Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉመሬትን የሽያጭ አካል አድርጎ ታክስ ማሥላት ሕገ መንግሥቱን ይፃረራል

መሬትን የሽያጭ አካል አድርጎ ታክስ ማሥላት ሕገ መንግሥቱን ይፃረራል

ቀን:

በባይሞት ፀጋዬ (አርክቴክት)

አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሬት አይሸጥም፣ አይለወጥም ይላል፡፡ በዚህም ምክንያት የሽያጭ ውል በሕግ ፊት እየፀደቀ ያለው በመሬቱ ላይ የቤት ግንባታ ያለው ሲሆን ብቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን መንግሥትም እየቀረበልኝ ባለው የቤት ሸያጭ ውል ላይ በሚገለጸው የውል መጠን ላይ እምነት የለኝም ሲል ተሰምቷል፡፡ ሕዝብም “ለሕዝብ  የጋራ ጥቅም” ሲባል በሚደረግ ልማትና በተለያዩ ምክንያቶች ቤቴን እንድለቅ ስደረግ፣ በመንግሥት የሚሰጠኝ ካሳ መጠን የቤቴን ትክክለኛ የገበያ ዋጋ መሠረት ያደረገ አይደለም እያለ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው በቤት ንብረት የገበያ ዋጋ መረጃ ላይ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን አለመኖሩን ነው፡፡ 

የንብረት ሽያጭ ዋጋ እንደ ነባራዊ ሁኔታው ተለዋዋጭ ነው፡፡ የሽያጭ ዋጋ የብዙ ሁነቶች ውጤት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከአገር ሰላምና የፖለቲካ መረጋጋት ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛና ፍትሐዊ የሽያጭ ዋጋ በአንድ የሒሳብ ቀመር ብቻ ሊተመን አይችልም፡፡ ከቤት ንብረት ግመታ ቀመር ከመለወጥ በፊት፣ ከሁሉም በላይ በመንግሥትና በሕዝብ መሀል መተማመን ያለበት መስተጋብር መገንባት ቀዳሚ ጉዳይ መሆን ነበረበት፡፡ ጊዜውን የዋጀ፣ ግልጽና ትክክለኛ የንብረት ሽያጭ መረጃና ግመታ ሥርዓት ለመንግሥትም ሆነ ለንብረት ባለቤቱም አስፈላጊ ነው፡፡ ፍትሐዊ አሠራር ማስፈን የሚቻለው በቅን እምነት ላይ ነው፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ የቤት ሽያጭ ግምት ቀመር በሥራ ላይ ያዋለ መሆኑን በ2015 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሲዘዋወር ተመልክቻለሁ፡፡ አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ሽያጭና ባለቤትነት ስም ዝውውር ታክስ (አሹራ) አሠራርን በተመለከተ የሚከተለውን አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ቀመሩን በሚገልጸው ሰንጠረዥ ሦስት መሠረት አፈጻጸሙ እንደሚከተለው ነው።

  1. የቤት የወለል ስፋት ሜትር ካሬ × 30,000 ብር/ሜትር ካሬ = የቤቱ ግምት
  2. የመሬቱ ስፋት ሜትር ካሬ × የመጠቀም መብት ብር/ሜትር ካሬ = የመሬት ግምት (የመጠቀም መብት ነጠላ ዋጋ እንደ መሬቱ እርከን የተለያየ መሆኑን በሰንጠረዡ ላይ ይታያል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ በካርታ ላይ የተቀመጠው የቦታ እርከን ወይም “Land Grade” ከሕግ ውጪ ተክዷል)፡፡
  3. የቤቱ ግምት + የመሬት ግምት = ጠቅላላ የሽያጭ ግምት
  4. የመኖሪያ ቤት አሹራ = የሽያጭ ግምት × ስድስት በመቶ ይሆናል ማለት ነው (የዓለም ንግድ ድርጅት ወይም “WTO” እንደሚመክረው ከሆነ አሹራ ከሦስት በመቶ አይበልጥም፣ ዌብሳይት ላይ ናሙና ሕጎችን ማየት ይቻላል)፡፡ ይህ አሠራር በእኔ ዕይታ ስድስት ዋና ዋና ስህተቶች አሉበት።

አንደኛ መሬትን የሽያጭ አካል አድርጎ ታሳቢ ያደረገ ስለሆነ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው። መሬትን የሽያጭ አካል አድርጎ ታክስ ማሥላት “መሬት አይሸጥም፣ አይለወጥም” የሚለውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ ይፃረራል። 

ሁለተኛ የመጠቀም መብት የተባለውም፣ እናት አዋጅ የሌለውና አዲስ ሐሳብ ስለሆነ ያለ መሪ አዋጅና ያለ ደንብ በቃለ ጉባዔ ብቻ ተፈጻሚ ማድረግ ሕገወጥ ነው። ባለው ሕግ በቤት ሽያጭ ጊዜ ነባር ይዞታዎችም ወደ ሊዝ ሥሪት ስለሚገቡ፣ ከሊዝ ክፍያው በተጨማሪ “የመጠቀም መብት” የሚባለው ሥሌት ኢፍትሐዊ ነው፡፡

ሦስተኛ ለአሮጌ ፈራሽ ቤት፣ ለአዲስ ቤት፣ ለጭቃ ቤት፣ ለቆርቆሮ ቤት፣ ለሸክላ ቤት፣ ለብሎኬት ቤት፣ ለአርማታ ቤት፣ ለፎቅ ቤት፣ በአጠቃላይ ለሁሉም ዓይነት ቤት በካሬ 30,000 ብር ሒሳብ ማሥላት ስህተት ነው።

አራተኛ ግምት ለማስተመን የክፍለ ከተማ ባለሙያ በራስ መኪና ወስዶ ማስለካት ውጣ ውረድ ያለው፣ ተመኑንም ለግላዊ ውሳኔ (Subjective Judgment) ተጋላጭ የሚያደርገው በመሆኑ ስህተት ነው።

አምስተኛ የአዲስ አበባ የቦታ ዕርከን ዓይነቶች ከሃያ የማያንሱ ሆነው ሳለ ወደ አራት ብቻ መጨፍለቁ ስህተት ነው።

ስድስተኛ ከፊሉን የሽያጭ ሥሌት ምንጭ ከመሬቱ ጋር ማስተሳሰሩ፣ የካሳ ክፍያን ሥሌት ዋጋ የሚያሳጣ በመሆኑ የሥሌት ቀመሩ በቅን ህሊና የተዘጋጀ አይመስልም።

በአዲስ አበባ መሀል ከተማ ባደረግሁት የናሙና ዳሰሳ ጥናት መሠረት በመሀል አዲስ አበባ በሚደረጉ የነባር ቤት ሽያጭ ላይ አዲሱ የአሹራ ታክስ ሥሌት መጠን ከጠቅላላ ሊዝ ዋጋው በላይ እስከ አምስት እጥፍ ከፍ እንዲል አድርጎታል። አሁን በዚህ ሥሌት ምክንያት ተገልጋይ የስም ዝውውር መጠየቅ አቁሟል። እንዲህ ዓይነት አሠራር ለመከተል ከተፈለገ ወይ ሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ አለበለዚያ አሠራርን ሕገ መንግሥትን የተከተለ ማድረግ ያስፈልጋል። 

ስለዚህ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቃለ ጉባዔ የተዘጋጀው አዲስ የቤት ሽያጭ ግመት ቀመር ሕገወጥ ተብሎ ሊታገድ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...