ አንዳንድ ጊዜ መለየት ሲቻል፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሩቁ ታዛ የታሰሩ ላሞች ድምፅ ይሰማል፡፡ አቶ ሀውቸኮርን ግን ዕለቱ ይቀናው እንደሆነና እንዳልሆነ ያስባል፡፡ ቢያስተውሉትም ባያስተውሉትም ገበያው በገጠሬዎች በመሞላቱ በረት በረት፣ ወተት ወተት፣ ገለባ ገለባ ይሸታል፡፡ መተንፈስ የሚቻለውም የከፊል ሰው ከፊል እንስሳት ሽታ የተሞላውን አየር ነው፡፡  

በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታና ጊዜ ከብሬዩት የመጣውን ሀውቸኮርን ስለዕለቱ ገድ መቅናት ወይም አለመቅናት ሲያስብ፣ በጎድርሺልን ጎዳና ወደ አደባባዩ አንዲት ቁራጭ ክር አገኘ፡፡ ሀውቸኮርን ምንም በሪህ የሚሰቃይ ሰው ቢሆንም ያችን ቁራጭ ክር ያያት እንደ ማንኛውም የአካባቢው ኅብረተሰብ ወድቆ የተገኘ ዕቃን ማንሳት እንደ ገድ እንደሚቆጥረው ሲሆን፣ ያነሳትም ትንሽም ንብረት ብትሆን ‹‹ሳትጠቅም አትቀርም›› በማለት ነበር፡፡

ሀውቸኮርን ክሯን አንስቶ በመጠቅለል ኪሱ ውስጥ ሲያስገባ ግን የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ማላንዴይን የተባለው ምናምንቴ እየሰበሰበ በጋሪ ወስዶ የሚጥል ጠላቱ በሩቅ ሲያስተውለው ተመለከተ፡፡ ሀውቸንኮርን ከማላንዴን ጋር በትንሽ ጠፍር ምክንያት ተጣልተውና ተኳርፈው ስለነበረ ቁራጭ ክር የምታህልን ነገር ከቆሻሻው ላይ አንስቶ ኪሱ ውስጥ ሲያስገባ ስላየው በኃፍረት ተሸማቀቀ፡፡ ወዲውኑም ያገኛትን ክር ለመደበቅና የሆነ ነገር የወደቀበት ይመስል ዓይኖቹን መሬት ላይ ሳይነቅል ማስተዋል ጀመረ፡፡

በመጨረሻም ሳይጥል የጠፋበትን ዕቃ እንዳጣ ሁሉ ለማስመሰል ሲል እየተናደደ ሄደ፡፡ በዚህም ጊዜ ሪሁ ከጠላቱ ትዝብት ጋር ተዳምሮ ይልቁን አመመው፡፡ ሆኖም ምንም ያህል ቢያመውም እንደምንም ችሎ ከጠላቱ ዓይን ለመሰወር እየተጣደፈ ከገበያተኞቹ ጋር ተቀላቀለ፡፡ ሀውቸኮርን ከጠላቱ ለመሸሽ እንጂ ገበያ ውስጥ የሚገዛው ነገር ባለመኖሩ፣ አንዱ ላም ፈላጊ ዓይኑ ያረፈበትን ለመግዛት ቀረብ ብሎ ያስተውላትና ዋጋ ሲጠይቅ ሲከራከር ሻጭ እንዳያታልለው ወይም እንዳይጎዳው ደግሞና ደጋግሞ ሲመረምር ከራሱ ጋር ሲሟገት፣ ላሟ እንከን እንዳይኖርባት አካሏን አንድ በአንድ ሲፈትሽ ቆም ብሎ አስተዋለ፡፡

ጎንበስ ብሎ ያነሳት ቁራጭ ክር በጠላቱ ፊት ዝቅተኛ ግምት ስላሳደረችበት እየተራገመ ከከብቶች ተራ አልፎ ሴቶች በትልልቅ ቅርጫት ዕንቁላል፣ ድንች፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት ይዘው ከተቀመጡበት ተራ ደረሰ፡፡ እዚህም ተራ ሸማቾች ከአንዷ ባለ ቅርጫት ወደ ሌላዋ በመመላለስ የበለጠውን በዓይናቸው በመመዘን፣ እንዲሸጡላቸው ሲጠይቁና ‹‹ይቀንሱ አልቀንስም›› ሲከራከሩ፣ አንድ ጊዜ ሸማች በሌላ ጊዜ ሻጭ ኮስተር ሲሉና ሲለማመጡ ሲመለከት ከሌላው ጊዜ የተለየ ስሜት አደረበት፡፡

በእንዲህ ያለው ሁኔታ ቆየና ፀሐይ እየጠረረች ስትሄድ ሰዎች ወደ ምግብና መጠጥ ቤቶች መሄድ ጀመሩ፡፡ ከጠላቱ ከማላዴይን የሚሸሸው ባለቁራጭ ክሯ ሀውቸኮርን ወደ ምግብ ቤቶቹ አቀና፡፡

የዮርዳኖሳዊው ትልቅ አዳራሽ የሚያህል ሻይ ቤት ከመቸውም ጊዜ የበለጠ ግጥም ብሎ ሞልቷል፡፡ ያ ሁሉ በላተኛ ልዩ ልዩ ነገሮችን ለመሸጥና ለመለወጥ ወደ ገበያ የመጣ እንደ መሆኑ መጠን ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ ባህሪው፣ ቁመቱ፣ ውፍረቱና ቅጥነቱ፣ ቀለሙ፣ ልብሱ፣ አቆራረሱ፣ አጎራረሱና አበላሉ ሁሉ ለየቅል መሆኑን ላስተዋለ አንድም ያስገርማል አለበለዚያም ያስቃል፡፡ በቁራጯ ክር ምክንያት ከጠላቱ የሚሸሸው ሀውቸከርን እንኳን ኃፍረቱን እያስረሳው ነበር፡፡

የሻይ ቤቱ አስተናጋጆችም በሌላ ጊዜ ሀውቸኮርን ሲሄድ፣ ‹‹ምን ልታዘዝ፣ ዛሬስ ገበያ ጠፋ፣ ኃላፊያችን ከየት አምጥቶ ደመወዝ ሊከፍለን ነው…›› እያሉ ያልተጨነቁትን ያህል፣ በዚህ ዕለት ከሥራው መብዛት የተነሳ ደንበኞችን ሲያመናጭቁ ታይተዋል፡፡ ገንዘቡን ከፍሎ ከሚመገበው ገበያተኛ መካከል በአስተናጋጆቹ ትህትና የጎደለው አገልግሎት የሚበሳጭ ቢኖርም እየበሉም ቢሆን የሚያወሩ ነበሩ፡፡ ሀውቸኮርንም ርቦት ስለነበር መቀመጫ ፈልጎ ተቀመጠና ምሳ አዞ መጠበቅ ጀመረ፡፡

ወዲያውኑም በሩቅ ይሰማ የነበረው የእንቢልታና የነጋሪት ድምፅ በቅርቡ ተደመጠ፡፡ ከአንዳንድ በስተቀር ገበያተኛው፣ ‹‹ምን አዲስ አዋጅ ሊነገር ይሆን?›› በማለት የአፉን እንኳን ሳይውጥ ግልብጥ ብሎ ወደ በሩና ወደ መስኮቶቹ ሄደ፡፡ የእንቢልታውና የነጋሪቱ ድምፅ ሲቆምም፣ ‹‹እሽ ገበያ! እሽ ገበያ! ያልሰማህ ስማ! ላልሰማም አሰማ! የጎደርቪል ነዋሪዎችም ሆናችሁ ለገበያ የመጣችሁ ሁሉ፣ ዛሬ ጠዋት በሦስትና በአራት ሰዓት መካከል አንዲት ከጥቁር ቆዳ የተሠራች የኪስ ቦርሳ ጠፍታለች፡፡ በዚች ቦርሳ ውስጥ አምስት መቶ ፍራንክና ጠቃሚ የንግድ ውሎችን የያዙ ወረቀቶች ነበሩ፡፡ ስለዚህም ይህችን ቦርሳ ያገኘ ወደ ከተማዋ ከንቲባ ቢሮ እንዲያመጣ ተብሏል፡፡ ይህችንም ቦርሳ ላመጣ ሃያ ፍራንክ ይሰጠዋል…›› የሚል ማስታወቂያ ተደጋግሞ ተነገረ፡፡

