Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወጋገን ባንክ ከታክስ በፊት 1.2 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸውና የትርፍ ምጣኔያቸው ላይ ተፅዕኖ አሳርፎባቸው ከነበሩ የፋይናንስ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ወጋገን ባንክ፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ገቢና ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ፡፡

ባንኩ ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.2 ቢሊዮን ብር፣ ከታክስ በኋላ ደግሞ 823.8 ሚሊዮን ብር ማትረፍ ችሏል፡፡ ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት የ109 በመቶ ብለጫ ያለው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ወጋገን ባንክ በቀዳሚው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አግኝቶት የነበረው ትርፍ 572 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

ባንኩ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከአንድ ሦስተኛ በላይ ቅርንጫፎቹ ከአገልግሎት ውጪ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፣ በቀደሙት ሁለት ዓመታት የባንኩ የትርፍ ምጣኔ ወርዶ፣ በተለይ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 193 ሚሊዮን ብር ማትረፉ በወቅቱ የነበረውን ችግር የሚያመለክት  ነው፡፡

ወጋገን ባንክ ከታክስ በፊት 1.2 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ወጋገን ባንክ ከጦርነቱ በፊት ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ አስመዝግቦ የነበረው በ2012 የሒሳብ ዓመት ሲሆን፣ በወቅቱ ከታክስ በፊት 1.07 ቢሊዮን ብር አትርፎ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ እንደገና የትርፍ መጠኑን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማድረስ፣ በ2015 መጨረሻ ያስመዘገበው የ1.2 ቢሊዮን ብር ትርፍ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ ሆኖ የሚመዘገብ ሆኗል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አብዲሹ ሁሴን፣ ‹‹ባንካችን በ2015 ሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ የባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን ትርፍ ወርዶ የነበረውን የትርፍ ድርሻ ክፍፍል (ዲቪደንድ) ምጣኔ በማሳደግ 22.7 በመቶ የትርፍ ድርሻ እንዲከፈል አስችሎታል፡፡ በ2014 የአንድ አክሲዮን ትርፍ ድርሻ 16.6 በመቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ዝቅተኛ ትርፍ ባስመዘገበበት በ2013 የሒሳብ ዓመት ደግሞ የትርፍ ክፍፍል መጠኑ ከዚህም በታች ዝቅ ብሎ ነበር፡፡

ከትርፍ ዕድገቱ ባሻገር በ2015 ከፍተኛ የተባለ ገቢ ማግኘቱን የገለጸው ወጋገን ባንክ፣ አጠቃላይ ገቢው ሰባት ቢሊዮን ብር መድረሱንም አስታውቋል፡፡ እንደትርፉ ሁሉ የሰሜን ጦርነት በገቢው ላይም ተፅዕኖ ፈጥሮበት እንደነበር ከባንኩ የተከታታይ ዓመታት ሪፖርት መገንዘብ ተችሏል፡፡ ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ያገኘው ገቢ አምስት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያገኘው ገቢ ደግሞ የአንድ መቶ ሚሊየን ብር ጭማሪ ብቻ በማሳየት 5.1 ቢሊየን ብር ነበር፡፡ በ2015 የሒሳብ ዓመት ግን የገቢውን መጠን በ36 በመቶ በማሳደግ ሰባት ቢሊዮን ብር ማድረስ በመቻሉ፣ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ ተብሎ ሊመዘገብ የሚችል እንደሆነ ከቀረበው ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡  

ወጋገን ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን በ17 በመቶ በማሳደግ አራት ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፤ ጠቅላላ ካፒታሉም በ23 በመቶ በማደግ 6.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ የባንኩ ጠቅላላ ሀብትም በሒሳብ ዓመቱ የ24 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ከ53.5 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ባንኩ በ2014 መጨረሻ ላይ አስመዝግቦት የነበረው የሐብት መጠን 43.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

ወጋገን ባንክ በሒሳብ ዓመቱ በሁሉም የአፈጻጸም መለኪያዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል ያሉት አቶ አብዲሹ፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑንም በቀዳሚው ዓመት ከነበረበት 33.9 ቢሊዮን ብር በ26 በመቶ በ2015 የሒሳብ ዓመት 42.8 ቢሊዮን ብር መድረስ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ የብድር መጠኑም 32 በመቶ ዕድገት በማሳየት ወደ 39.9 ቢሊዮን ብር ማደጉን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ባንኩ በቀደመው ዓመት መጨረሻ ላይ የነበረው የብድር ክምችት 30.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡  

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ውጤት በገቢና በትርፍ ዕድገቱ ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑን የሚገልጹት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አክሊሉ ውበት (ዶ/ር)፣ አጠቃላይ የፋይናንስ አፈጻጸሙን ውጤታማ ነበር፡ በተለይ ምንም ዓይነት የገንዘብ እጥረት (ሊኪውዲቲ) ሳይገጥመን መሥራት ችለናል፡፡ ከውጭ ኮርስፖንዳንት ባንኮች ጋር ያለን ግንኙነት መጠናከርና ጤናማ የሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴያችን ተጨማሪ ላኪዎችን የሳበልን በመሆኑ እንዲህ ያሉ አሠራሮችን ለውጤቱ መገኘትእንደ ምሳሌ የሚጠቀሙ መሆናቸውን አክሊሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የባንኩ የተበላሸ ብድር እስከ 21 በመቶ ደርሶ እንደነበር፣ መረጃዎቹ ያመለክታሉ፡

አሁን ላይ የባንኩ የተበላሸ ብድርምጣኔ በየኣመቱ መሻሻሎችን እያሳየ መሄዱን የገለጹት ባለፉት ሦስት ዓመታት በተወሰዱ የአሠረር ማሻሻያዎችና የተለያዩ ዕርምጃዎች የተበላሸው ብድሩን ወደ 12.52 በመቶ እንዲወርድ ከተደረገ በኋላ፣ በ2014 ሒሳብ ዓመት ወደ 10.2 በመቶ፣ በ2015 ደግሞ ወደ ሰባት በመቶ በማውረድ የባንኩን የተበላሸ ብድር ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል፡፡

በትግራይ ክልል አካባቢ የተሰጠውን ብድር ወደ ጤናማነት ለመመለስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብድር ማራዘሚያ እንዲደረግ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ለትግራይ ክልል ተበዳሪዎ የብድር ማራዘሚያ መሰጠቱ፣ የባንኩን የተበላሸ የብድር ምጣኔ ዝቅ ለማድረግ ማስቻሉንም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል አካባቢ ላሉ ተበዳሪዎች ቢዝነሳቸውን ለማስቀጠል ለአንዳንዶቹ ተጨማሪ ብድር ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረትም የተበላሸ የብድር ምጣኔውን በመቀነስ ብድሩ የሚመለስበትን ዕድል እያመቻቸ መሆኑንና አጠቃላይ የብድር አመላለስ ላይ ጥሩ መሻሻሎች መታየታቸውንም አመልክተዋል፡፡

በማኔጅመንት ደረጃ የተደረገው ማሻሻያና አዳዲስ የአሠራር ሥልት ባንኩን ውጤታ ስለማድረጉም ያከሉት አክሊሉ (ዶ/ር) በቀጣይ ጊዜም ችግር ቢገጥም በሚል ከወዲሁ ታሳቢ የተደረጉ ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ ተደርጓል፡፡ ይህም በመጪው ጊዜ ባንኩ ያለ ምንም ችግር እንዲቀጥል የሚያስችለው ሲሆን፣ የገጠሙትንም ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመፍታት የሚቀጥል መሆኑን እየተገኘ ያለው ውጤት አመላካች መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡  

ወጋገን ባንክ በመላ ኢትዮጵያ ያሉትን ቅርንጫፎች 410 ማድረሱ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር 10,885 የደረሰ ሲሆን፣ አጠቃላይ የሠራተኞቹ ቁጥር ከ5,000 በላይ ነው፡፡ ወጋገን ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር በ2015 የሒሳብ ዓመት ለተለያዩ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ለተሰማሩ አገር በቀል ድርጅቶች እና በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ 35 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች