Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኤክስፖርትን እናበረታታለን ከተባለ አደናቃፊ ነገሮችን ማረም ያሻል!

‹‹ለመንቀሳቀሻ ፈቃድ ጠያቂዎች በሙሉ ከጥቅምት 12-02-2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ምንም ዓይነት የተሽከርካሪ መንቀሳቀሻ ፈቃድ የማንሰጥ መሆኑን እንገልጻለን›› የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ

ይህ ማስታወቂያ ሁሉንም ዓይነት የጭነት ተሽከርካሪዎችን የሚመለከት ነው፡፡ እነዚህ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው ሰዓት ውጪ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ከተፈቀደላቸው ሰዓት ውጪ መንቀሳቀስ ግድ የሚላቸው ከሆነ የግድ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ማኔጅመንት ኤጀንሲን ፈቃድ ማግኘት አለባቸው፡፡

እንዲህ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ የከተማዋን የትራፈክ መጨናነቅ ለማቃለል ታስቦ የተተገበረ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ያቃልላል ተብሎ እየተተገበረ ያለው አሠራር በሌላ መንገድ ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡ በተለይ የቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑ ይታመናል፡፡

ፈቃዱን ለማግኘት ያለው መጉላላትም ቀላል አይደለም፡፡ ለአንድ ወር ፈቃድ አልሰጥም ያለው ኤጀንሲ ከዚህ በኋላ ፈቃዱን ለመስጠት የሚችል መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡ ፈቃዱን ደግሞ ለመስጠት የከተማ አስተዳደሩን ውሳኔ እየተጠባበቀ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ለማንኛውም የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች የአገልግሎት ዓይነት የተለያየ ቢሆንም በዚህ አሠራር የበለጠ ችግር እየገጠማቸው ያሉት የወጪ ንግድ ምርቶችን የሚያመላልሱ ማቀዝቀዣ ያላቸው ተሽከርካሪዎች ጉዳይ ግን በተለየ ሊታይ የሚባው ነው፡፡ እንደ ሌሎች የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በዚህ አሠራር ማዕቀፍ ውስጥ መግባታቸው ላኪዎችን ያልታሰበ ችግር ውስጥ እየከተታቸው መሆኑ እየሰተማ ነው፡፡ ለውጭ ገበያ መቅረብ ያለበትን ምርት በቶሎ ለማቅረብ እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡

የእነዚህ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች ለወጭ ንግድ የሚቀርቡ ምርቶቻቸውን በፈለጉት ሰዓት ከምርት ቦታው ወደ ኤርፖርት ለማድረስ ከፈለጉ የግድ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ፈቃድ ማግኘት ስለሚኖርባቸው ይህንን ፈቃድ ካላገኙ ምርቱን ሊልኩ አይችሉም፡፡

በዋናነት ፍቃዱ የሚያስፈልጋቸው ለከባድ ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደው ሰዓት ውጪ በአዲስ አበባ ከተማ አውራ ጎዳናዎች መንቀሳቀስ እንዲችሉ ቢሆንም የፈቃድ አሰጣጡ ቢሮክራሲ የበዛበት ሆኗል፡፡ አሁን ደግሞ ኤጀንሲው መጀመርያ አንድ ወር አገልግሎቱን ካቆመ በኋላ አሁን ጭራሽ ይህንን የመንቀሳቀሻ ፈቃድ እየሰጠ አለመሆኑ ጉዳዩን አወሳስቦታል፡፡

የወጪ ንግድ ምርቶችን የሚያጓጉዙት የእነዚህ ተሸከርካሪዎች ባለንብረቶች ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ተሽከርካሪውን ለማንቀሳቀስ መውሰድ ያለባቸው ፈቃድ ደግሞ በየወሩ መታደስ ስለሚኖርበት ይህንን ማድረግ ግዴታቸው ነው፡፡

የወጪ ንግድ ምርቶችን የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች እንደ ሌሎች የጭነት ተሽከርካሪዎች በተጠቀሰው ሰዓት ለማንቀሳቀስ በአስገዳጅነት ሥራ ላይ ያለው አሠራር አስፈላጊነት ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡

የወጪ ንግድ ምርትን ያህል ዕቃ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ኤጀንሲው ባለፉት ሁለት ዓመታት እየሠራበት ባለው ደንብ ተገዥ ሆነው ለመሥራት የሚገጥማቸው ችግር ሥራቸው ላይ እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ከላይ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ማስታወቂያ ለችግሩ አንድ ማሳያ የሚሆነው በተቀመጠው አሠራር እንኳን እነዚህን ተሽከርካሪዎች ለማስተናገድ አለመቻሉን ነው፡፡

ስለዚህ የኤጀንሲው አሠራር ችግር አያለበት በመሆኑ አሠራሩን መፈተሽ እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ከማስታወቂያው በደንብ መገንዘብ እንደሚቻለው በግልጽ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ አገልግሎት አንሰጥም ማለት አንድ የወጪ ንግድ ምርት ማቀዝቀዣ ባለው ተሽከርካሪ መላክ ያለበት ምርቱን መላክ አይችልም ማለት ነው፡፡ ይህ ፈቃድ አገልግሎቱ በተቋረጠበት ወቅት ተሽከርካሪዎቹን ለማንቀሳቀስ ፍቃዳቸውን ለማሳደስ የቀረቡ ድርጅቶች ሊስተናገዱ ሳይችሉ መቅረታቸው ሥራቸው ላይ ጫና እንዳሳደረ ሲገልጹም ተሰምቷል፡፡ አስገራሚ ነገር ግን ከቢሮ የሚሰጠው የማንቀሳቀሻ ፈቃድ በተጠቀሱት ጊዜያት ውስጥ አንሰጥም እየተባለ በሌላ በኩል ደግሞ ምርቱን ጭነው ሲንቀሳቀሱ በትራፊክ እየተጋለጡ መሆኑ አሠራሩን ጉራማይሌ ያደርገዋል፡፡

በዚህ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ አለ የተባለው ችግር ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ተሽከርካሪዎችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችለውን ፈቃድ ለጊዜው አንሰጥም በተባለበት የጊዜ ገደብ ውስጥ አንዳንዶች ፈቃድ አግኝተው መንቀሳቀሳቸው ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው አሠራሩ ለሙስና ተጋላጭ መሆኑን ነው፡፡ ለሁሉም አገልግሎቱ አይሰጥም ከተባለ ለአንዱ ሰጥቶ  ለሌላው የሚከለከልበት ምክንያት ምንድነው?

በአጠቃላይ በአንድ አገር ውስጥ ተጨባጭ ፋይዳ ያለውን የወጪ ንግድ ምርቶች ከማምረቻ ቦታ ወደ ኤርፖርት የሚያጓጉዙ እነዚህን ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዲህ ባለው አሠራር መተብተቡ በራሱ አግባብ አይሆንም፡፡

ሥጋ፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ወደ ውጪ ሲላክ ደግሞ የበረራ ሰዓቱና የሚጫንበትም አገር የተለያዩ በመሆኑ እነዚህን ምርቶች የሚያጓጉዙ ተሽከርከሪዎችን የመንቀሳቀሻ ሰዓት መገደብ የወጪ ንግድ ሥራ ላይ እንቅፋት መሆን ነው፡፡

ኤክስፖርትን እናበረታታለን እየተባለ እንዲህ ያሉ አደነቃቃፊ አሠራሮች አስፈላጊነታቸው ደግሞ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ አንድ የአበባ የአትክልት፣ ፍራፍሬ ሥጋና መሰል ማቀዝቀዣ ያላቸው ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ግድ የሚለው ኤክስፖርተር ተሽከርካሪውን ለማንቀሳቀስ በየወሩ የመንግሥትን ደጃፍ እንዲጠኑስ የሚደረገው ለምንድነው? በየወሩ ፈቃዱን ለማግኘት የሚከፈለውስ ክፍያ ምን ይጠቅማል፡፡

በአገር ደረጃ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ከደረጃ ዝቅ ከምንልባቸው ጉዳዮች አንዱ እንዲህ ያሉ አስፈላጊነታቸው ትርጉም የማይሰጡ አሠራሮች ተደማምረው እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ኤክስፖርትን እናበረታታለን ከተባለ እንዲህ አደናቃፊ ነገሮችንም በማረም መሆን አለበት፡፡ በሌሎች አገሮች የወጪ ንግድ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱበት አሠራር አላቸው፡፡ የወጪ ንግድ ምርቱን ለማጓጓዝ ገደብ የለባቸውም፡፡ ስትንቀሳቀሱ ደግሞ ይህንን ክፈሉ የሚባልበት አሠራር የለም፡፡

በኢትዮጵያ ግን ለውጭ ገበያ ምርት የያዙ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ አይችሉም መባሉ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ምርቱን በፈለገበት ሰዓት የተፈለገው ቦት እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ የተቀመጠውን መመርያ ለመፈጸም ሲባል የተጫነ ምርት የሚበላሽበትም አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚወስደውም ጊዜ ሲታሰብ ጉዳቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡

ኤጀንሲው የእነዚህን ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በሰዓት ለመገደብ የተነሳበት ምክንያት ምንም ይሁን ምንም ከተፈቀደው ሰዓት ውጪ መንቀሳቀስ አትችሉም በመባላቸው ሊታጣ የሚችለው አገራዊ ጥቅም መታሰብ ነበረበት፡፡ ደግሞስ በትክክል ሥራቸውን እየሠሩ ከሆነና 24 ሰዓት ቢንቀሳቀሱ የሚያመጡት ችግር አለ ተብሎ አይታሰብም፡፡

ምክንያቱም የትራፊክ መጨናነቅ ይፈጥራሉ እንዳይባል፣ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ሊፈጥሩ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ቀድሞም ቢሆን ኤጀንሲው በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ሲተገበር የቆየው አሠራር ነገሮችን ከማወሳሰብ በቀር ያስገኘው ጥቅም እንደሌለ ሊገነዘበው ይገባል፡፡

 እንዲያውም አሠራሩ ለሌብነት በር የከፈተም ነው እየተባለውና እነዚህን ተሽከርካሪዎች በሚመለከት እየተተገበረ ያለውን አሠራር ዳግም በመፈተሽና ማስቀረት አለበት፡፡ አስተዳደሩም ቢሆን ጉዳዩን በቸልታ መመልከት ስለሌለበት አፋጣኝ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት