Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየጨረጨሰች ቅንጣት ዕውቀት አልዋጥ ብላ ታስቸግረን?

የጨረጨሰች ቅንጣት ዕውቀት አልዋጥ ብላ ታስቸግረን?

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

አዕምሮን ቀርቅሮ ዛሬም ከታሪክና ከልምድ ላለመማር መንገታገት በብሔርተኞችና በጎጠኞች ብሶ ይገኛል፡፡ የማንነትን ሁለ ነገር ብሔርተኞች ብሔረሰባዊ ማንነት አድርገው በሰየሙና ይህንኑ ማንነት የሁሉ ነገር መክፈቻና መዝጊያ አድርገው አዕምሮንና ሕይወትን በቃኙ ጊዜ፣ ‹‹አዲስ›› መጡን ቅኝት የተቀናቀኑ ደግሞ ግለሰባዊ ማንነትን (እኔነትን) ሰው የመሆን ተቀዳሚ መለኪያ አደረጉት፡፡ ይህ የሁለት በኩል አንድ ዓይና ምክክቶሽ ሲተች ቆይቶ፣ ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ ወደ እዚህ ከሁለቱም ጠርዘኞች ርቆ ወደ መሀል የመጣ አተያይና የፖለቲካ መስመር መምጣቱ አንድ ዕርምጃ ነበር፡፡

ጠርዘኞች ግን ዛሬም ትምህርት የዘለቃቸው አይመስልም፡፡ 2016 ዓ.ም. ኅዳር ወር ውስጥ የተካሄደ አንድ የ‹ሻይ ቡና› ውይይት ለዚህ መስተዋት ነው፡፡ በ‹ዩቲዩብ› የወጣው ቪዲዮ ሁሉንም የውይይት ዝርዝር ያቀረበ ባይመስልም፣ ድምዳሜዬን ስህተት ላይ የሚጥል መረጃ ያጎደለብኝ አይመስለኝም፡፡ አሁን በመንግሥትነት ኢትዮጵያን እየመራ ያለው ብልፅግና ፓርቲ፣ ልዩነት ከሚያደምቅ ብሔርተኝነትም ሆነ የብሔረሰቦችን ማንነት መዘንጋት ከሚፈልግ የአንድነት አቋም የሸሸ፣ ብዝኃነትን ይዘቴ/ሀብቴ ያለ፣ የአገር አንድነትንና ማኅበረሰቦችን ያስተሳሰረ የጋራ ትርክትን የፖለቲካ ውሉ ያደረገ ፓርቲ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ አገርን ለመምራት በሚጣጣር መንግሥት ውስጥ ሹመት የተቋደሰ አንድ ብሔርተኛ ሰው፣ ‹‹ማንነት ምንድነው…?›› በተሰኘ የ‹ሻይ ቡና› አንድ (የኅዳር) ውይይት ላይ ማንነት ብዙ ዓይነት ስለመሆኑ ለአመል ካባዘተ በኋላ ‹‹ዋናው ማንነት ግን ብሔራዊ ማንነት (ኤትኒሲቲ) ነው›› ብሎት አረፈ፡፡ ከእሱ በኋላ ደግሞ ሌላ ሰው ዋናው ማንነት ሰውነት ስለመሆኑ፣ ሰውም ሕይወት ያለው ግለሰብ ስለመሆኑ ይናገርና ግለሰባዊ ማንነትን ተቀዳሚ ያደርጋል፡፡ ሁለቱ ጠርዘኛ ሐሳቦች ከተነገሩ በኋላ አንድ ዶክተር የሁለቱንም ሐሳቦች አንካሳነት ያሳየ ሐሳብ ይፈነጥቃል፡፡ የሰው ማንነትን ግለሰባዊ ብቻ ማድረግም ቡድናዊ ማድረግም ልክ ስላለመሆኑ፣ እያንዳንዳንዱ ግለሰብ ከቤተሰብ ጀምሮ በማኅበራዊ አስተዋጽኦዎች የሚታነፅ ስለመሆኑ ከማውራቱ አወያዩ ጣልቃ ይገባና፣ ‹‹ስለማንነት አገነባብ ለብቻው እናወራለን፣ አሁን ማንነት ምንድነው በሚለው ላይ ብቻ እናትኩር›› በማለት ውል ያስተዋል፡፡ ዶክተሩ የማወራው ስለማንነት አገነባብ ብቻ ሳይሆን ማንነት ራሱ ባለሁለት ገጽ ስለመሆኑ ነው የማለት ፅናት ሳያሳይ ቀረ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዶክተሩ በኋላ፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪው ኦባንግ ሜቶ ንግግር ይመጣል፡፡ ኦባንግ ስለሰውነት ራሱን ምሳሌ አድርጎ ሲያስረዳ፣ ሲወለድ ስም እንኳ ያልነበረው እንደ ነበር በማስገንዘብ ይጀምራል፡፡ እንደ ሥፍራዎች ለውጥ የመጤን ዕድላቸው የሚበላለጥ ብዙ ማንነቶች እንዳሉት ለማስረዳትም ከጋምቤላ አንስቶ ራሱን ፈረንጅ አገር ድረስ እየወሰደ፣ ኦባንግ ወንድ ሰው፣ አኙዋክ፣ የጋምቤላ ሰው፣ ኢትዮጵያዊ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሰው፣ አፍሪካዊ፣ ጥቁር ስለመሆኑ ይናገራል፡፡

