Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገዳ ባንክ የ87 ሚሊዮን ብር ኪሣራ እንዳጋጠመው አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ በ2015 ዓ.ም. የተቀላቀለው ገዳ ባንክ አገልግሎቱን በይፋ በጀመረበት በ2015 የሒሳብ ዓመት እንቅስቃሴው 87 ሚሊዮን ብር ኪሣራ እንደገጠመው አስታወቀ። 

ይሁን እንጂ፣ ባንኩ ያጋጠመው ኪሣራ በመጀመሪያ የሥራ ዓመት የሚጠበቅ መሆኑን፣ ከሌሎች አዳዲስ ባንኮች አንፃር ሲታይም ያጋጠመው ኪሣራ ዝቅተኛ እንደሆነ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወልዴ ቡልቶ ገልጸዋል። 

ገዳ ባንክ ታኅሳስ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የ2015 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ያቀረበ ሲሆን፣ ባንኩ በ2015 ሒሳብ ዓመት አጋማሽ ወደ ሥራ የገባ ከመሆኑ አኳያ የተመዘገበው ኪሣራ ተጠባቂ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንቱ አቶ ወልዴ ቡልቶ ገልጸዋል።

በመጀመርያው ዓመት ትርፍ የማይጠበቅ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት፣ የተመዘገበው ኪሣራ ከሌሎች አዳዲስ ባንኮች አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። አክለውም፣ ባንካቸው ይህንን እንደ ኪሣራ እንደማይመለከተው የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህም እንደምክንያት ያቀረቡት ባንኩ ሥራ በጀመረበት ዓመት አገልግሎት የሚሰጥበትን የራሱን ሕንፃ መግዛቱን ነው።

ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት፣ ገዳ ባንክ አገልግሎቱን በ2015 ሒሳብ ዓመት የጀመረው የራሱን ሕንፃ በመግዛት በመሆኑ በሒሳብ ዓመቱ የተመዘገበው ኪሣራ ሕንፃው ላይ በዋለው ሀብት የሚያካክስ ነው። ባንኩ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ባስቀመጠው ስትራቴጂ መሠረት አሁን የሚጠቀምበትን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በመግዛት የራሱ ማድረጉን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ይህንን ሕንፃ ቢሸጥ ከተገዛበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ የሚያወጣ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ አቶ ወልዴ፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ ባለው ከፍተኛ ግሽበት ምክንያት ዋጋ ሳያጣ ለቋሚ ንብረት ግዥ መዋሉ የባለአክሲዮኖችን ጥቅም ያስከበረ መሆኑን አስረድተዋል።

‹‹የ2015 የሥራ አፈጻጸማችንን ስናይ ሥራ ላይ የቆየንበት ጊዜ ስድስት ወር ብቻ ነው፡፡ የመጀመርያዎቹን ስድስት ወራት ዝግጅት ላይ ነበርን›› ያሉት አቶ ወልዴ፣ የ2015 ሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውም ባንኩ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ያደረገውን ዝግጅትና ሥራ ከጀመረ በኋላ ያከናወነውን አፈጻጸም የሚመለከት መሆኑን አስረድተዋል።

በዝግጅቱ ወቅት ከተከናወኑት ተግባራት ዋነኛው የባንኩን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ መቅረጽ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህ የባንኩ ስትራቴጂ ሌሎች የዝግጅት ሥራዎች ባንኩን በ2016 የሒሳብ ዓመት ወደ ትርፋማነት እንደ ሚያሸጋግሩ እምነታቸውን ገልጸዋል።

‹‹በዚህ ዓመት ኢንቨስትመንት ላይ ስለነበርን ትርፍ አልተመዘገበም፣›› በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ወልዴ ‹‹የተመዘገበው ኪሣራ በጣም ትንሽ ከመሆኑም ሌላ ከሐምሌ 2015 በኋላ ጥሩ የፋይናንስ አቋም ላይ ነን›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ የባንኩ ቀጣይ ጉዞ ውጤታማ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

በመጀመርያው የሥራ ዘመኑ በዋናነት ትኩረት ያደረገው ባንኩን በማደራጀት ቢሆንም በትክክል ወደ ሥራ በተገባበት ስድስት ወራት ውስጥ ግን በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገቡንም አመልክተዋል፡፡ 

ባንኩ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉ አንዱ ነው፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ደግሞ የሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 73.9 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ መቀሌን ጨምሮ በተመረጡ ቦታዎች የከፈታቸው ቅርንጫፎች ቁጥር 60 መድረሱም ተገልጿል፡፡ ከ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ በኋላም አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈት ቁጥሩን 73 መድረስ መቻሉ ተገልጿል፡፡ 

ይህም አጠቃላይ የአስቀማጮችም ቁጥር 75,480 በላይ እንዲደርስ ያስቻለ ሲሆን ከ847 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንደሰጠ አመልክቷል፡፡ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት አንፃር ከሬሚታንስ 5.77 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ችሏል፡፡ 

ባንኩ ወደ ሥራ ከገባበት ወዲህ አጠቃላይ ያገኘው አጠቃላይ ገቢው ከ111.4 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን ወጪው ደግሞ 246.3 ሚሊዮን ብር እንደነበር በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ 

ገዳ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን 2.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 890.2 ሚሊዮን ብር መሆኑ የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች