Monday, February 26, 2024

የአልጀርስ ስምምነትና ሰሞነኛው የምዕራባውያኑ ጥሪ አንደምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መቶ ሺሕ ለሚጠጉ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ጦርነትን የማቆም ስምምነት ሰኔ 1992 ዓ.ም. ከተፈረመ ከጥቂት ወራት፣ በኋላ፣ ሁለቱ ተፋላሚ አገሮች ከኃይል ዕርምጃ ለመቆጠብና ከባላንጣነት ለመውጣት ወደ ድርድር ገብተዋል። 

ይህ ድርድርም ፍሬ አፍርቶ ሁለቱ ወገኖች ከባላንጣነት ለመውጣትና ከኃይል ዕርምጃ ለመቆጠብ፣ እንዲሁም ወደ ጦርነት የከተታቸውን የድንበር ጉዳይ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ የድንበር ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚፈቅድ ስምምነት ታኅሣሥ 3 ቀን 1993  ዓ.ም. በአልጀሪያ ዋና ከተማ አልጀርስ ተፈራርመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረገውን የአልጀርስ ስምምነት፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብርና ለአካባቢው ሰላም መስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመጥቀስ፣ ስምምነቱ በሁለቱ አገራት ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ የጸና እንዲሆን በማለት በአዋጅ 225/1993 ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡

ግንቦት 16 ቀን 1985 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ነጻ የወጣቸው ኤርትራ ሚያዚያ 1990 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ጋር ምዕራብ ትግራይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ‹‹ባድሜ››፣ በምሥራቅ ትግራይ ዛላንበሳ አካባቢና በኤርትራ በኩል ጾረና እንዲሁም በሰሜናዊ የአፋር ክፍል ቡሬና ባዳ በሚባሉ አካባቢዎች በነበሩ የድንበር ውዘግቦች ጦርነቱ መቀስቀሱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ 

ሁለቱን አገሮች ለጦርነት የዳረገው አወዛጋቢ የድንበር ጉዳይ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ክርክር ተደርጎበት ውሳኔ ካገኘ በኋላ፣ በአልጄሪያ በተደረገው የሰላም ስምምነትና በዚህ ስምምነት የተመሠረተው የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን በአየር ላይ በካርታ (Delimitation) የድንበር ማካለል መፈጸሙን መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ሁለቱ አገሮች ከጦርነቱ በፊት ይዘውት የነበረውን የድንበር ግዛት ይዘው እንዲቆዩና የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ፣ ባደመ የተባለውን ዋነኛ አወዛጋቢ የድንበር ከተማ በአመዛኙ ወደ ኤርትራ እንዲካለል የሚያርግ ሲሆን፣ ዛላንበሳ ከተማ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ እንዲካለል የሚያደርግ መሆኑን ስምምነቱን መሠረት አድርገው የሚወጡ መረጃዎች ያሰረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ሁለቱም አገሮች ከያዙት አቋም ፈቀቅ ለማለት ባለመፍቀዳቸው ሊተገበር አልቻለም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የድንበር ጉዳይም እስከ ዘንድሮ ድረስ የተሟላ እልባት ሳያገኝ ዘልቋል።

ይህ በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና በኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የተፈረመው የአልጀርሱ ስምምነት፣ በያዝነው ወር 23ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። ይህ ስድስት አንቀጾችን የያዘው የአልጀርሱ ስምምነት፣ የተፈረመበት 23ኛ ዓመትን በማስመልከትም የአሜሪካ መንግሥት፣ የእንግሊዝ መንግሥት እና የአውሮፓ ኅብረት ከሰሞኑ መግለጫ አውጥተዋል። 

እነዚህ ሦስት አካላት ባልተለመደ መልኩ ‹‹የአልጀርሱ ስምምነት 23ኛ ዓመት ክብረ በዓል›› በማለት ባወጡት ተመሳሳይ ይዘት ያለው አጭር መግለጫ፣ የአልጄርሱ ስምምነት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ለመፍጠርና የተሰመረ የጋራ ድንበር ለማበጀት የተስማሙበት ውሳኔ ስለመሆኑ ገልጸው፣ ለስምምነቱ መከበር ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