ውይይቱ ሄዶ ሄዶ እዚያና እዚህ የተነገሩ እውነቶችን አሰባስቦ ሲሸርብ አላየሁምና ወደ እዚያ ላምራ፡፡ ሰው በአንድ ጊዜ ግለሰባዊም ማኅበራዊም ‹‹እንስሳ›› መሆኑ ያፆለሌ ጊዜ ተራ ዕውቀት ነው፡፡ የእኛ ትምህርት ቀመሶች ግን አዲስ ሆኖብን ስንት ሌላ ሥራ በሚሠራበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ግለሰብነትና ቡድንነት የሚባሉ ጥጎች ላይ ቆመን እንከራከራለን፡፡  የምስጦችንና የጉንዳኖችን ህልውና ብናስተውል በአንድ ጊዜ አንዳንድነትን እንደምናይ ሁሉ ቡድንነትንም እናያለን፡፡ አንዷ ጉንዳን ለመኖር የምትችለው በመንጋው/በቡድኑ ውስጥ ነው፡፡ ቡድኑም ቡድናዊ ህልውናው የሚሟላው የተዋቀረ ሥራ በሚሠሩት በእያንዳንዶቹ ጉንዳኖች አማይነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ስለጉንዳኖች አንዳንድነትና ስለቡድናዊነታቸው ስናወራ፣ ስለሁለት ቀዳሚና ተከታይ ነገሮች እያወራን ሳይሆን፣ ስለአንድ ህላዌ ሁለት ገጾች ነው፡፡ በተናጠል/በአንዳንድነት ያየናቸውን ጉንዳኖች በተዋቀረ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ስንመለከታቸው ቡድን ይሆናሉ፡፡ ደመ ነፍሳዊ ከመሆንና ካለመሆን ልዩነት በስተቀር የሰውም ህልውና እንደዚያው ነው፡፡ አንድ የሰው ጨቅላ የሚወለደው በሰዎች ቡድናዊ/ማኅበራዊ መወቅር ውስጥ፣ በቋንቋ ባህር ውስጥ፣ በዕውቀት/በክህሎቶችና በጥበቦች (ቴክኖሎጂዎች) ባህር ውስጥ ነው፡፡ እነዚህ ባህሮች ማኅበራዊ ባህሮች ናቸው፡፡ ሰው ለተራቀቀ የማሰብና የማወቅ ሥራ የሚያስፈልገውን ቋንቋ የሚያገኘው ከማኅፀን ወጥቶ ባህሩ ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ ማኅበራዊ ባህሩ ውስጥ እስካልገባ ድረስ ሰውነቱ ይጎድልና ያልተሟላ ዱዳ እንስሳ ብቻ ይሆናል፡፡ ነፍሱን የማቆየት ዕድሉም ከባህር የወጣ ዓሳ ከሚደርስበት መንፈራፈር ያልራቀ ነው፡፡ በዛሬው ዓይነት የሰው ኅብረተሰብ አንድ ሰው ብቻውን ተገልሎ መኖር ‹‹መቻሉ›› ግለሰቡ ያለ ማኅበሩ መኖር እንደሚችል የሚያረጋግጥ ሳይሆን፣ የደረስንበት ውስብስብ ማኅበራዊ ባህር ለእያንዳንድነታችን የሚሰጠው የዋናተኝነት ነፃነት ሰፊ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

በተረፈ ሰው ‹‹ጡት›› እየጠባ እንዳደገ ሁሉ፣ የኅብረተሰቡን ልዩ ልዩ የልማት/የዕውቀት ጡቶች ‹‹እየጠባ›› እሱም ትነስም ትብዛ ወተት እየሰጠ ነው የሚኖረው፡፡ በአጭሩ የሰው ማንነት በአንድ ጊዜ ማኅበራዊም ግለሰባዊም ፈርጆች ያሉት ነው፡፡ ህልውናውም በግለሰባዊነቱና በቡድናዊ ተራክቦው ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን አይተካውም፡፡ ከነጠላ ግለሰቦቹ ገለታና በቀለች ተነስተን የቡድን ቀለበቱን እያሰፋን በመላው ዓለም ወዳለው ሰው ብንሄድም ሆነ፣ ከመላው ዓለም ሰው ተነስተን ቀለበቱን እያጠበብን ወደ አንድ ግለሰብ ብናመራም ልዩነት አናመጣም፡፡ በሁለቱም አካሄድ እያንዳንዱ ሰው ከግል ቤቱ አንስቶ እስከ መላ ዓለማችን ድረስ ህልውናውን በሚወስኑ መዓት ክሮች ወይም በብዙ ቀለበቶች የተያያዘ ነው፡፡ የተያያዝንባቸው ቀለበቶች/ክሮች አብረውን ያሉ፣ አብረውን የሚንቀሳቀሱና ህልውናችንን የሚወስኑ ስለመሆናቸው ልብ ላንል እንችላለን፡፡ ከጊዜ ጊዜ ግን ከአንዲት ቤት እስከ መላ ምድሪቱ ህልውናችን መያያዙን የሚያስታውሱን ክስተቶች አይታጡም፡፡ የምድራችንን ሙቀት የሚጨምር አኗኗራችን ከጊዜ ጊዜ እያሰማ ያለው አዳጊ የቅጣት ደወልና ከቅርብ ጊዜ በፊት ዓለማችንን አርበትብቶ የነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ ከእነክትባቱ እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

እነዚህን የመሳሰሉ ትልልቅ አስተዋሾች እያሉን ነው ተቀዳሚው ማንነት ‹‹ግለሰብነት ነው››/‹‹ብሔረሰባዊ ማንነት (ኤትኒሲቲ) ነው›› እያልን የምንደናቆረው! ብሔርተኞች ‹‹ዋናው ማንነት የብሔር/ብሔረሰብ ማንነት ነው›› ሲሉ እውነቱ ከብዷቸው ሳይሆን፣ ዋና ፍላጎታቸው በብሔር ሠፈር ውስጥ ተወሽቆ ሁሉን ነገር (ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን፣ መሬቱን፣ ሥልጣኑን ሁሉ) በዚያ ግቢ ውስጥ መተሳሰብ ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹ግለሰባዊ ማንነት ዋና ነው›› ባዮችም ይህንን የሚሉት፣ የኢትዮጵያን ማኅበረሰበ-ብዙነት በመጋረድ ብሔርተኛነትን የበለጡት እየመሰላቸው ነው፡፡ በሁለቱም አንድ ዓይና አስተሳሰቦች አንጭበርበር፡፡ ዓለምን ከሚያካልሉ ታላላቅ ክስተቶች ዝቅ ብለን፣ ከአካባቢ አካባቢ ያሉ የፖለቲካ ጥልፍልፎቻንን ብንመለከት፣ በግልና በብሔር ግቢ ውስጥ ይቅርና በትልቅ አገር የማንነት ግቢም ውስጥም በሚላወስ ጥረት ታጥረን ዕጣ ፈንታችንን መወሰን አይቻለንም፡፡ ህልውናና ስኬታችን በቀጣና፣ በአኅጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለ ማንነታችን ውስጥ ከሚከናወኑ ጥፋቶችና ልማቶች ጋር ሁሉ የሚሳሳብ ነው፡፡ ቀጣዩ ጽሑፍ ይህንን ለማጤን የሚያግዝ ነው፡፡

ጭቦ የነገሠበት የዛሬ ዓለም

1) በቅርቡ ‹‹Pain Hustlers›› የተሰኘ የሰዎችን ሕመም ስግብግቦች ሲወነብዱበት የሚያሳይ አንድ ፊልም ተመልክቼ ነበር፡፡ ፊልሙ በሁለት ሺሕ አሥራ ምናምን ውስጥ የተሠራ ነው፣ ልብ ወለድም አይደለም፡፡ በአሜሪካ ውስጥ የሆኑ እውነተኛ ድርጊቶችን በጥበብ ያቀናበረ ነው፡፡ የሕመም ሥቃይን ገንዘብ መነገጃ ባደረገው በዚህ ነውረኛ ውንብድና ውስጥ የተሳተፉት የመድኃኒት ኩባንያ ሰዎችና ሐኪሞች ጭምር ናቸው፡፡ ለካንሰር ሕመም የሚታዘዝ ሕመም ማቅለያ መድኃኒትን ከካንሰር ውጪ ብዙ ተጠቃሚ እንዲያገኝ በማድረግ፣ ነውረኞቹ በቶሎ የመክበር ጥማታቸውን ሲያረኩ፣ ብዙ ሰዎችን የመድኃኒቱ ሱሰኛና ጉዳተኛ አደረጉ፡፡ ያደረሱት ጉዳትም በመድኃኒቱ ጠንቅ እስከ መሞት ያደረሰ ነበር፡፡ በወንጀል መያዝና ፀፀት የመጣው ከዚያ በኋላ ነበር፡፡ ዓለምን ባዳረሰው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜም የክትባቱ ምርት የበለፀጉት አገሮች የመድኃኒት ፋብሪካዎች ትልቅ ማትረፊያ እንዲሆን መደረጉንና በክትባቱ ሥርጭትም ጊዜ የምዕራውያኑ ነፍስ ከታዳጊ አገሮች ነፍስ በልጦ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

በዛሬው ጊዜ ስለሰው ልጅ መብትና ስለሕይወት መቆርቆር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የፖለቲካ መነገጃ ሆኗል፡፡ ለሰዎች በመቆርቆር ስም እነ ሊቢያ ውስጥ የተፈጸመው አገር ማተራመስ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሰሜኑ ጦርነት ወቅትም፣ ‹‹ረሃብ እንደ ጦር መሣሪያ ተሠራበት! ዕርዳታ ካልገባ! ተኩስ ማቆም ካልተደረገ! ወዘተ›› የሚሉ ጩኸቶችና ጫናዎች የበረከቱባቸውን ጊዜያት እናስታውሳለን፡፡ እነዚያ ጩኸቶች ከእነዕርዳታ አቅርቦታቸው የጉዳት ቦታን የመረጡ (በፖለቲካ ምክንያት) እንደነበሩም አይረሳም፡፡ ጦርነቱ ከቆመ በኋላ ደግሞ የአሳቢነታቸው ጩኸትና አጣዳፊነት ምን ያህል እንደኮሰሰና ቢጠሩት የማይሰማ እስከ መሆን እንደደረሰ ይኼው እያየነው ነው፡፡ ያኔ በኢትዮጵያ ሁኔታ ‹‹ጦርነት ቆሞ ድርድር ካልተደረገ!›› እያለ መቆሚያ መተንፈሻ አሳጥቶ የነበር የአሜሪካና የአውሮፓ ለሰው ልጆች ‹‹ያሰበ›› ድምፅ፣ ምሥራቅ አውሮፓ ላይ ሲደርስ ሚዛኑ ተገለበጠ፡፡ ምዕራባውያኑ ለሰው ልጅ ካላቸው ‹‹አሳቢነት›› ይልቅ ሩሲያን በጦርነት መስበር በለጠባቸው፡፡ ኔቶን በማስፋፋት ሩሲያን ተንኩሰው ሩሲያ በዩክሬይን ላይ ጦርነት በከፈተች ጊዜ፣ ለዩክሬናውያን ኑሮ መፈራረስ፣ መሞትና በሚሊዮኖች መሰደድ ተንገብግበው ጦርነቱን ለማስቆም ከመታገል ፈንታ፣ ለዩክሬን  መንግሥት መሣሪያ እያገዙ የጦርነቱ ኢቅጥተኛ ተሳታፊ መሆንን መረጡ፡፡

ሐማስ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በግድያና በዕገታ የተነኮሳት እስራኤል በሁለት ወራት የአየርና የየብስ ወረራ ጋዛን ወደ ፍርስራሽነት ለወጠች፡፡ በአሥራ ሺሕ ቤት የሚቆጠሩ ፍልስጤሞች ረገፉ፡፡ ዕልፍ አዕላፍ ፍልስጤማውያን መድረሻ ያጡ ስደተኞችና ሜዳ አዳሪዎች ሆኑ፡፡ ይህንን ሁሉ የንፁኃን ጉዳት፣ ‹‹ለሰው ልጅ ተቆርቋሪዎቹ›› እነ አሜሪካ ሊቋጥሩት የሞከሩት ‹‹እስራኤል ራሷን ከጥቃት የመከላከል መብት አላት›› በሚልና  ‹‹ሐማስ ሲቪሎችንና ሲቪል ተቋማትን ለወታደራዊ ተገንነት ይጠቀማል›› በሚል ከረጢት ነው፡፡ ይህንን ከ‹‹ጋኔሉ›› ይልቅ ‹‹ጋኔል›› ጎታቹን ቡድን ዋና ተጠያቂ ያደረገ ሰበብ በመያዝም፣ አሜሪካ ከሐማስ ሠራዊት ይበልጥ የሲቪሎችን ሕይወት ገፍ በገፍ አፈር ድሜ እያበላ ላለው ጦርነት የመሣሪያ አጋዥና በተወሰነ መጠንም የተኩስ ተሳታፊ ስትሆን አየናት፡፡ በጥቅሉ ከፍልስጤሞች በኩል ሊሰነዘር የሚችል የኃይል ጥቃት ዳግም እንዳይሞከር አድርጎ ለመሰባበር ፍልስጤሞች ላይ የሚወርደው ውርጅብኝ ገና አለበቃም፡፡ እስካሁን በ60 ቀናት ፍጥነት የደረሰው የውርጅብኝ ጉዳትም በቅርብ ዓለማችን ውስጥ ከደረሱ ውድመቶች ተወዳዳሪ የሚገኝለት አይመስልም፡፡ ፍልስጤሞችም በጦርነት ሰቆቃ ታላላቅ የጨለማ ወራት ብለው የሚያስተውሷቸው ወራት የ2016 ጥቅምትና ኅዳር (ምናልባትም ታኅሳስ) ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ የደቡብ አፍሪካዋ የውጭ ጉይይ ሚኒስትር ናላዲ ፓንዶር ከ‹ሲኤንኤን› ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ በፍልስጤማውያን ላይ ዛሬ የደረሰውን፣ ሕዝብን መድረሻ ያሳጣ የአየርና የምድር ዘመቻ አከፋፍ ሲገልጡት፣ ‹‹የዚህ ዓይነት ጥቃት በደቡብ አፍሪካ የዘር መድልኦ ጊዜ እንኳ አልተፈጸመም ነበር›› ያሉት፡፡

ይህ ዛሬ የምንገኝበት ምዕራፍ፣ ‹ሥልጡኑ› እና ‹ለሰው ልጆች መብት የቆመው› ዓለም የስላቅ ቀንድ ያበቀለበትና ራሱ በራሱ ላይ የሚስቅበት ጊዜ ነው፡፡ ይህንን የሚያሳዩ ምልክቶች ጥቂት አይደሉም፡፡ የአሜሪካ የሴኔት ተወካይና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ መሪ ወደ ነበረ ሰው በገባ በአንዲት ታዳጊ አገር (በግብፅ) ጉቦ አማካይነት፣ የ‹ታላቋ› አሜሪካ ውጭ ጉዳይ አካሄድ እንደ ዋዛ ሲቃኝ ያየነው ዛሬ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ስደተኛ መቀበል የታከታቸው አውሮፓውያን አንዱ አጋዣችን ብለው የያዙት (ሊያሸንፉት ያልፈለጉት) የሜድትራኒያን ባህርን ስደተኛ-በላነት ነው፡፡ አውሮፓውያኑ ‹‹አዛኞች›› ባያሌው የሚደርሱት ከሜድትራኒያን የሞት ባህር የተረፉትን ለማዳን ነው፡፡ እንግሊዝ ወደ አገሯ የገቡትን ጥቁር  ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ ማዛወር ከጀመረች ውላ አድራለች፡፡ ‹‹ማዛወር›› እንግዲህ የስደተኞችን መሸጥና ለእነሱ ማራገፊያነት አገር የመከራየት ገመናን ‹‹የማይናገር›› ጨዋ ቃል ነው፡፡

በዓለማችን ውስጥ፣ የፍልስጤሞችን ፍትሐዊ ጥያቄና ትግል በመደገፍ ከእስራኤል ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት እስከ ማቋረጥ ድረስ ጠንካራ አቋም ማየት ብርቅ ያልነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ በደልን ጥቅሜ ያለ ፖለቲካን የሚቃረን/ፍትሐዊ ለመሆን የሚጥር (የሠራተኛ ፓርቲ ፖለቲካ) የነበረበት ጊዜም ነበር፡፡ የሠራተኛ ፓርቲ አባል የነበረና ከኃይል ይልቅ በድርድር የእስራኤል-ፍልስጤምን ጉዳዮች በማስተናገድ ተግባሩ የኖቤል ሽልማት ያገኘና አክራሪዎች የጠመዱት፣ በመጨራሻም ለእነሱ የማይዋጥ ውል ያደርግ ይሆናል በሚል ፍርኃት ያስገደሉት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ይሳሃቅ ራቢን ታሪክም የሩቅ ጊዜ ታሪክ አይደለም፡፡ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ እ.ኤ.አ. በ1995 የተፈጸመ ታሪክ ነው፡፡ ከራቢን መገደል በኋላ የፍልስጤሞች ጉዳይ ተሰሚነት እያሽቆለቆ መጣ ማለት ይቻላል፡፡

ዛሬ መሽቆልቆሉ ከፍቶ፣ የፍልስጤሞች ዕልቂት ‹‹15 ሺሕ ደረሰ…፣ 16 ሺሕ ገባ…፣ ከ17 ሺሕ ዘለለ…››  በሚባልበት ጊዜ የተመድ ጨኸት እንኳ ሰሚ ያጣ ጩኸት ሆኖ ዋና ጸሐፊው አንቀጽ ጠቅሶ ራሱ የፀጥታ ምክር ቤቱን ስብሰባ ጠሪ ሲሆን አየን፡፡ ለሰው በማሰብ ከእኛ በላይ ማን ሊመጣ ከሚሉት ምዕራባውያን በላይ ልቃ፣ እስራኤል በዓለም ፍርድ ቤት እንድትቆም ከመጠየቅ ባለፈ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እስከ ማቋረጥ የጨከነች ተቆርቋሪ አንድ ደቡብ አፍሪካ ሆና መውጣቷም፣ ምዕራባውያኑ ምን ያህል ማፈሪያ የመሆን ደረጃ ላይ እንደደረሱ የሚያጋልጥ ነው፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ውጪ ያለው ቀሪ ቅዋሜም ከልስላሴ ያለፈ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ነፃነት አለ በሚባልባቸው በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች መንግሥታቶቻቸው የጠነከረ ጫና በእስራኤል ላይ እንዲያደርጉ የሚጫን ግዙፍ የቅዋሜ ማዕበል ሲፈጥሩ አላየንም፡፡ ይህም የፖለቲካ ነፃነት የሚታሰረው በሕግ አንቀጽ ብቻ ሳይሆን በፕሮፓጋንዳ አጠባም እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የፖለቲካ ነፃነት ከሠለጠነው ዓለም የኑሮ ዓውድ ከተሰለበ ውሎ አድሯል ለማለት ይቻላል፡፡

ፍልስጤሞች ላይ የደረሰውን ሲዖል በተመለከተ ከሐማስ የሚሰጠው መረጃ፣ በተመድ ከሚሰጠው መረጃ ጋር ይነስም ይብዛ ተቀራራቢ ነው፡፡ አንቶኒ ጉቴሬዝ በኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ስብስባ ላይ፣ ከጋዛ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ 85 በመቶ (ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋው) ስለመፈናቀሉ፣ ከጋዛ ቤቶች 70 በመቶ ያህሉ ስለመፈራረሱና ስለመጎዳቱ ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ መረጃዎች ሲገናዘቡ መጠለያ የለሹ የትየለሌ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ሐኪም ቤቶች ፈራርሰዋል፡፡ ሕክምና ግቢና ሜዳ ላይ የሚሰጥ ሆኗል፡፡ 90 በመቶ ሕዝቡ በምግብ እጥረት ውስጥ ወድቋል፡፡ ከአየርና ከየብስ ጥቃቱ ባሻገር፣ የምግብ፣ የሕክምናና የመድኃኒት፣ የንፅህናና የመጠለያ እጥረቱ፣ ከእነ ትፍግፍጉ ሌላ ሞትና ሕመም ያመርታል፡፡ የሕክምና ሠራተኛ፣ ጋዜጠኛ፣ የተመድ ሠራተኛ፣ ደርዘን በደርዘን ያልሞተ የለም፡፡ ‹‹ደርዘን በደርዘን›› ቁጥር ለመናገር አያመችም፡፡ ለምሳሌ ከተመድ ሠራተኞች የሞቱት ከመቶ አልፈዋል፣ የሞቱ ጋዜጠኞች ቁጥርም 80 ገብቷል እየተባለ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ቁጥር መሽቶ ሲነጋ ነግቶ ሲመሽ የሚቀየር ነው፡፡ ቢሆንም ትልልቆቹ ሚዲያዎች እንዴት እንደሚዋሹ ላየን ኢትዮጵያውያን የቁጥር በፍጥነት ማደግ ብዙም አንጀታችን አይገባ ይሆናል፡፡ የውጊያውን የውድመት አካሄድ ለማስተዋል መቻል ግን ለእውነት የቀረበ ግምት ለመያዝ በጣም ያግዛል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት በተሰበሰበበት ዕለት ይሁን በማግሥቱ ትዝ አይለኝም እንጂ፣ የአልጀዚራው ጋዜጠኛ አንድ ፍልስጤማዊ እያናገረ ዘገባ በሚያቀርብበት ወቅት ደህና የነበሩ ሕንፃዎች ሲደረመሱ፣ ቃለ መጠይቅ ይደረግለት የነበረ ሰው ቤቱ በቦምብ ሊደረመስ ስለመሆኑ የስልክ መረጃ ደርሶት ያንን ለጋዜጠኛው ሲያሳይ፣ ከዚያም በኋላ የድርመሳው ምሥል መጥቶ ለመከታተል ችያለሁ፡፡ ከደቂቃዎች በፊት የሕክምና አገልግሎት ይሰጥበት የነበረ ሥፍራም ቦምብ ፈንድቶበት ሕፃናትና አዋቂዎች ቆስለው ሲላቀሱ፣ በቤቱ መደርመስ ያላለቀሰ፣ የቃለ መጠይቅ ሰውየውም ዋይታ ውስጥ ሲገባ በበኩሌ አይቻለሁ፡፡

ዓረብ ኤምሬትስ ያረቀቀችው አስቸኳይ የተኩስ ማቆምን የሚጠራ የውሳኔ ሐሳብ እንዳይፀድቅ ለማድረግ የእስራኤሉ የተመድ አምባሳደር ያቀረበው መከራከሪያ፣ በዛሬው ዓለም ፍትሐዊ አስተሳሰብ ምን ያህል አዘቅት እንደወረደ ያሳየ ነበር፡፡ በሶሪያ፣ በየመን፣ በዩክሬይን ያ ሁሉ የጦርነት ውድመት/የሕዝብ ሞትና መፈናቀል ሲደርስ የተመድ ዋና ጸሐፊ በአንቀጽ 99 መሠረት የፀጥታ ምክር ቤቱን ለመጥራት አለመፍጠኑና ‹‹ተኩስ በአስቸኳይ ይቁም›› ዋና ጩኸት ያልነበረ መሆኑ ነበር መከራከሪያ ሆኖ የቀረበው፡፡ የአምባሳደሩን መከራከሪያ የአልጀዚራው ጋዜጠኛ ሊያሳጣ የሞከረበትም መከራከሪያ አስተዛዛቢ ነበር፡፡ “በእነዚያ አገሮች ውስጥ የፍልስጤሞችን የሁለት ወራት ግዙፍ ዕልቂትና ውድመት የሚያህል አልደረሰም›› የሚል፡፡ ጋዜጠኛው አድላዊ ባይሆን ኖሮ የሰዎች ሕይወት መፈራረስን በጊዜ ርዝማኔ ውስጥ የማበላለጥ ጅል ማነፃፀር ውስጥ ሳይገባ፣ ዛሬ በፍልስጤሞች ላይ ለደረሰውና የእስራኤሉ አምባሳደር መከራከሪያ ቢሆነኝ ብሎ በጠቀሳቸው አገሮችም ውስጥ በሕዝቦች ላይ ለደረሰው ሲዖል ዓለማችን ኡኡ ብሎ የሚጮህ ተቆርቋሪነት ያጣበት ዘመን ላይ መገኘታችንን ማሳየት በቻለ ነበር፡፡  አሜሪካም በተመድ አምባሳደሯ አማካይነት ለፀጥታው ምክር ቤት በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ የሰነዘረችው ማዋደቂያ ከእስራኤሉ ተወካይ ያልተሻለ ነበር፡፡ ረቂቁ ሐማስን ባለመንቀፉ ሽብርን ለማስቆም መፍትሔ ባለመሆኑ ስትነቅፍና ድምፅን በድምፅ በመሻር ሥልጣኗ የተኩስ መቆምን ውድቅ ስታደርግ፣ በጥቃትና በዕገታ እስራኤልንና እነ አሜሪካን የተዳፈረውን የወረራ ጋባዥ፣ ንፁኃንን በሰፊው እየቀጣ ካለው ወራሪ ይበልጥ ጥፋተኛ ማድረጓና ሰፊው ቅጣት እንዲቀጥል ፈቃድ መስጠቷ ነበር፡፡ የዘመናችን ቅሌት ይህንን ያህል ነው፡፡

2) ይህንን ሁሉ የነካካሁት የ‹‹ብሪክስ›› አባል መሆንን ተገን እንደ ማግኘት የሚያይ ቅዠት እንዳይፈጠር በመሥጋት ነው፡፡ ፍልስጤሞች ይህንን ያህል የከፋ የሁለት ወራት ሲዖል ሲያዩ የአሜሪካና የእስራኤል ማናለብኝነትን በቁጣ የሚገዳደር ቅዋሜ በማነቃቃትና የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ አስጠሪ በመሆን፣ የፍትሕ ሞራልን ከፍ የሚያደርግ ሙቀት ከብሪክስ አካባቢ አላየንም፡፡ የዛሬው ዓለማችን የፍትሐዊነት ችግር ሁሉም ሠፈር ውስጥ ያለ ቢሆንም፣ ከሠፈሮች ተቃርኖ ሊገኝ የሚችለውን ያህል መፈልቀቅ የሚቻልበት ብስል ሁኔታ ውስጥ አይደለም ያለነው፡፡ ሩሲያ ብልህ ባልሆነችበት ጦርነት ተወጥራለች፡፡ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ግንኙነት ውስጥ  ከገለልተኛነት የዘለለ ንቁ ተሳትፎ የጀማመረችው ቻይና፣ ገና መሽኮርመሟ አልተራገፈም፡፡ በአሜሪካ ነገር ፈላጊነት ከአሜሪካ ጋር ገብታበት የነበረ መቃቃርና መተነኳኮል በአሜሪካ ተነሳሽነት አሁን ‹‹የመለሳለስ›› ሁኔታ ውስጥ ገብቷል፡፡ በፍልስጤሞች መወረር ላይ አሜሪካ ያሳየችው አቋም ላይ ጠንካራ ቅዋሜ በመሰንዘር ቻይና ‹‹የበረደ›› ነገርን እንዳታደፈርስ ተቆጥባለች፡፡ እስካሁን ባላት የሲኖ-አሜሪካ ግንኙነት ውስጥም አሜሪካ ለምታሳየው ተለዋዋጭ አቋም አፀፋ ምላሽ ከመስጠት በቀር፣ የሁለቱን ግንኙነት በተመለተ በራሷ አነሳሽነት የአቋም ለውጥ ስታደርግ አልታየችም፡፡  ቻይና በተነሳሽነት የዓለምን አካሄድ የመቅዘፍ ሚናዋ እየጨመረ ጠንካራ ተገዳዳሪ መሆን እስካልጀመረችና ሩሲያም ከገባችበት የጦርነት ማጥ እስካልወጣች ድረስ፣ የብሪክስ ሠፈር የአሜሪካን ማናለብኝነት የመመከት ሚና አይኖረውም፡፡ በዚህ ክፍተት ውስጥ የፍልስጤሞች ትግል ትልቅ ስብራት ይደርስበት ይሆናል፡፡ ተስፋ በቆረጠ ስደት የፍልስጤሞች ቁጥር ሳስቶ፣ ከአሁኑ የተቸኮለበት መንደር የማስፋት የእስራኤል ሩጫ ይደላውም ይሆናል፡፡ አሜሪካም በሆድ እየተጠላችም ቢሆን መፈራቷና ማናለብኝነቷ ይቀጥላል፡፡ ጀርመንና ፈረንሣይ የሚመሩት የአውሮፓ ኅብረት እንደ ዶናልድ ትራምፕ ያለ ተጋፊ ካልመጣባቸው ብዙም አቋመ ፅኑ አይደሉም፡፡ አሜሪካ ከሩሲያና ከቻይና ጋር ቅራኔ በማሞቅ አውሮፓውያንን በቀላሉ ከጀርባዋ ማሠለፍ እንደምትችልም በጆ ባይደን ሥልጣን ጊዜ ዓይተነዋል፡፡ በእስራኤል ግፈኛ ጥቃት ላይ ያላቸው አቋምም የአሜሪካ አጫፋሪ ከመሆን እጅግም የራቀ አይደለም፡፡

ይህን መሰሉ የፖለቲካ ደመና ጥንቃቄን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ አገራችን በአሁኑ ጊዜ ከእነ ጀርመን አውሮፓ ጋር ያላት ግንኙነት በአንፃራዊነት ከአሜሪካ ጋር ካላት ይሻላል፡፡ ከአሜሪካ ጋር ያለን ግንኙነት ለስላሳ ብጤ ቢሆንም፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ ያደረጉት ስብሰባ እንደፈነጠቀልን ‹ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ይልቅ ወደ ሩሲያ ያዘነበለችና ከአሜሪካ የምትሻው ገንዘባችንን ነው› የሚል መሳይ ቅሬታ ሆዳቸው ውስጥ ሳይገባ አልቀረም፡፡ ይህ የቅሬታ ፍሬ ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ የአሜሪካ መንግሥት የግንኙነት መተለሚያ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ካለፈው ጊዜ ለበለጠ የውጭ ጣልቃ ገብነት አደጋ ተጋልጣ እንደምትገኝ መታወቅ አለበት፡፡ ለጣልቃ ገብነት አደጋ ራሳችንን የማናጋልጠው ፈጥነን ኦሮሚያና አማራ አካባቢ ያለውን የሰላም ዕጦት መፍታት ከቻልን ነው፡፡ እኛ ከእነዚህ ቀውሶች ጋር እያዘገምን አሜሪካ ከዞረችብን፣ የእነ ጀርመን አውሮፓ ኅብረት ከአሜሪካ ጋር ካላቸው የጥቅም ወዳጅነት የእኛን ወዳጅነት አስበልጠው ከእኛ ጋር ይቆማሉ ብሎ የሚያስብ የመንግሥት ሰው ካለ የዋህ መሆን አለበት፡፡

‹‹አሜሪካ ከዞረችብን›› ሲባል ምዕራብ አውሮፓን ልታሳድምብን ስለመቻሏ፣ ብድርና ዕርዳታ በመሸምቀቅና በማዕቀብ ስለመጉዳት አቅሟ ወይም የሆነ የውስጥ ቡድን ደግፋ በሴራ መንግሥት ስለመቀየር ልምዷ ሊታሰበን ይችል ይሆናል፡፡ እዚያ ሁሉ ውስጥ መግባት ሳያስፈልጋት ድምፁዋን አጥፍታ ኢኮኖሚያችንን ጣሪያ በነካ ግሽበት ድራሹን ልታጣፋውና ወደ ከፋ ምስቅልቅል ልታደርሰን የሚያስችል ድፍን ዕድል አለላት፡፡ ኦሮሚያና አማራ አካባቢዎች ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴንና መስተጋብርን እያወላከፈ ያለ የሰላም ማጣት እየባሰበት ከሄደና በቶሎ ካልተወገደ፣ በውጭ ሻጥር ለመመሳቀል የተመቸ አቅም ማነስ ውስጥ መግባታችን አይቀርም፡፡ ስለዚህ አቅም ማነስ ምንነትና ሌሎች አገሮች ምን እንደደረሰባቸው (በአፍሪካም ከአፍሪካ ውጪም) ማተት አይጠበቅብኝም፡፡ ከዚህ አጋላጭ አቅም ማነስ ለመውጣት ለሰላም መሥራት ይደር የማይባል ጉዳይ ነው፡፡

ጉዳዩ ከእጅ አዙር አተራማሽነት የማምለጥ ነገር ብቻ አይደለም፡፡ በሕዝብ ቁጣ ፍንዳታ፣ አዲስ የተጀመረ የታሪክ ጉዞ አቅጣጫውን ወደ ሳተ ቀውስ እንዳይገባ የመፍጠንም ጉዳይ ነው፡፡ የሕዝብ ቁጣ ሲባል ቅጥ እያጣ የመጣው የኑሮ ውድነት ሊፈጥረው ስለሚችል ፍንዳታ ለማውራት አይደለም፡፡ ከዚያ በላቀ ደረጃ ከተኩስ ድምፅ፣ ከግድያና ከመፈናቅል የመገላገል ጉዳይ መላ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ የሚንቆራጠጥበት ምሬት ሆኗል፡፡ ከሸኔ ጋር 2016 ዓ.ም. ኅዳር ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ድርድር ከሸፈ ሲባል፣ በኅብረተሰባችን ውስጥ የደረሰው መሳቀቅ ወሯ የገባ ነፍሰ ጡር ላይ የሚደርስ ማስወረድ የሚፈጥረውን ድንጋጤ ያህል ከባድ ነበር፡፡ መርዶውን ተከትሎ ከሃይማኖቶችና ከፖለቲከኞች አካባቢ፣ በውጭ ከሚገኙ የኦሮሞ ማኅበረሰብ በኩልም ድርድሩ እንዲቀጥል የተደረገው ተማፅኖ ይህንኑ የሚያስተጋባ ነው፡፡ በአማራ ውስጥ ያለው የሰላም ዕጦት እንዲቆምም የሁሉ ተማፅኖ ነው፡፡ ነጋ ጠባ ሰላም ውለን እናድር ይሆን ከሚል ሥጋት መላቀቅ፣ በተኩስ ከመደንበር—ከመተራመስ—ከመፈናቀል መላቀቅ፣ ከሥራ/ከልማት/ከትምህርት ከመተጓጎልና ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ ካለመቻል መገላገል፣  የምጥ ጭንቀት ያልሆነበት ማን አለ!! ከተዳጊ ተማሪ እስከ አዛውንት ድረስ፣ ከተራ ሠርቶ-በል እስከ ሃይማኖት መሪዎች ድረስ ያለው ድምፅ ያወጣና ድምፅ አልባ ጩኸት አንድ ነገር የሚናገር ነው፡፡ እንዴትም እንዴትም አድርጋችሁ ተደርድራችሁና ተስማምታችሁ ሰላምን ውለዷት!!!! የሚል፡፡ ይህ የሰላም ተማፅኖ ትግል ብላችሁ ጠመንጃ ለምትተኩሱ ጭምር ነው፡፡

ለሰላምና ለድርድር እንድንበረታ የሚጎተጉተን የሕዝብ ሰቆቃ ብቻ አይደለም፡፡ ኑሮ ውድነቱን የማቅለል፣ በመረብ የተሳሰረ ዘረፋን የመበጣጠስ፣ መልሶ ማቋቋምንና መልሶ ግንባታን የማቃናትና ልማትን የማስወንጨፍ ተግባራት ሁሉ ከጠመንጃ ተኩስ ትርምስ ከመገላገል ጋር እጅግ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ የተጠቀሱት ተግባራት የተያያዘ ስኬት ያለ ሰላም ፈፅሞ አይቃናም፡፡ ይህ ራሱ ሰላምን እጅግ እንድንጥርላት ግድ ይለናል፡፡

ሰላምን ልንጨብጣት ከቻልን፣ ዛሬ የተያያዝነው የለውጥ መንገድ እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ አሁን የተጀማመሩት የልማት ውጥኖችና በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊጨበጡ የሚችሉት የልማት ድሎች በሕወሓት/ከኢሕዴግ ጊዜ ያሳለፍናቸው የ27 ዓመታት ጊዜያት ምን ያህል የባከኑ ጊዜያት እንደነበሩ የማሳየት ግርምት ሊፈጥሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ በሕዝቦች የተያያዘ ተስፋና እልህ ብዙ ርቀት ለመሄድ እንደሚያንደረድሩንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሰላም ይህን ሁሉ የስኬት ዕድል ይዞልን ነው የሚመጣው፡፡ የዕድል በሩን የመክፈቱ ተግባር እጃችን ላይ ነው ያለውና አናባክነው፡፡ መንግሥት የምር ሰላም ቅርባችን ሊሆን የሚችልበትን ሰላማዊ መንገድ ሁሉ ከልቡ ሆኖ ይትጋበት፡፡ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ባለሀብቶች፣ የሕዝብ አባላት ሁሉ ባለጠመንጃ ቡድኖችን ከመደገፍ አባዜ ወጥተን ሰላም እንዲወርድ የመሸምገል/የመማለድ ተግባር ላይ እንረባረብ!!!

የኢትዮጵያ ሰላም አግኝቶ መዝለቅና በግስጋሴ ማብራት የኢትዮጵያውን ብቻ ጉዳይ አይደለም፡፡ የአፍሪካና የመላ ጥቁር ሕዝቦችም ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ከጠመንጃ ተኩስና ከመፈናቀል መገላገል ስለት በሆነበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ቅርስና ትምህርት ማዕከል እንድትሆን መመረጧ በራሱ፣ የሰላም ጥረታችንን እጥፍ ድርብ ከማድረግም በላይ ሁላችንም ሥራችን ብለን እንድንተጋበት አደራ ጥሎብናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...