ይኸው ልፈፋ በአንድ ቦታ ሳይወሰን በመላው ከተማ ተዳረሰ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላም አስተናጋጁ ሀውቸኮር ያዘዘውን ምግብ አቅርቦለት ሲመገብ አንድ ወታደር መጥቶ፣ ‹‹እዚህ ምግብ ቤት አቶ ሀውቸንኮር የተባሉ ሰው አሉ?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ምሳውን እየበላ የነበረውም ሀውቸንኮር ስሙ መጠራቱን ሲሰማ ‹‹አቤት አለሁ…›› አለ፡፡ ወታደሩም፣ ‹‹አቶ ሀውቸንኮር እባክዎን መልካም ፈቃድዎ ቢሆን ከንቲባው ሊያነጋግርዎት ይፈልጋሉና ከእኔ ጋር ቢሄዱ…›› አለ፡፡

ሀውቸንኮር በመደነቅ፣ ‹‹ምን ሠርቼ ይሆን?›› ብሎ ራሱን በመጠራጠር ለመጉረስ የጠቀለለውን ሳያነሳ በብርጭቆ የተዘጋጀለትን ውኃ በአንድ ትንፋሹ በመጨለጥ ወታደሩን ተከትሎ ወጣ፡፡

የከተማው ምክር ቤት ሲደርሱም ከንቲባው ይጠብቀው ነበር፡፡ ከንቲባውም ረጅም፣ ጥልቅ ስሜት ያለው የሚመስል፣ ግርማ ሞገስ ያለውና ድምፁም ጎርናና ነው፡፡ ሀውቸንኮር እንደገባም፣ ‹‹አቶ ሀውቸንከር ዛሬ ጠዋት የክቡር አቶ ወልብረክ ቦርሳ በጠፋበት መንገድ ስታልፍ እንዳነሳኸው መረጃ አግኝተናል…›› ይለዋል፡፡

ሀውቸኮርን ይህን ቃል ከአንድ የከተማ ከንቲባ ቃል ሲሰማ ክፉኛ ተሸማቀቀ፣ የሚናገርበት አንደበትም ተዘጋ፡፡ ከንቲባን ከሚያህል ሰው ያላገኘውን ቦርሳ አግኝተሃል የተባለበት ምክንያት ከቶ ሊገባው አልቻለም፡፡

‹‹እኔ የኪስ ቦርሳ አንስቼ?›› አለ ሀውቸኮርን፡፡

‹‹አዎን!›› አሉት፡፡

‹‹እኔ በአባቴም ሆነ በማንኛውም መማል እችላለሁ፡፡ እንኳንስ ላነሳ ስለመጥፋቱም የሰማሁት አሁን ከእርስዎ ነው…››፡፡

‹‹እንዴ! ታይተሃል?››

‹‹እኔን? ለመሆኑ ሳነሳ ያየኝ ማነው?›› ሲል፣

‹‹አቶ ማላዳይ የከተማችን ፅዳት ሠራተኛ በዓይናቸው በብረቱ አይተውሃል፡፡ ይህንን መካድ አትችልም!›› ተባለ፡፡

ሀውቸኮርን ይህንን ሲሰማ ደነገጠ፣ ፊቱም በአንዴ ፍም መሰለ፡፡ ከኪሱ ያችን ቁራጭ ክር እያወጣ፣ ‹‹አየ ጉድ! ይኼ ደደብ በዚህ ያጠቃኝ መስሎት ይህችን ለገድ ብዬ ያነሳኋትን ቁራጭ ክር ሳነሳ ዓይቶ ቦርሳ አነሳ ብሎ ነገራቸው ለጌታ ከንቲባው?››

የከተማው ከንቲባ ግን ራሱን በመነቅነቅና በፌዝ ስሜት፣ ‹‹አቶ ሀውቸኮርን ታማኝ ሠራተኛችን የሆነው ማላዳይን በክርና በቦርሳ መካከል ያለውን ልዩነት አያውቅም ብለህ ልታታልለኝ አትችልም…›› አለ፡፡

ለገድ ብሎ ባነሳት ቁራጭ ክር ምክንያት አንድ አጋጣሚ ሲፈልግለት የነበረው ጠላቱ ባቀረበበት የሐሰት ክስ የተደናገጠው ሀውቸኮርን፣ ‹‹ያ ቀጣፊ ይታመንም አይታመንም የራሱ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ግን ከዚች ቁራጭ ክር በስተቀር ሌላ ያነሳሁት ነገር እንደሌለ ለክቡር ከንቲባው በታማኝነት እንዳረጋግጥ ይፈቀድልኝ፡፡ ቁራጯ ክርም ይህችው ይይዋት ጌታዬ!›› በማለት የጠላቱን ደባ ለማጋለጥና የእሱን ሀቀኛነት ለማስረዳት ሞከረ፡፡ ኪሶቹንም አንድ በአንድ እየገለበጠ አሳየ፡፡

ሆኖም የሚያምነው ሰው አልተገኘም፡፡ እንዲያውም እንደ አጭበርባሪ አታላይ ተቆጥሮ አይዋረዱ ውርደት ተዋረደ፡፡ ‹‹በከንቲባው እሾማለሁ እሾማለሁ፣ ጠላቴንም እበቀላለሁ ብሎ በዋሸ ቀጣፊ ቁራጭ ክር ብቻ ያነሳው ሀውቸኮርን ገንዘብና ሰነድ የያዘ ቦርሳ ሰርቋል ተባለ፡፡ ይህም ሳይበቃው ቤተ ክርስቲያን እንደገባች ኩቲ ተካልቦ ከከንቲባው ቢሮ እንዲወጣ መደረጉ፣ እንዲሁም በከተማው ሕዝብ ስሙ በሌብነት በመጥፋቱ ምክንያት የአዕምሮ ሕመምና ጭንቀት ያሰቃየው ጀመር፡፡

በማግሥቱ ከሰዓት በኋላ ፓውሜል የተባለ ሰው ቦርሳውን አግኝቶ ማንበብ ስለማይችል ለጌታው እንደሰጠው፣ ጌታውም ለከንቲባው እንዲመልስ እንዳደረገው አስረድቶ መስጠቱን የሚገልጽ ወሬ ተሰማ፡፡ ሀውቸኮርንም ይህንን ወሬ ሲሰማ በጣም ደስ አለው፡፡ በከተማ ውስጥ እየዞረ፣ በየቤተ ክርስቲያኑና ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ እየተገኘ ጠላቱ የሆነ ሰው ስሙን እንዳጠፋና እሱ ግን ንፁህ መሆኑን ለማስረዳት ዘመቻ ቀጠለ፡፡

ሆኖም ያው ጠላቱ በጎን፣ ‹‹አይምሰላችሁ መጀመርያ ያነሳው እሱ ነው፡፡ ነገር ግን በማፈሩ በሌላ ሰው ልኳል…›› እያለ በማስወራቱ የሀውቸኮርንን ንፅህና የሚቀበለው ታጣ፡፡ ሀቁን ከመጀመርያው አንስቶ እስከ መጨረሻ ለማስረዳት ቢሞክርም የሚያምነው አልተገኘም፡፡ እንዲያውም ጠላቱ በእጥፍ ድርብ የስም ማጥፋት ዘመቻውን በመቀጠሉና ከሀውቸኮርን ይልቅ ተቀባዮች ስለበዘሉለት የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ እንዲሉ ሆነለት፡፡

ይባስ ብሎም በየደረሰበት የሚያስረዳቸው ሰዎች ሁሉ ይቀልዱበት ጀመር፡፡ አንዳንዱም የቁራጯን ክር ታሪክ ሊነገራቸው ሲጀምር እነሱን ለማዝናናት የፈጠረው ተረት እንደሆነ አድርገው ቆጠሩት፡፡ ስለዚህም ምንጊዜም ቢሆን ተዓማኒነትን እንደማያገኝ ሲያውቅ ተስፋ እየቆረጠ ሄደ፡፡ አዕምሮውም መዳከም አሳየ፡፡ ከቤት መውጣት ለውርደት ካልሆነ ሌላ እንደማያስገኝለት ሲረዳ ቤት መዋል ጀመረ፡፡ የአልጋ ቁራኛም ሆነ፡፡ የመንፈስ ሕመም አደረበት፡፡

ሕይወቱ ልታልፍ በጣረሞት ላይ በነበረበት ጊዜም፣ ‹‹ክቡር ከንቲባ ይመለከታሉ፣ እኔ መንገድ ላይ ያገኘሁት ይህችን ቁራጭ ክር ነው፣ ይመልከቱ…›› እያለ ይደጋግም ነበር፡፡

መደምደሚያ

ውድ አንባቢያን የስም ማጥፋትና ማጉደፍ በአጭር ልቦለድ መልክ ይቅረብ እንጂ፣ የብዙ ተንኮለኞች መገለጫ ባህሪ ነው፡፡ በዓለማችን በሺዎች የሚቆጠሩ ሀውቸኮርኖች ባልሠሩት፣ ባላደረጉት፣ ጭራሹንም ባላሰቡት መንገዶች ተኮንነዋል፡፡ ራሳቸውንም ለአደጋ እንዲያጋልጡ ተደርገዋል፡፡ እንደ ማላዳይን ያሉት ወሽካቶች ደግሞ፣ ‹‹…ታማኝ ሠራተኛችን የሆነው ማላዳይን በክርና በቦርሳ መካከል ያለውን ልዩነት አያውቅም ብለህ ልታታልለኝ አትችልም…›› ተብለው ተሞግሰዋል፣ ተሞካሽተዋል፡፡ ባለሥልጣናት ታማኞቻቸው ባለሀብቶች ወይም የእነሱ የበታች ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ በዝቅተኛ መደብ የሚገኙ መሆናቸው ታሪኩ በግልጽ ያመለክታል፡፡

ከታሪኩ ለመረዳት እንደሚቻለው የሰውን ስም ለማጥፋትና ለማጉደፍ ብዙ ጥረት ማድረግ አያስፈልግም፣ ትንሽም ቢሆን ይበቃል፡፡ ስለዚህ ከስም አጥፊዎች የተንኮል ሴራ ማምለጥ በእጅጉ አስቸጋሪ ቢኖንም መጠንቀቅ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡

የታሪኩ ጸሐፊ አልበርት ካሙ፣ ‹‹የማኒፌስቶና የተቃውሞ ፊርማ በቀጣይነት መደረጉ የምሁራንን ቅልጥፍናና ክብር ለመናድ አንዱና ዋነኛው መንገድ መሆኑን ለምዕራቡ ዓለም ለራሳችን መመርያ መጠቆም አለበት። ሁላችንም የምናውቀውና ለመቃወም ብዙ ጊዜ የብቸኝነት ድፍረት ሊኖረን የሚገባ ዘላቂ ስም ማጥፋት፣ ስም ማጠልሸት አለ…›› በማለት ማስረዳቱ ይታወሳል፡፡

የቡርኪና ፋሶ መሪ ቶማስ ሳንካራም፣ ‹‹ኢምፔሪያሊዝም ክልልን ለመውረር በጠመንጃ በሚመጡ ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚፈጸም የብዝበዛ ሥርዓት ነው። ኢምፔሪያሊዝም ብዙውን ጊዜ ይበልጥ ሥውር በሆኑ ቅርፆች፣ በብድር፣ በምግብ ዕርዳታ፣ በስም ማጥፋትና በስም ማጉደፍ ይከሰታል፡፡ በምድር ላይ ያሉ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች የሰው ልጆችን ሁሉ እንዲገዙ የሚፈቅደውን ይህን ሥርዓት እየተዋጋን ነው…›› ብለው ነበር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles