Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢዜማ አባላት ባይለቁ ደስ ይለናል ነገር ግን የትግል ሥልትና የዓላማ ልዩነት ካለ ምን ማድረግ ይቻላል›› የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ፖለቲካን ከብሔር ተፅዕኖ የማላቀቅ ትልም ይዞ የፖለቲካ ምኅዳሩን የተቀላቀለው የኢትዮጵያ ዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ወዲህ ባሉት ጊዜያት ውስጥ በተለየ ሁኔታ የአባላት መልቀቅ እያጋጠመው ይገኛል። የኢዜማ አባላት በተደጋጋሚና ቀላል በማይባል ቁጥር ፓርቲያቸውን ጥለው የሚወጡበት ምክንያት በአሁኑ ወቅት የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል። የፓርቲው አባላት የሚለቁት ለምንድነው? በፓርቲው ውስጥ ባለ ውስጣዊ ችግር ነው? የሚለውንና በኢዜማ አጠቃላይ ወቅታዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዙሪያ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (/) ከዮሐንስ አንበርብር ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢዜማ አመራሮችን ጨምሮ የፓርቲው አባላት በከፍተኛ ቁጥር እየለቀቁ መሆኑ እየተሰማ ነው። ምንድን ነው ምክንያቱ? ይህ ጉዳይ ፓርቲያችሁ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ችግር አይኖርም ወይም አያሳስባችሁም?

/ ሙሉዓለም– የተለያዩ ሚዲያዎችና የተለያዩ አባለት በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ላይ እንዲህ ዓይነት መልዕክት ሲያስተላልፉ እናያለን። ነገር ግን የኢዜማን አደረጃጀት ካለመረዳት የመነጨ ነው ብለን እናስባለን። ሪፖርተር ጋዜጣም ይህንን የአባላት መልቀቅ በተመለከተ ያወጣው የተሳሳተ ዘገባ አለ፣ መስተካከልም አለበት ብለን እናምናለን። በመሠረታዊነት የኢዜማ አደረጃጀት በምርጫ ክልል ደረጃ ነው። የፓርቲው መሪም፣ ሊቀመንበርም ሆነ አባል በምርጫ ክልል ደረጃ ይመዘገባሉ። በተመዘገቡበት የምርጫ ክልል የፓርቲው አባል ይሆናሉ። ከዚያ በኋላ በሚኖሩ ሒደቶች እያንዳንዱ የምርጫ ክልል የራሱን የጉባዔ ተመራጭ ይልካል፡፡ በዚህ ጉባዔ አማካይነትም የፓርቲው መሪና ሊቀመንበሮች ይመረጣሉ። ሊቀመንበሩ የፓርቲውን ሥራ አስፈጻሚ ይሾማል፣ የፓርቲው መሪ ደግሞ የፓርቲውን ትይዩ ካቢኔ ይሾማል። ይህ ትይዩ ካቤኔ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ካቢኔ የዕለት ተዕለት ተግባር የሚከታተልና የሚቆጣጠር ነው። የትይዩ ካቤኔ አባላት በምርጫ ሳይሆን በፓርቲው መሪ አማካይነት የሚሾሙ እንጂ በምርጫ የሚሰጥ አይደለም። በተመሳሳይም የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ለምሳሌ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ፣ የሴቶች ጉዳይ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና መሰል የሥራ አስፈጻሚ አባላት በሊቀመንበሩ ይሾማሉ። ስለዚህ ይህም በምርጫ ሳይሆን በሹመት የሚሰጥ ነው። እነዚህ ሹመቶች ከምርጫ ክልልና ከወረዳ አደረጃጀቶች ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ስለዚህ በአመራርነት የተመዘገበ አባል በሌለበት ሁኔታ አንድ አመራር ከአመራርነት ለቀኩኝ ሊል አይችልም። ከፓርቲው የለቀቀ አባል ሊለቅ የሚችለው ከምርጫ ክልሉ ነው። ኢዜማ በሁሉም የአገሪቱ ቦታዎች ላይ አደረጃጀቶች አሉት፣ በምርጫው ወቅት እንኳን ወደ 400 አካባቢዎች አደረጃጀቶችን ፈጥሮ ወደ 278 ቢሮዎች ኖረውት የተንቀሳቀሰ ድርጅት ነው። ስለዚህ ከእነዚህ ሁሉ አካባቢዎች የሚገባውንና የሚወጣውን አባል ቁጥር በማየት ብቻ አስር ሰው ለቀቀ፣ በርካታ ሰው ወጣ ማለት ስህተት ውስጥ ይከታል። ስለዚህ እኛ የአባላት መልቀቅን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች የፓርቲውን አደረጃጀት ካለመረዳት የሚመነጭ ነው ብለን ነው የምናነው። 

ሪፖርተርየአባላት መልቀቅ ሁኔታ በስፋት መነሳት የጀመረው ከመጋቢት 2015 .. ጀምሮ ይመስለኛል። ለምሳሌ እኔ ባለኝ መረጃ በመጋቢት ወር 41 የሚሆኑ አባላት ለቀቁ፡፡ በመቀጠል በሰኔ ወር ወደ 250 የሚሆኑት አባላት መልቀቃቸው ተሰማ። ስለዚህ ነገሩ በአመራር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአባላት ደረጃ ጭምር ነው። በዚህን ያህል መጠን አባላት የሚለቁ ከሆነ ደግሞ ፓርቲው ውስጥ አንድ ችግር መኖሩን የሚያመላክት ይመስለኛል። ለዚህ ምክንያት የሆነ ውስጣዊ ችግር በፓርቲው ውስጥለም?

/ ሙሉዓለም– የአባላት መልቀቅን አሁን ባልከው ደረጃ መመልከት ካስፈለገ በ2013 ዓ.ም. ከተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ በጣም ብዙ አባላት ለቀዋል፣ ምናልባትም ትልቁ ቁጥር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እነዚህ አባላት በፓርቲው ውስጣዊ ችግር ነው የለቀቅነው አላሉም። ቀጥሎ ደግሞ ከመንግሥት ጋር መሥራት አለመሥራት የሚል አጀንዳ ተነስቶ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ ከማንኛውም አገራዊ ፓርቲ ጋር እንተባበራለን ብሎ ውሳኔ አሳለፈ። በዚህ ውሳኔ ደስተኛ ያልነበሩ አባሎች ለቀቁ፡፡ ነገር ግን ውስጣዊ ችግር አለ አላሉም። ከዚያ ቀጥሎ ጠቅላላ ጉባዔ አካሄድን። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ ውስጥ የፓርቲ አመራር ላይ የነበሩ ሰዎች ከአመራርነት አይወርዱም ከወረዱ ደግሞ ፓርቲያቸውን ይለቃሉ፣ እንዲሁም የለቀቁትን ፓርቲ የሚቃረን ተግባር ውስጥ ይሳተፋሉ። የእኛ ጠቅላላ ጉባዔ ከተካሄደ በኋላ የተፈጠረው ነገር ይህ ነው። ከዚህ ጉባዔ በኋላ የኢዜማ አመራሮች ለቀቁ የሚል ዜና ተሠራጨ፣ ነገር ግን ውሸት ነበር። አንዳቸውም በወቅቱ አመራር አልነበሩም። እያንዳንዱን ጉዳይ እግር በእግር እየተከታተሉ መልስ መስጠት ትክክል አይደለም ብለን ስለማናምን መልስ አልሰጠንም። በመቀጠል ደግሞ 41 የኢዜማ 80 በመቶ አባላት ለቀቁ ተባለ። በሌላ መልኩ ደግሞ 80 በመቶ የኢዜማ አባላት ለቀቀ ተባለ። ሰማኒያ በመቶ የለቀቀበት ድርጅት እኮ ድርጅት ሆኖ መቀጠል እንደማይችል አልተረዱትም። ለቀቁ የተባሉት 41 አባላት በሙሉ የአንድ የምርጫ ክልል አባላት ነበሩ። ነገር ግን ለቀቁ ከተባሉት 41 ውስጥ ሦስቱ ሰዎች በሕይወት የሉም። በወቅቱ ዝርዝር ምላሽ ሰጥተንበታል። የሚለቀውን ሰው ብዛትና በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ሚና በትክክል ከማየት ባሻገር፣ በፓርቲው የውስጥ ችግር፣ ለምሳሌ በአመራር መከፋፈል ወይም በተፈጠረ የሐሳብ አለመግባባት ምክንያት አንድም የለቀቀ ሰው የለም። አመራር ሆኖ በሕግና ዲሲፕሊን ተጠይቆ የወጣም የለም። የአባላት መልቀቅ ዜና መሆኑ በራሱ ፓርቲው ጠንካራ መሆኑን ያሳያል። እዚህ ፓርቲው ውስጥ ጥሩ ነገር አለ ማለት ነው። በአጠቃላይ በፓርቲው ውስጥ የሐሳብ ልዩነት አይኖርም ማለት አይቻልም። የሐሳብ ልዩነት አለ፣ ወደፊትም ይኖራል። ይህ ግን የሚጠበቅም ነገር ነው። ምክንያቱም አንድን ሰው ሐሳብ ብቻ የሚያቀነቅን ድርጅት አይደለም። የሐሳብ ልዩነት ሲኖር ደግሞ ልዩነቱ የሚጠራበት የፓርቲው አሠራር አለ።

ሪፖርተርከለቀቁት የኢዜማ ፓርቲ አባላት መካከል እኛ ያነጋገርናቸው ሰዎች ለመልቀቃቸው ምክንያት ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች መሠረታዊ የሚባሉት ፓርቲው ዓላማውን ስቷልእንዲሁም የመንግሥት ተከጣፊ ሆኖ እየሠራ ነው፣ ገዥው ፓርቲ እንዲነካበት አይፈልግም፣ እንዲያውም አንድ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ከፓርቲው ጋር መቀጠል አንፈልግም ይላሉ። ለዚህ ምን ምላሽ ይሰጣሉ? ይህንን ጉዳይ ገምግማችኋል?

/ ሙሉዓለም፡- ሁለት ጥያቄዎችን ነው ያነሳኸው። አንደኛው ዓላማ ነው፣ ሌላው ከመንግሥት ጋር መሥራትን የተመለከተ ነው። ዓላማን በተመለከተ ከተነሳው ጥያቄ እንጀምር። እንግዲህ ዓላማ በፕሮግራምህ ውስጥ የምታስቀምጠው ነው። ኢዜማ ደግሞ የፕሮግራም ወይም የዓላማ ለውጥ አላደረገም። ኢዜማ የዜግነት ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ፍትሕና ዴምክራሲያዊ የሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ይፈልጋል። ከዚህ ዓላማችን በፍፁም አልወጣንም። ሰላማዊ ትግል ነው ምርጫችን፣ ከዚህም በፍፁም አልወጣንም። ለማንኛውም በብሔር ስናዳላ አንታይም፡፡ ምክንያቱም መንገዳችንና ዓላማችን ስላልሆነ። በዚህ ቅር የሚላቸው ሰዎች ካሉ ማዘን ብቻ ነው ያለን አማራጭ። ባይለቁ ደስ ይለናል፡፡ ነገር ግን የትግል ሥልት ልዩነት፣ የዓላማ ልዩነት ካለ ምን ማድረግ ይቻላል። ኢዜማ ዓላማውን ስቷል ሊባል የሚችለው ሦስት ነገሮችን ሲስት ነው። በዘውግ ማንነት ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፍ ከተገኘ፣ የሚያቀርባቸው ፖሊሲዎች ማኅበራዊ ፍትሕን ማስፈን የማይችሉ ከሆነ፣ በቋንቋ ላይ ወይም በዘውግ ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝምን ከደገፈ ዓላማውን ስቷል ያስብላል። ኢዜማ እነዚህን እንዳልሳተ እርግጠኛ ነኝ። ሁለተኛ የተነሳው ሐሳብ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ከመንግሥት ጋር መሥራትን በሚመለከት ነው፡፡ ይህ ሐሳብ በ2014 ዓ.ም. በተነሳበት ወቅትም አከራካሪ ጉዳይ ነበር። ይህ ሐሳብ አንዱ ትልቁ ችግሩ አሁን ያለው መንግሥትን ጨምሮ ፓርቲና መንግሥትን ለይቶ የመሥራት ጉዳይ ነው። እኛ ኢዜማን ስንመሠርት መንግሥትና ፓርቲን ለመለየት ብለን የፓርቲው መሪና የፓርቲው ሊቀመንበር የሚል አደረጃጀት ፈጥረናል። የኢዜማ ሊቀመንበር ከመንግሥት ጋር የሚሠራበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም። ሊቀመንበር የሚመራው የፓርቲውን አደረጃጀት ንፁህ የሆነ የፓርቲ ሥራ ነው የሚከውነው። የኢዜማ መሪ ግን ከመንግሥት ጋር መሥራት ይችላል። ከመንግሥት ጋር እንሠራለን ስንልም በምን በምን መንገድ መሥራት እንችላለን ብለን በጉባዔ ያስቀመጥናቸው ሰባት ነጥቦች አሉ። ከመንግሥት ጋር ለመሥራት ካስቀመጥናቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የተመለከተ ነው። አሁን ከኢዜማ ከለቀቁት ውስጥ ብዙዎቹ ከመንግሥት ጋር መሥራትን ደግፈው ድምፅ የሰጡ ናቸው። የልዩነት ሐሳብ ካለ ለማስረጽ መሥራት እንጂ የደገፉትን ሐሳብ ከፓርቲው ለመልቀቅ ምክንያት አድርጎ ማቅረብ ትክክል አይደለም። ከመንግሥት ጋር መሥራት ከመርሀችን ጋር ያለንን ግንኙነት መቆማችንን እንጂ ልዩነትን አያሳይም። ከአባልነት የለቀቁት ብዙዎቹ በፓርቲው ውስጥ የነበራቸውን ሥልጣን ሲያጡ፣ ፓርቲው ከመንግሥት ጋር አብሮ መሥራቱን አንደግፍም አሉ እንጂ፣ በወቅቱ የነበረው ሥራ አስፈጻሚ ሲወሰን ከሁለት ሰዎች በስተቀር ሁሉም ተስማምቷል። ይህንን ሐሳብ ለመቀበል ዴሞክራሲያዊ አሠራርን አለመልመድ፣ እንዲሁም ፓርቲን ገንጥሎ የመውሰድ ፍላጎት ነው። ‹‹እኔ ነኝ ኢዜማ›› የሚሉ ፍላጎቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ፓርቲው አልተከፋፈለም፡፡ ምክንያቱም መዋቅሩ በትክክል የተሠራ በመሆኑ። 

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በኢዜማ ግምገማ አባላቱ የሚለቁበት ምክንያት ምንድን ነው? 

/ ሙሉዓለም፡- ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው። አንዱ የፓርቲው አደረጃጀት ይዞ የተነሳው ዓላማ አዲስ መሆን በራሱ የፈጠረው ችግር አለ። ለምሳሌ የፓርቲው አደረጃጀት መንግሥትና ፓርቲ የሚለውን ግልጽ አድርጎ ለይቷል። የፓርቲው መሪ ኃላፊነቱ እስከምን ድረስ ነው? የሊቀመንበሩ ኃላፊነት ምንድነው? የሚለውን ተረድቶ የመንቀሳቀስ ችግር አለ። ሌላው የትግል ሥልት ልምድ ችግር ነው። ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በሰላማዊ መንግድ የመንግሥት ሥልጣን የተያዘበት ልምድ የለም። የተለመደው በኃይል ሥልጣን መያዝ ነው። ከዚያ በተወረሰ አስተሳሰብ የትግል ሥልትን የመቀላቀል ችግር ነው። 

ሪፖርተር፡- ገዥው ፓርቲ በመንግሥትና በፓርቲ ሥራ መካከል መደበላለቅ እንዳይኖር መስመር ቢያበጅ ትክክልና ተገቢነት አለው የሚል ዕሳቤ አለ። ተቃዋሚ ፓርቲ ግን ሙሉ በሙሉ መንግሥት እስኪሆን ድረስ የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ነው የሚያደርገው። ኢዜማ እንደ ዕድል ሆኖ በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ ውክልና አግኝቷል። እነዚህ የኢዜማ አባላት በመንግሥት ካቤኔ ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ በካቢኔው ውስጥ የሚወስኑት ውሳኔ በፓርቲው እንቅስቃሴ ላይ ችግር አይፈጥርም? ከመንግሥት ጋር ተለጣፊ ነው የሚል ፍረጃና ይህንን የተከተለ ጉዳት አያመጣም? 

/ ሙሉዓለም፡- አንድ ፓርቲ የሚቋቋመው መንግሥት ለመሆን ነው። እኛ መንግሥት ለመሆን ነው የምንሠራው። ስለዚህ ገና መንግሥት ሳንሆን በመንግሥትና በፓርቲ ሥራ መካከል ጥርት ያለ መስመር ማበጀታችን ጥቅም አለው። የፓርቲና የመንግሥት ሥራን መለያየት ያለብን መንግሥት ስንሆን አይደለም ብለን ነው ይህንን አደረጃጀት የፈጠርነው።

ሪፖርተር፡- ጥያቄዬን በምሳሌ ላስረዳ፡፡ ኢዜማ አሁንም የመንግሥትነት ሥልጣን አላገኘም፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ አንድ ውክልና አግኝቷል፡፡ ኢዜማን መስለው በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ የሚሳተፉት አባልና በሚይዙት አቋም በጉዳዮች ላይ የሚሰጡት አስተያየት፣ በኢዜማ ላይ መልሶ ጉዳት አያመጣም ወይ? ‹‹ከመንግሥት ጋር ተለጣፊ›› የሚል ትርጓሜ አላመጣባችሁም ወይ?

