Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጎህ ቤቶች ባንክ ፕሬዚዳንት መልቀቂያ አስገቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጎህ ቤቶች ባንክ እንዲቋቋም ዕገዛ በማድረግ የሚጠቀሱትና የባንኩ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አስማረ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ።

አቶ ሙሉጌታ ኃላፊነታቸውን የሚለቁት በገዛ ፈቃዳቸው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ጥያቄያቸውንም የባንኩ ቦርድ እንደተቀበለው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት በቅርቡ የተካሄደው የባንኩ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ከተጠናቀቀ በኋላ ቢሆንም፣ ቀደም ብሎም ከጤና ችግር ጋር በተያያዘ የመልቀቂያ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከፕሬዚዳንቱ የሥራ መልቀቂያ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው የጎህ ቤቶች ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጌታሁን ናና፣ አቶ ሙሉጌታ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን አረጋግጠዋል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ከባንኩ መሥረታ ጀምሮ ትልቅ ዕገዛ ያደረጉና ለባንኩ ቁልፍ ሰው መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ጥያቄያቸው በመግፋቱ መልቀቂያውን ለመቀበል ግድ እንደሆነባቸው አቶ ጌታሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

አቶ ሙሉጌታ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ አሁን የቀረበ ሳይሆን፣ በግል ጉዳይ (ከጤና ጋር የተያያዘ) ቀደም ብሎ የቀረበ ስለመሆኑ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ ጥያቄውን የተመለከተው የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ቢያንስ በቅርቡ እስከተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ እንዲቆዩ በማግባባት እንዳቆያቸው ለማወቅ ተችሏል። 

የአቶ ሙሉጌታ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም፣ የባንኩ ቦርዱ አዲስ ፕሬዚዳንት እስኪሰይም ድረስ ሥራቸውን እየሠሩ እንደሚቆዩ አቶ ጌታሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የጎህ ቤቶች ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ባንኩ የተቋቋመለትን ዓላማ ሊያሳካ የሚችል አዲስ ፕሬዚዳንት በማፈላለግ ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡

ጎህ ቤቶች ባንክ ከሌሎች ባንኮች በተለየ የሞርጌጅ ባንክ (የቤት መሥሪያ ብድር) አገልግሎቶችን በዋናነት የሚያቀርብ በመሆኑና በዚህ ዘርፍ ላይ ልምድ ያለው ባለሙያ እጥረት መኖሩ ይገለጻል። በመሆኑም ባንኩ መልቀቂያ ያስገቡትን ፕሬዚዳንት የሚተካ ባለሙያ ለማግኘት እየጣረ ይገኛል ተብሏል፡፡ 

በኢትዮጵያ በብቸኝነት የሞርጌጅ ባንክ በመሆን ሲሠራ የቆየው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንዲቀላቀል ከተደረገ በኋላ፣ በዘርፉ ራሱን ችሎ የሚሠራ ባንክ ሳይኖር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ከኮንስትራክሽንና ከቢዝነስ ባንክ መክሰም በኋላ፣ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ለመሥራት ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው ብቸኛው ባንክ የጎህ ቤቶች ባንክ ነው፡፡ 

አሁንም ጎህ ቤቶች ባንክ በዘርፉ ልምድ ያለውን የሥራ መሪ ለማግኘት ሊፈተን ይችላል የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፣ ቦርዱ ግን ለባንኩ የሚሆን ባለሙያ ለማግኘት ጥረቱን መቀጠሉ ታውቋል፡፡  

አቶ ሙሉጌታ ከ30 ዓመታት በላይ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሠሩ ሲሆን፣ 17 ዓመታት ያገለገሉት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመምርያ ኃላፊነትን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ መደቦች አገልግለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከለቀቁ በኋላ ደግሞ በአቢሲኒያ ባንክ ከመምርያ ኃላፊነት እስከ ፕሬዚዳንትነት ድረስ ለዘጠኝ ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለአራት ዓመታት ተኩል የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ባንኩን መርተዋል፡፡ የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆንም አገልግለዋል፡፡ አቢሲኒያ ባንክን የለቀቁት የቀድሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ለነበሩት አቶ በቃሉ ዘለቀ ኃላፊነታቸውን በማስረከብ መሆኑ ይታወሳል፡፡ አቶ ሙሉጌታ የጎህ ቤቶች ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሰየሙት ኅዳር 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡ 

ጎህ ቤቶች ባንኩ የተመሠረተው ለ530 ሚሊዮን ብር በተከፈለ ካፒታልና በ1.2 ቢሊዮን ብር በተፈረመ ካፒታል ነው፡፡ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉን 69.3 በመቶ አሳድጎ 1.3 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ውስጥ ለብድር ካዋለው ወደ 1.3 ቢሊዮን ብር ውስጥ ግማሽ ያህሉን ለሞርጌጅ (ቤት) ብድር ማዋሉንና ይህ የብድር አቅርቦትም ከቀዳሚው ዓመት በ342 በመቶ ብልጫ እንደነበረው መጥቀሱ ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች