Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

እኔና ቢጤዎቼ አጋጣሚዎች አገናኝተውን ያለፈውን የወጣትነታችንን ዘመን ስናስታውስ፣ ይህ ትውልድ እየገጠመው ካለው ፈተና ጋር እያነፃፀርን ወቅቶችን ስናወዳድር በመሀል ትዝታዎቻችን ይዘውን ጭልጥ ይላሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት ነዋሪነታቸው አሜሪካ ከሆኑ የድሮ አብሮ አደጎቼ ጋር ምሳ እየበላን ስንጫወት አንድ ትዝታ ተነሳ፡፡ የትዝታው መነሻ በነጭና በቀይ ሽብር የተገደሉ ታላላቆቻችን ጉዳይ ነበር፡፡ ለእናቴም ሆነ ለአባቴ ሁለተኛ ልጅ የሆነው ታላቅ ወንድሜ በደርግ ቀይ ሽብር የተገደለ ሲሆን፣ አምስት የአክስቴና የአጎቴ ልጆችም ተገድለውብናል፡፡ የአጎቴና የመጀመሪያዋ ታላቅ እህታችን ባለቤት ሕይወት ያለፈው በኢሕአፓ በተተኮሱ ጥይቶች ነበር፡፡ ልክ እንደ እኔ ቤተሰብ ሁሉ የብዙ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች የቅርብ ሰዎቻቸው በዚህ ሁኔታ ተገድለው አልፈዋል፡፡

ከአሜሪካ ከመጡ አብሮ አደጎቼ አንደኛው አባትና እህቱ በደርግ ቀይ ሽብር ሲገደሉ፣ አንደኛው ወንድሙ በኢሕአፓ ስኳዶች ነበር የተገደለው፡፡ የአባቱና የእህቱ አስከሬን ሠፈራችን የአንበሳ አውቶቡስ ፌርማታ ሥር መጣሉን ሁላችንም በሰቀቀን የምናስታውሰው ሲሆን፣ በኢሕአፓ ተኳሾች የተገደለው ወንድሙ አባትና እናታቸው በተገደሉ ሰሞን ከመሥሪያ ቤቱ ሥራውን ጨርሶ ሲወጣ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ያ ሁሉ ሰቆቃና መከራ በወረደባት አገር ውስጥ ምን ያህል አባቶች፣ እናቶች፣ ሕፃናት ልጆችና ሌሎች ቤተ ዘመዶች እንዳነቡ ሁላችንም አይዘነጋንም፡፡ በተለይ ከ1969 እስከ 1970 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የነበረው የመከራ ቀንበር አሁንም አይረሳም፡፡

አንደኛዋ የልጅነት ጓደኛችን ያንን አስከፊ ጊዜ ለመርሳት ብትሞክር በስደት አገር አሜሪካም ሊረሳት እንዳልቻለ ስትናገር፣ ያንን ሁሉ ዓመት አዕምሮዋ ምን ያህል ሰቆቃ ተሸክሞ እንደኖረ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹አንድ ቀን ሞል ውስጥ ከልጆቼ ጋር ልብስና ጫማ ስናማርጥ አንድ ሰው ፊቴ ግጥም አለ፡፡ ያ ሰው ‹የአንድ ታጋይ ደም በሺሕ አናርኪስት ደም ይመነዘራል› እያለ በሜጋፎን ሲደነፋብን የነበረውና ሁለት ወንድሞቼን የረሸነው የቀበሌያችን የአብዮት ጥበቃ ሊቀመንበር ነበር…›› ብላ ዕንባዋ በዓይኖቿ ላይ ኩልል ሲል ደነገጥን፡፡ ያ ያለችው የአብዮት ጥበቃ ሊቀመንበር ስምንት ዓመት ታስሮ ቢፈታም፣ ‹‹እኔ ምንም ባልሠራሁት ኃጢያት የቀበሌያችን ክፉ ሰዎች አሳልፈው ሰጡኝ…›› በማለት ከተፈታ በኋላ ሲመፃደቅ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህች የሦስት ልጆች እናትና የጥርስ ሐኪም የሆነች ጓደኛችን፣ ‹‹እውነት እላችኋለሁ ገና ሳየው ዓይኔ ጭልምልም አለብኝ፡፡ እንዴ… እንዴ… እያልኩ ወደ እሱ እያመለከትኩ መጮህ ስጀምር ለካ ድንጋጤው አዙሮብኝ ወድቄያለሁ፡፡ ልጆቼ በዚያ ቅፅበት ምን እንዳጋጠመኝ ግራ ገብቷቸው ዙሪያዬን ከበው እያለቀሱ ሳሉ፣ ድንገት ስነቃ ራሴን ነጭ በነጭ የሆነ ክፍል ውስጥ አገኘሁት፡፡ እኔ ራሴን ስቼ ለአራት ሰዓታት ያህል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ መድኃኒት ተሰጥቶኝ ተኝቼ ነበር፡፡ በኋላ የሆነውን ነገር ስጠይቅ በድንገት ሞል ውስጥ ተዝለፍልፌ ወድቄ ለሕክምና ክሊኒክ መምጣቴን ነገሩኝ…›› አለችን፡፡

‹‹…ልጆቼ ከመውደቄ በፊት ምን እንዳስጮኸኝ ሲጠይቁኝ ያለፈውን ዘመን ሰቆቃና ግፍ ሲሠራ የነበረውን የአብዮት ጠባቂ ሹም ታሪክ ነገርኳቸው፡፡ ድንገት ዓይን ለዓይን ግጥም ስንል እሱ ባያውቀኝም እኔ ግን አወቅኩት፡፡ ልጆቹ ግን ‹ሌሎች ሰዎች መጥተው ዕገዛ አድርገውልን ከመሬት አነሳንሽ እንጂ፣ አንቺ የምትይው ዓይነት ሰው አላየንም› ሲሉኝ፣ እሱማ በየሄደበት ነውሩን የሚያጋልጡ ሰዎች መሀል ስለሚኖር የእኔ ድንጋጤና መውደቅ እንደ አላርም ስላገለገለው ማንም ሳያየው ሹልክ ብሎ መጥፋት ልማዱ ስለሆነ ነው ብዬ አስረዳኋቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያ ክፉ ሰው በሕልሜ ጭምር እየመጣ ጎራዴ ወይም ጠመንጃ ይዞ እያስፈራራኝ በስንት መከራ በሥነ አዕምሮ ሕክምና ነው የተሻለኝ…›› ብላ ሥቃይዋን ስታጋራን ከልባችን አዘንን፡፡

ይህ ዓይነቱ ሥቃይ ዛሬም ከሕዝባችን ጫንቃ ላይ ሊወርድ አልቻለም፡፡ ያ አሰቃቂ ዘመን አልፎ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ተብሎ በተስፋ ቢጠበቅም፣ ዛሬም ወንድም ከወንድሙ የሚተላለቅበትና ሕዝባችን መሪር የሆነ መከራ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ያኔ በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር የተሳተፉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀው የፈጣሪን ምሕረት መጠየቅ ሲገባቸው፣ እነሱ ላይ ሰፍሮ የነበረው ዲያቢሎስ ገጽታውን ቀይሮ ሕዝባችን ደም ዕንባ ያለቅሳል፡፡ ያኔ ከማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮተ ዓለም ያጣቅሱ የነበሩ በመስመር የተለያዩ ኮሙዩኒስቶች፣ አሁን በብሔርተኞች ተተክተው ኢትዮጵያ የማያባራ ግጭት ውስጥ ተቀርቅራለች፡፡

ከአብሮ አደጎቼ ጋር የነበረን የምሳ ሰዓትና የጨዋታ ጊዜ ተገባዶ ልንለያይ ስንል አንደኛው፣ ‹‹መቼም ሥልጣንና ጥቅም ታሳቢ ሲደረጉ አገርና ሕዝብ መኖራቸው አይታሰብም፡፡ ያኔ ወጣቱ ሆ ብሎ ተነስቶ ወደ ሞት የተነዳው አውቀናል በቅተናል የሚሉትን ተከትሎ ነበር፡፡ አሁንም የዚህ ትውልድ ወጣት በየጎራው የሚነዳው በዚያው በበፊቱ መንገድ እየተታለለ ነው፡፡ የፈለገ ቢሆን በሆነ ዓላማ ሥር እየተደራጀ ወገን ከወገኑ እንዲፋጅ ሲደረግ ለምን ብሎ መጠየቅ ነበረበት፡፡ ችግሩ ግን ያኔ ሶሻሊዝምን አንፀባራቂ ሥርዓት አስመስለው ትውልዱን ያወናበዱት እንዳሉ ሁሉ፣ ዛሬ ደግሞ የአንተ ብሔር ከሌላው በተለየ የተጨቆነ ስለሆነ እንዲህ ብታደርግ የምትፈልገውን ታገኛለህ ተብሎ እየተወናበደ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ወጣቱን በአንክሮ ማስተማር እንጂ ዳር ይዞ መውቀስ አይደለም…›› ነበር ያለው፡፡

እኔ ግን ወጣቱን ማስተማርና ማብቃት በሚለው ብስማማም አሁን ከማያቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች አኳያ፣ ከአገራዊ ፍቅርና ህልውና በላይ የግል ጥቅማቸው የበረታባቸው መብዛታቸው ነው እላለሁ፡፡ ማንም በሕዝብና በአገር ስም ቢምልና ቢገዘትም በጥቅሙና በሥልጣኑ ከመጡበት ምንም ከማድረግ እንደማይመለስ ከተረዳሁ በጣም ቆይቻለሁ፡፡ ለዚህ መድኃኒቱ ሕዝባችን ልጆቹን ጠንክሮ ማስተማር፣ ሥርዓት ማስያዝ፣ እንደ ወረዱ የሚለቀቁ ፕሮፓጋንዳዎችንና ዘገባዎችን በቅጡ መመርመር፣ የሚወደውን ወይም የሚፈልገውን ማዳመጥና መደሰት ሳይሆን እውነትን ጥግ ድረስ ሄዶ መረዳት ከቻለ ማንም አይጫወትበትም፣ በስሙም አይነግድበትም እላለሁ፡፡

(ማስረሻ ነገደ፣ ከጎሮ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...