/ ሙሉዓለም፡- እሱ ችግር በደንብ አለ፡፡ አሁንም እነዚህም ሁለት ነገሮችን እንመልክት፡፡ አንደኛ ኢዜማ ተቋማዊ አደረጃጀቱ የተለየና አዲስ መሆኑ በራሱ የፈጠረው ችግር አለ፡፡ ይህ ችግር በአባላቱም ሆነ ከአባላቱ ውጪ ባሉ ሰዎች ላይ ይታያል፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ደግሞ ከቀደመው በተለየ መልኩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተወሰነ ደረጃ ማሳተፍ ጀምሯል፡፡ ለምሳሌ የትምህርት ሚኒስትሩ እንደ ትምህርት ሚኒስትር የሚያደርጉትን ንግግርና እንደ ኢዜማ መሪ የሚደርጉትን ንግግር መለየት ብዙ ሰዎች ሲቸገሩ ወይም ሲስቱ እንመለከታለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንም ይህንኑ ጥያቄ እንደ ምሳሌ በመጨመር ለማጥራት ልሞክር፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሙሉ ድምፅ ሲያውጅ፣ ኢዜማን የሚወክሉት የካቢኔ አባላትም የድጋፍ ድምፅ የሰጡ ይመስለኛል፡፡ በእንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ የካቢኔ አባሉ የሚሰጡት ድምፅ ማኅበራዊ መሠረታችሁን አያሳጣችሁም ወይ?

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- በመጀመሪያ ድርጅቱ ግለሰብ አይደለም፡፡ እኛ የኢዜማ አቋም ብለን የምንወስደው በመግለጫ ያስታወቅነው፣ በፕሮግራም፣ በፖሊሲና በመፍትሔ ሐሳቦች ብለን በምናወጣቸው ሰነዶች የገለጽናቸውን ነው፡፡ ከእነዚህ በሰነድ ከገለጽናቸው አቋሞቻችን ተቃራኒ ንግግር ወይም አስተያየት የኢዜማ አቋሞች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ኢዜማ የግለሰብ ድርጅት አይደለም፡፡ በተለመደው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ድርጅትን ለአንድ ሰው አጣብቆ መስጠት ኢዜማ ላይ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም ይህ እንዳይሆን በአደረጃጀትና በአሠራር የጠራ ፓርቲ መሥርተናል፡፡ ነገር ግን የፓርቲው አመራር ወጥተው በሚያደርጉት ንግግር ኢዜማ እንዲህ አለ ተብሎ ይወራል፡፡ ኢዜማ ሐሳብን ወይም አቋሙን የሚገልጸው በራሱ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽና በራሱ መግለጫ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ አመራሮቻችን ከኢዜማ መርህ ውጪ የሆነ ንግግር አድርጎ ያገኘነው መሪ የለም፡፡ በመሠረታዊነት ግን እየገጠመን ያለው የተቃውሞ ምንጭ አሁን ያለውን የገነገነ ብሔርተኝነት ፖለቲካ በመቃወማችን ነው፡፡ ቁጭ ብለን ስንገመግመው የቆምንበትን መርህ የሚያናጋ ጥያቄ ነው እያመጣብን ያለው፡፡ ለአገር ይጠቅማሉ ያልናቸውን የፖሊሲ አቋሞችን እንናገራለን፡፡ በዚያ አቋማችን የሚመጣብን ተቃውሞ ካለ እንቀበላለን፡፡ ድጋፎችም ካሉ እሰየው ነው ብለን ወስነናል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዜማ ከመፈጠሩ ትንሽ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት በጣም ገንግኖ ወጥቷል፡፡ ለዚህ ማሳያው ምናልባትም ለኢዜማ ማኅበራዊ መሠረት ሊሆን የሚችለው አማራ ክልል አካባቢ የአማራ ብሔርተኝነት ገንግኗል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት በገነገነበት ወቅት ኢዜማ የዜግነት ፖለቲካን ይዞ መምጣቱ ትክክል ነው?