ሦስቱ ምዕራባዊያን ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ፣ የኤርትራ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስትር በኤክስ (ቲዩተር) ገጻቸው፣ አገራቸው ኤርትራ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በማክበር እንከን የለሽ ጥሩ ታሪክ እንዳላት ጠቅሰው፣ ለስምምነቱ ተግባራዊ አለመሆን የሕወሓትን ሥርዓት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን እስካሁን ስለጉዳዩ ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለው ድንበር በቅኝ ገዥዎች ዘመን በጣሊያን ወረራ ጊዜ የተሰመረ እንደሆነ ቢነገርም፣ ሁለቱ አገሮች ካካሄዱት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ቢያንስ ጦርነት ቆሞ ሰላም ያወረደው የአልጀርስ ስምምነት መሬት ላይ ያለውን የሁለቱ ድንበር መስመር እንዲሰመር የሚያደርግ ነበር፡፡

በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት መቀመጫውን ዘሄግ ያደረገ አምስት አባላት ያሉት የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ምርመራ አድርጎ፣ አለመግባባት ባለባቸው የድንበር ቦታዎች እ.ኤ.አ በ1900፣ 1902 እና 1908 በተደረጉ አግባብነት ባላቸው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት መሠረት የተሰመረ የግዛት ወሰንን፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መሠረት በማድረግ የድንበር ውዝግቡን የሚፈታ ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡ 

ይሁን እንጂ የአልጀርስ ስምምነት ከተፈረመ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ሁለቱ መሪዎች በፊርማቸው ባረጋገጡት ሰነድም ይሁን በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት፣ ሁለቱም አገሮች ከያዙት አቋም ፈቀቅ ለማለት ባለመፍቀዳቸው ሰላም የማስፈኑና የድንበር ማካለሉ ሥራ አስካሁን የማይጨበጥና የተንጠለጠለ ጉዳይ ሆኖል። 

የአልጀርሱ ስምምነት ይዘት በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የአገሪቱን ጥቅም የሚጎዳ ነው ተብሎ ይታመናል። ከዚህም ባለፈ፣ ስምምነቱ ሲካሄድ ኢትዮጵያን በውሉና በአግባቡ ሊወክል የሚችል ክርክር እንዳልተደረገ በማንሳት፣ ውሳኔው ፍትሐዊ እንዳልሆነና ኢትዮጵያ ይህንን ውሳኔ እንድትቀበል መገደዷን በተለያየ መንገድ የሚያነሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ 

ከአምስት ዓመታት በፊት በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በፓርላማ  በዓለ ሲመታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን የሰላም ዕጦት ፈተው ግንኙነቱን  እንደሚያድሱ  ቃል በገቡ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበሉ ማስታውቃቸው ይታወሳል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተከትሎም፣ የቀድሞው ገዥ ፓርቲ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለሃያ ዓመታት ኢትዮጵያና ኤርትራ በጦርነት ውስጥ ተፋጠው እንዲቆዩ ላደረጋቸው የድንበር ፍጥጫ መፍትሔ ይሰጣል የተባለውን የአልጀርስ ስምምነትን አንደሚቀበሉ አስታውቀዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ የኢሕአዴግ ስብሰባ በሁለቱ አገሮች ድንበር መካከል ለ20 ዓመታት ውጥረት እንደነበር ጠቅሰው፣ ሠራዊቱ ከአሁን አሁን እጠቃ ይሆን በሚል የሥነ ልቦና ሥጋት እየተሰቃየ ስለመሆኑ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ሞት አልባ ጦርነት›› ባሉት የአገር መከላከያ የድንበር ላይ የኑሮ ሁኔታ በአስመራና በአዲስ አበባ መካከል አውቶቡስ፣ ባቡር እንዲመላለስ፣ ኢኮኖሚው እንዲስፋፋና ወንድማማች ሕዝቦች እንዲገናኙ ለማድረግ ቀዳሚውን ዕርምጃ መውሰድ ከኢትዮጵያ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረውም ነበር፡፡  

‹‹ባላፉት 20 ዓመታት በነበረው ሁኔታ ያተረፍነው ውጥረት ብቻ ነው፣ ከውጥረት ኢትዮጵያም ኤርትራም አይጠቀሙም፣ ሙሉ አቅማችን፣ ሙሉ ጉልበታችን ወደ ሰላም፣ ወደ ፍቅርና ወደ እርቅ እንዲሸጋገርና የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ ሐሳባችንን ከሚከፋፍሉ ነገሮች፣ ከትናንሽ ግጭቶችና ጥላቻዎች ወጥተን የኢትዮጵያን ዕድገት፣ ሰላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ እንሠራለን›› ሲሉም በወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡ በመቀጠልም በሳዑዲ ዓረቢያ አሸማጋይነት ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ዳግም ለማደስ የሚያስችል አዲስ የሰላም ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2018 አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአልጀርሱን የድንበር ስምምነት ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ እንደምትቀበል በአደባባይ ከተናገሩ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ጉዳዩ ከጅምሩ እንዴትና በምን መልኩ እንደሚፈጸም ሳይብራራ ከመቅረቱም በላይ፣ እያደረ እየዋለ የተገባው ቃል የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡

ሁለቱ መሪዎች ተደጋጋሚ የሆነ ጉብኝት ወደ አዲስ አበባና አስመራ አድርገዋል፣ ሻምፓይን ከፍተው ግንኙነቱን እንደ አዲስ ዘክረዋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአስመራ ጎዳናዎች ተንሸራሽረዋል። ይህንንም ተከትሎ ለ20 ዓመታት የተለያዩት የሁለቱ አገር ወንድማማች ሕዝቦች ዳግም ተገናኝተው እንባ ተራጭተው ተቃቅፈዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስም ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተደጋጋሚ ሲያሞግሷቸው ተድምጠዋል፡፡

የኤርትራ ወዳጅ እንደሆነች በሚነገርላት ሳዑዲ ዓረቢያ አሸማጋይነት ግንኙነታቸውን ዳግም ለማደስ የተስማሙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)ና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ የሰላም አየር መፈጠሩንና የጦርነት ዘመን ማብቃቱን የሚገልጽ መግለጫ አውጥተው ነበር።

በተመሳሳይ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ሊያስከብር የሚችል የደኅንነት፣ የፖለቲካ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ትብብሮችን ለማከናወን፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ትራንስፖርትና ንግድ የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶች ለመጀመር፣ የድንበር ስምምነቶች ለመፈጸም፣ ሁለቱ አገሮች ለቀጣናዊ ሰላም በጋራ ለመሥራት ተስማምተው ነበር፡፡

ሁለቱ መሪዎች ይህን ሁሉ ድግስ ሲደግሱና ተደጋጋሚ የሆኑ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ጉብኝቶችን ሲያደረጉ፣ ለሁለቱም ሕዝብች በግልጽ የሚታወቅ ስምምነት አለመደረጉ እስካሁን እንቆቅልሽ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡

በትራንስፖርት፣ በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች በርካታ ስምምነቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሹማምንቶች በተለያየ መልኩ ሲያነሱ ቢደመጡም፣ አንድም ወቅት ግን ምን ዓይነት ስምምነት እንደተፈጸመ ለማወቅ የቻለ አካል የለም፡፡

ይባስ ብሎ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ታጣቂዎች ከሁለት ዓመት በፊት በገቡበት ደም አፋሳሽ ጦርነት፣ የኤርትራ መንግሥት ላደረገው ድጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ ወጥተው ሲያመሰግኑ ተደምጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኤርትራ መንግሥት ውለታ ምሥጋናቸውን በፓርላማው ጭምር ቢገልጹም፣ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ገብተው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማድረሳቸውና በርካታ ሀብት መዝረፋቸውን ከክልሉ ኃላፊዎች፣ የጉዳቱ ሰላባ ከሆኑ ዜጎችና ከዓለም አቀፍ የመብት ተቆርቋሪዎች አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን ፣ ተፈጸመ የተባለው ወንጀልም በገለልተኛ ወገን ምርመራ ተካሂዶ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ በአሁኑ ወቅት እየተጠየቀ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኙ ሲያነሱ የሚደመጡት ምዕራባውያኑ ዲፕሎማቶችና ባለሥልጣናት፣ የኤርትራ ወታደሮች ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያን ድንበር ለቀው እንዲወጡ እያቀረቡት ያለውን ጥሪ በተደጋጋሚ ሲያሰሙ ይደመጣሉ፡፡ እነዚህ አገሮች ይህን ጉዳይ አጠንክረው እየጠየቁ ባሉበት ተመሳሳይ ወቅት የአልጀርስ ስምምነትን 23ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በመጥቀስ ሁለቱ አገሮች ስምምነቱን አንዲፈጽሙ የቀረበው ድንገተኛ ጥያቄ ለምን ይሆን በሚል ሪፖርተር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን አካላት ጠይቋል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና ፖለቲከኛው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) መሪ አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር)፣ ስምምነቱ ከጅምሩ ግልጽ ያልነበሩ አካሄዶች እንደበሩበት ይጠቅሳሉ። የሁለቱ አገሮች ጦርነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ሲደረግ በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና ስብስባቸው የተወሰኑ ሰዎችን በድርድሩ በማሳተፍ ጨረሱት እንጂ፣ የኢትዮጵያን ፍላጎት መሠረት አድርጎ ጥናት እንዳልተካሄደበት፣ በምሁራዊ ዕይታና አገራዊ ጥብቅና እንዳልነበረው ይከራከራሉ። በመጨረሻም በድርድሩ ኢትዮጵያ እንዳሸነፈች የሚገልጽ መግለጫ ቢወጣም እውነታው ግን የሕወሓት ሽንፈት ነበር ይላሉ፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት የተሰጠውን ውሳኔ ተቀብለው እንደሚፈጽሙ ቢናገሩም ፣ በግልጽ ግን ምን ለማለት እንደፈለጉ ማንም እንዳልተረዳው አረጋዊ በርኸ ይናራሉ፡፡ 

በዚህ ሁሉ መሐል የአሜሪካም ይሁን የምዕራባውያኑ መግለጫ ምን እንዳዘለ ለማወቅ እንደሚከብድ፣ በአመዛኙ ግን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ከተነሳው የባህር በር ጥያቄ ጋር የሚገናኝ ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል፡፡ 

አረጋዊ (ዶ/ር) የአልጀርሱን ስምምነት በአንድ በኩል የኤርትራን የቅኝ ገዥዎች የድንበር ስምምነት ዕውቅና የመስጠት ዓላማ የነበረው በመሆኑና ይህ ስምምነት ሳይፈጸም የቆየ ጉዳይ በመሆኑ፣ የድንበር ጥያቄው ባልተመለሰበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ማንስቷ ወደ ቀውስ ሊወስደው ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሮባቸው ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ጥሩ እንዳልሆነ ማሳያዎች መኖራቸውን፣ ከእነዚህም መካከል የኤርትራ መንግሥት ለአማራ ክልል ታጣቂዎች ድጋፍ ያደርጋል የሚል ስሞታ መኖሩንና የኤርትራ ጦር ትግራይ ውስጥ ያደረሰውን በደል በማየት ብቻ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ጥሩ አይደለም የሚያስብል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ የሺጥላ ወንድምነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአልጀርሱ ስምምነት ለረዥም ጊዜ እንቅፋት ሆኗል በሚል ሲወቀስ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑንና ለዚህም ዋነኛ ምክንያት በስምምነቱ መሠረት ለኤርትራ ይገባታል ተብሎ ተወስኖ የነበረውን የባድሜንና አካባቢዎች በስምምነቱ መሠረት ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆን መቆየቱ ነው ይላሉ፡፡ 

ይሁን እንጂ ከአምስት ዓመት ወዲህ በተለይም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ፣ የኤርትራ ሠራዊት የቀድሞውን ድንበር ጨምሮ በርካታ አካባቢዎችን በአሁኑ ወቅት መቆጣጠሩ በተደጋጋሚ እየተነሳ መሆኑ፣ ሁለቱ አገሮች ዳግም ወደ ግጭት ይገባሉ የሚል ሥጋት ሳይፈጥር እንዳልቀረ ይናገራሉ፡፡ በዚህ መሀል አሜሪካ፣ አውሮፓ ኅብረትና የእንግሊዝ መንግሥት ሰሞኑን ያወጡት መግለጫ በዋናነት የኤርትራ መንግሥት ከምዕራባውያን ጋር ባለው ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት የተነሳ ኃላፊነት የማይሰማውና በቀጣናው የብጥብጥ ምልክት ተደርጎ እንዲታይ ከመፈለግ ነው ብለው ያምናሉ። በመሆኑም የእነዚህ አካላት የሰሞኑ መግለጫ ኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ እንድትገፋ የማድረግ እሳቤን ያዘለ ወይም መሰል አዝማሚያ መያዙን ይገልጻሉ።

በተመሳሳይ የኤርትራ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ተሳትፎ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መቀያየር የተነሳ የፈጸማቸው የመብት ጥሰቶች እየተሸፈኑለትና እየደበዘዙ በመምጣታቸው እነዚህን ክሶች በአዲስ ለማንሳትና የኤርትራን መንግሥት ለምዕራባውያኑ እንደ ሥጋት የሚታይ በመሆኑ አገዛዙ እንዲቀየር ግፊት የማድረግ ፍላጎት መያዙን፣ ይህም በሌላ በኩል ከቀጣናው የጂኦፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር የሚገናኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሌለ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የባህር በር ጥያቄን ካነሳ ወዲህ በአንድም ሆነ በሌላ በኩል ምዕራባውያኑ አሁንም ለኤርትራ ባላቸው ጥላቻ የተነሳ የቀይ ባህርን ፖለቲካ ከኤርትራ ይልቅ የኢትዮጵያ እንድትቆጣጠር ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት አንዱ መንገዳቸው ሊሆን ይችላል ብለዋል። ከዚያም አልፎ ኤርትራ ያለውን አገዛዙ ሊቀይር የሚችል አቅም መፍጠርና ወሳኝ የሆኑ የቀይ ባህር ዳርቻዎችን በቀጣናው ተመራጭና የተሻለች ለምትባለው ኢትዮጵያ በመስጠት ምዕራባውያኑ ቀጥተኛ የጂኦፖለቲካ ፍላጎታቸውን የሚያሳካላቸው ትልም ይዘው ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በተለይም በየመን በኩል የሁቲ ታጣቂዎች ቀይ ባህር ላይ ለደቀኑት ሥጋት ይህን ሊቀለበስ የሚቻልበት ስትራቴጂክ ቦታ ላይ ያለችው አገር ኤርትራ ብትሆንም፣ ምዕራባውያኑ ከኤርትራ ጋር ያላቸው ግንኙነት የተበላሸ በመሆኑ ይህን እንቅፋትና ደንቃራ የሆነ ግንኙነት በማስወገድ፣ ኢትዮጵያን ለዚህ ተልዕኮ ዝግጁ ከማድረግ ባላፈ መልዕክቱ አንድም ኤርትራ እንደትቆጠብ ወይም ለቀጣይ ዕርምጃ ማስጠንቀቂያ ደውል ሊሆን እንደሚችልም የሽጥላ (ዶ/ር) ሐሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከዓመታት በፊት እንደ አዲስ ግንኙነታቸውን ሲያድሱና ወደ ሰላም መጣን ብለው ሲናገሩ ግንኙነቱ ተቋማዊና ዲፕሎማቲክ መልክ ይዞ ሳይሆን በሁለቱ መሪዎች ግለሰባዊ የሚመስል የእርስ በርስ ግንኙነት ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ስምምነቱ በውል አለመታሰሩን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እጂ ይህ ታሪካዊ ግንኙነት ተቋማዊ ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ ይህን ስምምነት ማን ጣሰው፣ ማን አከበረው በሚል ተነጋግሮና ተያይቶ ለመፍታት ይቻል እንደነበር የሚናገሩት የሽጥላ (ዶ/ር) አሁን ባለው ሁኔታ ግን ምንም ግልጽ የሆነ ነገር ባለመኖሩ፣ ከሁለቱ ወገን አንዱን አንስቶ ለመውቀስ የሚያስችል አይደለም ብለዋል፡፡ በቀጣይ ስምምነቶች ተቋማዊና በሕግ የተሠሩ እንደሆኑ ትልቅ ትምህርት የተወሰደበት አንደሆነም አክለው ገልጸዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአልጀርስ ስምምነት ድንበሩ መሬት ላይ ወርዶ ችካል መቸከል የነበረበት ቢሆንም፣ የተሠራው የድንበር አከላለል ግን አየር ላይ (Virtually) በመሆኑ ያንን መሬት ላይ ማውረድ እንዳልተቻለ ይገልጻሉ። በመሆኑም ይህ የድንበር ጉዳይ የመጨረሻ መፍትሔ ባለማግኘቱ፣ እንዲሁም የኤርትራ ጦር በጦርነቱ ምክንያት ወደ ትግራይ ክልል ከገባ በኋላ፣ ጦሩን ሙሉ በሙሉ እንዳላስወጣ፣ ለዚህም የሚሰጠው ምላሽ ‹‹በድንበሬ ውስጥ ነኝ›› የሚል በመሆኑ፣ ይህ ጉዳይ ወደ ጦርነት እንዳያመራ ምዕራባዊያኑን አስግቷቸው ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

የሰሞነኛው የአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት መግለጫ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ሰላም እንዲመጣ ከመፈለግና የኢትዮጵያና ኤርትራ አሁናዊ ሁኔታ ወደ ግጭት እንዳያመራ ከመፈለግ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች የገቡበትን እንቆቅልሽ ለመፍታት መሬት ላይ ችካል ማስቀመጥ አንድ አማራጭ መፍትሔ ይሆናል በሚል ዕሳቤ ያወጡት መግለጣ ሊሆን እንደሚችል ዳርእስከዳር (ዶ/ር)  አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -