Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉይድረስ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ -

ይድረስ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ –

ቀን:

ለውጭ ምንዛሪ እጥረት የብርን የመግዛት አቅም መቀነስ መፍትሔ ይሆናል እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም

 “መለኪያ በሌለበት ኢኮኖሚ ሁሉም ነገር ልክ ነው” (In an economy where there is no measure, everything is right.)

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መነሻ ሐሳብ

ብሔራዊ ባንክ የብርን የመግዛት አቅም ከተጓዳኝ የጥቁር ገበያ ጋር በማወዳደር እስከ 95 በመቶ ለማቀራረብ ዕቅድ እንዳለው የሚያመላክት ሰነድ ለተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ መቅረቡን መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው። ውይይቱ ብዙ ጥያቄዎችን አጭሯል፡፡ አነጋጋሪ ሆኖም ሰንብቷል። በአሁኑ ወቅት የዶላር ሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመን 55.5 ብር የደረሰ ሲሆን፣ በጥቁር ገበያው ግን አንድ ዶላር እስከ 110 ብር እየተመነዘረ ይገኛል።

ምንም እንኳን የብርን አቅም የማዳከም ጉዳይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሰሞኑን መነጋገሪያ ሆኖ ቢከርምም፣ መንግሥት ስለጉዳዩ ያለው ነገር አልነበረም፡፡ እኔ አላልኩም ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ክዷል፡፡ “ሪፖርተር ጋዜጣ” ላይ ወጥቷል ባለው አሳሳች ዘገባና አሉባልታ ምክንያት በዋጋ ላይ የሚፈጠር ማንኛውም ሰው ሠራሽ ጭማሪ ተቀባይነት የለውም፣ ጥብቅ ክትትልም ይደረጋል ሲል እርስ በርሱ የሚጋጭ መግለጫ አውጥቷል፡፡

የብሔራዊ ባንክ በሕጋዊ የውጭ ምንዛሪውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን ልዩነትን በ95 በመቶ እናቀራርበዋለን ሲል፣ የትኛውን የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት አድርጎ እንደሆነም አልተብራራም።

በተለይ ይህን ዓይነት ዕርምጃ (የብርን የመግዛት አቅም መቀነስ) በከፍተኛ ሚስጥር የሚከወን እንደ መሆኑ መጠን፣ የመንግሥት ውሳኔ ምንም ይሁን ምንም ድንገተኛ ሊሆን እንደሚችል ከዚህ ቀደም የተወሰዱ ተመሳሳይ ዕርምጃዎች ያሳያሉ፡፡ ግና የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሸከመው ውጣ ውረድና መዓት ከባድ ስለሆነ እየመጣ ያለውን የበዛ የኢኮኖሚ መከራ መጠቆምም ሆነ መውጫ ጫፎችን ማሳየት የግድ ይላል።

ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ሁለት ጊዜ ብር ከዶላር ጋር ያለውን ዋጋ ተመን ማሳነሷ የሚዘነጋ አይደለም። የመጀመርያው እ.ኤ.አ. በ2010 ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በ2017 የተደረገ ለውጥ ነው፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ መንግሥት የብር አቅም እንዲዳከም (Devaluation) ውሳኔ ያስተላለፈው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ዘመን ሲሆን፣ በወቅቱም ብር በ15 በመቶ እንዲዳከም ተደርጎ ነበር፡፡ ከዚያም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር የውጭ ምንዛሪን ገበያ መሠረት በማድረግ (Gradual Devaluation) የብር አቅም እንዲዳከም ተደርጓል፡፡ ለአብነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ አንድ ዶላር 27 ብር አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ በየዓመቱ ቢያንስ በ25 በመቶ እንዲዳከም ተደርጎ ከ55 ብር በላይ ደርሷል፡፡