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- በእኛ ለትግራይ ሕዝብ ያልጠቀመ ብሔርተኝነት፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ያልጠቀመ ብሔርተኝነት፣ ለአማራ ሕዝብ ይጠቅማል ብለን አናስብም፡፡ ስለዚህ የመጣንበት ጊዜ ውስጥ ገዝፎ የሚታየው ብሔርተኝነት የገነገነበት በሚስልም ጊዜያዊ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ቢሆን ከምርጫችን ጋር መቆምን መቀጠልን ወስነናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ ጨርሶ ብሔርተኝነት የለም ባይባልም ከሌላው አካባቢ የተሻለ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝታችኋል?

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- በአዲስ አበባ ጠንካራ አደረጃጀት አለን፡፡ በነገራችን ላይ ከአዲስ አበባ ውጪም በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ያለን ማኅበራዊ መሠረት ጠንካራ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ለምሳሌ ሰዎችን በዘውግና በቋንቋ የመመዘን አዝማሚያ ዝቅተኛ ነው፡፡ በሌሎች ከተሞችም ያለው ማኅበራዊ ሥሪት ይህንን የሚያበረታታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ብሔርተኝነት ብለን ፖለቲካ ማለት በራሱ ትክክል አይደለም፡፡ የሚለያዩን እንጂ አንተንም እኔንም በእኩልነትና በነፃነት እንድንታይ የሚያደርግ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሌላ ጉዳይ ልውሰድዎት። የኢዜማ መሪ የትምህርት ሚኒስትር ናቸው። ትምህርት ሚኒስቴር ከሚያንቀሳቅሳቸው ተቋማት መካከል ደግሞ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል። በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአዲሱ ትውልድ አካል የሆኑ ወጣት ተማሪዎች አሉ። የፓርቲው መሪ በዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሥርዓትና የትምህርት ጥራት ላይ የሚያስመዘግቡት ውጤት ለኢዜማ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጥሩ ዕድል ሊያመጣ ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ? ለወደፊት የፓርቲው ማኅበራዊ መሠረት ይጠቅማል ብላችሁ ታስባላችሁ?

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- አስበነውም አናውቅም። 

ሪፖርተርጥያቄዬን በሌላ መልኩ ላቅርብልዎት። የኢዜማ መሪ አሁን በሚገኙበት የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነት ላይ ውጤታማ ባይሆኑ፣ በኢዜማ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ችግር ያመጣል የሚል ሥጋት አይፈጥርባችሁም?

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- ጥያቄህን በትክልል ተረድቼው ከሆነ፣ በመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ሚኒስትሩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩት ያለው ነገር በትምህርትና በፖለቲካ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመበጠስ ነው። በጣም ተሳክቶላቸዋል ብዬ ከማስባቸው ነገር አንዱም ይህ ነው። 

ሪፖርተር፡- አሁን የገለጹት ስኬት በራሱ የኢዜማን ገጽታ ይገነባል ብዬ ነው። እንደዚህ ዓይነት በጎ ነገሮች በተደጋገሙ ቁጥር ደግሞ በትምህርት ዘርፍ ያሉ ሰዎች ወደ ኢዜማ እንዲሳቡ ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ዕድሎችን ለመጠቀም ምን ያህል ተዘጋጅታችሁ እየሠራችሁ ነው? በዚህ ዘርፍ ላይ የሚኖር ውድቀት በኢዜማ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ምን ያህል ተዘጋጅታችሁ እየሠራችሁ እንደሆነ ለማወቅ ነው ጥያቄውን ያቀረብኩልዎት። 

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- በግሌ ያነሳኸውን ነገር እጋራለሁ፡፡ ምክንያቱም ብቃት ማሳያም ስለሆነ። አንድ ሰው የመሪነት ብቃቱን የሚያሳይበት ቦታ ስለሆነ። በነገራችን ላይ ሁሉም ኃላፊነት የወሰዱ የኢዜማ አመራሮች በሥራ አፈጻጸማቸው ተሸላሚ ናቸው። ይህንን በማድረጋቸው ለኢዜማ ጥሩ ነው፣ መልካም ነገር ያመጣል። በዚያ ቦታ ላይ ውጤታማ መሆን ካልቻሉ ወይም ሕዝብን የማይጠቅም ነገር ከፈጸሙ ለኢዜማ የሚያመጣው ጉዳት እንዳለው በድንብ አምናለሁ። ከፖለቲካ አንፃር ብንመለከተው ግን ፖለቲካና ትምህርት እስካልተለያዩ ድረስ ጥሩ አይደለም። በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተጀመረው ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዥ የማድረግ ጥረት የትምህርት ሚኒስቴር ሥራ ነው፣ ወይም የኢዜማ ተግባር አይደለም። ነገር ግን ይህንን ተልዕኮ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ለመፈጸም ጥረት እያደረጉ ያሉት የኢዜማ አመራር ትምህርት የሚገባውን ጥራት፣ የሚጠበቅበት ነፃነት ላይ ለማድረስ የሚያደርጉት ጥረት ለኢዜማ ብቻ ሳይሆን ለአገር ሲባል መደገፍ አለበት ብዬ አምናለሁ። የተጀመረው ጥረት ስኬታማ ከሆነ ትልቁ ፋይዳ ለአገር ነው። ምናልባትም ለኢዜማ የሚያተርፈው እንጥፍጣፊ ሊኖር ይችላል፣ ላይኖረውም ይችላል። ምክንያቱም ሁሉንም ስኬት የመንግሥት ስኬት ነው ተብሎ ፕሮፓጋንዳ ሊሠራበትም ይችላል። እኛ በዚህ ሒደት ውስጥ ለአገር የሚጠቅም ፋይዳ ይኖረዋል ወይ የሚለውን ነው የምንገመግመው። ምክንያቱም ድርጅት ከአገር በታች ነው። ይህንን የምንለው ለአፋችን ሳይሆን ከልብ ስለምናምንበት ነው።

ሪፖርተር፡- እዚሁ የትምህርት ዘርፍ ላይ ላቆይዎትና፣ የኢዜማ መሪ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ቅድሚያ ትኩረት የሰጡት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አሰጣጥ ከኩረጃ የፀዳ ለማድረግ ነው። በዚህ ጥረት የመጀመሪያ ዓመት ተግባራቸው በፈተና አሰጣጥ ላይ የነበረውን ዝቅጠት ፍንትው አድርገው ያሳዩ ቢሆንም፣ በቀጣዩ ዓመት ግን ሁኔታው ባለመሻሻሉ በርካታ ወላጆችን አስደንግጧል። በዚህም ምክንያት የትምህርት አሰጣጥ ላይ ያሉት በርካታ ችግሮች ሳይቀረፉ ፈተና አሰጣጡ ላይ ብቻ ማተኮር ከፈረሱ ጋሪው የቀደመ ነው የሚል ትችትን አስከትሏል። ኢዜማ ይህንን ጉዳይ እንዴት ይገመግመዋል? 

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የኢዜማ የትምህርት ሚኒስቴር ትይዩ ካቢኔ ሰዓት ወስደው በእያንዳንዱ ጉዳይ ከዕውቀት የመነጨ አስተያየት ቢሰጡበት እመርጣለሁ። ነገሩን ጠቅለል ባለ መልኩ ብንመለከተው ግን ይህ መሆኑ በማኅበረሰብ ደረጃ ለትምህርት ትልቅ ትኩረት እንዲሰጥ አደርጓል። ለትምህርት የተሰጠው አትኩሮት መቀየር ጀምሯል። ውጤቱ ግን በባለሙያ ቢተነተን እመርጣለሁ። 

ሪፖርተር – ኢዜማ ትይዩ ካቢኔ የሚለውን በሌሎች አገሮች የተለመደ ዕሳቤ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማምጣቱ በርካቶች ላይ ተስፋን መፍጠሩን አስታውሳለሁ። ምክንያቱም የኢዜማ ትይዩ ሚኒስትሮች የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የሥራ አፈጻጸም፣ ፖሊሲና ሌሎች ተግባራት እግር በእግር እየተከታተሉ እንዲታረሙ የማድረግ፣ ኢዜማ ቢሆን ምን ሊያደርግ እንደሚችል የፖሊሲ አማራጮችን ለፖለቲካ ማኅበረሰቡ ያቀርባል የሚል እምነትና ተስፋ በመጫሩ ነው። ነገር ግን እንደተጠበቀው የኢዜማ ትይዩ ካቢኔ ሲንቀሳቀስ አልታየም። ለምንድነው?

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- ከጥያቄህ የምቀበለው ትይዩ ካቢኔው ሲጀመር በነበረው ንቃትና ጉልበት አልቀጠለም። ትክክል ነው፣ እንዳሰብነው አልሄደም። በዚህም ምክንያት ጥቅምት 2016 ዓ.ም. ላይ የፓርቲው መሪ ትይዩ ካቢኔውን እንደ አዲስ አደራጅተውታል።

ሪፖርተር፡- ለምንድነው የፓርቲው መሪ ትይዩ ካባኔውን እንደ አዲስ የማደራጀት ተግባር የተመለከታቸው?

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- በመተዳደሪያ ደንባችን መሠረት ትይዩ ካባኔውን የማደራጀትና የመሾም ሥልጣን የተሰጠው ለኢዜማ መሪ ነው። 

ሪፖርተር፡- ይህ መሆኑ ግን ግጭት የለውም? አሁን ባለው ሁኔታ የኢዜማ መሪ የመንግሥት ካቢኔ አባል ናቸው። የመንግሥት ካቢኔ አባሎች ሆነው የኢዜማን ትይዩ ካቢኔ ለእሳቸው ተጠሪ እንዲሆን ማድረግ ትክክል ነው? ትይዩ ካቢኔውን እሳቸው የሚያደራጁ ከሆነ የመጠለፍ ዕድል አይኖረውም?

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- ያው የፓርቲው መሪ በቋሚነት የመንግሥት ካባኔ አባል አይሆኑም። በተጨማሪም ይህ ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት ካቢኔ አባል ከመሆናቸው አስቀደሞ ነው። የፓርቲው ፕሮግራም የተጻፈው፣ ኢዜማ ምርጫ ቢያሸንፍ መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ፣ በምርጫ ማሸነፍ ካልቻለ ደግሞ መሪው ትይዩ ካቢኔው በመምራት የመንግሥትን እንቅስቃሴ የመከታተል ሚና ይኖረዋል በሚል ዕሳቤ ነው። 

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ ግን የፓርቲው መሪ ትይዩ ካቢኔው መምራታቸው ግጭት የለውም?

ዶ/ር ሙሉዓለም፡- አሁን ባለው ሁኔታ ከሆነ የምትለው፣ የትምህርት ሚኒስትሩ የኢዜማ መሪ ቢሆኑም ለትምህርት ሚኒስቴር የተመደበው የኢዜማ ትይዩ ካቢኔ እግር በእግር እየተከታተለ ኃላፊነቱን መወጣት የሚከለክለው ነገር የለም። ይህንን አለማድረጋችን የእኛ ችግር ነው። በአጠቃላይ ግን ኢዜማ ምንም ችግር የለበትም ፍፁም ነው የሚል አቋም የለኝም። ድክመቶች እንዳሉብን እንረዳለን። አንዱም ይህ ነው። ትይዩ ካባኔው ሊሠራ ያሰበውን አልሠራም። ስለዚህ በድጋሚ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ ጠንካራ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋ አለኝ። 

ሪፖርተር፡- መንግሥት በቅርቡ የባህር ወደብ ስለማግኘትና የቀይ ባህር ፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ የመሆን ፍላጎት እንዳለው ይፋ ማድረጉ፣ አሁን ድረስ ትልቅ የመወያያ ነጥብ ሆኗል። ኢዜማ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንድነው አቋሙ? 

ዶ/ር ሙሉዓለም – በመጽሔቶቻችን ላይ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በየወሩ አቋማችንን እንገልጻለን። ይህም ጉዳይ በመጽሔታችን ላይ ተገልጿል። በነገራችን ላይ ኢዜማ 2011 ዓ.ም. ላይ ሲመሠረት በፀደቀው ፕሮግራማችን ላይ በግልጽ ተቀምጧል። ገና ስንመሠረት ኢትዮጵያ በሕጋዊ፣ በፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ያስፈልጋታል ብለን አስቀምጠናል። ነገር ግን አሁን መንግሥት ጉዳዩን ለፕሮፓጋንዳና ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋሉ ትክክል ነው ብዬ አላስብም፣ ጥቅም የለውም። በተለይ አሁን ያሉብን ብዙ መሠረታዊ ችግሮች ላይ ቁጭ ብለን መነጋገርና ቅራኔዎቻችንን መፍታት ላይ ማተኮር አለብን። 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...