በኢሕአዴግም ሆነ በብልፅግና የመንግሥት አስተዳደር የብርን አቅም የማዳከም ፖሊሲ ዓላማው፣ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለመጨመርና የገቢ ንግዱን ደግሞ ለመቀነስ የንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማጣጣም፣ የመንግሥታዊ ብድር ወለድን በርካሽ ለመክፈል (Agregate Demand) በማሳደግ ጥቅል አገራዊ ምርትን (GDP) ማጎልበት የመሳሰሉት ናቸው። ይሁን እንጂ መንግሥት ብርን ካዳከመ በኋላ ይህንን ዓላማ ለማሳካት ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት ብር ከአምስት ጊዜ በላይ በመንግሥት ድንገተኛ ውሳኔ እንዲዳከም ቢደረግም፣ የወጪ ንግድ ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ፈቅ ሊል አልቻለም፡፡ ምንም እንኳን ባለፈው በጀት ዓመት ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ቢልም፣ በተመሳሳይ የገቢ ንግድ ወጪ ወደ 18 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡

ብርን የማዳከም ፖሊሲ ከወጪና ከገቢ ንግድ አኳያ ያመጣው ለውጥ እምብዛም መሆኑን፣ ከዚህ ዓይነቱ ዕርምጃ አገሪቱ ያተረፈችው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በእርግጥም መረጃዎች የሚያረጋግጡት ይህንኑ ድምዳሜ ነው፡፡ ዶላር፣ ፓውንድ፣ ዩሮና የመሳሰሉ የውጭ መገበያያዎች ከብር አኳያ ያላቸው ዋጋ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ከዘይትና ከስኳር አንስቶ እስከ የተለያዩ አልባሳቶች፣ እንዲሁም የተሽከርካሪዎች ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሳዩት ጭማሪ ባለፉት ሦስት ዓመት ከሃያ በመቶ ሳያልፍ፣ በኢትዮጵያ ከ150 በመቶ በላይ ጭማሪ ያሳዩበት ዋነኛ ምክንያት የብር አቅም መዳከም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ግፊት

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ገንዘቧ በገበያ ዋጋ እንዲተመን ግፊት እንደሚያሳድሩ ይነገራል። ለዚህ አንዱን ምክንያት አይኤምኤፍ ከተመሠረተባቸው ምክንያቶች አንዱ ዓለም የአገሮች የመገበያያ ገንዘብ ዋጋ እንዲረጋጋ ለማድረግ በመሆኑ ነው።

በእነሱ ፍልስፍና የምንዛሪ ተመን የተረጋጋ የሚሆነው ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ ሲሆን ነው። ምክንያቱም ምንዛሪ እንደ ማንኛውም ሸቀጥ ዋጋ አለው። እንደ ሌሎች ሸቀጦች ሁሉ ይህ ዋጋ በገበያ ኃይል መወሰን አለበት ብለው ያምናሉ።

ኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ያዘዘላትን የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ተቀብላ እንደወረደ እየተገበረች እንደምትገኝ፣ የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴርም ሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ፖሊሲ ከመቅረፅ ይልቅ  ቁልቁል ወርደው የአገሪቱን ኢኮኖሚ ቴክኒካዊ ጉዳይ አስፈጻሚ ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ችግሯን መቅረፍ ባለመቻሏ ፈጣን መዋቅራዊ ማስተካከያ (Strucural Adjustment) እንድትተገብር ማዘዙን፣ ይህንንም የኢትዮጵያ መንግሥት ተቀብሎ በመተግበር ላይ እያዋለ እንደሚገኝ ዋቢ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። መዋቅራዊ ማስተካከያ (Strucural Adjustment) ግዴታዎች አምስት ሲሆኑ፣ እነዚህም 1)  የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም (Devalutuion)፣ 2) መንግሥት የሚያደርገውን ኢኮኖሚያዊ ድጎማ ማቆም (የነዳጅ ድጎማ መንሳቱን ልብ ይሏል)፣ 3) የታክስ መሠረቱን ማስፋት (የንብረት ቀረጥ “Property Tax” ተግባራዊ መደረጉ)፣ 4) ኢኮኖሚውን ክፍት (Liberalization) ማድረግ (የኢትዮ ቴሌኮምን ሽያጭ ለውጭ ኩባንያዎች ፈቃድ መስጠት መጥቀስ ይቻላል)፣ 5) የመንግሥትን ወጪ መቀነስ ናቸው።

ለዛሬ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም (Devalutuion) የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ አንድምታ እንመልከት፡፡

የወጪና የገቢ ንግድ በጨረፍታ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጭ ምንዛሪ (ዶላር) ፍላጎትና ዋጋ መጨመር አንደኛው ምክንያት የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛናዊ አለመሆን ነው። በሌላ ቋንቋ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት (Export)) ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባው (Import) በጣም ያነሰ ነው።

እ.ኤ.አ. በ2022 ወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ በገፍ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል የተጣራ ነዳጅ፣ መድኃኒት፣ የሰውና የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም ማዳበሪያ በብዛት ታስገባለች ሲል ያመለክታል። ሪፖርቱ አክሎም ሩዝ፣ ስኳር፣ ስንዴ፣ ፉርኖ ዱቄትና ዘይትን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶች በርከት ብለው እንደሚገቡም ዘርዝሯል።

በተቃራኒው ወደ ውጭ የምትልካቸው ቡና፣ አበባ፣ አልባሳት፣ ወርቅ፣ ጥራጥሬና የቆዳ ውጤቶች ናቸው። ቢሆንም ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የምታወጣው ገንዘብ ወደ ውጭ በመላክ ከምታስገባው ገንዘብ እጅግ የላቀ መሆኑ የንግድ ጉድለት (Trade Deficit) ፈጥሯል።

በዓለም የገንዘብ ድርጅት እምነት የኢትዮጵያ ብር ከሚገባው በላይ ስለተተመነ (Overvalued)፣ በዚህም የተነሳ ላኪዎች ወደ ውጭ የሚልኩትን ጥሬ ሀብት እንደ ልብ ለመሸጥ አይችሉም። ገንዘባቸውን ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ከቀነሱ ግን ይበልጥ መሸጥ ይችላሉ፣ ስለሆነም በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር  ገቢ ያገኛሉ ይላሉ። ይህ ዓይነቱ አካሄድ የፍላጎት መለጠጥ (Elasticity of Demand) በመባል ሲታወቅ፣ አንድ አገር የገንዘቧን ትመና በአንድ ፐርሰንት ብትቀንስ የምትሸጠውም የምርት መጠን እንዲሁ በአንድ ፐርሰንት ያድጋል እንደ ማለት ነው። ይሁንና ስታትስቲክሶች እንደሚያሳዩትና እንደሚያረጋግጡት ከሆነ በማደግ ላይ ካሉ አገሮች የገንዘባቸውን ምጣኔ የቀነሱ  በሙሉ የንግድ ሚዛናቸው በከፍተኛ ደረጃ እንደተዛባ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው 70 በመቶ ቡና ሲሆን፣ ከዚህና ከሌሎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች እ.ኤ.አ. በ2021 3.3 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ስታገኝ፣ ከውጭ ላስመጣቻቸው ልዩ ልዩ ዕቃዎች ደግሞ ክ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንዳደረገች ስታትስቲክሱ ያሳያል። ይህም ማለት የውጭ ንግድ ሚዛኗ በከፍተኛ ደረጃ የተዛባ ሲሆን፣ ይህም ወደ 11.7 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የውጭ ዕዳዋም በከፍተኛ ደረጃ ተቆልሏል። ከቻይናና ከዓለም የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ የተበደረችው ጠቅላላ ዕዳ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር ሲጠጋ፣ ከቻይና ብቻ 12 ቢሊዮን ዶላር ተበድራለች። ይህም ማለት አገራችን ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጠች፣ መንግሥት ወይም አገዛዙ ኢኮኖሚውን በፈለገው መልክ ለማደራጀትና ለሰፊው ሕዝብ ደግሞ በቂ ግልጋሎትና ለሰው ሕይወት ጠቃሚ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ በፍጹም አይችልም ማለት ነው።

ይህም የሚያረጋግጠው የኢትዮጵያን ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በተከታታይ ዝቅ ማድረጉ ጤናማ ኢኮኖሚ እንድንገነባና ነፃ እንድንሆን አላደረገንም። ከዚህም በላይ እንደ ቡና የመሳሰሉትን ምርቶች ሌሎች አገሮችም ስለሚያመርቱና በኮታም ስለሚሸጥ፣ አንድ አገር ገንዘቧን በመቀነሷ የግዴታ በብዙ ሚሊዮን ቶን የሚቆጠር ቡና ልትሸጥ አትችልም። ይህ ዓይነቱ የገንዘብ ቅነሳ (Devalutuion) ሊሠራ የሚችለው በቴክኖሎጂ ላደጉ አገሮች ብቻ ሲሆን፣ እነዚህም አገሮች በመንግሥት ወይም በባንክ ጣልቃ ገብነት ገንዘባቸውን መቀነስ አያስፈልጋቸውም። በተለይም በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ባለው ውድድርና በተለያዩ የፖለቲካና የጦርነት ምክንያቶች የተነሳ፣ ለምሳሌ ካፒታል ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ በሚሸሽበት ጊዜ የዶላር ምጣኔ ከዩሮ ጋር ሲነፃፀር ከፍ ሊል ይችላል። ይህ ዓይነቱ አካሄድ አውቶማቲክ ዲቫሉዌሽን (Automatic Devaluation) በመባል ሲታወቅ፣ ዩሮ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በሚቀንስበት ጊዜ እንደ ጀርመንና ፈረንሣይ የመሳሰሉት ለኢንዱስትሪ ተከላ የሚያገለግሉ ማሽኖችንና ልዩ ልዩ የመለዋወጫ ዕቃዎችን የሚያመርቱ አገሮች ምርቶቻቸውን በብዛት ለመሸጥ ይችላሉ። ምክንያቱም አንድ የውጭ አገር ኩባንያ ወይም አገር አንድ ዩሮ ለመግዛት ከፈለገ አንድ ዩሮ ከአንድ ዶላር በታች ስለሚገዛ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ እንደ ጀርመንና ፈረንሣይ የመሳሰሉት ኢኮኖሚዎች ማሽኖችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን በብዛት ስለሚሸጡ በውጭ ንግዳቸው ጤናማ ይሆናሉ ማለት ነው።

ወደ አገራችን ስንመጣ የብልፅግና ፓርቲ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የእነ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን (አይኤምኤፍ) ምክር በመቀበሉና የኢትዮጵያንም ብር በተከታታይ እንዲቀንስ (Continuous and Gradual  Devaluation) በማድረጉ፣ ኢትዮጵያ በንግድ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ መዛባት ብቻ ሳይሆን በዕዳም ለመተብተብ ለመሆን በቅታለች። ከዚህ በተረፈ የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በተከታታይ እንዲቀንስ መደረጉ ወደ ውስጥ የመግዛት ኃይሉንም በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ እንዲል አድርጎታል። በተለይም ከውጭ የመለዋወጫ ዕቃዎችንና ማሽኖችን የሚያስመጡ አምራቾች የኢትዮጵያ ብር ዝቅ በሚልበት ጊዜ፣ አንድ ዶላር ለመግዛት ከድሮው ጋር ሲወዳደር ብዙ የኢትዮጵያ ብር መክፈል አለባቸው ማለት ነው። ይህ በራሱ ደግሞ የማምረቻ ዋጋን ከፍ ያደርገዋል። ይህም ማለት ምርቱ በገበያ ላይ ይወደዳል ማለት ነው። ባለፉት ዓመታት በአገራችን ገበያ ውስጥ የሚታየው የዋጋ ግሽበት አንደኛውና ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ብር በሰው ሠራሽ (አርቲፊሻል) በሆነ መንገድ በተደጋጋሚ እንዲቀንስ በመደረጉ ነው። ይህ ሁኔታ በተለይም ከተወሰነው የኅብረተሰብ የአኗኗር ሥልት መለወጥ ጋር በመያያዝ ለኑሮ ውድነት ዋናው ምክንያት ሊሆን ችሏል።

“በእንቅርት ላይ…” እንዲሉ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አስገራሚ የሚባሉ ክስተቶችን ፈጥሯል፡፡ ይኸውም የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል የአገሪቱ ላኪዎች ቁጥር አስገራሚ በሚባል ደረጃ መጨመሩ ነው፡፡ በጥናቶች መገንዘብ እንደተቻለው እ.ኤ.አ. ከ2008 በፊት በዓመት 2,500 ላኪዎች ፈቃድ የወሰዱና ያደሱ ሲሆን፣ በ2019 ቁጥሩ ወደ 6,000 ማደጉን፣ በ2021 ደግሞ ፈቃድ የወሰዱ ላኪዎች ቁጥር 16,000 መድረሱ ታውቋል፡፡ ይህ የሆነበትም ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ዕድል የሚኖረው የላኪነት (የኤክስፖርት) ፈቃድ ሲኖር ነው የሚል አስተሳሰብ በመፈጠሩ ሲሆን፣ ይህም የንግዱ ማኅበረሰብ የኤክስፖርት ንግድ አትራፊ ይሁን አክሳሪ መገምገም ሳያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ለማኘት ሲል ብቻ የኤክስፖርት ንግድን እንዲያማትር ሊያደርግ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሰው ወደ ኤክስፖርት ንግድ ውስጥ በመግባቱ በአገር ውስጥ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ትልቅ ችግር መፍጠሩን፣ ይህም ዞሮ ዞሮ የብርን የመግዛት አቅም መቀነስ መፍትሔን ዋጋ ቢስ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት የብርን የመግዛት አቅም እንዲዳከም የማደርገው/ያደረግኩት የወጪ ንግድ (Export) ለማበረታታት ነው ሲል እንዴት አድርገህ? ተብሎ ሊጠየቅ ይገባል፡፡

ብሔራዊ ባንክና የመቆጣጠር አቅሙ፣ የባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ሀብትና ዕዳ ልዩነት (Open Position) እያሰፋ መምጣቱ እጅግ አደገኛነቱ ና የሚያስከትለው የከፋ ውጤት

ሰሞኑን የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው ባንኮች በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ እጅግ የዘገየና አስተማማኝ ያልሆነ የኤልሲ ክፍያ ዕዳ አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ ዕዳ የተከማቸው ላኪው ድርጅት ኤልሲ ከተከፈተና ዕቃውን ከላከ በኋላ ከባንኩ ጋር ባለው ስምምነት መሠረት ክፍያ ሳይፈጸምለት እስከ አንድ ዓመት ድረስ በመቆየቱ ነው፡፡ የሚያስደንቀው ነገር አስመጪው በብር የውጭ ምንዛሪውን ተመጣጣኝ ለባንኩ ከፍሏል፣ ባንኩ ተገቢው ኮሚሽንና የአገልግሎት ክፍያውን ወስዷል፣ ዕቃውም ለአስመጪው ደርሷል፣ ለላኪው ክፍያውን የነፈገው ባንኩ መሆኑ ነው፡፡

አንድ ኤልሲ ተከፍቶለት ግብይቱ ተፈጽሞ ወደ አገር የገባ ምርት ሒሳብ መወራረድ ያለበት በሦስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡ አሁን በብዙ ባንኮች እየታየ ነው የሚባለው ግን በሦስት ቀናት መክፈል ያለበት ክፍያ ሳይከፈል ዓመታት እያስቆጠረ እየሆነ ነው፡፡ ይህ እየታወቀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ ዕርምጃ አለመውሰዱ ያመጣው ችግር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ማንኛውም ባንክ በሌለው የውጭ ምንዛሪ የሚከፈተው ኤልሲ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ክፍያ ለሚፈልገው የውጭ ኩባንያ ካልተከፈለ የአገርን ስም ያስነሳል፣ እየተነሳም ነው፡፡

በዚህ መንገድ ክፍያ በወቅቱ ባለመድረስ በላኪና በአስመጪ መካከል የሚነሱ ውዝግቦች አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው በተለያዩ ጊዜያት ለንግድ ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ ባንክና ለመንግሥት የተለያዩ አካላት አቤት ቢባልም ባንኮቹን ሥርዓት ማስያዝ ግን አለመቻሉ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ይዋል ይደር እንጂ የአገራችንን ገጽታ ከማጥፋቱም በላይ ላኪ ድርጅትና አስመጪዎችን የሚያቆራርጥ፣ አቀባባይ ባንኮችን የሚያሳጣና የውጭ ግብይት ሥርዓታችንን ሊያዛባ የሚችል አደገኛ የስግብግብነት አካሄድ ነው፡፡

ክፍያው ሳይፈጸም ከሦስት ቀናት በላይ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ምን ይጠብቅ ነበር? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባንኮች በወቅቱ ላለመክፈል ከሥር ከሥር ብዙ ኤልሲ እየከፈቱ መዝለቃቸው ዋነኛ ምክንያት ሲፈተሽ አንድ ሁለት ገፊ ምክንያቶች ልብ እንዲባሉ ያስገድዳል፡፡ ይህም ባንኮች ለከፈቱት ኤልሲ በወቅቱ ክፍያ ላለመክፈላቸው አንዱ ምክንያት፣ የባንኮችን ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔያቸውን ከፍ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ ጭምር የሚሠራ መሆኑ ነው፡፡ ኤልሲውን በመክፈት የሚገኘውን ኮሚሽን ትርፋቸውን ለማሳደግ ይጠቀሙበታል መባሉ ለጆሮ ደስ አይልም፡፡ ለእነሱም አደጋ መሆኑን እያወቁ ማድረጋቸው ደግሞ ለምን ያሰኛል፡፡

ባንኮች የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ እንደ ሀብት የማይዙት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የተወሰነውን የውጭ ምንዛሪ ለደንበኞቻቸው ሲደለድሉ ቀሪውን ለክፍያ የሚያቆዩት ነው፡፡ አሁን ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንፃር የብዙ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሀብትና ዕዳ ልዩነት ቅናሽ (Negative or Short Position) ላይ ያለ ሲሆን፣ ይህን አሳሳቢ የሚያደርገው ልዩነቱ እየሰፋና ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የ15 በመቶ ቅናሽ (Negative or Short Position) ወሰን ርቆ መገኘቱ ነው፡፡ ይህም ማለት ባንኮች ካላቸው የውጭ ምንዛሪ ሀብት በላይ ነገ እናገኛለን ብለው በማሰብ ብቻ ከአቅም በላይ የውጭ ምንዛሪ ለአስመጪው ያከፋፈሉና የደለደሉ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የ15 በመቶ ወሰን በብሔራዊ ባንክ ብቻ የተቀመጠ መለኪያ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ አሠራር (International Best Practice) የሚባል ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በስፋት ከባንኮች ዓመታዊ የሒሳብ መግለጫ (Financial Report 2022/23) እንደታዘበው፣ የብዙ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ዕዳ (Negative or Short position) ልዩነት ካላቸው ካፒታል ጋር ያለው ጥምረት ከ40 እስከ 50 በመቶ (ከሚጠበቀው ሦስት እጥፍ) በላይ እንደሚገኝ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የባንኮች የውጭ ምንዛሪ ዕዳ ከሀብታቸው በላይ እየሄደና ከውጭ ምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ጋር (Devalutuion) ተያይዞ ከሚመጣው ኪሳራ (Loss on Exchange)፣ እንዲሁም ያለባቸውን ዕዳ ከመክፈል አቅም እየተዳከመ መምጣት ጋር መያያዙን ነው፡፡

በባንክ የውጭ ምንዛሪ አደላደልና አሠራር መሠረት ትልቁ ሙያ የውጭ ምንዛሪ  ለአስመጭው መደልደል ሳይሆን፣ በድልድሉ ምክንያት የሚመጣውን ዕዳ (Commitment) በጊዜው መክፈል መቻል ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ ነጋዴ ከውጭ ያስመጣው ዕቃ አገር ከገባ በኋላ ክፍያ በጊዜው ሊፈጸምለት ይገባል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ሕግ የኢምፖርት ዶክመንት በመጣ በሦስት ቀናት ውስጥ መከፈል ይገባል ቢልም፣ ባንኮች ከስድስት ወራት በላይ ሳይከፍሉ ያስቀመጡት የውጭ ምንዛሪ ዕዳ እንዳለባቸው ሀቅ ነው፡፡ በተለይም በሌተር ኦፍ ክሬዲት የገቡ ዕቃዎች ክፍያ በዓለም ሕጎች መሠረት በጊዜ መክፈል መቻል ቢገባቸውም፣ አለመደረጉ ብዙ የውጭ ነጋዴዎች ከአገራችን ነጋዴዎች ጋር የመሥራት ፍላጎት እየቀነሰ እየመጣ ነው፡፡ በተጨማሪም የዚህ ዕዳ መከማቸት ነገ የባንኮችን የመክፈል አቅም መፈታተን ብቻ ሳይሆን አለመቻል ማምጣቱ የማይቀር ሲሆን፣ ይህም የአገሪቱ ዕዳ ሆኖ የሚቀጥል ነው፡፡ በጊዜ የመፍትሔ ዕርምጃ ካልተወሰደ ጉዳቱ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡

ከ15 በመቶ ወሰን በላይ የውጭ ምንዛሪ ሀብትና ዕዳ ልዩነት ያለው ባንክ፣ በውጭ ምንዛሪ ዋጋ ለውጥ (Devaluatuion) ምክንያት ሊጠቃ (Loss on Exchange) ወይም ጨርሶ ሊጠፋ እንደሚችል በዓለም ያለው ተሞክሮ ያሳያል፡፡ ይህንን ለመከላከል የተለያዩ ማስታገሻዎች (Hedging) መውሰድ የግድ ቢልም፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ በገንዘብ ገበያው ምክንያት ጨርሶ የሚታሰቡ አይደለም፡፡ ስለዚህ ተጋላጭነቱ ሙሉ በሙሉ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት ከባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሀብትና ዕዳ መጠን ከመስፋት ጋር በተገናኘ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርቡ ሪፖርቶች የሚያካትቱ ባንኮች፣ የብሔራዊ ባንክ ወሰንን አክብረው እንደሚሠሩ ቢመስልም ትክክለኛ መረጃ መስጠታቸው አጠራጣሪ ብቻ ሳይሆን፣ “ውስጡን ለቄስ” እንደሚባለው ነው፡፡ አንድም ባንኮች ሪፖርታቸውን በግልጽ ቢያስቀምጡ የሚደርስባቸውን ቅጣት በመፍራት፣ ሌላው ደግሞ ነገሮች ከአቅማቸውና ከቁጥጥራቸው በላይ ስለሄዱም ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ዋነኛው ተዋናይ ብሔራዊ ባንክ ራሱ መሆኑ አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ፣ ከባንኮች ጋር ያለው የድብብቆሽ ጨዋታ ነገ አገራዊ ችግር ሊፈጥር መቻሉ አሳሳቢ ነው፡፡

ምን ቢደረግ ይሻላል?

በአጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ምን ቢደረግ ይሻላል? አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር ለመፍታት ከባድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ለብቻ አንድ መፍትሔ በመስጠት (የብርን የመግዛት አቅም መቀነስ) ውጤት ይመጣል ብሎ ማመን አይቻልም፡፡ የታመመው ሙሉ ኢኮኖሚው በመሆኑ መታከም ያለበት ሙሉ ኢኮኖሚው ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ከምንም በላይ ወሳኝ ነው፡፡ ሰላም እስካልሰፈነ ኢኮኖሚው ጥሩ ሊሆን እንደማይችል፣ ኢኮኖሚው ጥሩ ካልሆነ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ችግር ሊፈታ እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለመፍታትም ሆነ አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ መንግሥት ለኢኮኖሚውና ለንግድ እንቅስቃሴው ከሌሎች ጉዳዮች በተለየ ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል፡፡ ይህ ጉዳይ ከፖለቲካውም በላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በተለይም ለግብርናው የተለየ ፖሊሲና አሠራር ያስፈልጋል፡፡ የግብርና ዘርፉ መጨቆኑን በአኃዛዊ መረጃ ማየት ይቻላል፡፡ የግብርና ዘርፍ የአገሪቱ ዋነኛ የወጪ ንግድ ገቢ አመንጪ ሆኖ ሳለ፣ ባለፉት አሥር ዓመታት በአማካይ በጠቅላላ ወደ አገር ውስጥ ከገባው የካፒታል ዕቃ ውስጥ የግብርና ካፒታል ዕቃ ድርሻ ሁለት በመቶ ብቻ ነው። በአንፃሩ ግን የኢንዱስትሪ የካፒታል ዕቃዎች ግን ከ20 እስከ 25 በመቶ በየዓመቱ እንዲገባ በመደረጉ፣ ይህ ያስገኘው ውጤት ግን በወጪ ንግዱ ላይ በበቂ ሁኔታ አልታየም፡፡ ይህንን ጉዳይ መፈተሽ ተገቢም ወቅታዊም ነው፡፡

የብርን የመግዛት አቅም ከመቀነስ በፊት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ለአብነት ያህል የመጀመሪያው ማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት፣ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር፣ በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መኖር፣ እንዲሁም የንግድ ሚዛን ጉድለት ማጥበብ ያስፈልጋል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመከፋፈል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ብቻ ማስገባት፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈልገዋልና። ብሔራዊ ባንክ ይህንን መምራት ያለበት በመሆኑም ለዚህ በሚበቃ ልክ መደራጀትና አቅሙን ማሳደግ የውዴታ ግዴታ ነው።

ሁለተኛው ብሔራዊ ባንክ ከተቋቋመባቸው ዋነኛ ዓላማዎች መካከል የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሥርዓትና የተፋጠነ ልማት ማምጣት በመሆኑ፣ ከላይ በዝርዝር ያነሳናቸው የባንኮቹ ድክመት (የውጭ ምንዛሪ ሀብትና ዕዳ ልዩነት “Open position”) እንዲታረም ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፣ በተቃራኒው ደግሞ የባንኮቹን አቅም በማሳደግና አቅጣጫ በማስያዝ በቂ ሚና አለመጫወቱ ከፍተኛ ሥጋት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የሁለት ባንኮች ኃላፊዎች በሕገወጥ መንገድ የሚፈልጉትን ብቻ ለመጥቀም ሲሉ የውጭ ምንዛሪ በመፍቀዳቸው፣ በሒሳባቸው ውስጥ በቂ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ ሳይኖር ኤልሲ በመክፈታቸው፣ ላኪዎች በተገቢው ጊዜ ለላኩት ቁሳቁስ ክፍያ እንዳያገኙ በማድረግና የተዛባ የግብይት ሥርዓት በመዘርጋት የአገሪቱን የወጪ ንግድ ግብይት አደጋ ላይ ጥለው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከውጭ ምንዛሪ አቅራቢዎችና ተጠቃሚዎች ጋር በመመሳጠር በአየር በአየርና በደላላ አማካይነት ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርና ትስስር በመፍጠራቸው፣ ከፍተኛ የሥራ አመራሮቻቸውና የቦርድ አባላቶቻቸውን ጨምሮ ሌሎችም ሠራተኞች በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጉን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተከታትለን ነበር፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከወገንተኝነት በፀዳ መንገድ በዚህ ዓይነቱ ራስንና ውስጥን የመፈተሽ፣ አልፎ ተርፎም ቤትን የማፅዳት አሠራር ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ በሥርዓት ስለሚመሩ ባንኮች ማቀድና ችግር ሲኖር የእርምት ዕርምጃ መውስድ ከውዴታ በላይ አገራዊ ግዴታ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክም “በዕንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ” ውሎ አድሮ ከመከሰቱ በፊት የቁጥጥር አድማሱን አስፍቶ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ የባንኮችን ጓዳ ጎድጓዳ መንግሥትና ብሔራዊ ባንክ ሳይዘገዩ መፈተሽ ይኖርባቸዋል፣ ይገባቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ነዋሪነታቸው በሰሜን አሜሪካ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...